mandag 27. oktober 2014

የ “ካዛንችሱ መንግስት በአዲሰ አበባ ማዘጋጃ ቤት” – ከግርማ ሰይፉ ማሩ


October 27.2014
ዛሬ ጥቅምት 17/ 2007 እግር ጥሎኝ አዲሰ አበባ ማዘጋጃ ቤት ጎራ ብዬ ነበር፡፡ የታዘብኩት ነገር ያስታወኝ ኤርሚያስ ለገስ “የመለስ ትሩፋቶች” በሚል ባወጣው መፅሃፍ ውስጥ “የካዛንችስ መንግሰት” ብሎ ያስነበበንን በገሃድ ከካዛንችስ ቦታ ቀይሮ አዲስ አበባ መስተዳደር ግቢ ውስጥ መኖሩን ነው፡፡ የካዛንችሱ መንግሰት ምን እንደሚሰራ እዚህ መዘርዘር አይጠበቅብኝም፤ በጥቅሉ ግን የአዲስ አበባ ህዝብ “መርጦ” ወይም ቀጥሮ ያስቀመጣቸው ሰዎች ሳይሆን ውሳኔ የሚስጡት ሌሎች በስውር በደህንነት ስም በኢህአዴግ የተቀመጡ ሰውር እጆች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
እነዚህ ሰውር እጆች ለእኛ ለተቃዋሚዎች አዲስ አይደሉም ለምሳሌ፤
· በሆቴሎች አዳራሽ ለማከራየት አንችልም ምንም ጠቃሚ ገንዘብ ቢሆን ሆቴሎች ፈቃደኞች አይደለም፤
· ማተሚያ ቤቶች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም እነርሱን ይደግፋሉ የሚባሉ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አያትሙም
· መብራት ኃይል ለአንድነት የማተሚያ ማሽን ሊያንቀሳቅስ የሚችል የኤሌትሪክ ሀይል (ሰሪ ፌዝ የሚባል ሀይል) ለፓርቲ ለማስገባት ፈቃደኛ አይደለም፤
· ቤት አከራዮች ቤታቸውን ለማከራየት ይፈራሉ፤
· በቅስቀሳ ጊዜ መኪና እና የድምፅ መሳሪያዎች ማግኘት ፈተና ነው፤
· ለቅስቀሳ የወጡ ሰዎች እንደ በግ በየጣቢያው ሲታሰሩ የሚያስሩት ሰዎች በግልፅ ዩኒፎርም የለበሱት ፖሊሶች ሳይሆኑ በሬዲዮ የሚያዙ ማን እንደሆኑ የማይታወቁ ናቸው፤ ወዘተ ይህ ሁሉ የሚሆነው በህግ አግባብ ሳይሆን በሰውር መንግስት ውስጥ ያሉ ሰውር እጆች የሚሰሩት ነው፡፡
ለዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ ግን በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ኦፌሰር የሆኑት አቶ ማርቆስ ብዙነህ የሰጡን ምላሽ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ በቀጣይ ፓርቲው በሚያደርገው እንቅስቃሴዎች የፓርቲ አባላትን በስነ ምግባር የታነፁ እና ሰላማዊ ትግል በሰለጠነ መንገድ የሚደረግና በግብግብ ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ለሚያካሂደው ስልጠና ለማካሄድ አዳራሽ ለመከራየት ባቀረብነው ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደሌለ ከውስጥ ሰምተን ምክንያቱን በግንባር ለማወቅ ሄጄ የሰማሁት ምላሽ በአንድ መንግሰታዊ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ ደሞዝ ከሚበላ ሲቪል ሰራተኛ የሚጠበቅ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ የሰጡን ምላሽ “አራት ሰዎች መጥተው ፍቃዱ እንዳይስጥ ጠይቀው አለቃይ እንዳትሰጥ ስለአለኝ ነው የሚል ነው፡፡” በቃ ይህ ነው ምክንያቱ፡፡ አንድነት ፓርቲ ይህን ፈቃዳ ላለማግኘት አንድም ያጎደለው መስፈርት የለም፡፡ አቶ ማርቆስ አለቃቸው ይህን መልስ ሲሰጣቸው ለምን? እንዴት ብዬ? ከመመሪያ አንጻር ልክ አይደለም ብለው አይጠይቁም፡፡ አለቃቸውንም አይሞግቱም፡፡ እርሳቸውም የሚያውቁት አለቃቸውም ቢሆን እራሳቸው እንደማይወስኑ፡፡ የሚወስነው ይህ ስውር እጅ ያለው ካዛንችስ የነበረው አሁን በመስተዳድር ቅፅር ግቢ የሚገኘው መንግሰት እንደሆነ፡፡
አንድ መስሪያ ቤት ሰራውን የሚሰራው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን በደንብ እና መመሪያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኦፊሰሮች ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ደግሞ እነዚህ የህግ ማዕቀፎች መሰረት አድረገው ነው ብለን እንጠብቃለን፡፡ በዚህች ምስኪን ሀገር ግን ይህ ምፀት ነው፡፡ በህግ ማዕቀፍ የሚሰራ ኦፊስር ማግኘት ዘበት እየሆነ መጥቶዋል፡፡ አለቃው በቃል አድርግ ያለውን የሚያደርግ የማርቆስ ዓይነት ኦፊሰር ሞልቶ ተርፎዋል፡፡ በጣም የሚገርመኝ የዚህ ዓይነት ኦፊሰሮች ለልጆቻቸው ሰራ ሄጃላሁ የሚሉ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ባይሉ
ዋቸው ደግ ነው፡፡ ይህን ሊያደርጉ መሄዳቸውን ሲያውቁ ያፍሩባቸዋል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ ለምን ለልጆቻችን ማፈሪያ እንደምንሆን አይገባኝም፡፡
መልካም አስተዳደር አስፍናለሁ የሚል መንግሰት መልካም አሰተዳደር የሚሰፍነው በአዳራሽ ኮፍያና ቲ ሸርት ለብሶ በሚደረግ ዲስኩር እንዳልሆነ የገባው አይመስለም፡፡ መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው በህግ ማዕቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ አገልግሎት ሲሰጥ እንጂ በስውር በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ እንዳለሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡ ማርቆስ በሚሰጠው መልስ እየተበሳጨ፣ እያዘነ ሲከፋውም እየተሳደበ የሚሄድ ተገልጋይ መዘዝ እንደሚያመጠ ግን የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ በስውር መንግሰት በዚህ መንገድ እንዲሆን ስለሚፈልግ ነው፡፡
ዛሬ በግልፅ የተረዳሁት በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም አስተዳደር የማሰፈን ችግር ምንጭ በደህንነት ስም በስውር ያለው መንግሰት የሚሰጠው ትዕዛዝ ሲሆን፣ ሲቀጥልም አድርግ ያሉትን ለማድረግ በተጠንቀቅ ዝግጁ የሆነው የማርቆስ ዓይነት ደሞዝ እየበሉ ያሉ ሲቪል ሰራተኞች ናቸው፡፡ አለቃዬ እንዲህ አድርግ ብሎኝ ነው በሚል መመሪያን መሰረት ያላደረግ ትዕዛዝ የሚሰፈፅሙ የማርቆስ ዓይነት ኦፊሰሮች የዚህች ሀገር መከራ እንዲረዝም፣ ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ትሩፋት እንዳያገኝ ተባባሪ እንደሆኑ አበክረን መንገር ይኖርብናል፡፡ ይህንን አሜን ብሎ የተቀበለ ህዝብ መከራውና ግፉ ተስማምቶኛል እንዳለ ይቆጠራል፡፡ የዚህ ዓይነት ህዝብ ደግሞ ምንም ዓይነት አንባገነን መንግስት ቢመጣ የሚገባው ነው ማለት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ አይመጥነንም ያለ ህዝብ በቃ!!!! ሊለው ይገባል፡፡ ኢህአዴግ በቃ ሊባል ይገባል!!!!
ቸር ይግጠምን

tirsdag 21. oktober 2014

ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፡ በአሜሪካ ሲያትል ዋሽንግተን ዉስጥ የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደ

የግንቦት 7 ንቅናቄ ቅዳሜ ኦክቶበር 11 ቀን 2014 አ.ም በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ደማቅ ህዝባዊ ስብሰባ ማካሄዱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በሲያትልና አጎራባች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት የታደሙበት እንደነበር ያደረሰን ዘጋቢያችን አገር ወዳድ ኢትዮጵያኑ በስብሰባው ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት የንቅናቄው ሊቀመንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሰፊ አገራዊ ውይይት ማካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። በሲያትል የተካሄደው ይህ ህዝባዊ ስብሰባ ኢትዮጵያውያን በዘር በሃይማኖት በጎሳ ሳይለያዩ በአንድነት በመሰባሰብ በአገራቸው ጉዳይ ላይ በሰፊው የመከሩበት፤ ኢትዮጵያዊነት እጅግ አምሮና አሸብርቆ የታየበት እንደነበርም ተመልክቷል።

በህዝባዊ ስብሰባው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ዶ/ር ብርሀኑ ለስብሰባው ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር “የምንገኝበት ወቅት ጊዜያችንን እንደ ከዚህ ቀደሙ መቋጫ በሌለው ውይይትና ጭቅጭቅ የምናጠፋበት ሳይሆን፤ ስለ ነፃነቴ እታገላለሁ የሚል ወደ ተግባራዊው ትግል የሚቀላቀልበት፤ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ትግሉን መቀላቀል የፈራ ዝም ሊል የሚገባበት ወቅት መሆኑን በአንክሮ በማስገንዘብ በተጨማሪ የነፃነት ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ የሚገኘውን የእርስ በርስ ጥልና ሽኩቻ በአስቸኳይ ቆሞ ሁላችንም በአንድነት በመነሳት በዋናው አላማችን ላይ ማለትም የጉጅሌው ወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ መዝመት ይገባናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በተለይ የነፃነት ትግሉ ለመቀላቀል እስካሁን እድሉን ላላገኙና በትግሉ ላይ የራሳቸው የታሪክ አሻራ ማሳረፍ ለሚሹ ወገኖችም የተቀላቀሉን ጥር ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል። የቀረበላቸውን ጥሪ በመጠቀም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያን በአባልነት እንዲሁም በደጋፊነት በመመዝገብ ግንቦት 7 ትን መቀላቀል መቻላቸው ታውቋል። ትግሉ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ለታዳሚዎች በስፋት ያብራሩት ዶ/ር ብርሃኑ ተሰብሳቢዎቹ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግንቦት 7 ለነደፋቸው የትግል ስልቶች ማለትም ለሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ ዛሬ ነገ ሳይባል ምላሽ መስጠት መጀመር እንዳለበት ማሳሰብያ ማቅረቡ ታውቋል። በተለይ እነዚህን ስልቶች በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ በተቀናጀ ሁኔታ መተገበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊገባ የሚገባበት ሰአት አሁን ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ ይህንን በተሳካ ሁኔታ መተግበር ስንችል ጉጅሌዎቹን ከአገራችንንና ከህዝባችን ጫንቃ ማውረድ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ብርሃኑ ከተሰብሳቢው ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎችም አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ በኤርትራ በኩል እየተደረገ ያለውን ትግል አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት በተሰብሳቢዎች ዘንድ የነበረውን ብዥታ ማጥራት መቻላቸውንና ተሰብሳቢዎቹ እየተደረገ ላለው ትግል በጭብጨባ ድጋፍ መስጠታቸውን ከስፍረሰው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በመጨረሻም በስብሰባው ላይ በጠላት እጅ ወድቀው የሚገኙት የንቅናቄያችን ዋና ፀሐፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች በስፋት መወሳታቸውን ለማውቅ የተቻለ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ የአቶ አንዳርጋቸው ስራዎች ሲቀርቡ አብዛኞቹ በሐዘን እና በቁጭት ሲያነቡ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በስብሰባው መገባደጃ ላይ ለጨረታ የቀረበው የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ፎቶግራፍም በከፍተኛ ገንዘብ መሸጡ ታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ በጋራ እጅ ለእጅ በመያያዝ እየተደረገ ያለውን የነፃነት ትግል ከዳር ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን በቃለ መሐላ ካረጋገጡ በኋላ ስብሰባው መፈጸሙም ታውቋል

