mandag 30. november 2015

እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ! (አንዳርጋቸው ጽጌና እስክንድር ነጋ ለምስክርነት ተጠርተዋል)


esknderበእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል፡፡ በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾችም ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባህሩ ደጉ፣ ሰለሞን ግርማ እና ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ ከሰኞ ህዳር 13/2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ለአራት ቀናት ምስክሮቻቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ 11 ምስክሮች፣ ዮናታን ወልዴ 5፣ ሰለሞን ግርማ 3፣ እና ባህሩ ደጉ እና ተስፋዬ ተፈሪ እያንዳንዳቸው 8 ምስክሮችን ጠርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በአንደኛ ተከሳሽ ለምስክርነት የተጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲቀርቡ አለመደረጋቸው ታውቋል፤ በተጨማሪም በእስር ቃሊቲ የሚገኙትና ለምስክርነት የተጠሩት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽን ማረሚያ ቤቱ ለተከታታይ ቀናት ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢተላለፍለትም ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡
በዋናነት ተከሳሾች በማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸውን አስከፊ የምርመራ ሁኔታና በዚሁ ምክንያት ተገድደው ስለሰጡት ቃል የሚመሰክሩ ምስክሮችን አሰምተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ በምርመራ ወቅት አብረዋቸው ታስረው የነበሩና በኋላ ላይ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ቀርበው የመሰከሩ ግለሰቦች እንዴት ተገድደው በሀሰት እንደመሰከሩባቸው ያስረዱልናል ያሏቸውን ምስክሮች አስደምጠዋል፡፡
ተከሳሾች የተከሳሽነት መከላከያ ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ህዳር 16/2008 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል፣ የቀረበበት ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው (politically motivated) እንደሆነና በምርመራ ወቅትም በፖሊስና ደህንነት ከተከሰሰበት ጋር በማይገናኝ መልኩ ‹‹ምርጫ 2007ን ለማደናቀፍ ቡድን አደራጅተሃል›› በሚል ሲመረመር እንደነበር አመልክቷል፡፡
ዘላለም በሰጠው ቃል የጸረ-ሽብር ህጉ አሸባሪዎችን ለመከላከልና ለመቅጣት ሳይሆን የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ዜጎችን እና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት እየዋለ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ ‹‹በእኔ እምነት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውና ግንኙነት አለህ በሚል የተከሰስኩበት ድርጅት አሸባሪ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ግን እንደ እኔ አይነቶችን ለማጥቃት መጠቀሚያ እንዲሆን ሊፈረጅ ችሏል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ለተከታታይ 41 ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ክፍል በማዕከላዊ እንዳሳለፈና ለአንድ ወር ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኝ እንደተደረገ የተናገረው ዘላለም፣ ‹‹ለለውጥ የሚታገሉ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ላለማሳደር የደረሰብኝን በደል ሁሉ እዚህ መዘርዘር አልሻም›› ሲል ገልጹዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም ተከሳሾች በሰጡት ቃል በማዕከላዊ አስከፊ ምርመራ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡
በዚህ መዝገብ የተካተቱት አቶ ባህሩ ደጉ እስካሁን ምስክሮቻቸውን አቅርበው ያላሰሙ ሲሆን፣ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ እና 6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ ደግሞ ቀሪ ምስክሮቻቸውን የሚያሰሙ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ህዳር 17/2008 ዓ.ም ‹‹ዳኞች አልተሟሉም›› በሚል ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ባለመቻላቸው ለህዳር 24/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚሁ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ እንዲሁም መምህር አብርሃም ሰለሞን በዚሁ ችሎት ነጻ መሆናቸው ቢበየንም በአቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እየተከታተሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡
 
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

søndag 15. november 2015

በረሀብ ለተጠቁ ወገኖቻችን እንድረስላቸው !!!

def-thumb 

በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳግም ለአስከፊ ረሀብና ችጋር ተጋልጧል፤ ስፋት ጥልቀቱ በ70ዎቹና 80ዎቹ ከነበሩት ጋር ይስተካከላል ተብሎ ተፈርቷል። ከአሁኑ ሰው በረሀብ መሞት መጀመሩ ከአራትና አምስት ወራት በኋላ የሚመጣውን አደጋ ከባድነት መገመት ያስችላል።
ለአስር ተከታታይ ዓመታት ከአስር በመቶ በላይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት ዓለምን እየመራን ነው የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ “የህዳሴ ብስራቶች”፣ የአባይ ግድብና የከተማ ባቡር ግንባታ ዜናዎች ለኢትዮጵያዊው አርሶ አደር ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
“አድገናል”፣ “ተመንድገናል”፣ “በምግብ ራሳችንን ችለናል” ሲል የከረመው የህወሓት አገዛዝ የረሀቡ ዜና አፈትልኮ ሲወጣ እና የዓለም መገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ሲሆን የተራበውን ወገናችንን ለማብላት ከመሯሯጥ ይልቅ ተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ከዚህ አልፎ ዓመታዊ ድግሶቹ እና ለባለሥልጣናቱ የሚሰጡ ጥቅማጥቅሞች ጉዳይ ከረሀብ በላይ አሳሳቢ በመሆኑ 15 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በሞት አፋፍ ላይ እያለ የአገሪቱ ሀብት ለድግስና ፈንጠዚያ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ባለሥልጣን ቤተመንግሥት አከል መኖሪያ ቤት ማሠሪያ እየዋለ ነው። መቀሌ ላይ ህወሃት 40ኛ ልደቱን ለማክበር ወደ ግማሽ ቢልዮን ብር ባወጣ ማግስት በአማራ ስም ለወያኔ ባርነት የገባው ብአዴን 300 ሚሊዮን ወጪ በማድረግ በረሃብተኛው ሕዝብ አናት ላይ እየጨፈረ ነው:: ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ደጋግሞ ከመግደል የሚቆጠር ወንጀል ነው።
ለመሆኑ የአየር ንብረት መዛባት እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? ለምንድነው ፍትህና ነፃነት በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ዝናብ ጠፍቶ የእርሻ ምርት ቢቀንስ እንኳን ሰው በረሀብ የማይሞተው? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸውስ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? ለምንድነው ተደጋግሞ ከሚመጣ የረሀብ አዙሪት መውጣት ያቃተን?
የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ አጭርና ቀጥተኛ ነው። ለችግሮች መፍትሄ መሻት የሚቻለው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ለዚህም ነው የአስተዳደር በደልና ረሀብ ምክንያትና ውጤት ብቻ ሳይሆን እጅና ጓንትም ጭምር የሆኑት።
ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት መሆኑ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ሀቅ ነው። ከረሀብ መገላገያ መንገድም የተበላሸ አስተዳደር ተወግዶ ኃላፊነት የሚሰማው፣ የዜጎች የማሰብ ነፃነት የሚያረጋግጥ ሕዝባዊ አስተዳደር ሲኖር ነው።
አገራችን ኢትዮጵያን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የወያኔ “የዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1.ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች መሬት አልባ ሆነዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም ለህወሓት ጉልተኞችና ምስለኔዎቻቸው ታድሏል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን ሽጠውታል። ኢትዮጵያዊው አርሶ አደር በሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። በዚህም ምክንያት ገበሬው እንኳንስ ትልቁን የአየር መዛባት ትንሿንም የዋጋ ንረት መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2.ዘርን መሠረተ ባደረገ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊው ጎበዝ አርሶ አደር አንዱ ቦታ ቢከፋ ወደ ተሻለ ቦታ ተዛውሮ ማረስ አልቻለም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሄደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ባህር ተሻግሮ የመጣ ኤንቨርስተር ነኝ ባይ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ገበሬ በዱላና በጥይት ሲባረር፤ ከባዕድ አገር የመጣው ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3.የህወሓት ባላሥልጣኖችና በየቦታው ያስቀመጧቸው ምስለኔዎቻቸው ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች፣ ከፍ ሲልም ባለ ቢሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር ከትቢያ የተነሱ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ረሀብ እጣ ፈንታችን እንዲሆን አድርጓል።
4.በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት ማደር መሆኑን የህወሓት አበጋዞች በተግባር እያሳዩ ሠርቶ፣ ለፍቶ ማደግ ሞኝነት እንዲሆን አድርገውታል። በዚህም ምክንያት በባህላችን ውስጥ ኮትኩተው ያሳደጓቸው አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
5.ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በህወሓት የአገዛዝ ዘመን የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
6.ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ድርቅን መቋቋም ስለሚችሉ ሰብሎች ወይም የአስተራረስ ዘዴዎች ማሰብ፣ መመራመርና መፈተሽ አይችሉም። አዲስ ነገር መሞከር “የኢህአዴግ የግብርና ፓሊሲን“ በመቃወም ወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ሆኗል። በዚህም ምክንያት ገበሬው ድርቅን መቋቋሚያ አዳዲስ ዘዴዎች መፈለግ ቀርቶ በተለምዶ የሚያውቃቸውንም መጠቀም አልቻለም።
7.የህወሓት አገዛዝ፣ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። አገዛዙ ውጤታማ የስነ ሕዝብ ፓሊሲ የለውም፤ እንኳንስ የቀጣይ ዓመታት የሕዝብ እድገት ምጣኔን ሊቆጣጠር አሁን ያለነው ቁጥራችን ስንት እንደሆነ እንኳን በትክክል ሊነግረን አልቻለም፤ ረሀብ ነው መብዛታችንን እየነገረን ያለው።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ ያሰፈነው ብልሹ አስተዳደር መሆኑን በአንጽዖት ይናገራል። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን መከላከያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ረሀብን ለማጥፋት ህወሓትን ከሥልጣን ማስወገድ ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ላይ ተደርሶአል ብሎ አርበኖች ግንቦት 7 ያምናል።
ነገር ግን ረሀብ ጊዜ አይሰጥም። የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ በሞት አፋፍ ላይ ላለ ወገናችን መፍትሄ አይሆንም። ስለሆነም ለረሀቡ መሠረታዊ መፍትሄ የሆነውን ትግላችንን ሳንዘነጋ የወገኖቻችንን ሕይወት ለመታገድ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል። ሲቪክ ማኅበራት የተራበው ወገናችን የወያኔ መጠቀሚያ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያገኝበት መንገድ እንዲያፈላልጉ እና ወገን ለወገን የሚቆምበትን ዘመቻ እንዲያስተባብሩ ጥሪ ያደርጋል። ለወገኖቻችን የሚላከው እርዳታ ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ ወደአገዛዙ ባለሥልጣኖች የግል ኪስ እንዳይፈስ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባል። ለወገኖቻችን ለመድረስ እያንዳንዳችን በግል፤ እንዲሁም በቡድን የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም.

