torsdag 13. februar 2014

አንድነት እና መኢአድ የካቲት 16 በባህር ዳር ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ


(ከዚህ ቀደም አንድነት በባህር ዳር ያደረገው ሰልፍ – ፎቶ ፋይል)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ብአዴንን በመቃወም በባህርዳር ከተማ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ጠሩ፡፡ፓርቲዎቹ ነገ ሰዓት በአንድነት ፓርቲ /ቤት በጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ ለተቃውሞ ሰልፉ አስፈላጊው የማሳወቅ ተግባርመጠናቀቁ ታውቋል፡፡
አንድነትና መኢአድ እሁድ የካቲት 16 ቀን 2006 . የጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ ምክንያት እንዲያስረዱ በፍኖተ ነፃነት የተጠየቁት የአንድነትፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሰለሞን ስዩም “አማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብአዴን የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንንየአማራን ህዝብን ክብር የሚያዋርድና በለሌሎች ብሔረሰቦች በክፉ እንዲታይ የሚያደርግ የጥላቻ ንግግር በማድረጋቸውና ብአዴንም እንደ ፓርቲማስተባበያም ሆነ የማስተካከያ እርምጃ ባለመውሰዱ የግለሰቡን አቋም እንደሚጋራ ያመለክታል” ብለዋል፡፡ የመኢአድ /ፕሬዝደንት አቶ ተስፋዬመላኩ በበኩላቸው “የአማራ ህዝብን እየመራሁ ነው እያለ እንደዚህ አይነት አስነዋሪ ንግግር ያደረገውን ባለስልጣና የሚወክለውን ፓርቲ ለማውገዝእንዲሁም ለህግ እንዲቀርብ ለመጠየቅ ነው ሰልፉ የተጠራው” ብለዋል፡፡ 
የፓርቲዎቹ የባህርዳርና አካባቢዋ መዋቅሮች የተቃውሞ ሰልፉን ለማስተባበር ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን የባህርዳር ከተማና የአካባቢዋ ህዝብበነቂስ በመውጣት በሰልፉ ተቃውሞውን እንዲገልፅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ እንደዘገበው።

   http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12748

søndag 9. februar 2014

የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ!!!


“የግብርና ሚኒስትር” በሚል “የሆድ ሲያውቅ፤ ዶሮ ማታ” ስያሜ የወያኔ የመሬት ሽያጭ ጉዳይ አስፈፃሚው የሆነው የሥርዓቱ ቀንደኛ አገልጋይ “መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም” ብሎ ሲናገር የሰማነው እና ያነበብነው በከፍተኛ ትዝብት ነው።
ለመሆኑ የመሬት ቅርምት ከኢትዮጵያ በላይ ማንን ሊመለከት ነው? ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ሳውዲን፣ ቻይናን፣ ህንድን ወይስ አሜሪካን? ከራሱ ከወያኔ ሹማምንት የተራረፈው መሬት ለአረብ አገራትና ለእስያ ቱጃሮች በነፃ የሚታደለው ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? ባዕዳን የሚረከቡት መሬት ስፋት በሄክታር መለካት ሲሰለቻቸው “ቤልጂየምን የሚያክል” እያሉ በስጦታ ያገኙትን መሬት በአገር ስፋት የሚለኩት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን ካልተመለከተ ከቶ ማንን ሊመለከት ነው?
ወያኔ ለም መሬት ለራሱ ማግበስበሱ ሳያንስ “ልማታዊ ባለሀብቶች” እያለ ለሚያሞካሻቸው ለቅርብም ለሩቅም አገራት ቱጃሮች ሰጥቶ ባለሀገሩን አርሶ አደር ሜዳ ላይ በተነ። መጤው ቱጃር ባለመሬት ሆኖ ባለሀገሩ ለስደት አሊያም ለቀን ሠራተኝነት ተዳረገ። ይህ ግፍ የሚፈጥረው ስቃይ የማይበቃ ይመስል “በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ መሬት ሻጩ “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆኑ ነፃ መሬቶችን ብቻ ነው ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የምንሰጠው። ማንም ከቀዬው አልተፈናቀለም” እያለ ይዘባበትብናል። “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት” የሚባለው መሬት የወያኔ የግል ሀብት ከሆነ ሃያ ሶስት ዓመታት መቆጠራቸው እኛ ብቻ ሳንሆን እሱም ያውቀዋል።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ለብናኝ አፈር በመሰሰት ጎብኚዎችን እግር አሳጥበው ሲሸኙ እንዳልነበር ዛሬ በልማት ስም ከጋምቤላ እስከ መተማ፣ ከባሌ እስከ ሰላሌ፣ ከከፋ እስከ አፋር ያለው መሬታችን በሙሉ ወይ በወያኔ ሹማምንት አሊያም በባዕዳን ቱዳሮች ይዞታ ሥር ሆኗል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሳዎችና ወጣቶች፣ ሕፃናት ሳይቀር የአዳዲሶቹ ባለመሬቶች ተቀጣሪዎች ሆነዋል። ጉልተኛው ሥርዓት ከቀድሞው በባሰ መልኩ ተመልሶ መጥቷል።
ወያኔ እንደሚያወራው ሰፋፊ መሬቶችን የመስጠት ዓላማው ግብርናችንን ለማዘመን ከሆነ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ጠፍተው ነው እሩቅ ምስራቅ እስያ ድረስ የተጓዘው? እነሱስ ለምንድነው ለሊዝ የሚጠየቁትን እዚህ ግባ የማይባለውን ገንዘብ እንኳን ከራሷ ከኢትዮጵያ ተበድረው የሚከፍሉት? ይህ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው? ከዛሬ አርባና አምሳ አመታት በፊት በሁመራ፣ ተንዳሆና ስምጥ ሸለቆዎች ውስጥ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች የነበሯቸው ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ያኔ ኖረው ዛሬ እንደምን ላይኖሩ ቻሉ? የመሬት ባለቤት የመሆን መብት ያለው ኢትዮጵያዊ ወያኔ ብቻ እንዲሆን የተደረገው ለምንድነው? ኢትዮጵያ፣ ወያኔ ወይም የወያኔ አሽከር ላልሆነ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነች? ባለሃገሩን መሬት አልባ፤ ባዕዳንን ደግሞ ባለመሬት ማድረግ ምን ያስከትላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ግብዓት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ከግብዓትም በላይ የፓለቲካ ሥልጣን ምንጭም ነው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ፓለቲካ የመሬት ጥያቄ ቁልፍ የፓለቲካ ጥያቄ ሆኖ የቆየው። ደርግ መሬትን ከጉልተኞችም ከአርሶ አደሮችም በአዋጅ ቀምቶ የመንግሥት በማድረግ መንግሥትን አሳብጦ ገበሬውን አዳከመው። ወያኔ ይኸንኑ መሬት ያለአዋጅ ከመንግሥት ቀምቶ የራሱ በማድረግ ራሱን አሳብጦ ገበሬውን ከቀደሞው በባሰ አዳከመው። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ይህንኑ መሬት ለባዕዳን በመስጠት ገበሬውን በአጠቃላይ ከመሬት ነጥሎ የቀን ሠራተኛ እያደረገው ነው። ይህ ከጪሰኝነት እጅግ የባሰ ባርነት ነው።
በወያኔ እና ታማኝ ተላላኪዎቹ እየተፈፀመ ያለው የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያዊያንን አገር የሚያሳጣ፤ ስብዕናችንን የሚያዋርድ፤ ክብራችንን የሚገፍ፤ ሀብታችንን የሚያዘርፍ በመሆኑ በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል።
ሰው ባገሩ ሰው በወንዙ
ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ
ይታወቅ የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ
ግንቦት7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለባዕዳን መሬታችንን፣ አገራችንን፣ ነፃነታችንን ሰጥተን ከሚገኘው ጥቅም … ባለቅኔው እንዳለው … ሰውነታችን ታውቆ፣ ክብራችን ተጠብቆ ሳርም ይሁን መቅመቆ መብላት እንመርጣለን። የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ። አገራችንን ለማዳን ቆርጠን እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

fredag 31. januar 2014

በሀረማያ ዩኒቨርስቲ በርካታ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደበደቡ

ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስትቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ባለፈው ማክሰኞ  የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት የዩኒቨርስቲግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ በነበሩ  ተማሪዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ  የአንዲት ተማሪ ጆሮመቆረጡንና በርካታ ተማሪዎች እጆቻቸውና እግሮቻቸው መሰበሩን ተማሪዎችና የዩኒቨርስቲው መምህራን ለኢሳትገልጸዋል።
ችግሩ የተፈጠረው የውሃ ኢንጂነሪንግር ተማሪዎች የትምህርት ዘርፍ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።ዩኒቨርስቲው የትምህርት-ዘርፍ  ለውጥ እንደማያደርግ እና መማር የማይፈልጉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣትእንደሚችሉ ማስታወቂያ መለጠፉን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በሚወጡበት ጊዜ የፌደራል ፖሊሶች መንገድላይ በመጠበቅ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ደብደባ ፈጽመዋል።
በአሁኑ ጊዜ የውሃ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ በፖሊሶች እየተጠበቁ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውንአስተዳደር ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

torsdag 30. januar 2014

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው?

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።
ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።
ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?
ሌላው አስገራሚ ክስተት በአገር ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ ታማኝነታችን ለአገራችን ነው ወይስ የሥርዓቱን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም? ብለው ላነሱት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው የህግ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሰጠው መልስ ነው። ደህንነት ብቻ ሳይሆን የመከላኪያ ሠራዊትና ፖሊስ ጭማር ታማኝነታቸውና ግዴታቸው ሥርዓቱን ሥልጣን ላይ ማቆየት መሆን አለበት ሲል ጌታቸው እንቅቹን ነግሮአቸዋል ። በምላሹ “ላለፉት 23 አመታት እያደረግነው ያለው ይሄው ሆኖ ሳለ አሁን ምን ብታስቡ ነው ጥያቄ ያነሳችሁ?” የሚል ይመስላል ። ይባስ ብሎም ሥርአቱን ለመጠበቅ ያልቻለና በግንቦት 7 መንገድ የሚጓዝ ደህንነት ሠራተኛ የተስፋየ ገብረስላሴን ያህል የደህንነት እውቀት ቢኖረውም ሆነ እስራኤል አገር የዓመታት ስልጠና ያገኘ ቢሆን ዋጋ የለውም ብሏቸዋል።
ለመሆኑ ወያኔዎች እንደመርገም የቆጠሩትና ተከታዮቻቸውን የሚያስፈራሩበት የግንቦት 7 መንገድ ምንድ ነው።?
ግንቦት 7 የፍትህና፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረባት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረባት ሃገር ሆና ማየትን ብቸኛ ራዕይ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው። ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ደግሞ እስከ ዛሬ በጠመንጃ ኃይልና በጉልበተኖች ጡንቻ ከአንዱ ወደሌላው የሚፈራረቀው የመንግሥት ና የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትን ፤ የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበት፤ ማኅበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም። ወያኔ የዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሩን ከፈት አድርጎ በነበረበት ምርጫ 97 ወቅት ከተገኘው ልምድና ከተመዘገበው ውጤት ሕዝባችን በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ለመገዛት አለመፈለጉን በግልጽ አስመስክሮአል።
ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ሕዝባችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን የመረጠበትንና ድሉን የተነጠቀመበትን ታሪካዊ የግንቦት 7 1997ን ቀን ምን ጊዜም አይረሳም። መጠሪያ ስሙንም በዚያ ታሪካዊ ቀን የሰየመው ሕዝብ የተነጠቀውን ድል በማስመለስ ፍትህ የሰፈነባት፤ የበለጸገችና የተከበረች አገር ባለቤት እንሆን ዘንድ ነው። ሁላችንም አትራፊ እንጂ ተጎጂ ለማንሆንበት ለዚህ ቅን አለማና ራዕይ ደንቃራ ሆኖ የተገኘው ወያኔና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከወያኔ ጋር የተጣበቁ አንዳንድ ባዕዳን አገሮች ናቸው።
ወያኔ የግንቦት 7 መንገድ የሚለው ለዚህ ክቡር ዓላማ ሲባል እንቅፋት የሆነውን ሥርዓቱን በሁለ- ገብ ትግል አስገድዶ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አካል ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በተባበረ ትግል አስወግዶ በምትኩ በሕዝብ ለሕዝብ ከሕዝብ የሚመጣ ሰላማዊ የመንግሥት ሥርዓት መመሥረትን ነው። ይህንን የተቀደስ አላማ ለማክሸፍና የተጀመረውን ትግል ለመጨፍለቅ ሲባልም ወደ ሥልጣን ለመምጣት በጦርነት ማግዶ ካስጨረሳቸው የደሃ ልጆች በእጥፍ የሚበልጡትን መልምሎ በጸረ ሽምቅ ውጊያ ከማሰልጠን ጎን ለጎን ለግንባታ ቢውል ስንት ፋይዳ ሊያስገኝ ይችል የነበረ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ድምጽ ለማፈንና ለመሰለል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለአገራችን ሉአላዊነት ጠቀሜታው እስከዛሬ ምንም ባልታወቀ ጦርነት ወደ መቶ ሺ የሚጠጉትን ያስጨፈጨፈ፤ የተልዕኮ ጦርነት ለማካሄድ በመንግሥት አልባዋ ጎረቤት ሱማሌ እስከዛሬ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ወገን ያስፈጀ ፤ ለሥራ ፍለጋ ውትድርና የገቡትን ወጣቶች ለይቶ በሰላም አስከባሪ ስም በድንበር ዘለል ጦርነቶች እየማገደ ገንዘብ የሚቀበል፤ ስለአገርና ስለወገን ምን ሊገደው ይችላል?
ትናንት ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የቀደምቶቹ መንግስታት ልጆቻቸውን ለትምህረት ወደ ፈረንጅ አገር እየላኩ የደሃውን ልጅ በጦርነት ይማግዳሉ በማለት በጅምላ ሲከስ የኖረ ዛሬ በተራቸው ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዘርማንዘሮቻቸውን ታይቶ በማይታወቅ ብዛት ወደ ፈረንጅ አገር ለትምህርት እየላኩ ለነጻነታችንና ለክብራችን የምንታገለውን እርስ በርስ ለማጨራረስ ሲዶልቱ ዝም ብሎ መመልከት ከየትኛውም ቅን ዜጋ የሚጠበቅ አይሆንም።
ስለሆነም የበላይ አዛዦቻቸው በሚሰርቁት የሕዝብ ገንዘብ ፎቅ ላይ ፎቅ እየገነቡ ሃብት በሚያካብቱት አገር ሠራዊቱን እረፍት ለመንሳት ሆን ተብለው በሚቀሰቂሱት ግጭቶች ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላው ማዕዘን ያለ ዕረፍት እየተንከራተተ ያለው የመከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት ኃይል ለአገዛዙ አልታዘዝም በማለት ተገዶ ሥልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የማድረግ ወገናዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።
የግንቦት 7 መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን ለማስፈን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የጎጠኞችና የዘራፊዎች ስብስብ በማስገደድ ወይም በማስወገድ ሰላማዊ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህንን ደግሞ የሚፈሩት በሥልጣን ቱርፋትና በሃብት ዘረፋ የሰከሩ ብቻ ናቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

የወያኔ ውሸቶች ለኢትዮጵያ ድሀ ምግብና መጠለያ አይሆኑለትም።

“ኦክስፋም” በመልካም ሥራቸው ከታወቁ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው። በቅርቡ አንድ መቶ ሀያ አምስት አገሮችን ያካተተ ከምግብ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ አራት ዝርዝርና አንድ አጠቃላይ አመላካቾች አሉት። 1. አመላካች አንድ: የምግብ እጥረት ይህ አመላካች “በየአገሮቹ ምን ያህል ለበላተኛው የሚበቃ ምግብ አለ?” የሚለውን ይለካል። በጥናቱ ውጤት መሠረት በምግብ እጥረት እጅግ የተጎዱ የመጨረሻዎቹ አስር አገሮች የሚከተሉት ናቸው: – ቡሩንዲ፣ የመን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ላኦስ፣ ባንግላዴሽ፣ መካከለኛዉ አፍሪካ ሪፑብሊክ እና ህንድ። ኢትዮጵያ አገራችን ከመጨረሻ አራተኛ ናት። 2. አመላካች ሁለት: ለምግብ የመክፈል አቅም (Affordability) ይህ አመላካች “የአገሩ ሕዝብ በአገሩ ዋጋ ምግብ ገዝቶ ለመብላት ምን ያህል አቅሙ ይፈቅድለታል?” የሚለውን የሚመልስ ነው። አሁንም ከመጨረሻ እንጀምር። አንጎላ፣ ዚምባቡዌ፣ ቻድ፣ ጉያና፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ጋምቢያ እና ኢራን የየአገሩ ሕዝብ ምግብ መሸመት የሚቸገሩባቸው አገሮች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ ከመጨረሻ አምስተኛ ናት። 3. አመላካች ሶስት: የምግብ ጥራት ይህ የምግብ ይዘትንና የአያያዝ ንጽህናን የሚመለከት ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ሞዛምቢክ፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሌሶቶ ከመጨረሻው እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ በምግብ ጥራት የመጨረሻዋ አገር ናት። 4. አመላካች አራት፡ የሰውነት ውፍረት እና የስኳር በሽታ ይህ አመላካች ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም ዓቀፍ የጤና ችግር እየሆነ በመምጣቱ የገባ አመልካች ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥሩ ውጤት ያመጣችሁ በዚህ አመላካች ብቻ ነው። ኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝቧ ቀጫጫ ነው፤ የስኳር በሽታም እንደሌላው አገር የተስፋፋባት አገር አይደለችም። 5. አማካይ ውጤት የእነዚህ አራት አመላካቾች ድምር ውጤት አጠቃላይ ውጤትን ይሰጣል። በአጠቃላይ ውጤት: ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ማዳካስካር፣ የመን፣ ቡሩንዲ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌ፣ ሴራሊዮን ከመጨረሻ እስከ አስረኛ ወጥተዋል። ኢትዮጵያ ከመጨረሻ ሁለተኛ ነች። ይህ ምንን ያመለክታል? ወያኔ ባለፉት አስር ዓመታት በተከታታይ ከ11% በላይ ኢኮኖሚውን አሳድጌዋለሁ ሲለን ነበር። እድገቱ ያተኮረው ገጠር፤ ምንጩም ግብርና ነው ብሎን ነበር። ሐቁ ግን ከላይ የተመለከተው ነው። እርግጥ ነው የወያኔ ሹማምንት በከተሞች ሕንፃዎችን ይገነባሉ፤ በገጠሮች በመቶዎች ሄክታር የሚለካ ለም መሬት ይዘው ፈጣን ገንዘብ በሚያስገኙ የአበባ፣ የጫትና የቃጫ ምርት ላይ ተሰማርተዋል። ከራሳቸውም አልፈው ሀብታም የውጭ አገራት ሸሪኮቻቸውን በአገራችን ለም መሬት ይበልጥ ያበለፅጓቸዋል። የእነሱ የግላቸው፣ የቤተሰቦቻቸው፣ የዘመዶቻቸው እና የሸሪኮቻቸው ኢኮኖሚ እየተመነደገ መሆኑን እናውቃለን። ይህን በገዛ ዓይኖቻችን የምናየው ሀቅ ነው። ሆኖም ግን የእነሱ ኢኮኖሚ ማደግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ አለመሆኑ እናውቃለን። አገራችን ከጓረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር ወደ ኋላ እየቀረች መሆኑ ያንገበግበናል። በቅርቡ አክስፋም በጥናት ያረጋገጠዉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በየቤታቸው ከወዳጆቻቸው ጋር በምስጢር የሚያወሩትን እውነት ነው። ከሳምንት በፊት ደግሞ “ኢኮኖሚክ ኢንተለጀንስ ዩኒት” የተሰኘው ታዋቂ የምርምር ተቋም አንድ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ የጥናት ውጤት መሠረት በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉ አስር አገሮች በቅደም ተከተል ሞንጎሊያ፣ ሴራሊዮን፣ ቱርክሜንስታን፣ ቡታን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ላኦስ፣ ቲሞር-ሊስቲ፣ ኤርትራ እና ዛምቢያ ናቸው። በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ አገራችን የለችበትም። በዓለም አቀፍ መድረኮችም የወያኔ መረጃዎች ውሸትነት እየተጋለጡ መሆናቸው በጎ ምልክት ነው። የሚያሳዝነው ግን ይህንን ሀቅ የሚያዉቁ ምዕራባዉያን ለጋሽ አገሮች አሁንም ወያኔን እየረዱና እየደገፉ ሥቃያችን የሚያራዝሙብን መሆኑ ነው። ለዚህም ነው ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው በአገራችን መሠረዊ የሆነ የአስተዳደር ለውጥ ሲኖር ነው ብሎ የሚያምነው። የወያኔ አገዛዝ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተተካ ድረስ የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ መደህየቱ፤ ጥቂት ሀብታሞች ደግሞ በብዙሀኑ ድህነት መበልፀጋቸው አይቀርም። የወያኔ ውሸቶች ለኢትዮጵያ ድሀ ምግብና መጠለያ አይሆኑለትም። ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ማምጣት የምንችለው ወያኔን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ሁለተናዊ እድገት የሚጨነቅ መንግሥት መምረጥ ስንችል ብቻ ነው። ስለሆነም ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በውሸት እድገት እያደናቆረን፤ በተግባር ግን እያደኸየን ያለውን ዘራፊውን ወያኔን አስወግደን በሕዝብ ነፃ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖረን ትግላችን እናጠንክር ይላል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የ2014 የዓለም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች የ2014 የዓለም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ

በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ሊከሰቱ የሚችሉ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋዎች ይፋ ሆኑ፡፡ በርካታዎቹ በአፍሪካ አገራት ሲሆኑ አደጋው ካንዣበበባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሜሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ጄይ ዑልፌልደር የተለያዩ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የ2014ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ትንበያ ከሆነ 40 አገራት ቀይ የአደጋ ምልክት በርቶባቸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲሆን የሚመኙት ነገር ባይሆንም የመከሰቱ ጉዳይ ግን መነገር ያለበት ነው ይላሉ ምሁሩ፡፡
በተለያዩ የአሜሪካ አንጋፋ ጋዜጦች ላይ የተዘገበው ይኸው ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ 40 አገራት ከፍተኛ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ ያነጣጠረባቸው መሆናቸውን በጥናቱ ተገልጾዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ከአፍሪካ መሆናቸው አሁንም አህጉሪቱ ለበለጠ ቀውስ የተጋለጠች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
በቀዳሚነት የመፈንቅለ መንግሥት የሚያሰጋቸው አገራት ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ጊኒ ቢሳው እና ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡ ከአውሮጳ ምንም አገር በዝርዝሩ ውስጥ ያልገባ ሲሆን ዩክሬይን አደጋው ጥላ ካጠላባቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ ከወደ አሜሪካ ዩኳዶርና ሃይቲ ቀዩ የአደጋ ምልክት የታየባቸው ሲሆን ከእስያ ታላንድ፣ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታንን ጨምሮ ስድስት አገራት የመፈንቅለ መንግሥት የቀይ ምልክት አደጋ ካለባቸው 40 አገራት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከ40ዎቹ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 25ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣኑን ለራሱ ታማኞች ብቻ በመከፋፈል እንዲያም ሲል በቤተሰብ ደረጃ በማውረድ እየሸነሸነው በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አዲስ አድማስ ሲዘግብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን እና የነጻው ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገልጾ ነበር፡፡
አፋኝ ሕጎችን በማውጣትና ማንኛውንም ዓይነት የግለሰብ መብት በመንፈግ በአንጻሩ ሊኖር የማይችል የቡድን መብት አስከብራለሁ የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ በተመሳሳይ የሚወጡ መረጃዎችን በማጣጣል ዋጋ ቢስ ሲያደርግ መቆየቱን የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡ በተቀረው ደግሞ “ልማት፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ … ” በማለት የለውጥ ሃሳብ ከመጣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይስተጓጎላሉ በሚል በሕዝቡ ዘንድ ማደናገሪያ በመፍጠር በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች “ጸረ ልማት” በማለት እንደሚወነጅላቸው ያማርራሉ፡፡ በምርጫ ማጭበርበርና ማንኛውንም ፖለቲካዊ ሆነ ማኅበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በሙሉ ቁጥጥር ሥር ማዋል ኢህአዴግ በሥልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ዓይነተኛ መንገዶቹ እንደሆኑ በስፋት ይጠቀሳል፡፡
ይህንን የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ የቀመሩት ምሁር ስሌታቸውን ለማቀናበር የተለያዩ መረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገራቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቅኝ ግዛት የመያዝ ሁኔታ፣ የአገራቱ ዕድሜ፣ ከነጻነት በኋላ የኖሩበት ዓመታት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የእርስበርስ ግጭት፣ የነጻ ምርጫ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በየቀጣናው ያለ የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ፣ ወዘተ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ይህንን አያይዘውም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ ማድረግ የግድ መፈንቅለ መንግሥት ይሆናል ማለት እንዳይደለ ነገር ግን አደጋውን ተመልክቶ አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ እንዳይሆን መከላከል ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ካርታዎቹ የተወሰዱት ከጄይ ዑልፌልደር ብሎግ ነው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የዛሬ ዓመት የአሜሪካንን የደኅንነት ምክርቤት ጠቅሶ ባወጣው ዜና በ2030 እኤአ ከሚከሽፉ መንግሥታት (failed states) መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘግቦ ነበር፡፡ ዜናውን ከዚህ በታች በድጋሚ አትመነዋል፡፡

“በ2030 ከሚከሽፉ መንግሥታት አንዷ ኢትዮጵያ ነች”