ኤልያስ ገብሩ ዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተጠራ


ደስ ባለው ጊዜ ክስ የሚቀሰቀስ መንግሥት
እንግዲህ፣ ‹‹ማዕከላዊ ናና ክስህን ውሰድ›› ተብያለሁ
Elias-Gebru6
ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ሞባይል ስልኬ አቃጨለች፡፡ ከጎኔ ወዳጄ አቤል አለማየሁ ነበር፡፡ የመስመር ስልክ ነው፡፡ አነሳሁት፡፡ ‹‹አቶ ኤልያስ›› የሚል የሴት ድምጽ አደመጥኩ፡፡ ‹‹አዎን›› በማለት መለስኩላት፡፡ ‹‹ቆይ አንዴ መስመር ላይ ጠብቅ›› አለችኝ፡፡


ወዲያው አንድ ወንድ አነሳና ሰላምታ ሰጥቶ አናገረኝ፡፡ የሚደውለው ከፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ጠቆመኝና ‹‹ባለፈው ተቋርጦ የነበረው ክስህ ስለተዘጋጀ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቁጥር 76 መጥተህ ውሰድ›› አለኝ፡፡ ስለጉዳዩ ጥቂት ቃላቶች ተለዋወጥን፡፡ 
‹‹እሺ ሰሞኑን መጥቼ እወስዳለሁ›› አልኩት፡፡ ‹‹ዛሬም የምትችል ከሆነ መምጣት ትችላለህ›› አለኝ፡፡ ጎሳዬ ሲልም ስሙን ነገረኝ፡፡


…በውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ መታሰር ሳይኖርብህ ትታሰራለህ፡፡ ዋስትና መከልከል ሳይኖርብህ ትከለከላለህ፡፡ ዳኛ የሰጠው የተጨማሪ የምርመራ ቀን ሳይደርስ ‹‹ስንፈልግህ ትመጣለህ፤ ዋስ አምጥተህ ውጣ›› ትባልና ከእስር ትለቀቃለህ፡፡ ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ ትጠራና ‹‹ከስህ ተዘጋጅቷል ና›› ትባላለህ፡፡ …ነገ የሚሆነውን ነገር ደግሞ አታውቅም፡፡ …እንግዲህ እንዲህ ነች የዛሬዋ ኢትዮጵያ!


ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

‹‹ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አይሰራም፤ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን፡፡››

በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ ጫናው በርትቷል

• ‹‹ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አይሰራም፤ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን፡፡›› 
የብአዴን አመራሮች

በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት የሚደርስባቸው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ጸሃፊ የሆነው ጠበቃ ሳሙኤል አወቀ በእሱና በሌሎች የፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ ዛቻ እንደሚፈጸምባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ ቢሮ በ2006 ዓ.ም የእቅድ ግምገማ እና የ2007 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም እቅድ በተወያየበት እና የሁሉም ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የስራ ሂደት ባለቤቶች በተገኙበት፣ ‹‹ሳሙኤል አወቀ የሚባል በጥብቅና ሽፋን የመሬት ፖሊሲውን የሚታገል፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊ አርሶ አደሮች ጥብቅና የሚቆም፣ ከአሸባሪ ጋር ግንኙነት ባለው ድርጅት አመራር የሆነን ግለሰብ በህግ ሽፋን እስር ቤት እንዲወርድ ያላደረገ አቃቤ ህግ አቃቤ ህግ አይደለም›› ተብሎ በህግ ስም እርምጃ እንዲወሰድበት ትዕዛዝ መተላለፉን ጠበቃው ገልጾአል፡፡
በተለይ የደብረማርቆስ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት አቃቤ ህጎች ዋነኛ ችግራቸው ጠበቃ ሳሙኤልን በህግ ስም ማስቀጣት አለመቻላቸው እንደሆነ ተገምግመዋል ተብሏል፡፡ ጠበቃው ወዲያውኑ የፈጠራ ክስ እንደተመሰረተበት፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ‹‹ለፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ባለመሆኑ›› በሚል መከሰሱንና ባልተከራከረበት ፍርድ ሂደትም 8000 ብር ቅጣት እንዲከፍል እንደተወሰነበት ገልጾአል፡፡
ጠበቃው በ28/1 እናርጅ እናውጋ ለቀጠሮ ባቀናበት ወቅትም የእናርጅ እናውጋ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ አቶ ስራው በረኩ እና የብአዴን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ መኳንንት አበበ እና ሌሎችም ከፖሊስና ከጸጥታ የመጡ አመራሮች ‹‹ምን ልታደርግ ነው? ልትቀሰቅስ ነው?›› በሚል እንዳዋከቡትና አቶ ስራው በረኩ ‹‹አንጠልጥዬ ነው እስር ቤት የማስገባህ፡፡ ማንም ሊያድንህ አይችልም›› ብለው እንደዛቱበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆነህ በፍትህ ስርዓቱ መገልገል አትችልም፣ ጥብቅናህን መልቀቅ አለብህ፣ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ትጽፋለህ፣ የፍትህ መምሪያ ሃላፊውን (ጸጋየ መንግስቴ) ችግር እንደሚፈጽምብህ በነገረ ኢትዮጵያና በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ጽፈህበታል፣ እንዲህ እያደረክ መኖር አትችልም፣ አንተን ገሎ መጣል ቀላል ነው፣ ለነፍስህ የምታዝን ከሆነ አገር ልቅቅ›› ብለው እንደዛቱበት ገልጾአል፡፡
ሌሎች ጠበቃ ጓደኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሄዱ ‹‹እሱ ማለት ሰማያዊ ነው፡፡ ሰማያዊ ደግሞ የአክራሪ ሙስሊም ፓርቲ ነው፡፡ እናንተ ለምን ከእሱ ጋር ትሄዳላችሁ?›› ብለው እንደሚያስፈራሯቸውና ደንበኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሰሩ ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ጠበቃው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ጠበቃውን ጨምሮ ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባል ሆነው ማደራጀት መብታቸው መሆኑን ሲገልጹ የብአዴን አመራሮች ‹‹እናንተ እኛን ስለማትረዱን ነው፡፡ እኛ ጋር ሰላማዊ ትግል የሚባል አይሰራም፡፡ ወንድ ከሆናችሁ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን›› በሚል ለህግ የማይገዙና ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነት እንደሌላቸው አሳይተውናል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲና አመራር የሆኑ ነጋዴዎች ከፓርቲው እንዲለቁ ለማድረግ የንግድ ድርጅታቸውን እንደሚዘጉ እያስፈራሩ እንደሆነ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም አቶ ይኸይስ ቀጸላ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ‹‹ሻይ ቤት ከፍተው እያደራጁ ነው፡፡ የንግድ ድርጅቱን እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበታል፡፡ በመሆኑም ካላረፉ ሻይ ቤቱን እንዘጋዋለን›› እያሉ እንደሚያስፈራሩ ታውቋል፡፡
የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የገዥው ፓርቲ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እርምጃዎች እየተጠናከሩ ቢሆንም እርምጃው እነሱ ተጽዕኖ በመፍጠራቸው የመጣ በመሆኑ ይበልጡን እንደሚያበረታታቸውና የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቶ መኳንንት አበበን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን የእጅ ስልካቸው ላይ በመወደል ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

lørdag 18. oktober 2014

Breaking News: የቀድሞው የኦነግ መሪ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ኢትዮጵያ ገቡ


(ዘ-ሐበሻ) ዶክተር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ መግባታቸውን የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች አረጋገጡ::
የኦነግ መስራቾችና አንጋፋ መሪዎች፣ እነ ዶ/ር ዲማ ነግዎ፣ አቶ ሌንጮ ለታ የመሳሰሉት፣ የኦሮሞ ጥያቄ የመገንጠል ሳይሆን የዴሞክራሲ ጥያቄ ነዉ በሚል፣ ራሳቸውን ከኦነግ አግልለው፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፎረም (ኦዴፍ) የሚባል ድርጅት ማቋቋማቸውን ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ መግለጹዋ ይታወሳል::
የቀድሞው የኦነግ መሪ ዶ/ር ዲማ ነገዎ
የቀድሞው የኦነግ መሪ ዶ/ር ዲማ ነገዎ

ዘንድሮ በሚደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ለመሳተፍና ድርጅቱንም በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ወደ አዲስ አበባ እንዳቀኑ የገለጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ጉዳዩ ብዙዎችን ማስገረሙን ገልጸዋል::

በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ አማካኝነት በተለይ በሚኒሶታ የቀድሞ የኦነግ መሪዎችን ለማግባባት ከፍተኛ ሥራ ይሰራ እንደነበር ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም በፎቶ ግራፍ በተደገፈ ማስረጃ ስትዘግብ የቆየች ሲሆን በዶ/ር ዲማ ነገዎና በኦቦ ሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴፍ ለኦሮሞ ሕዝብ አዲስ የትግል ራዕይ አለኝ በሚል ሃገር ቤት ገብቶ ለመታገል መወሰኑንና ከዚህ በኋላም የኦሮሞ ሕዝብ ስለመገንጠል ሳይሆን በአንድነት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚኖርበትን መንገድ ፈጥሮ ለመታገል መወሰኑን መግለጹ ይታወሳል::
በቀጣዩ ዲሴምበር ወር አካባቢ አቶ ሌንጮ ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ በሰፊው ሲወራ የቆየ ቢሆንም ምክትላቸው ዶ/ር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ ቀድመው ገብተው ድርጅቱን በኢትዮጵያ ለማስመዝገብ እየተሯሯጡ ይገኛሉ ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ኦዲኤፍ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚወዳደርም ጠቁመዋል::
ዶ/ር ዲማ ነገዎ በሽግግር መንግስት ወቅት በማስታወቂያ ሚ/ርነት ያገለገሉ መሆናቸው ይታወሳል::
ይህን ተከትሎ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች በሚኒሶታ አካባቢ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ያነጋገሩ ሲሆን የዶ/ር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ መግባትና የኦዲኤፍ በምርጫ መሳተፍ በገደል አፋፍ ላይ የነበረውን የወያኔ/ኢሕ አዴግ መንግስት ነብስ ይዘራበታል ሲሉ ይህን ውሳኔ ይተቻሉ:: እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉትም ኢሕ አዲኤግን በኃይል ለመጣል የመጨረሻው ሰዓት ላይ የደረሰ ቢሆንም የአቶ ሌንጮና የዶክተር ዲማ ኦዲኤፍ ኢትዮጵያ መግባት ኢሕ አዴግ ለሚፈልገው ና በምርጫ ስም ለሚያገኘው የፕሮፓጋንዳ ጥቅም አንድ አጋዥ ይሆንለታል ሲሉ ትችታቸውን ያስከትላሉ::
በሌላ በኩል የኦዲ ኤፍ ኢትዮጵያ መግባት ለኦሮሞና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ድል ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለይ እነዚህ የኦነግ መስራቾች የመገንጠል አላማቸውን ትተው በአንድነት ለመታገል መወሰናቸው ለሁሉም የምስራች ነው ይላሉ::
የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች በዚህ ዙሪያ የምትሰጡትን አስተያየት እንጠብቃለን::
የኦዲኤፍን ውሳኔ እንዴት አዩት?

“አቅም ግንባታ” እና “የወፍጮ ቤቶቹ” የዲግሪና የዲፕሎማ ሚና በኢህአዴግ

“የዲግሪና የዲፕሎማ ወፍጮ ቤቶች”

