የአቃቤ ህግ ይግባኝ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለው ጥቅምት 17/2008 ይወሰናል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ በተረኛ ችሎት ይግባኙ ያስቀርባል ቢባልም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ይህንን ውሳኔ በመሻር ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ለመበየን ለጥቅምት 17/2008 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ ጥቅምት 3/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረቡት የፓርቲ አመራሮቹ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብሯቸው ይግባኝ የተጠየቀበት አብርሃም ሰለሞን ዛሬ የቃል ክርክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ የነበር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን በነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ተረኛ ችሎት ይግባኙ ያስቀርባል ያለውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው አቃቤ ህግ የይግባኝ አቤቱታውን እንደገና እንዲያሰማ አድርጓል፡፡
በመሆኑም አቃቤ ህግ የስር ፍርድ ቤት በአቃቤ ህግ የቀረቡትን የቴክኒክና የሰነድ ማስረጃዎች ይዘት በአግባቡ ሳይመረምር ውሳኔ ስለሰጠብን ውሳኔው አግባብ ስላልሆነ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ እንዲመረምርለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ የይግባኝ አቤቱታ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 17/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው ተከሳሾች እስካሁን በእስር ላይ የቆዩበት ምክንያት አግባብ ስላልሆነ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ተከሳሾች ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በእስር ላይ ሊቆዩ የቻሉት ተረኛ ችሎቱ በሰጠው እግድ መሆኑ ቢገለጽም፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግን አቤቱታው እንዲቀርብ ፈቅዷል፡፡ ተረኛ ችሎቱ ነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ብይኑን ሲሰጥ ተከሳሾች ችሎት ሳይቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar