(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ባለፉት 4 ወራት በነበረው የሕዝብ ተቃውሞ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን ሳይማሩ ቀርተዋል:: ይህን ተከትሎም ያልተምሩትን እንዳይፈተኑ; ለፈተናም በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው እንዲራዘም ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥያቄው ውድቅ በመደረጉ በስርዓቱ ውስጥ ያሉት የውስጥ አርበኞች ተቃውሟቸውን ለማሳየት ፈተናውን በኢንተርኔት ለቀውት ነበር::
ትናንት የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ “የተሰረቀ ፈተና የለም; ብሔራዊ ፈተናው በታሰበለት እና በታቀደለት ጊዜ ይካሄዳል” ቢሉም ፈተናው ግን በሶሻል ሚድያዎች መራባቱን ቀጥሎ ነበር:: ዛሬ ጠዋት እንደገና እኚሁ የትምህርት ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ “እንደማንኛውም ሰው ፈተናው በኢንተርኔት ቀድሞ መበተኑን አይቻለሁ” በሚል ፈተናው እንዲቋረጥ መታዘዙን አስታውቀዋል::
ፈተናው ከመቋረጡ በፊት ዛሬ ጠዋት የተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች ፈተና ተስጥቶ እንደነበርም ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል::
እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ በሃገሪቱ 800 የፈተና ጣቢያዎች እንዳሉና ከየትኛው ቦታ ተሰርቆ እንደወጣ መንግስት የሚጣራ ይሆናል::
One Response to መንግስት የ12ኛ ክፍል ፈተናው መሰረቁን አምኖ ዛሬ ሊሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና እንዲቋረጥ አደረገ