ተፈጭና ተመረቅ – አስተምሮ መለስ
degree mill
በእንግሊዝኛው አጠራር የዲፕሎማ/የዲግሪ ወፍጮ ቤት (diploma/degree mills) ይባላሉ፡፡ በርካታዎቹ ሠለጠነ በሚባለው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ “ወፍጮ ቤቶች” የ“ትምህርት መረጃ” ለማግኘት በጣም ቀላል ነው፡፡ ዋናው መስፈርት አስፈላጊውን “የትምህርት ክፍያ” መፈጸም ብቻ ነው ፡፡ ከዚያ በወርቅ ቅብ የተንቆጠቆጠ “የባችለር” ወይም “የማስተርስ” ወይም “የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ.)” ዲግሪዎችን ማፈስ ነው፡፡ በቀጣይ የሚሆነው የ…ሚ/ር ወይም የ…ሚኒስትር ደኤታ ወዘተ መሆንና “በሹመት መዳበር” ነው፡፡ ከዚያ ህዝብ አናት ላይ “በስያሜ” ተቀምጦ መጋለብ ነው።
ከዓመታት በፊት የአሜሪካው የመንግሥት ተጠያቂነት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ አካሂዶ ነበር፡፡ ያገኘውንም ውጤት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርብ “የወፍጮ ቤቶቹን” አሠራር በግልጽ ዘርዝሯል፡፡ ለምርመራው ያነሳሳው በአሜሪካ የመንግሥት መ/ቤቶች ውስጥ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ የሚሠሩ “ከወፍጮ ቤቶቹ” የትምህርት ማስረጃ የሸመቱ መኖራቸውን በማረጋገጡ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቢሮው ያቋቋመው መርማሪ ቡድን ለሦስት ዓመታት በርካታ ዲፕሎማዎችንና ዲግሪዎችን ከአሜሪካና ከሌሎች የውጭ አገራት በቀላሉ በድብቅ ለመግዛት መቻሉን አረጋግጧል፡፡
አሠራሩን እንዴት እንደሆነ ሲገልጽም፤ ከመርማሪ ቡድን አባላት አንዱ ተማሪ በመምሰል “የትምህርት ተቋማቱን” ዲግሪ እንደሚፈልግ መስሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ክፍያ ካጠናቀቀ መግዛት እንደሚችል “ወፍጮ ቤቶቹ” በነገሩት መሠረት የሳይንስ ባችለር ዲግሪ በባዮሎጂ እንዲሁም የሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በሜዲካል ቴክኖሎጂ “ሸምቷል”፡፡ ክፍያ ለጨመረም ሥራ ቀጣሪዎች የትምህርት ማስረጃውን ለማረጋገጥ ሲደውሉ ሊያነጋግሩበት የሚችሉበት የስልክ መስመር አብሮ ይሰጣል፤ በዚሁ አንጻር በየዲግሪዎቹ “የማዕረግ ተመራቂ” መሆን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ በአሜሪካ!!!
diploma-millተማሪዎች ክፍል ገብተውም ሆነ በተልዕኮ ትምህርታቸውን የመከታተል ግዴታ እንደሌለባቸው፤ ሙሉውን ክፍያ በአንድ ጊዜ ሲፈጽሙ ለትራንስክሪፕት እንዲያመች ክፍያው በኮርስ ተሸንሽኖ ደረሰኝ እንደሚቆረጥላቸው በምርመራው ተደርሶበታል፡፡ ክፍያው በጨመረ ቁጥር የሚገኘው አገልግሎት እየጨመረና ዲግሪው “እውነተኛ” እየመሰለ እንደሚሄድም ተጠቁሟል፡፡
እንዲህ ያለው ምርመራ ከተካሄደ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም አሠራሩ ቀጥሏል፡፡ “ወፍጮ ቤቶቹ” አሁንም ዲግሪ መቸብቸባቸውን አላቆሙም፡፡ ከዚህም አልፎ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የሚሆን ጽሁፍ (ዲሰርቴሽን) አብሮ ተገዝቶ በገዢው ስም እንደሚሰጥ፤ አከፋፈሉ ካማረም ጽሁፉ የሸማቹ መመረቂያ ጽሁፍ ሆኖ በስሙ በኢንተርኔት ይበተናል። እንዲህ ያለው አሰራር አሁን ድረስ ይሰራበታል፡፡ በዚሁ “ወፍጮ ቤት” አማካይነት ተፈጭተው “ዶ/ር” እየተባሉ የመጠራት ጥማት ያላቸው በተለይ የሦስተኛው ዓለም ባለሥልጣናት ገበያውን መቆጣጠራቸው ይታወቃል፡፡
“አቅም ግንባታ” እና “የወፍጮ ቤቶቹ” ሚና በኢህአዴግ
ወደ አገራችን ስንመለስ “በነጻአውጪ” ስም በረሃ የቆዩና አጫፋሪዎቻቸው ለሥልጣን ሲመቻቹ አስቀድሞ የሚደረገው የ“አቅም ግንባታ” ማከናወን ነው። በዚሁ መለስ በነደፉት አቅም አልባ የሚያደርግ የ“አቅም ግንባታ” በርካታዎች “ከወፍጮ ቤት” ደጅ እንዲገረደፉና እንዲፈጩ ተደርገዋል። አሁንም ለመፈጨት ተራ የሚጠብቁና እየተፈጩ ያሉ አቅም አልባ ካድሬዎቹ ቁጥር ቀላል አይደለም። በዚህ አሠራር ቀዳሚዎቹ የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም የሌሎቹ ድቃይ ድርጅቶች አባላትም በሸመታው ዋንኛ ተሳታፊ መሆናቸው ራሳቸው ሸማቾቹ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲናገሩ በአንድ ወቅት ያገኙት በመከላከያ ሚ/ር የሚሠራ የህወሃት ባለስልጣንን የትምህርት ሁኔታ ይጠቅሳሉ፡፡ ግለሰቡ በትግራይ ነጻ አውጪነት ተሰልፎ በነበረበት ጊዜ ራሱ እንደተናገረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አላጠናቀቀም ነበር፡፡ “ከድል” በኋላ ግን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ብቻ ሳይሆን የኮሌጅ ትምህርቱን “አጠናቅቆ” በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንደተቀበለ ወዲያዉኑ የማስተርስ ዲግሪውን በመቀበል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁም መከላከያ ሚ/ር ውስጥ በኮሎኔል ማዕረግ የመምሪያ ኃላፊነት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግሯል፡፡ “ይህንን ሁሉ በርካታ ዓመታት የሚፈጅ ትምህርት እንኳን ተምሮ፣ በታክሲ ወይም በአውሮፕላን ተሳፍሮ ቢጋልብ፣ እንደ ጥይት አረር ቢተኮስ ሊደርስበት አይችልም፤ ከብርሃን ፍጥነት ጋር በሚስተካከል መተኮስ ለዚህ ሁሉ በመብቃቱ “የብርሃን ዲግሪ” ልንለው እንችላለን” በማለት አስተያየት ሰጪው ተሳልቀዋል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ በውጭ ካሉት “የዲግሪ ወፍጮ ቤቶች” የሚሻውን የትምህርት ማስረጃ፣ ለሚወደው ለመሸመትና ያለከልካይ ለመጠቀም እንዲችል “ባለራዕዩ” መለስ ሥልጣን ላይ እንደወጡ ያደረጉት የመንግሥት አመራራቸውንም ሆነ የአስተዳደር ፖሊሲያቸውን አብጠልጥለው ብትንትኑን ሊያወጡ የሚችሉ 42 የኢትዮጵያን ድንቅ ምሁራን በዱሪ መሐመድ ሁለት መስመር ደብዳቤ ማባረር ነበር፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የተደገሰው አዲሱ “የአቅም ግንባታ” መሆኑ ነው። ከዚያም “ሲቪል ሰርቪስ” የተባለ “የዲግሪ/ዲፕሎማ ወፍጮ ቤት” አገር ውስጥ ከፈቱ፡፡ የህወሃት ሹማምንት ከውጪዎቹ “ወፍጮ ቤቶች” የፈረንጅ ዲግሪ ሲገዙ የተላላኪዎቹ ፓርቲዎች አባላት ደግሞ “ከአገር ውስጥ የመለስ ወፍጮ ቤቶች” እንዲሸምቱ ተደረገ፡፡ecsc
ይህ በሥርዓትና በጥናት የተደረገ አካሄድ መለስ በአንድ ወቅት ሚኒስትሮች ሲሾሙ በወቅቱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተሹዋሚዎቹን የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ችሎታ በዝርዝር ይቅረብልን፤ ለቦታውም እንዴት ሊመጥኑ እንደቻሉ ይነገረን በማለት እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡ “በዲግሪ ወፍጮ ቤት ምሩቃን” ራሳቸውን ከብበው “ቆራጡ፣ አስተዋዩ፣ ብልሁ …” መሪ ሲባሉ የነበሩት መለስ ሲመልሱ መሐይምም እንኳን ቢሆን የኢህአዴግን ዓላማ እስካስፈጸመ ድረስ ሚኒስትር መሆን ይችላል ብለው ነበር፡፡
መለስ የከተማ ጥሩንባ ነፊዎች ነበሩዋቸው። ቅጠል ከሚመነዠክበት የሴሰኞች ሰፈር ጀምሮ እስከ ላይ መለስን ሲያውድሱ የሚውሉ ድርጎ ለቃሚዎች ነበሩ። እነዚህ ድርጎ ለቃሚዎች “አንድ መለስ ብቻ” በማለት የመለስን ዝናና “ልዩ ብቃት፣ ስማርት መሆን” ሲሰብኩ ይውላሉ። መለስ ባይኖር ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት፣ ህወሃት የሚባለው “ነጻ አውጪ” አፍታ እንኳ እድሜ ሊኖረው እንደማይችል ይጠነቁላሉ። መለስ ዋለታና ምሰሶ ባይሆኑ አገር ጨለማ እንደሚውጣት ያስፈራራሉ። ወሬ ፈጣኑ እየነጎደ መለስን አገነነ።
መለስ በባህሪያቸው የሚፎካከራቸውና እሳቸው የሚያስቡትን አስቀድሞ የሚረዳ የትግል አጋር ስለማይወዱ ህወሃት ላይ የወሰዱት የማጽዳት ዘመቻ ምስክር ነው። እነ ተወልደ /ውህዳኑ/ ብዙ ማለት ይችላሉ። ታዲያ የሚፎካከሯቸው ከሌሉ “አላዋቂዎችን ሰብስበው ገነኑ” እንዳይባል በዙሪያቸው ያሉትን ሚስታቸውን ጨምሮ ከ“ወፍጮ ቤት ዲግሪ” ሸመታ ደጅ ማሰለፍ ነበረባቸው። በዚሁ እንደ ግንፍልፍል ምግብ ባስቸኳይ በክፍያ ብቻ በሚሰጥ ዲግሪ ያንበሸበሿቸውን ካድሬዎች ሰብስበው ሲፈላሰፉ ብቻቸውን አዋቂ ሆነው አረፉት፤ “ስማርት መሪ ተባሉ”። በዚያው ስሜት “ተሰው”፤ ይህ ቀድሞ የተሰራና የተፈጠረ ስሜት ካድሬውን ውጦት ስለኖረ የመለስ “መሰዋት” ማረፊያው የማይታወቅ ጉድጓድ ሆነባቸው። ከመለስ ይልቅ ራሳቸው ላይ ሞትን አውጀው በሙት መንፈስ ለመመራት ተማማሉ። ሲማሩ ሳይሆን ሲፈጩ መኖራቸውን መሰከሩ።
online-college-scamsየመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የት እንዳገኙ የማይታወቀው መለስ የሥልጣን መንበሩ ላይ እንደተፈናጠጡ በትምህርት መስክ ራሳቸውን ለመቻል ባስመዘገቡት ፈጣን ሪኮርድ መሠረት በኢትዮጵያ ሃብት በከፈሉት ገንዘብ ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎች ከአውሮጳ በፖስታ ቤት ተልኮላቸዋል፡፡ ከግለታሪካቸው ጋር አብሮ የሚጠቀሱት የትምህርት ማስረጃዎችም እነዚሁ በፈጣን መልዕክት አገልግሎት የተላኩላቸው የፖስታ “ዲግሪዎች” ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጭንቅላት ለሁለት ዓስርተ ዓመታት ሲበጠብጡ ቆይተው በመጨረሻም የራሳቸውን በጥብጠው “የተሰዉት” መለስ አጠገባቸው በራሳቸው ልክ እያሰፉ “በፈጠሯቸው” የዲግሪና የዲፕሎማ ሸማቾች ተከብበው በመኖራቸው ከዝንጀሮዎች መካከል እንደተገኘች “ቆንጆ” እና “ብልጥ” ጦጣ አድርጓቸው እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ።
በምዕራቡ ዓለም በተለይ በአሜሪካ እነዚህ የዲፕሎማ ወፍጮ ቤቶች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ እጅግ አደናጋሪ ናቸው፡፡ እነዚህ “ኮሌጆች” ለመግቢያ የሚያስፈልጉ ፈተናዎችን አይጠይቁም፡፡ በተለይ ለማስተርስ የዲግሪ ትምህርት መግቢያ የሚያስፈልጉትን ዓለምአቀፍ ዕውቅና ያላቸውን GMAT ወይም GRE ፈተናዎች ተመዝጋቢው እንዲወስድ አይጠይቁም፡፡ አቶ መለስ በፖስታ ከተላከላቸው ዲግሪዎች አንዱ MBA – Master of Business Administration ሲሆን ይህንን ዲግሪ ለማግኘት አብዛኛዎቹ ዕውቅና ያላቸው ተቋማት ተመዝጋቢው GMAT (Graduate Management Admission Test) ፈተና እንዲወስድ የግድ ይላሉ፡፡ ዲግሪው በፖስታ የሚላክ ከሆነ ግን ፈተናውን የመውሰድ አስፈላጊነት አይኖረውም፡፡ ፓርቲያቸው በግድ መሪ ሁን እያለ የሥራ ጫና እያበዛ የሰዋቸው መለስ ከፈተና አምልጠው ለዲግሪ መብቃታቸው ለሁለተኛ ሙት ዓመታቸው የተሠራው “ያልተጠኑ ገጾች” ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ሳይካተት ያመለጠ “ያልተጠናው የመለስ ገጽ” ነው፡፡
አቶ መለስ ሁለተኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በፖስታ ቤት ፈጣን መልዕክት በተቀበሉበትdog and cat 2004እኤአ በአሜሪካ በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ዳላስ ከተማ ከሚገኝ Trinity Southern University ከተባለ “የዲግሪ ወፍጮ ቤት” ኮልቢ ኖላን የተባለ ድመት $299 ዶላር በመክፈል የባችለር ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ በድመታቸው ስም ማመልከቻውን ያስገቡትና በወቅቱ “ወፍጮ ቤቶቹን” እየመረመሩ የነበሩት የፔንስቬኒያው ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ጄሪ ፓፐርት ነበሩ፡፡ ድመቱ የማመልከቻ ደብዳቤውን ሲልክ ከዚህ በፊት ሌሎች ኮርሶችን የወሰደ መሆኑን እንዲሁም ልጅ በመጠበቅ፣ ትኩስ ምግብ መሸጫ ቤት በአሻሻጭነትና በጋዜጣ አዟሪነት የሰራ መሆኑ በተጨማሪ ተገልጾ ነበር፡፡ ይህንን የትምህርት “ብቃት” እና “አመርቂ የሥራ ልምድ” የመረመረው “ዩኒቨርሲቲ” ለኮልቢ በላከው የምላሽ ደብዳቤ የሥራ ልምዱን እና በተጨማሪ የወሰዳቸውን ኮርሶች በመመልከት ለExecutive MBA ብቁ ስለሆነ $100 ዶላር ከጨመረ የባችለር ዲግሪውን ወደ [አቶ መለስ ዓይነት] MBA ዲግሪ እንደሚያሳድግለት ማረጋገጫ ልኮለታል፡፡
በ2010ዓም ደግሞ ለታወቀ የሕግ ኩባንያ የሚሠሩ ማርክ ሃዋርድ የተባሉ የሕግ ባለሙያ ውሻቸው ሉሉ ከኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ MBA ዲግሪ እንዲቀበል አድርገውታል፡፡ ሉሉ “ዲግሪውን” በማዕረግ መቀበል መቻሉ በወቅቱ አብሮ የተነገረ ሲሆን “በዩኒቨርሲቲውም” በአካል ተገኝቶ ክፍል ስለመከታተሉ (ስለውሻ እንደሚመሰክር ያላወቀው ምስክር) በሃሰት መስክሮለታል፡፡
ከላይ ለማለት እንደተሞከረው “የወፍጮ ቤቶቹ” መብዛት አደናጋሪነታቸውን የሰፋ አድርጎታል፡፡ በተለይም ደግሞ ከሚሰበስቡት ገንዘብ አንጻር የሚያካሂዱት የተጠና የማስታወቂያ ሥራ “እውነተኛ” እንዲመስሉ አድርጓቸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ መረጃ ለመሰብሰብ የሚፈልጉ በተለያዩ ፎረሞች ላይ ምርምር ሲያደርጉ “ወፍጮ ቤቶቹ” ያሰማሯቸው “ካድሬዎች” የሚሰጡት ምላሽ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትክክለኛ ምላሽ ይወሰዳል፡፡
በዚህ የዲግሪ “ወፍጮ ቤት” ሙያ ከተካኑት መካከል የሚጠቀሱት ካፔላ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ እጅግ በርካታ ክሶችና ወቀሳዎች ደርሰውበታል፡፡ የሃሰት ዲግሪ በመስጠት፣ ብቃት የሌላቸው መምህራን በመቅጠር፣ የሚቀጥራቸው መምህራን ከአሜሪካ ውጪ የመጡና የትምህርት ማስረጃቸውን እርግጠኝነት መናገር የማይቻል መሆኑ፣ በቂ ገንዘብ እስከተከፈ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት ዲግሪ (ዶክትሬትም ቢሆን) እንደሚሰጥ፣ … fake-diploma1እጅግ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በአሜሪካ የሚገኘው ብሔራዊው የሕዝብ ሬዲዮ (NPR) ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የምርመራ ዘገባም ሰርቶበታል፡፡ “ዩኒቨርሲቲው” ብዙውን ነገር ለማሻሻል የሞከረ ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ግን እየወሰደ ያለው እርምጃ ባሰማራቸው የማስታወቂያ ካድሬዎቹ አማካኝነት ስሙን እያደሰ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ካፔላ ዩኒቨርሲቲ እያተመ በፖስታ የሚልከው ዲግሪ ለብዙ ከፋዮች ደርሷል፤ የአንዳንዶችም “ማዕረጋቸውን” ከአቶነት ወደ “ዶ/ር” አስቀይረውበታል፡፡ አድዋ ተወልደው ያደጉትና የህወሃት የስለላ ሞተር እንዲሁም ዋንኛ የስልክ፣ የሬዲዮ፣ ወዘተ ሞገድ ጠላፊ የሆኑት “ዶ/ር” ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የካፔላ ዩኒቨርሲቲ “ምሩቅ” ናቸው፡፡ አሽቃባጭ ደጋፊዎቻቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሃርቫርድ የተቀበሉ ለማስመሰል በየቦታው በሚለጥፉት ግለህይወታቸው ላይ ፕሮፓጋንዳ ለመንፋት ቢሞክሩም ካፔላ “ወፍጮ ቤት” ዩኒቨርሲቲ ግን “ዶ/ር” ብዬ ለዚህ ያበቃኋቸው እኔ ነኝ በማለት በማስረጃ የተደገፈ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
ገዢው ኢህአዴግና ቁንጮው ህወሃት በዚህ መልኩ ታማኞቹን “አቅም እየነሳ” በየዘርፉ አሰማርቷቸዋል። በሽታውና ችግሩ ለህወሃት ባይሆንም አገርን ጤና እየነሳ ነው። ህወሃት እንደስሙ መቼ ነጻነቱን አውጆ አገር እንደሚሰራ ባይታወቅም በራሱ ምድር፣ ለራሱ “የተስፋ ቀበሌ” የተለያዩ “ስፔሻል” የሚባሉ እቅዶች እንዳሉት አይዘነጋም። በልዩ ክትትል የሚያስተምራቸው ተተኪ ካድሬዎችም እያመረተ ነው። የሚዋኝበት ሃብትም ሰብስቧል። ጉዞው ቀጥሏል። መለስ አስፈጪ የሆኑበት ወፍጮ የሚፈጫቸውና የተፈጩት ባለስልጣናት አልመው የሚያደቁት ህዝብ መጨረሻ ምን ይሆን? በዚህ ጉዳይ ላይ በውክልና ካድሬዎችን ወፍጮ ቤት /በሊደርሺፕ ስልጠና ስም/ የሚያጠምቁት ፕሮፌሰሩ ፓስተር ምን ይሉ ይሆን? “ተቋማቸው” በግልጽ ማስረጃ ከነፎቷቸው በዘረዘረው መሠረት ሃይለማርያም ደሳለኝ (ፊንላንድ በወጉ ተምረው በውክልና ሊደርሺፕ ተፈጭተዋል)፣ አባዱላ ገመዳ፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምዖን፣ አብዲ ሞሐመድ ዑመር፣ ጁነዲን ሳዶ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ሙክታር ከዲር፣ ሽፈራው ተክለማርያም፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አስቴር ማሞ፣ ድሪባ ኩማ፣ ዘነቡ ታደሰ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ አርአያ ገብረእግዚአብሔር፣ ኦሞድ ኦባንግ፣ … ዝርዝሩ ሊያልቅ አይችልም፡፡ እነዚህ ሁሉ በአገር ውስጡ “ወፍጮ ቤት” የተመረቱና “በሊደርሺፕ የተጠመቁ” ናቸው – የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጋፋ ምሁራን! እዚህ ላይ ከቅቅል ባቄላ ውስጥ አንድ ጥሬ እንደማይጠፋ አለመዘንጋቱ ይስተዋላል፡፡
ህወሃት በሚነዳት አገራችን አውራ ዶሮ “አኩኩሉ” ሲል በሚያሳይ ማስታወቂያ እስከ ገጠር ዘልቆ ብር እያመረተ ካለው ኮሌጅ ይቅርታ “ወፍጮ ቤት” ጀምሮ በበቅሎ ጀምረው በሃመር ገጠር ገብተው በራሪ ወረቀት የማሰራጨት ደረጃ የደረሱትን ማን ይመርምራቸው? የትምህርት ጥራት ገደል ገባ እየተባለ ደረት ሲመታ ማን ዋናውን ችግር ይንካው? አላቅሙ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር፣ አላቅሙ ሚኒስትር የሚሆን፣ አላቅሙ አገር የመምራት ጭነት የሚጫንበት … ሁሉም አላቅሙ በከመረው የውድቀት ክምር ይኮራል፤ በእርሱ አላዋቂነት አገርን ያከለ ታላቅ ነገር ሲወድምና ትውልድ ሲጠፋ ምንም አልሰማ ብሎት ደንዝዟል፤ ስብ ደፍኖታል፡፡ በውድመቱ ውስጥ ግን የራሱን ማንነት ጨምሮ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ አብረው እየወደሙ መሆናቸው አይታየውም፤ በሞራ የተሸፈነው ዓይኑ የሩቁን እንዳያይ ጋርዶታል፡፡ ይህ ውርደቱ ሊሆን ሲገባው እንዲያውም ኩራቱ ነው፡፡ በቃኝ፣ እኔ ለዚህ አልመጥንም፣ እስከዛሬ ያለ እውቀቴ ሳንቦራጭቅ ኖሬያለሁና ይቅርታ የሚል ትውልድ ሳናይ ሁለት መንግስታትና አንድ ቅኝ ገዢ ነዱን። ይህ መሰሉ በሽታ የገዢዎቻችን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎቻቸውም መሆኑ ችግሩን እጅግ የባሰ አድርጎታል፡፡ ግን እስከመቼ?
አሜሪካ ፓርላማ/ምክር ቤት ስላላት ጉዳዩን መረመረች። በጀት መድባ ሰለለች። መረጃውን በማስረጃ አረጋግጣ እውነቱን ደረሰችበት። እኛ ምን ፓርላማ አለን? ቢኖረንስ ማንን ሊመረምሩና ሊያስመረምሩ? አስፈጪውና ተፈጪው ብቻ ሳይሆን የወፍጮ ቤቱ ባለቤት ሁሉ አብረው ቀጥለዋል፤ ወፍጮው አሁንም ይፈጫል። የቀድሞውን አስፈጪ የተካቸው በግልጽ አልታወቀም። ለኢትዮጵያ አቅም ግንባታ መፈጨት አማራጭ የለውም። “ተፈጭና ተመረቅ” አስተምህሮተ መለስ!! ለጊዜው!!