ዘገባው የ15 አገራትን ዝርዝር አውጥቷል
የአሜሪካ የብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2030 የሚከሽፉ 15 መንግሥታትን (failed states) ዝርዝር አውጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” ይከሽፋሉ ተብለው ከተተነበዩት የአፍሪካ፣ የእስያና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
እጅግ የነጠረ፣ ያልተዛባና የተጠና ዘገባ ለአሜሪካ የስለላ ተቋማት፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አውጪዎችና ለዓለምዓቀፍ ግንኙነት ተመራማሪዎች በማውጣት የታወቀው የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ምክርቤቱ በሚያወጣቸው ዘገባዎች የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የተለያዩ መ/ቤቶች ተጽዕኖ እንደማያደርጉበት የሚናገር ሲሆን፤ ዘገባዎቹንም ከአድልዎ እና ከአሜሪካ መንግሥት አቋም ነጻ በመሆን እንደሚያዘጋጃቸው ይናገራል፡፡
የም/ቤቱ ዘገባ በተለይ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ለመጪው ፕሬዚዳንት የወደፊቱን የዓለማችን መልክ ምን እንደሚመስል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰቦች እና ዓለምአቀፋዊ ዝንባሌዎች ላይ አቅጣጫ የሚጠቁም ትንበያ ያደርጋል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ ዓለምአቀፋዊ የደኅንነት ዘገባ ያቀርባል፤ ለብሔራዊ የጸጥታ ምክርቤት እና ለአገር ውስጥ ደኅንነት መ/ቤት ምክር ያቀብላል፤ በአጠቃላይ የአሜሪካን የስለላና የደኅንነት ማኅበረሰብ ሊከተል በሚገባው ጉዳይ ላይ አቅጣጫ የሚያስይዝ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
በዚሁም መሠረት ባለፈው የታህሳስ ወር “በ2030 የዓለም አቅጣጫ፡ አማራጭ አገራት” በሚል ርዕስ አንድ ዳጎስ ያለ ጥናት አቅርቧል፡፡ ይኸው 160ገጽ ያለው ዘገባ የዛሬ 17ዓመት የዓለማችን ገጽታ ምን እንደሚመስል ከየአገራቱ በተወሰደ ጥናትና እዚያው በሚገኙ ተመራማሪዎች የሰበሰበውን ያካተተ ነው፡፡ ዓለማችን የምታዘነብልባቸው ቀዳሚ ሁኔታዎች አንዱ ሰዎች በራሳቸው አነሳሽነት ድህነትን ለመቀነስ፣ በትምህርት ለማደግ፣ በቴክኖሎጂና በህክምና ለመራቀቅ እንዲሁም በገቢም የመካከለኛው መደብ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቀሱት አንዱ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው፡፡
ሌሎቹ ዓለምን አንድ አድርጎ በመዳፉ ሥር የሚገዛ ኃይል የማይነሳ መሆኑ ከሚታዩት ከፍተኛ ዝንባሌዎች ተጠቃሽ ሲሆን አሜሪካ ምንም እንኳ “የዓለም ፖሊስ” የመሆኗ ሁኔታ የሚቀንስ ቢሆንም የዓለምን አቅጣጫ መቆጣጠሯ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ የዓለም የሕዝብ ቁጥር ከመጨመሩ አኳያ “እያረጁ” የሚሄዱ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንደሚያሽቆለቁልና ከገጠር ወደከተማ ፍልሰት እንደሚጨምር፤ 60በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በከተሞች አካባቢ ኑሮውን እንደሚያደርግ ይተነብያል፡፡ በዚህም ምክንያት የውሃ፣ የምግብና የኃይል (ኤነርጂ) ፍላጎት ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግ ይናገራል፡፡ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎትም የዓለማችንን አቅጣጫ እንደሚቀይር ያስረዳል፡፡
የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት በስፋት እንደሚቀጥልና በበርካታ ፈርጆች ትብብርና ስምምነት እየፈጸሙ ሰፋ ያለ ዓለምአቀፋዊ ኅብረት እንደሚያደርጉ የሚናገረው ይህ ሪፖርት በየአገራቱ እየሰፋ የመጣው በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ክፍተት የማኅበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ይጠቁማል፡፡ ይህም ቀውስ በአንዳንድ አገራት ውስጥ እየሰፋ በመምጣት ለተባባሰ ግጭትና ክስረት እንደሚያጋልጥ የኑሮ ልዩነቱም የማኅበራዊ ቀውሱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሰው ይተነትናል፡፡ የሃይማኖት ሚና እንደሚጨምር የጠቆመው ዘገባ ይህንኑ ተከትሎ መካረርና ግጭት እንዲሁም አሸባሪነት ለመስፋፋት ሃይማኖት ምክንያት እየሆነ እንደሚሄድ ይናገራል፡፡