søndag 25. oktober 2015

የኢሳት 5ተኛ አመት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ!


 ዲቦራ ለማ/ኖርዌ

አርቲስና አክቲቪስት ታማኝ በየነ እንዲሁም ታዋቂው የኢሳት ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው በተገኙበት ኢሳት የተቋቋመበትን የአምስተኛ አመት በአል በደማቅ ሁኔታ በኦክቶበር 24፣ 2015 በኦስሎ ከተማ ተካሄደ። በዝግጅቱ ላይ ከተለያየ የኖርዌ ከተማዎች የመጡ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተውበታል።



ዝግጅቱ በኖርዌ የሚኖሩ ታዳጊዎች ኢሳት የተመለከተ ዝማሬ አቅርበው ታዳሚውን ያስደመሙ ሲሆን በመቀጠል በኖርዌ የኢሳት ኮሚቴ ሊቀመንበር የእንኳን ደህና መጣችሁና የመግቢያ ንግግር በማድረግ ፕሮግራሙን ጀምሯል። በመቀጠል የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ መጣጥፎችና ግጥሞች እንዲሁም አጭር ጭውት በዝግጅቱ ላይ ቀርቧል። ለገቢ ማሰባሰቢያው የሚውል የምግብና መጠጥ ሽያጭ፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች ሽያጭ እንዲሁም የትኬት ሽያጮች ተካሂዷል።

ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው የሚያስደንቅ ስራውን በመድረክ ያቀረበ ሲሆን አርቲስት ታማኝ በየነም የተለያዩ መረጃዎችን ለህዝቡ አቅርቧል። የጨረታው ሰአት ሲደርስ ጨረታውን አርቲስት ታማኝ በየነ የመራ ሲሆን በጨረታው ላይ በርካታ ተሳታፊዎች ተሳትፈዋል። የጨረታውን ዋንጫ ያቀረቡት በኖርዌ በርገን ከተማ ነዋሪ የሆኑ የኢሳት ቤተሰቦች ሲሆኑ በመድረክላይም ኢሳት ይቀጥላል የሚል የራሳቸውን ዝማሬ አቅርበዋል።