fredag 17. oktober 2014

ሰማያዊ፣ መኢዴፓና ኢብአፓ የምርጫ ቦርድን ስብሰባ ረግጠው ወጡ

ከደቡብ ኅብረት ፕሮፌሰር በየነ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል
eth election

ምርጫ ቦርድ በጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመወያየት በጊዮን ሆቴል የጠራውን ስብሰባ “ጥያቄዎቻችን የሚመልስ አይደለም” በሚል የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ በተጨማሪም የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በትናንትናው ዕለት ከምርጫ 2007 ዓ.ም በፊት ውይይት ሊደረግባቸውና ሊፈቱ ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ ያስገቡ ቢሆንም በዛሬው ስብሰባ በደብዳቤ ካሳወቋቸው ችግሮች ይልቅ የጊዜ ሰሌዳ ቅድሚያ የተሰጠው በመሆኑ የምርጫ ምህዳሩን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ስብሰባውን ረግጠው ከወጡት መካከል የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ዋና ጸኃፊ ወ/ት መሊሃ ጀሃድ “ትናንትና 12 ፓርቲዎች ሆነን ፈርመን ያስገባነው ደብዳቤ ነበር፡፡ በዚህ ደብዳቤ ባነሳናቸው ጥያቄዎች ላይ መልስ ካልተሰጠን በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ እንደማንነጋገር ገልጸን ነበር፡፡ ቦርዱ ደግሞ ትናንትና ባስገባነው ደብዳቤ ላይ ከመነጋገርና ለጥያቄዎቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ነው የምንነጋገረው አለን፡፡ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንድንነጋገር ሲያደርጉ እኛ በአካሄድ ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲሰጥ ጠየቅን፡፡ የቦርዱ ተወካዮች እሱን በሌላ ጊዜ ስብሰባዎች ላይ እንፈታዋለን፣ ዛሬ ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንነጋገር በማለታቸው ስብሰባውን ረግጠን ወጥተናል” ስትል ረግጠው የወጡበትን መነሻ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡
eth electionበተመሳሳይ የመኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ኑሪ ሙደሂር “ምርጫ ቦርድ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አደርጋለሁ የሚለው አባባሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጥያቄዎችን አቅርበን ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ የዛሬ 5 አመትም ጠይቀናል፡፡ ትናንትም በጋራ በደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ከጀመረ 5 አመቱ ነው፡፡ ይህን ቅስቀሳ የሚያደርገው በመንግስት ገንዘብ ነው፡፡ የእኛ ጥያቄ የምርጫ ምህዳሩ መስፋት አለበት ነው፡፡ ትርጉም ያለው ምርጫ መደረግ አለበት ነው የእኛ እምነት፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው እኛ ስብሰባውን ረግጠን የወጣነው” ብለዋል፡፡
ሌላኛው የመኢዴፓ ተወካይና የፓርቲው ዋና ጸኃፊ አቶ ዘመኑ ሞላ በበኩላቸው “እነሱ ካቀረቡት የጊዜ ሰሌዳ ይልቅ የሚቀድመው ሜዳውን ማስፋት ነው፡፡ ትናንትና 12 ፓርቲዎች ተፈራርመን ያስገባነው ደብዳቤ ነበር፡፡ እኛም ቀድመን በተነጋገርነው መሰረት የጊዜ ሰሌዳው ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን የለበትን የሚል አቋም ይዘናል” ሲሉ ስብሰባውን ካዘጋጀው ምርጫ ቦርድ ጋር ያላቸውን ልዩነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ በሚቀጥለው ስለ ችግሮቻችሁ ቁጭ ብለን እንወያያለን በሚል የማባበል ስራ እንደያዘ የገለጹት አቶ ዘመኑ “የ2002ትን ምርጫን ገምግመናል፡፡ ፓርቲዎች ያስገባነው ደብዳቤ አለ፡፡ አሁንም ገዥው ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሜዳውን እያጠበበና ራሱ ብቻ እየተጫወተበት ይገኛል፡፡ ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ ከታሰበ እናንተም ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቆም ብላችሁ አስቡበት ብለናቸዋል፡፡ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ቅድሚያ ስላልተሰጣቸው ስብሰባውን ረግጠን ለመውጣት ተገደናል” ብለዋል፡፡
ዘግይቶ በደረሰን መረጃ የኢትዮጵያ ማህረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ተግልጾአል፡፡
በትናንትናው ዕለት 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ከምርጫ ከጊዜ ሰሌዳው በፊት በውይይት መፈታት አለባቸው ብለው ያመኑባቸውን ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ (ምንጭ፤ ነገረ ኢትዮጵያ)

torsdag 16. oktober 2014

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ወገንተኝነቱን የሚያሳይበት ወቅት አሁን ነው!