በዘገባው ከተነገረው በተጻጻሪ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ወዲህ እስካሁን በ44 አገራት ጉዳይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጣልቃ በመግባት ጦርነት ያካሄደችው አሜሪካ የዓለም ኃያል ሆና እንደምትቀጥል በመናገር ሪፖርቱን የሚያጣጥሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንደማስረጃም አድርገው አሜሪካ በተለያዩ አገራት ያላትን 737 የወታደራዊ ተቋማት ይጠቅሳሉ፡፡ ስለሆነም ዘገባው የአሜሪካ የበላይነት የመቀነሱን ጉዳይ አንስቶ የተናገረውን አይቀበሉም፡፡
ዘገባው የዓለማችንን የወደፊት ሁኔታ ሲተነብይ በዋንኛነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች አንዱ በ2030 የሚከሽፉ መንግሥታትን ዝርዝር ሰጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” የሚከሽፉ መንግሥታት ተብለው ከተጠቀሱት 15 አገራት መካከል ኢትዮጵያ እንዷ ስትሆን አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ኬኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ሃይቲና የመን የተቀሩት ናቸው፡፡
ይሁንና ይኸው ም/ቤት እኤአ በ2015 ፓኪስታን የምትከሽፍ አገር ትሆናለች በማለት ትንቢት ሰጥቶ ይኸው እስካሁን አለች በማለት ዘገባውን የሚያጣጥሉ ክፍሎች ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎቹ አገራት ለመክሸፋቸው በቂ ማስረጃ የለም በማለት የዘገባውን ጥቆማ ይቃረናሉ፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው የመክሸፍ ሁኔታ ሊዋጥለት የማይችለው ኢህአዴግ “ህዳሴ፣ ውዳሴ” ከማለት ይልቅ ይህንን ጉዳይ አጥብቆ ሊያስብበት እንደሚገባና የሥርዓት መበስበስ አመላካች የሆነውን “የመንግሥት ሌቦች” መበራከት መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚገባ ደጋፊዎቹና አመራሩ በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡
በዚሁ የኢትዮጵያ እንደ አገር የመክሸፍ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አሁን ካላቸው ተግባር አኳያ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአውሮጳ የሚገኙ የፖለቲካና ዓለምአቀፋዊ ግንኙነት ተመራማሪ “ችግሩ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውም ነው” ይላሉ፡፡ “በአገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ ከውስጥ የሥልጣን ሽኩቻና ከስብሰባ/ውይይት ጋጋታ ባለፈ መልኩ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የሚችል የተቀናጀና ውጤታማ ተግባር ሊፈጽሙ ይገባቸዋል” የሚሉት ምሁር በውጭ ያለውም “ከጊዜያዊና ጥቃቅን የራስ ክብር የመፈለግ አካሄድ በመላቀቅ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ጡንቻውን በወያኔ ላይ ማሳረፍ ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡ “የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው ዘገባ ላይ በግልጽ እንደተነበየው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ የመጨመሩ ያህል በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህንኑ ለውጥ ማምጣት የሚችል የዘመኑ ቴክኖሎጂ ለአሉባልታና ተራ የፖለቲካ ወሬ ከመጠቀም ይልቅ አገር ለማዳን ተግባር ሊጠቀምበት ይገባል” በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
source: ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

onsdag 29. januar 2014

የኢትዮጵያ መንግስት የግንቦት7 መሪዎችን ኮምፒዩተሮች በዘመናዊ የስለላ መሳሪያዎች ሲሰልል እንደተደረሰበት አንድ አለማቀፍ ተቋም አጋለጠ



-የህዝቦችን ደህንነት ከመንግስታት ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው  ተቋም ለእንግሊዝ መንግስት የገቢዎቸና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአለም ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ለሚታወቁ አገሮች ኮምፒይተሮችን፣ የሞባይልና የስካይፕ የስልክ ግንኙነቶችን እንዲሁም የኢሜል ልውውጦችን በርቀት ሆኖ ለመከታተል የሚያስችለውን ፊን ፊሸር ወይም ፊን ስፓይ በሚል ስም የሚጠራውን የመሰለያ መሳሪያ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ላሉ አገሮች በመሸጥ ዜጎች እንዲሰለሉና ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ  ምርመራ እንዲጀመር” ሲል ጠይቋል።
የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር በሆኑት በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግል ኮምፒዩተር ላይ የመሰለያ ቫይረሱ መገኘቱን በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሙንክ ስኩል ግሎባል አየምርምር ተቋም የሆነው ሲትዝን ላብ ማረጋገጡን ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በደብዳቤው ገልጿል።
የመሰለያ መሳሪያው የሰብአዊ መብቶችን በሚጥሱ 36 አገራት ላይ መሸጡን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በተለይም በቬትናም፣ ማሌዚያና ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለመሰለያነት እየዋለ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኮምፒተራቸው ሲሰለል መቆየቱን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በአንድ የብሃሬን የሰብአዊ መብት ተማጓች ኮምፒዩተር ላይም ተመሳሳይ የስለላ ሶፍት ዌር መገኘቱን ገልጿል።
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለፕራይቪሴ ኢንተርናሽናል ጠበቃ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል። ፕራይቪሲ ኢንተርናሽናል የስለላ ቫይረሱን የሸጠውን ጋማ ኢንተርናሽናልን የተባለውን ድርጅት ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማቀዱን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡ ኢሳት ዜና