mandag 6. juli 2015

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ይናገራል

 Share0  New
11010956_1001144369918403_7418431852582786272_n
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
«ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት እንደተዘዋወርኩ ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና አበበ ቀስቶ ጋር ነበርን፡፡ ከጥቂት ጊዜያቶች በኋላ አበበ ቀስቶ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወር ውብሸት ታዬ ወደ ሌላ ዞን ተቀየሯል፡፡ ዛሬ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በማንም እንዳይጎበኝ ተከልክሏል፡፡ እኔም ለተወሰኑ ወራት በማንም እንዳልጎበኝ እግድ ተጥሎብኝ እንደነበር ታውቃላችሁ፡፡ በኋላ ላይ ቤተሰቦቼ እና ወዳጆቼ እንዲጠይቁኝ ተፈቅዶ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ከአዲስ አበባ የመጡ ጠያቂዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ዛሬም እናንተን እንዴት እንዳስገቧችሁ እንጃ፡፡»
«ምንም እንኳ የእስር ቤት መልካም ባይኖረውም ይህ ግቢ ፋሺዝም የነገሰበት ማረሚያ ቤት ነው፡፡ ማረሚያ ቤት የሰዎችን እኩይ ባህሪ ለማረምና ለማስተካከል የታነፀ ቢሆንም ይህ ማረሚያ ቤት የትኛውንም ታራሚ ለማረም ብቁ አይደለም፡፡ መሰረታዊ ነገሮች አልተሟሉበትም፡፡ ውሃ ከ3 ተከታታይ ቀናት በላይ ይጠፋል፡፡ ታራሚዎች እነዚህን ጉድለቶች በራሳቸው ገንዘብ ገዝተው እንዳይጠቀሙ እንኳ በወር ከ200 ብር የበለጠ ከቤተሰብ እንድንቀበል አይፈቀድልንም፡፡ ከተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚመጡ ታራሚዎች እዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ምግብ የሚያስገባላቸው ቤተሰብ በአቅራቢያቸው የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች በገንዘባቸው ገዝተው እንዳይጠቀሙ እንኳ በወር ከ200 ብር በላይ እንዳይቀበሉ ስለተከለከሉ ከፍተኛ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡»
«እኔ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወርኩ አንስቶ በግቢው ውስጥ የሚገኘው ቤተመጻሕፍት አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኗል፡፡ የእስር ጊዜን በንባብ ማሳለፍ አለመቻል በጣም ከባድ ነው፡፡ ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ የሚያመጡልኝ ማንኛውንም አይነት መጻሕፍቶች ሊገባልኝ አልተፈቀደም፡፡ ፖለቲካ ነክ ከሆኑ መጽሓፍት ውጪ ያሉትን የልብወለድ መጽሓፍቶች እንኳ እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡ እዚህ ያለው አብዛኛው ታራሚ ማንበብ ይፈልጋል፡፡ ከመከልከሉ በፊት ታራሚዎች እጅ ላይ ያሉት ጥቂት መጻሕፍቶችን ሁሉም ተቀባብሎ አንብቦ ጨርሷቸዋል፡፡ ንባብ የማረምና የመለወጥ አቅም አለው፤ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎች በንባብ ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉና እንዳይለወጡ አድርጓል፡፡»
«በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ታራሚዎች ከእኔ ጋር እንዳይሆኑ ተከልክለዋል፡፡ ብዙዎች ሊያወሩኝና አብረውኝ ሊሆኑ እንኳ ቢፈልጉ የሚደርስባቸውን ቅጣት በማሰብ ሊቀርቡኝ አይደፍሩም፡፡ ከእኔ ጋር ሆነው የታዩ ሁሉ በጨለማ ቤት ውስጥ እንዲታሰሩ ይደረጋሉ፡፡ ያለብኝን የጀርባ እና የጆሮ ህመም መታከም አልቻልኩም፡፡ እነዚህና ተመሳሳይ ጭቆናዎች እኔ ከማምንበትና እከተለው ከነበረው አካሄድ መደ ኋላ አይመልሱኝም፡፡ በፊት የተናገርኩትን ዛሬም እደግመዋለሁ፤ ጉዟችን እስከ ቀራንዮ ድረስ ነው፡፡»
(ከተመስገን ደሳለኝ ጋር ከነበረን አጭር ቆይታ መካከል ቃል በቃል ያልተወሰደ)
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/8372#sthash.YwH4gUiw.dpuf

fredag 3. juli 2015

በህወሓት አገዛዝ እየተሰቃዩ ላሉ ወገኖቻችን ደህንነት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጫና ይቀጥል!

ከሣምንት በፊት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የሚመለከት አንድ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መግለጫው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአንድ ዓመት ሙሉ መሠረታዊ የሆኑ የታሳሪዎች መብት እንኳን ተነፍጎት ባልታወቀ እስር ቤት የሚገኝ መሆኑ እና በእንግሊዝ ባለሥልጣናትና በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቅ፣ ቋሚ የቆንስላና የህግ ምክር እንዲያገኝ በተደጋጋሚ የቀረበው ጥያቄ በወያኔ አገዛዝ ውድቅ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑ ከወትሮው ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጿል። አዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ አምባሳደርም እንደዚሁ ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ ለስላሳነት ወጣ ያለ ያለ መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚታተመው ሪፓርተር ጋዜጣ ሰጥቷል። እነዚህ የሰሞኑ የእንግሊዝ መንግሥት መግለጫዎች በቀና የሚታዩ ቢሆንም የብሪታኒያ መንግሥት ማድረግ ይገባው ከነበረው እና ማድረግ ከሚችለው አንፃር ሲታይ ብዙ ይቀረዋል። የአውሮፓ ኅብረት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተደጋጋሚ አንስቷል። የተባበሩት መንግሥታትም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግበት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከላይ የተዘረዘሩት ኩነቶች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያለሟቋረጥ የሚያደርጉት ውትወታ ውጤት እያመጣ መሆኑ ያሳያል። ይህ ጥረት ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስልጥኖ አሰማርቷችኋል” ተብለው እንደተለመደው በሀሰት የተከሰሱ ወገኖቻችን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መከላከያ ምስክር እንዲሆኑን ይታዘዝልን“ ብለው ሲጠይቁ ዳኛ ተብየው “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ ብይን ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስር አያያዝ ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ወቅት በህወሓት አገዛዝ በተሾመ ዳኛ “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ” መባሉ አሳሳቢ ጉዳይ አድርጎ ይመለከተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተከሳሾች፣ የአቃቤ ህጉና የዳኛው ምልልስ ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለእንግሊዝ መንግሥት እንዲደርስ እንዲያደርጉም ያሳስባል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ሳይሆን በህወሓት እስርቤቶችና ከእስር ቤቶች ውጭ ባልታውቁ ቦታዎች ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ የሚወጣው፣ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ራሳችንን፣ ወገኖቻችንና አገራችን ነፃ ለማውጣት የምናደርገው ትግል ማጠናከር ግዴታችን ነው። እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ነፃነታችንን አያጎናጽፈልንም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሓትን እኩይ ተግባራት በዓለም አደባባዮች ማጋለጥ፤ የህወሓት አገዛዝን ወዳጅ ማሳጣት እና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ደህነት የሚያሻሽሉ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ተግባር በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ በህወሓት እጅ ለወደቁ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚያሰሙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www.patriotg7.org

torsdag 2. juli 2015

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ አሳሰበ -


amnestyintl.logo.2አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ሰኔ 24/2007 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብረውም የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቋቸው አሳስቧል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ወይንሸት ሞላን፣ ኤርሚያስ ፀጋዬን፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄለም አካለ ወርቅን ፍርድ ቤት በአስር ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲለቀቁ ቢያዝም አራቱ ግለሰቦች አሁንም እስር ቤት ውስጥ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጾአል፡፡
አይ ኤስን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ ላይ ፖሊስ የሀገሪቱንና የዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ በሰልፉ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር ጥሯል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን አስታውሷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ፣ ማቲያስ መኩሪያ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ሜሮን አለማየሁና ንግስት ወንዲፍራው በሰልፉ ሰበብ መታሰራቸውን በአብነት የጠቀሰው ሪፖርቱ ከሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተጨማሪ የሌሎች ታሳሪዎች ፍርድም በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ናትናኤል ያለም ዘውድና የፓርቲ አባል ያልሆኑ አራት ግለሰቦችም በሰልፉ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰድበዋል፣ መንግስትን የሚቃወም መዝሙር አሰምተዋል በሚል ሰበብ ሶስት አመት እንደተፈረደባቸው ሪፖርቱ አውስቷል፡፡
ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄሌም አካለወርቅ ሁለት ወር ተፈርዶባቸው ለሁለት ወር ያህል እስር ቤት በመቆየታቸው እንዲፈቱ ቢታዘዝም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ወደ እስር ቤት እንደመለሳቸውም የአምነስቲ ሪፖርት አስታውሷል፡፡ በእነ ወይንሸት ላይ አዲስ ክስና ይግባኝ እንደተጠየቀባቸው የገለፀው የሰብአዊ መብት ተሟች ድርጅቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወይንሸት ሞላን፣ ኤርሚያስ ፀጋዬን፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄሌም አካለ ወርቅን እስር ቤት ውስጥ በማጎር የፍርድ ቤቱን ቅቡልነትና የህግ የበላይነትን እየሸተሸሩ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ የሚያደርሱትን ስቃይ ማቆምና በነፃ የመዳኘት መብታቸውን ሊያከብሩላቸው እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44744#sthash.Qud8fsrO.dpuf

mandag 29. juni 2015

እነ ወይንሸት ሞላ ይግባኝ ተጠየቀባቸው

 June29,2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ እስር ላይ ቆይተው ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት እንዲፈቱ ተወስኖላቸው ሰኔ 16/2007 ዓ.ም ከእስር ቤት ሲወጡ እንደገና በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ወንይሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለወርቅ ዛሬ ሰኔ 22/2007 ልደታ ፍርድ ቤት 11ኛ ምድብ ችሎት ቀርበው ቀደም ሲል ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል›› በሚል በተከሰሱበትና ከእስር በተለቀቁበት ክስ ላይ ይግባኝ ተጠየቀባቸው፡፡
አቃቤ ህግ እነ ወይንሸት የዋስትና መብታቸውን ተነጥቀው ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቀ ቢሆንም ዳኛዋ ‹‹በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ ከእስር የተፈቱ በመሆናቸው ዋስትና ሊከለከሉ አይገባም፡፡›› ብለዋል፡፡ ዳኛዋ እነ ወይንሸት እንደተለቀቁ እንጅ በእስር ላይ መሆናቸውን እንደማያውቁ ገልጸው 3 ወር ተፈርዶበት ቂሊንጦ የሚገኘው ማስተዋል ፈቃዱ ባለመቅረቡ፣ ከእሱ ጋር ረቡዕ ሰኔ 24/2007 ዓ.ም ቀርበው ክርክር እንዲጀምሩ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ ሰኞ ሰኔ 29/2007 ዓ.ም ውሳኔ እንደሚሰጡም አሳውቀዋል፡፡
ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ኤርሚያስ ፀጋዬ በነፃ፣ እንዲሁም ወይንሸት ሞላና ዳንኤል ተስፋዬ ሁለት ወር እስር ተወስኖባቸው ሁለት ወር በመታሰራቸው እንዲፈቱ ተፈርዶላቸው ከእስር ሲለቀቁ እስር ቤት በር ላይ በፖሊስ ተይዘው ወደ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ መዛወራቸው ይታወቃል፡፡ ወይንሸት፣ ኤርሚያስና ዳንኤል ሰኔ 19/2007 ዓ.ም በቄራ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ‹‹ከእስ እንዲለቀቁ በተወሰነላቸው ወቅት ምስክሮችና የምስክሮቹ ጓደኞች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል›› የሚል አዲስ ክስ አቅርቦባቸው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡ በዚህ አዲስ ክስ ላይ የፖሊስን ምስክር ለመስማት ነገ ሰኔ 23/2007 ቄራ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡

søndag 28. juni 2015

5 የአጋዚ ክፍለጦር አባላት ኤርትራ ገብተው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄን ተቀላቀሉ

June27, 2015

(ዘ-ሐበሻ) የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ 5 የአጋዚ ጦር አባላት የነበሩ የስርዓቱ ታጋዮች የሕወሓትን መንግስት በመክዳት አስመራ ገቡ:: እነዚሁ 5 ታጋዮች ኤርትራ የሚገኘውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄን ተቀላቅለዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላማዊ ትግል ይታገሉ የነበሩም ሆነ የሕወሓት ጦርን ሲያገለግሉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች የትጥቅ ትግሉን በመምረጥ ወደ ኤርትራ በመሄድ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄን እየተቀላቀሉ መሆኑን ለዘ-ሐበሻ የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ሰሞኑን ይህንኑ ንቅናቄ የተቀላቀሉት 5ቶ የአጋዚ ጦር አባላት
1ኛ. ግራማ ተላይነሕ
2ኛ. ሄኖክ እንዳልካቸው
3ኛ ስለሺ ተስፋሁን
4ኛ. ምርት ይሁን መንገሻ
5ኛ ስማቸው ካሴ ይባላሉ። 

lørdag 27. juni 2015

5 የመኢአድ አባሎች አንዳርጋቸው ፅጌን ይመስክርልን አሉ

በነ ዘመነ ካሴ መዝገብ የተከሰሱት 5 የመኢአድ አባሎች ናቸው አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርብላቸው ነው የጠየቁት የተከሰሱት የግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው ነው በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ስልጠና ተሰጥቷችሁ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ስትንቀሳቀሱ ነበር ተብለው ላለፉት ሁለት አመታት በእስር የሚገኙት
እነዚህ ተከሳሾች አንዳርጋቸው ፅጌ የሚባል ሰው አናውቅም አንዳርጋቸው አሱ አውቃቸዋለሁ አሰልጥኛቸዋለሁ የሚል ከሆነም በናንተ ቁጥጥር ስር ስላለ ችሎቱ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ይዘዝልን እና ይመስክርልን ወይም ይመስክርብን ሲሉ ለፍርድ ቤት አመልክተዋል አቶ አንዳርጋቸው ቀርቦ ምስክርነት ይሰጥ ይሆን ? አቃቤ ህግ በህይወት ይኑር አይኑር የማይታወቅ ሠው ይቅረብልን ማለት አግባብነት የለውም ብሏል ለማንኛው ቀጠሮው ሀምሌ 03/2007 ዓም ስንተኛ ችሎት እንደሆነ አጣርቼ አሳውቃለሁ ፍርድ ቤቱ ግን ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ነው

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ኢትዮጵያን አስጠነቀቀች


የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ የአገራቱን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ

   
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌየሚገኙበት ሁኔታና አያያዛቸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያመስጠታቸውን  ጋርዲያን ዘገበ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የቆንስላ ድጋፍ ማግኘት በማይችሉበት ወይም ይግባኝ የመጠየቅ መብት ባላገኙበት ሁኔታ በግልጽ በማይታወቅ ስፍራ ከሰውተነጥለው ለብቻቸው መታሰራቸውን ያወገዙት ውጭ ጉዳይ ሚነስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰቡ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ማሻሻል እንዲያደርግጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ ባለፈው ረቡዕ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይዙሪያ በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ ግለሰቡ እስሩን በህግ ለመቃዎም ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሰው ተነጥለው ላለፈው አንድ አመት በእስር ላይመቆየታቸው ያሳስበኛል ብለዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን በየጊዜው ለመጎብኘት የምንችልበት ሁኔታ እንዲመቻችልን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቃልከመግባት ባሻገር ተገቢ ምላሽ ሊሰጠን አለመቻሉ አሳዝኖኛል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄምላሽ አለመስጠቱ ተቀባይነት የለውም፣ በግለሰቡ ጉዳይ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል መሻሻል አለመታየቱም ትልቅ ስፍራ የምንሰጠውን የሁለቱአገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለዶ/ ቴዎድሮስ መናገራቸውንም  ጋርዲያን ዘግቧል፡፡የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይሚንስቴር፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ለቤተሰባቸው የሚያደርገውን የቆንስላ ድጋፍ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ሃሞንድ ተናግረዋል፡፡የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይሚኒስቴር ግለሰቡ ከሰው ተነጥለው መታሰራቸውንና መጎብኘት እንዳለባቸው በማረጋገጥ እስሩን መቃወሙ አስደስቶናል፣ ይሄም ሆኖ የእንግሊዝመንግስት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተለቀው ወደ እንግሊዝ በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን እንጠይቃለንማለታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የተመድ የስቃይ ጉዳዮች ምርመራ ልዩ ባለሙያ ጁዋን ሜንዴዝ በበኩላቸው፤ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አያያዝበተመለከተ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ 
ለሁለቱም አገራት ንግስታት ማስታወቃቸውን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=16399:%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%8A%E1%8B%9D-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B3%E1%88%AD%E1%8C%8B%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%8C%BD%E1%8C%8C-%E1%8C%89%E1%8B%B3%E1%8B%AD-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8C%A0%E1%8A%90%E1%89%80%E1%89%80%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%89%A3%E1%88%88&Itemid=101