ከጨረታ፣ ከምግብና መጠጥ ሽያጭ፣ እንዲሁም ከትኬት ሽያጭ እንዲሁም ከተለያዩ ነገሮች ሽያጭ ለኢሳት ከፍተኛ ገቢ ተገኝቷል። ዝግጅቱ በደማቅ ሁኔታ በኖርዌይ የሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 23፡00 ተጠናቋል።



ኢሳት በእኛ ድጋፍ ይቀጥላል!!

tirsdag 20. oktober 2015

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት አስመረቀ

October 20, 2015
የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ
Professor Berhanu Nega with Patriotic Ginbot7 fighters
አርበኞች ግንቦት 7 በሁለት ድርጅቶች ማለትም በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና በግንቦት 7 ንቅናቄ ውህደት ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ከተመሰረተ በኋላ ከትናትና በፊት እሁድ ዕለት ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓም ለሁለተኛ ጊዜ ብዛት ያላቸውን አርበኛ ታጋዮች ለሦስት ወራት አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡
እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሁለተኛ ዙር ተመራቂ አርበኛ ታጋዮች ለሦስት ተከታታይ ወራት የተሰጣቸውን የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ የመረጃና ደህንነት ትምህርቶችን በሚገባ ወስደው በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ነው ሊመረቁ የቻሉት፡፡
እጅግ በጣም ደማቅ በሆነ ስነ-ስርዓት በተከናወነው የምረቃ በዓል ላይ ከተለያዩ ቦታዎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የታደሙ ሲሆን የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር አርበኛ ታጋይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የድርጅቱ የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አርበኛ ታጋይ ተስፋሁን ተገኝ ንግግር በማሰማት ለተመራቂ አርበኛ ታጋዮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከውህደቱ ኋላ የመጀመሪያውን ዙር ሰልጣኞች ያስመረቀው ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል፡፡
Patriotic Ginbot7 fighters

onsdag 14. oktober 2015

በእነ ሀብታሙ አያሌው ላይ ተረኛ ችሎት የወሰነውን ይግባኝ ሰሚ ሻረው

የአቃቤ ህግ ይግባኝ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለው ጥቅምት 17/2008 ይወሰናል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ በተረኛ ችሎት ይግባኙ ያስቀርባል ቢባልም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ይህንን ውሳኔ በመሻር ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ለመበየን ለጥቅምት 17/2008 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Habtamu abrhayeshiwas daniel
ዛሬ ጥቅምት 3/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረቡት የፓርቲ አመራሮቹ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብሯቸው ይግባኝ የተጠየቀበት አብርሃም ሰለሞን ዛሬ የቃል ክርክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ የነበር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን በነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ተረኛ ችሎት ይግባኙ ያስቀርባል ያለውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው አቃቤ ህግ የይግባኝ አቤቱታውን እንደገና እንዲያሰማ አድርጓል፡፡
በመሆኑም አቃቤ ህግ የስር ፍርድ ቤት በአቃቤ ህግ የቀረቡትን የቴክኒክና የሰነድ ማስረጃዎች ይዘት በአግባቡ ሳይመረምር ውሳኔ ስለሰጠብን ውሳኔው አግባብ ስላልሆነ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ እንዲመረምርለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ የይግባኝ አቤቱታ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 17/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው ተከሳሾች እስካሁን በእስር ላይ የቆዩበት ምክንያት አግባብ ስላልሆነ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ተከሳሾች ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በእስር ላይ ሊቆዩ የቻሉት ተረኛ ችሎቱ በሰጠው እግድ መሆኑ ቢገለጽም፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግን አቤቱታው እንዲቀርብ ፈቅዷል፡፡ ተረኛ ችሎቱ ነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ብይኑን ሲሰጥ ተከሳሾች ችሎት ሳይቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47406#sthash.fJjDuUvj.dpuf

tirsdag 13. oktober 2015

ሐብታሙ አያሌው በኩላሊት ጠጠር መታመሙ ተገለጸ * እነ አብርሃ ደስታ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

  • 27
     
    Share
habtamu ayalew
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47386#sthash.GZ4e0GZW.dpuf
(ዘ-ሐበሻ) በ እስር ቤት የሚገኘው ታዋቂው ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው ዛሬ በድንገተኛ ህመም ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስዶ እንደነበር ተዘገበ:: በአዲስ አበባ የሚገኙ የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳሉት ሃብታሙ ከ እስር ቤት ወደ ዘወዲቱ ሆስፒታል የተወሰደበት ምክንያት በሁለቱም ጎኖቹ ላይ የህመም ስሜት ስለተሰማው ነበር:: የዘውዲቱ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ምርመራ ካደረጉለት በኋላ ህመሙ የኩላሊት ጠጠር መሆኑን ለባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሄም መናገራቸውን እነዚሁ ምንጮች አብራርተዋል:: ሃብታሙ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተመለሰ ሲሆን በነገው ዕለትም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተገልጿል:: ከሃብታሙ አያሌው ጋር አብረው የተከሰሱትና በቅርቡ በከፍተኛው ፍርድ ቤት በነፃ የተለቀቁት አብርሃ ደስታ; ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋም በነገው ዕለት አቃቤ ሕግ ይግባኝ በጠየቀባቸው ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው የቃል ክርክር ያደርጋሉ ሲሉ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል:: 


søndag 4. oktober 2015

ኢሳት በእኛ ድጋፍ ይቀጥላል!!


ኦክቶበር 2, 2015
ዲቦራ ለማ/ኖርዌ/

አለማችን አሁን ያለችበት ዘመን በከፍተኛ  ደረጃ መረጃ ከአንዱ ወደ አንዱ በየሰከንዱ እየፈሰሰ አለምን ወደ አንድ ጎራ አምጥቶ የመረጃን ጠቃሚነት እያየን የመጣንበት ጊዜ ነው። መረጃ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴን ለማዳበር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።

እንደሀገራችን ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ በተቃራኒው መረጃ ለህዝብ እንዳይደርስ የመረጃ መረቦችን በሙሉ በመበጣጠስና በማገድ ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ እንዳይደርስ ሲከላከሉ እናያለን። በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው የመረጃ ምንጭ አንድ የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዝንና ራዲዮ ሲሆን ሌሎችም የስርአቱ አቀንቃኝ የሆኑ እንደ ሬዲዮ ፋና ያሉ የግል ልሳናት አሉ። እነኚህ የወያኔ ልሳኖች አርባ ስምን ሰአት ያለምንም እፍረት የስርአቱን ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ውለው ያድራሉ።
ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ ከፍተኛ ጫና በማሳደርና የህዝቡን ንብረት በመዝረፍና ህዝቡን ጦም በማሳደር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በመክፈል ትክክለኛ መረጃ እያቀረበልን የሚገኘውን የኢሳትን ጣቢያ በተደጋጋሚ በማፈን ስርጭቱን ለማቋረጥ ወያኔ ብዙ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

ሆኖም ግን ኢሳት በህዝብ ድጋፍ ዛሬም ትክክለኛ መረጃን እያደረሰ የህዝብ አይንና ጆሮ ሆኖ ቀጥሏል። አምባገነኑ የወያኔ ስርአት ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችንና ፀሀፊዎችን በእስር በማንገላታትና ከሀገር በማሰደድ መረጃን ሊያጠፋ ቢሞክርም ኢሳት ግን ዛሬም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ በሀገሪቱ ላይ የሚሰሩ ወንጀሎችን በማጋለጥ ለህዝቡ መረጃን እያቀረበ ይገኛል።

ኢሳት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለውና አንድ ብቸኛ ትክክለኛ መረጃ አቅራቢ ተቋም ሆኖ በህዝብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ የህዝብ ሀብት ነው። ኢሳት በዚህ መልኩ በብዙ መሰናክሎች ውስጥ አልፎ  እነሆ ዛሬ 5ተኛ አመቱን በተለያዩ ሀገራት እያከበረ ይገኛል። በኦክቶበር  24, 2015 ደግሞ የኖርዌ ዋና ከተማ በሆነችው ኦስሎ ኢሳት 5ተኛ አመቱን በከፍተኛ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በኖርዌ በተለያዩ ከተሞች የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደዚህ ዝግጅት ተጋብዛችኋል።

የአምባገነኖችን እድሜ ለማሳጠርና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ትክክለኛ መረጃ ለሀገራችን ህዝብ ወሳኝ በመሆኑ ኢሳት እንዲቀጥል የሁላችንም ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ በስፍራው ተገኝተን የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናድርግ ብዬ ጥሪዬን አቀርባለሁ።



መረጃ ኃይል ነው


በእኛ ድጋፍ ኢሳት ይቀጥላል!!!!