ዘረኛውና ፋሽስታዊው የህወሓት አገዛዝ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት በዘርና በፓለቲካ ወገንተኝነት በመከፋፈል ሹመቱና ጥቅማ ጥቅሙን ለራሱ ወገን፣ ችግሩንና መከራዉን ግን ለሌላው ኢትዮጵያዊ ያደለ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ሳይማሩና ሳይሰለጥኑ የጄኔራልነት ማዕረጎችን በሙሉ ሰብስበው የወሰዱት የህወሓት አባላት መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።
በወያኔ መዳፍ ውስጥ እየተሰቃየች ባለችው ኢትዮጵያችን ውስጥ በዘርም ይሁን በፓለቲካ አመለካከት ከህወሓት የተለዩ ኢትዮጵያዊያን ቢማሩም ቢሰለጥኑም ለከፍተኛ አመራርነት እንደማይበቁ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያየነው ነው። አገዛዙ ቅራኔ ውስጥ በገባባቸው ቦታ ሁሉ እየዘመቱ ሕይወታቸውን እየገበሩ ያሉት ግን በመካከለኛና ዝቅተኛ ማዕረጎች ያሉ ኢትዮጵያዊያን መኮንኖችና ብዙሃኑ የሠራዊቱ አባላት የሆኑ ወታደሮችናቸው። ብዙሃኑ የሠራዊት ክፍል አለቆቹን ከመጠበቅ ባለፈ ድምጹን ከፍ አድርጎ ለመናገር እንኳን የማይፈቀድለት ሎሌ ተደርጓል።
ለኢትዮጵያዊ ወታደር ለህወሓት ሎሌ ከመሆን በላይ የሞት ሞት የለም። ብዙሃኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊቱ አባላት በጥቂት የወያኔ ሹማምንት የሚረገጥ መሆኑ የሠራዊቱን አባላት የግል ስብዕና ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሠራዊቱን ክብር ይነካል። የሠራዊታችን የህወሓት አገልጋይ መሆን የምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያን ያዋርዳል። ይህ ዉርደት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም።
ከእንግዲህ ጄኔራሎችና ሌሎችም የበላይ አዛዦች ሁሉ የአንድ አካባቢ ተወላጆች በሆኑበት ሠራዊት ውስጥ ተስማምቶ መኖር መቀጠል እያንዳንዱን የመከላከያ ሠራዊት አባል ሊያሰፍር ይገባል። የህወሓት ጄኔራሎች ጮማ በውስኪ ሲያወራርዱ፤ በህንፃዎች ግንባታ፣ በባንኮች ንግድ፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው ቢዝነሳቸውን ሲያጧጥፉ፣ ምስኪኖቹ የሠራዊቱ አባላት በኦጋዴን፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአማራና በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች እየተወረወሩ ወገኖቻቸውን የሚፈጁበት ሥርዓት ማብቃት አለበት። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብዙሃኑ አባላት ቤተሰቦቻቸው በችጋር እየተቆሉ የአዛዦቻቸው ሀብት ጠባቂ መሆናቸው ማክተም አለበት።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የጭለማ ዘመን ታሪክ እያበቃ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ ነው። መሣሪያዎቻቸውን እንደያዙ የነፃነት ኃይሎችን የሚቀላቀሉ የሠራዊቱ አባላት ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨረመ መጥቷል። ሠራዊቱ ከሕዝብ ጎን እንደሚቆም ውስጥ ውስጡን የሚላኩ መልዕክቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ይህ አበረታች ዜና ነው፤ ግን በቂ አይደለም። ወያኔን ከውስጥም ከውጭም የምናጣድፍበት ጊዜው አሁን ነው። የነፃነት ኃይሎችን መቀላቀያ ጊዜ አሁን ነው፤ በሠራዊቱ ውስጥም በህቡዕ መደራጃ ጊዜ አሁን ነው። ይህን ጊዜ መጠቀም ብልህነት ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ጥቂት የህወሓት ጥጋበኞች በብዙሃኑ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚያደርሱት በደል ማብቃት አለበት ይላል። ግንቦት 7፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በሙስና የደለቡት፣ ትዕቢተኛና ጨካኝ መሪዎቻቸው ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህርይ የሌላቸው ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች እንደሆኑ በመረዳት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክንዱን እንዲያነሳባቸው ጥሪ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሕዝብም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አንድ ወጥ እንዳልሆነ እና በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ መኮንኖችና አብዛኞዎቹ ወታደሮች የሕዝብ ወገን መሆናቸውን እንዲገነዘብ ያሳስባል። “አብረን ነው ዘረኛውና ፋሽስቱን ወያኔን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ አውርደን የምንጥለው” ስንል አብዛኛው የመከላከያ ሠራዊታችን ኢትዮጵያዊ ወገናችን እንደሆነ እና በወደፊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥም ጉልህ ሚና እንዲጫወት የምንፈልግ መሆኑን ግልጽ ማድረግ እንሻለን። የመከላከያ ሠራዊቱም የሕዝብ ወገንተኝነቱ በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ እናደርጋለን። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ አካል ነው፤ የሕዝብ ወገናዊነቱ በተግባር የሚያሳይበት ትክክለኛ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው እንላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

tirsdag 14. oktober 2014

ደኢህዴን በአጼ ምኒልክ ላይ የሰራው ዶክመንተሪ ኢህአዴግ ውስጥ ቅራኔ ፈጠረ * • በርካታ የብአዴን ካድሬዎች በሰንደቅ አላማ በዓል አልተገኙም

October 14,2014
የደኢህዴን 22ኛ ዓመት ክብረ በዓልን ተከትሎ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ‹‹ጮራ ፈንጣቂው ጉዟችን›› በሚል የተሰራውና አጼ ምኒልክ የደቡብ ህዝቦች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንደፈጸሙ የሚሳየው ዶክመንተሪ በዴኢህዴንና በብአዴን መካከል አለመግባባት መፍጠሩን አንድ ከፍተኛ የብአዴን ካድሬ ነገረ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡
Minilikዶክመንተሪውን ተከትሎ የብአዴን ፖለቲከኞች ኢህአዴግ በተለይም የዶክመንተሪው አዘጋጅ ደኢህዴን ላይ ተቃውሞ ያስነሱ ሲሆን ‹‹በአንድ በኩል ምኒልክ ይወደሳል፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ይወገዛል፡፡ ፒያሳ ላይ ያለው ሀውልት ምኒልክ መልካም ነገር እንደሰሩ ለማሳየት የተሰራ ነው፡፡ እንዲህ የምታወግዙት ከሆነ ለምን ፒያሳ የሚገኘውን ሀውልቱንስ አታነሱትም?›› በማለት በህዝብ መካከል ግጭት ይፈጥራል ያሉት መቀስቀሻ ዶክመንተሪ ላይ ተቃውሟቸውን ማንሳታቸውን የብአዴን ከፍተኛ ካድሬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የብአዴን ካድሬዎች ዶክመንተሪውን ባዘጋጀው ደኢህዴንም ሆነ ኢህአዴግ ላይ ባላቸው ቅሬታ የዛሬው የሰንደቅ አላማ በዓል ላይ እንዳልተገኙ ተገልጾአል፡፡ በዶክመንተሪው ምክንያት በኢህአዴግ አንዳንድ ፖሊሲዎች ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ለአብነት ያህልም እስካሁን አንስተውት የማያውቁትንና ሰንደቅ አላማው ላይ ያለው ኮከብ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን የብአዴኑ ካድሬ ገልጾዋል፡፡
በቅርቡ አጼ ምኒልክን በመኮነን ከተላለፈው ዶክመንተሪ በተጨማሪ ተማሪዎች፣ ለሰራተኞችና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍል በተሰጠው ስልጠና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ታሪክ ነክ ወቀሳዎች የአብአዴን ካድሬዎች በደኢህዴንና ኢህአዴግ ላይ ላነሱት ተቃውሞ በተጨማሪ ምክንያትነት ተነስቷል፡፡

mandag 13. oktober 2014

ከወያኔ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሾልኮ የወጣ

mof

ይህ ባለ 16 ገጽ ዘገባና ሰነድ ሲሆን ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

“አሻራ” – በአንዳርጋቸው ጽጌ ዙሪያ ያጠነጠነች ልዩ ዕትም መጽሔት (PDF)

andargacew ashara magazine cover page

በአውስትራሊያ የሚገኙት ጋዜጠኞች አብይ አፈወርቅ እና ሳምሶን አስፋው በአንዳርጋቸው ጽጌ ዙሪያ ብቻ ያጠነጠነች አሻራ የተባለች የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችን ቃለምልልስ እና ወቅታዊ ጽሑፍ የያዘች መጽሔት አሳትመዋል:: በኦን ላይን ለማንበብ የምትሹ እነሆ ተካፈሉዋት::

torsdag 9. oktober 2014

ጋጠ ወጡ ማን ነው?


የህወሃት ጉጅሌና ሎሌዎቹ መቼም ራሳቸውን የሚያይ አይንም መስታዎትም ያላቸው አይመስሉም። ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች በአጠገባቸው የዘሩ የማይመስሉት ለዚህ ሳይሆን ይቀራል። ምናልባትም ብልግና፣ ጭካኔ፣ ግፍ፣ አውሪያዊ ስብእና፣ ወገን ካለህግ መግደልና ማዋረድ፣ የህዝብ ሃብት በጠራራ ጸሃይ መዝረፍ ለእነሱ የተፈቀደና የተሰጠ ጸጋ አድርገው ሳይቆጥሩት ይቀራሉ?
ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰለጠነና የዳበረ ስርዓት አከባበር በሰፈነበት ከተማ ውስጥ ባልታጠቁ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ሲተኩሱና ሲያስተኩሱ በመዋላቸው ለደረሰባቸው ትዝብት የነውረኝነት ሀፍረት እንደማፈር ሰላማዊዎቹንና በሰላማዊ መንገድ እስከ ሲቪላዊ አልታዘዝም ባይነት መብት ያላቸውን ጠንቅቀው አወቀው የተንቀሳቀሱትን ዜጎች ጋጠ ወጥና ባለጌዎች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። ትንሽ ሲቀዠብርባቸው ደግሞ ኦባማ ስላነጋገረን የቀኑ ተቃዋሚዎች፣ ይህ አልበቃ ሲል ደግሞ የሻእቢያ ተላላኪዎች ሲሉም ተደምጠዋል። ከአውሬነት ብዙ ያልተለዩት ደጋፊዎቻቸው ተኩሱን ሲያንጣጣ የነበረው የቀድሞ የስዩም መስፍን የግል አሽከርና ሹፌር የነበረው ወዲ ወይኒ ግደይ ስለተባረረ ንዴታቸውን ከአደባባይ እንኳን መደበቅ አልቻሉም። እናስ እዚህ ውስጥ ጋጠወጡ ማነው? ሀገሩን የሚያስተዳድርበትን አራዊታዊና ህግ አልባ ስርአት በሰለጠነ ህዝብ ሀገር በአደባባይ ለኤግዚብሽን የሚያቀርብ መደዴ ወይስ እስከ ሲቪል እምቢተኝነት ድረስ ሊደርስ የሚችል መብታቸውን ጥንቅቀው የሚያውቁና በግፍ ስርአት ለሚኖረው ወገናቸው ድምጽ ያሰሙ የህዝብ ልጆች?
በዘሩ ታማኝነት ተመርጦ ከስዩም መስፍን ሾፌርነት ውጪ ቅንጣት የዲፕሎማሲ እውቀት የሌለውን ደንቆሮ የዲፕሎማት ማእረግና ሽጉጥ አስታጥቆ ዋሽንግተን ከሚልክ መንግስት በላይ ጋጠወጥና አጉራ ዘለል ከየት ይገኛል።
እውነቱ ግን ወዲህ ነው ያለው። ቢያንስ በነጻው አለምየሚኖሩ የኢትዮጵያ ልጆች በሀገራቸውና በወገናቸው ላይ በሚደርሰው ስቃይ ውርደትና ግፍ ተንገፍግፈዋል። የወያኔ ሹማምንት ግፋቸውን እንዲያቆሙ ያሰሩዋቸውን እንዲፈቱና ሀገር ዝርፊያ እስኪያቆሙ ድረስ በገቡበት እየገባ ቁም ስቅላቸውን ማሳየትና ጋጠወጥና የነውረኛ ስርአት አገልጋዮች መሆናቸውን ማጋለጡን ይገፉበታል። በሰሩት ወንጀል አለምአቀፍ ፍርድቤቶች መድረክ ላይ እየጎተተ የሚያቀርብበት ጊዜም ሩቅ አይደለም።
የወጋ ይርሳ እንደሆነ እንጂ የተወጋ አይረሳም። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሰላማዊ ተቃዋሚውን ድርጅት አባል በብረት ሶዶማዊ ምግባር የፈጸሙትን ጋጠ ወጥ የወያኔ ተላላኪዎች ማን ይረሳል። በየቤቱና በየጎዳናው በዱላ የሚቀጠቀጡትና ደማቸውን ሲጎርፍ ያየናቸው አዛውንት ሙስሊም ወገኖቻችን ደም እንዴት እንረሳለን። ሬሳቸው እንኳን ክብር አጥቶ የጋጠወጥ ወያኔ መጫወቻ የሆኑትን የኦጋዴን ወገኖቻችንን ማን ይረሳል። ጋምቤላ ጫካ ውስጥ እንደደኑ ተጨፍጭፈው የተቆለሉትን አኙዋኮች ማን ይረሳል። ከየኖሩበት ቦታ በግፍ እየተፈናቀሉ የሚንከራተቱትን እና የሚሞቱትን አማሮች ማን ይረሳል። በቆራጥነት ብቻ በሰላም መንገድ እንታገላለን ብለው በተነሱ ወህኒ የተወረወሩትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የታሰሩትንና የተሰደዱትን ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች የምንረሳቸው ስንሞት ብቻ ነው። ከየጎረቤት ሀገሩ እየታፈኑ የሚሰቃዩትን እነ አንዳርጋቸውን እና ሌሎች የሞቱትን ማን ይረሳል።
ህዝባችንን ወደ ሰላማዊ አመጽም ሆነ ወታደራዊ አመጽ እየገፋው ያለው ይህ የወያኔ ባህሪ ነው።
ግንቦት 7 ከዚህ አራዊታዊ ስርአት ጋር ሆናችሁ በተለያየ ምክንያት በህዝባችሁ ስቃይ ላይ የምትተባበሩ ወገኖች ሁሉ በአገኛችሁት አጋጣሚ ከእዚህ እኩይ ስርአት ተግባራት ራሳችሁን እንድታወጡ፣ ከቻላችሁ በውስጥም ሆናችሁ ወገናችሁን ሳትበድሉ ትግሉን እንድትቀላቀሉ ይመክራል።
መላው ህዝባችን በያለህበት ራስህን በራስህ እያደራጀህ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎችን ጀምር። በመላው አለም ዙሪያ ተሰደህ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለወገንህ ለራስህም ትንሳኤ ተነስ!!
ትግላችን የመጨረሻውን መጀመሪያ እየተያያዘ ነው። የትልቅ ሀገርና ትልቅ ህዝብ ባለቤቶች ስለሆንን ከወያኔ ወሮበላ ጉጅሌ በበለጠ የሚገባን ህዝብ ነን!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

lørdag 4. oktober 2014

ሰልጣኙንም አሰልጣኙንም ያንገሸገሻቸዉ ሥልጠና

አባትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጁ አምርረዉ ሲጨቃጨቁ እናት ትደርስና . . . . እባክሽ ልጄ አባትሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም ብላ ልጇን ትቆጣታለች። ልጅት ከተቀመጠችበት ትነሳና ምነዉ እማዬ ምኑን ነዉ የምሰማዉ፤ አባዬኮ እሱ እራሱ የማያዉቀዉን ነገር ላሳይሽ እያለኝ ነዉ ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ በቁጣዉ ብዛት ፊቱ እንደ ፊኛ ያበጠዉ አበቷ ካንቺ ማወቅ ዬኔ አለማወቅ ይሻላል፤ ይልቅ የምልሽን ስሚ ብሎ ጮኸባት። ወጣቷ ተማሪ ወላጅ አበቷ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ዘልቀዉ እንዳልተማሩ ብታዉቅም ለግዜዉ ማድረግ የምትችለዉ ምንም ነገር አልነበረምና እሽ አባዬ ብላ አባቷን መስማት ጀመረች። ይህ የአባትና የልጅ ስሚኝ አልሰማም ጭቅጭቅ ባለፉት ሁለት ወራት መሀይሞቹ የወያኔ ካድረዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየስልጠና አዳራሹ ያደረጉትን ፍጥጫ አስታወሰኝ። ይህ አብዛኛዉን ዕድሜያቸዉን ትምህርት በመማር በሳለፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በወጉ ስምንተኛ ክፍልን ባላጠናቀቁ የወያኔ ካድሬዎች መካከል በክረምቱ ወራት ተጀምሮ አሁን ድረስ የዘለቀዉ የ”አሰለጥናለሁ አታሰለጥንም” ትንግርታዊ ድራማ ወያኔ አስካሁን ከሰራቸዉ ድራማዎች በአይነቱ ለየት ያለ ድራማ ነዉ።
የወያኔ ምርጫዎች ምንም አይነት ዉድድር የማይታይባቸዉ ማንም ተወዳደረ ማንም ወያኔ ብቻ የሚያሸንፍባቸዉና ምርጫዎቹ ከመካሄዳቸዉ በፊት የት ቦታ እነማን ማሸነፍ እንዳለበቸዉ ተወስኖ ያለቀላቸዉ የለበጣ ምርጫዎች ናቸዉ። ወያኔ ግን “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለዉ ምርጫዉ በቀረበ ቁጥር የሚያክለፈልፍ በሽታ ይይዘዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ1997ና በ2002 ዓም የተደረጉትን ምርጫዎችና እርግጠኞች ነን አሁንም በ2007 ዓም የሚደረገዉን ምርጫ የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ምርጫ መኸል የአምስት አመት ልዩነት መኖሩ ነዉ እንጂ የምርጫዉን ዝግጅት፤ ሂደትና ዉጤት በተመለከተ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም። ሁሉም ምርጫዎች የሚካሄዱት ወያኔ የምርጫ ተቋሞች፤ ሜድያዉንና ፍርድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ቅድመ ምርጫዎችን የሚቆጣጠረዉ፤ በምርጫዉ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነዉና ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ የሚቆጥረዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። ይህም ሁሉ ሆኖ ወያኔ ከሱ ዉጭ ማንም ምርጫዉን እንደማያሸንፍ በልቡ እያወቀ አምስት አመት እየቆጠረ የሚመጣዉ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ግርግር መፍጠር ይወዳል። በ1997 በተደረገዉ ምርጫ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ሜድያዉንና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽም ቢሆን ለቀቅ አድርጎ የነበረዉ ወያኔ በ2002 ዓም ይጋፉኛል ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ ማሰር፤ መደብደብና እንቅስቃሴያቸዉን መግታት ጀመረ። አሁን በ2007 ዓም ደግሞ ገና በግንቦት ወር ለሚካሄደዉ ምርጫ የኢትዮጵያን ወጣት ካልተቆጣጠርኩ በሚል ትልቅ ዘመቻ ጀምሮ በከፍተኛ በሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙትን የአገሪቱ ወጣቶች በሥልጠና ሰበብ ወያኔያዊ የፖለቲካ ጠበል እያጠመቃቸዉ ነዉ።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወያኔን ዘረኛ ነዉ፤ ጎጠኛ ነዉ፤ ነብሰ ገዳይ ነዉ ይሉታል። አዎ እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚያሳዩ ቃላት ናቸዉ። ወያኔ ግን ከእነዚህ ዉጭ ሌሎች ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ለምሳሌ ወያኔ መዋሻት የማይሰለቸዉ ዉሸታም ነዉ፤ ዕኩይ ነዉ፤ ጨካኝና የለየለት መብት ረጋጭም ነዉ። እነዚህ የወያኔ ባህሪያት ሁሉ ያናድዱናል ወይም ያስቆጡናል እንጂ አይገርሙንም ወይም እየኮረኮሩ አያስቁንም። ጉደኛዉ ወያኔ የሚገርሙና የሚያስቁ ባህሪያትም አሉት። ወያኔ የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፤ በተለይ ከቁጥርና ከቁጥርም በዛ ካለ ቁጥር ጋር ለየት ያለ ፍቅር አለዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአገር ዉስጥ ምርት ከዉጭም ከዉስጥም ተገፍቶ 5% ከጨመረ ወያኔ የሚነግረን 10% አደገ ብሎ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትምህርት ጥራት ተንኮታኩቶ ከመዉደቁ የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀዉ ወደ ስራ አለም በሚገቡ ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ኮሌጅ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ ግን በኔ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርሲቲዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት ከ300% በላይ አደገ እያለ ይፏልላል። ካለፈዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለፍላጎታቸዉና ያለፈቃዳቸዉ በግድ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ የወያኔን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲጋቱ የሚገደዱ ወጣቶችም ጉዳይ ይህንኑ ወያኔ ከቁጥርና ከብዛት ጋር የተጠናወተዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ። ይህ ወያኔ በየክልሉ ሥልጠና ብሎ የጀመረዉ ቧልት የሰልጣኛቹን እዉቀት የሚያዳብር አይደለም ወይም ለአገራችን ለኢትዮጵያም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። የሥልጠናዉ ብቸኛ አላማና ጥቅም በወጣቱ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የወያኔን አባላት ማብዛት ነዉ። ወያኔ ድርጅታዊ የፓርቲ ስራዎችን የሚሰራዉ መንግስታዊ ተቋሞችን በመጠቀም ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ነዉና እሱን የሚያስደስተዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉት ተብሎ መነገሩ ነዉ እንጂ እነዚህ አባላት ታማኝ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ድርጅታዊ ስራ ይስሩ አይስሩ ለወያኔ ጉዳዩ አይደለም።
ወያኔ በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከያሉበት በግድ አስመጥቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ በወያኔና በተማሪዎቹ መካከል ያለዉን ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት አጉልቶ ከማዉጣቱ ባሻገር ይህ ሳይጀመር የከሸፈዉ ስልጠና ለወያኔ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። እንዳዉም አብዛኛዉ ተማሪ የወያኔ መሪዎችን አንገት የሚያስደፋ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሥልጠና የሚያስፈልገዉ ለተማሪዎቹ ሳይሆን ለራሳቸዉ ለአሰልጣኝ ነን ባዮቹ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በብዙዎቹ የስልጠና አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን ካድሬዎቹ በሚጠየቁት ጥያቄ እየተበሳጩ ጥርሳቸዉን ሲነክሱ ታይተዋል። በእርግጥም ጎንደር ዉስጥ የነበረዉን ጄኔሬተር ነቅላችሁ ዬት አደረሳችሁት ከሚል አፋጣጭ ጥያቄ ጀምሮ አንዳርጋቸዉ ጽጌን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ አሰልጣኝ ካድሬዎች “ከእናንተ ጋር በኋላ እንገናኛለን” እያሉ ሲዝቱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ካለ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታ መንፈቅ መዝለቅ የማትችል ደሃ አገር ናት፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብና አላግባብ የሚያባክኑትን የአገር ሃብት የተመለከተ ማንም ሰዉ ድርጊታቸዉ ከደሃዋ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በፍጹም እንደማይገናኝ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅበትም። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚያፈርሳቸዉንና በየስብሰባዉና በየጉባኤዉ ከሚያባክነዉ ግዙፍ የአገር ኃብት ዉጭ ከሰሞኑ ምንም አገራዊ ጥቅም በሌለዉና ሠልጣኞቹ አንፈልግም ብለዉ ለተዉት ሥልጠና የሚያባክነዉ የህዝብና የአገር ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ከሚወጣዉ የትርንፖርትና የዉሎ አበል ዉጭ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ተማሪ በቀን የሚከፈለዉ ሃምሳ ብር ቁጥራቸዉ ከ600 ሺ በላይ በሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች ልክ ሲሰላ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነዉ።
ለመሆኑ ዜጎች የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በሚራቡበት አገር፤ ወጣቶች ስራ ፍለጋ ያደጉበትን መንደር ጥለዉ ባሕር እየተሻገሩ በሚሰደዱበት አገርና የገንብዘብ እጥረት እየተባለ ብዙ ፕሮጀክቶች በሚታጠፉበት አገር ወያኔ ከየት እያመጣ ነዉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ ምንም እርባና የሌለዉ የፖለቲካ ሥልጠና ሥልጠናዉ በፍጹም ለማያስፈልገዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠዉ? ደግሞስ ከዉጭ አገር ምንጮች ምንም አይነት የገንዝብ እርዳታ እንዳያገኙ በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ማስኬጃ ወጪያቸዉን መሸፈን አቅቷቸዉ በሚንገዳገዱበት አገር ምን ቢደረግ ነዉ ወያኔ የራሱን ፓርቲ ስራዎች በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ የሚያሰራዉ?
የወያኔና የገንዝብ ጉዳይ ከተነሳ እነዚህ ጉደኞች ቢነገር ቢነገር የማያልቅ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ብዙ የቆሸሸ ታረክ አላቸዉ። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገሪቱን የአየር ሞገዶች ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቀዉ ከዚሁ ከወያኔ የረጂም ግዜ ቆሻሻ ታሪክ ጋር የተያያዘዉ የገንዘብ ጉዳይ ነዉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ባንኮች፤ ትላልቅ መደብሮችና ዘመናዊ የመገበያያ አዳራሾች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሀሰተኛ ገንዘብ ተጨናንቀዋል። ይህ ማን፤ መቼ፤ ከየትና እንዴት እንዳሰራጨዉ የማይታወቅ የሀሰተኛ ገንዝብ ዝርጭት ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱን ሰዉ እያነጋገረ ነዉ። የወያኔ ፖሊሶች ከየባንኩና ከየገበያ አዳራሹ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እየሰበሰቡ መሆናቸዉን ቢናገሩም ከዚህ ሀሰተና ገንዘብ ስርጭት በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ግን ምንም የተነፈሱት ነገር የለም። እንደዚህ ብዛት ያለዉ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ደግሞ አቅምና እዉቀት በሌላቸዉ ተራ ወንጀለኞች የሚሞከር ወንጀል አይደለም። ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያዉያን በዚህ ሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ዉስጥ ያለምንም ጥርጥር የወያኔ ባለስልጣኖች እጅ አለበት ብለዉ በድፍረት አፋቸዉን ሞልተዉ የሚናገሩት። መቼም መሬት ቆፍሮ ቦምብ እየቀበረ በተቃዋሚዎች የሚያሳብበዉና በፈንጂ ህዝባዊ ተቋሞችን እያፈረሰ ሽብርተኛ ብሎ በፈረጃቸዉ ድርጅቶች ላይ ጣቱን የሚቀስረዉ ወያኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት ለመሙላት ሀሰተኛ ገንዘብ አሰራጭቶ ሊያጠፋቸዉ በሚፈልጋቸዉ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አያመካኝም ማለት አይቻልም። ለሁሉም የወያኔ ነገር አንቺዉ ታመጪዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ነዉና ይህ የሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት የራሱ የወያኔ ስራ እንደሆነ ከራሱ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች የምንሰማበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያንን የሙጥኝ ብሎ ተጣብቆ የሚያሰቃያቸዉ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መንስኤዉ መለስ ዜናዊ በህይወት ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ከአገሪቱ የማምረት አቅም በላይ በሆነ መልኩ በገፍ እየታተመ ወደ ኤኮኖሚዉ ዉስጥ እንዲገባ የተደረገዉ የገንዘብ አቅርቦት ነዉ። ይህ ዘንድሮ ስሙን ቀይሮ “ሀሰተኛ የገንዝብ ስርጭት” ተብሎ አገራችንን የሚያምሳት በሽታም የዚሁ የተለመደ ወያኔ እያተመ የሚያሰራጨዉ የገንዘብ አቅርቦት ችግር አካል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም። አለዚያማ ወያኔ በነጋ በጠባ ሚሊዮንና ቢሊዮን እያለ የሚያባክነዉ ገንዘብ ከዬት ይመጣል?
ስልጠና በየትኛዉም ማህበረሰብ ዉስጥ የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ የሚረዳ ጠቃሚ ተግባር ነዉ፤ ሆኖም ስልጠና ሲባል አላማ፤ አትኩረትና ግብ ኖሮት በተወሰነ ቡድን ወይም ቡድኖች ላይ የሚያነጣጥር የእዉቀትና ልምድ መቀባበያ መሳሪያ ነዉ እንጂ እንዳዉ በጅምላ የአንድ አገር ህዝብ እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ይዉስድ እየተባለ የሚደገስ የጨረባ ተዝካር አይደለም። ደግሞም ስልጠና አሰልጣኝና ሰልጣኝ ተግባብተዉና ሁለቱም ሚናቸዉን ወድደዉና ፈቅደዉ የሚካሄድ የጋራ እንቅስቃሴ ነዉ እንጂ ሠልጣኝ አልሰልጥንም ካለና አሰልጣኝ ደግሞ ጥያቄ የጠየቀዉን ሁሉ “ቆይ ጠብቀኝ” እያለ የሚዝትበት ከሆነ ነገሩ ሥልጠና መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ይሆናል። ለመሆኑ ወያኔ የአገሪቱን ወጣቶች ሥልጠና ብሎ ሰብስቦ ምንድነዉ የሚላቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። ከብዙዎቹ ሰልጣኞች አንደበት በግልጽ እንደሰማነዉ፤ የወያኔ ካድሬዎች በየስልጠናዉ አዳራሽ የሚናገሩት በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ የወደፊት ዕድላችሁ ይጨልማል፤ ከሐይማኖት አክራሪዎች እራሳችሁን አጽዱ ወይም ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር እንዳትተባበሩ እያሉ ነዉ። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ አመታት ህይወቱ እንደ ሐምሌ ጨለማ የጨለመበት የኢትዮጵያ ወጣት ግን በየስልጠና አዳራሹ በተደጋጋሚ የሚጠይቀዉ እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱና ወያኔዎችን እራሳቸዉን በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ እያለ ነዉ።
ባለፈዉ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊ/መንበር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኑና ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት አብረን እንታገል የሚል አገራዊ ጥሪ አድረገዋል። በየዘመኑ ለወገኖቹ መብትና ነጻነት መከበር ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት መሪዉ ያቀረበለትን የፍትህና የእኩልነት ትግል ጥሪ ረግጦ ከወያኔ ጋር በተላላኪነት ከሚያስተሳስረዉ ሥልጠና ጋር በፍጹም እንደማይተባበር ሁላችንም እርግጠኞች ነን። ዛሬ ዕድሜዉ ከ35 አመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወጣት አብዛኛዉን ዕድሜዉን በወያኔ ስርዐት ዉስጥ የኖረ ወጣት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ወንድሙ፤ ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዉ በወያኔ ነብሰ ገዳዮች ሲገደሉ በአይኑ እየተመለከተ ያደገ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት የወያኔ በደልና ግፍ የሚነገረዉ ወጣት ሳይሆን ይህንን በደልና ግፍ ለማቆም ቆርጦ የተነሳ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት ወያኔ ሥልጠና እያለ የሚፈጥርለትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ እራሱንና ወገኖቹን ነጻ ያወጣል እንጂ በሥልጠና ስም ከወያኔ በሚመጣለት ኮቶቶ እጅና እግሩን አስሮ የወያኔ ባሪያ ሆኖ አይኖርም። ለዚህ ቆራጥና አርቆ አስተዋይ ለሆነ ወጣት ያለን መልዕክት አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና በድል የምንገናኝበትና የአገራችን ባለቤት የምንሆንበት ቀን ቅርብ ነዉ የሚል ወገናዊ መልዕክት ነዉ