ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዋና የመነጋገሪያ አርዕስት የነበረው አራት የአየር ሃይል አብራሪዎችና አስልጣኝ መኮንኖች ከዘረኞቹና ከዘራፊዎቹ ጎራ ወጥተው ወደ ነፃነት ታጋዮች ጎራ የመቀላቀላቸው ጉዳይ ነበር። እነዚህ ቆራጥና አገር ወዳድ አብራረዎች የወሰዱት እርምጃ ወገንን የሚያኮራና ከፍተኛ ጀግንነትን የሚጠይቅ ትልቅ ውሳኔ ነው።ይህ ውሳኔ ሰው ባጣች አገር፤ጀግና ባጣች አገር፤ለአገር ለወገን ተቆርቋሪ ባጣች አገር ውስጥ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በያለበት በተለያየ መንገድ ይህን የጀግና ውሳኔ የወሰኑ ልጆቹን እያደነቀም እያመሰገነም ይገኛል::
የግንቦት ሰባት ንቅናቄም ይህን የጀግና ውስኔ የወሰኑ ወንድሞቹን እንኳን ተወለዳችሁ፤ እንኳንም ተማራችሁ፤ እንኳንም ወደ ነፃነቱ ትግል ተቀላቀላችሁ እያለ ደስታውንና ለጀግኖቹ ያለዉን ከፍተኛ አክብሮት ይገልፃል። ውሳኔያችሁ ከፈርዖን ቤተ-መንግስት ምቾት ይልቅ ከህዝቤ ጋር መሰደደ ይሻለኛል ያለውን የታላቁን ሰው የሙሴን ውሳኔ ይመስላልና የወሰዳችሁትን ትክክለኛ እርምጃ ትውልድ ምን ግዜም አይረሳዉም።
የእነዚህ ቆራጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች፣ ሙያና ችሎታ ስጋዊ የሆነ ፍላጎታቸውን ለማርካት ከበቂ በላይ ነው።ከዘረኞቹና ከቃየላውያኑ ቡድኖች ጋር እየተሞዳሞዱ ለመኖርም የሚሳናቸው አልነበሩም።ሆኖም ግን ዘረኞቹ(ህወሃቶች) የሚፈፅሙትን ግፍ ተሸክመው ፤ብኩርናቸውን ሽጠው እና ከሰው ተራ ወርደው ለመኖር ሂሊናችው አልፈቀደላቸውም።ለሚበላና ለሚጠጣ ከንቱ ነገር ብለው ጥቂት ዘረኞችን ተሸክሞ ከመኖር ይልቅ የነፃነቱን መንገድ መርጠዋልና ጀግኖች ብለን ብናወድሳቸው ተገቢ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ የሚወስን ሃሞተ ኮስታራ ጀግና እንጂ ሌላ አይደለም።
አሁንም ለራሳችሁ ክብር ያላችሁና ተመሳሳይ እርምጃ ለመዉሰድ በዝግጅት ላይ የምትገኙ የአገር መከላከያ አባላት እንዳላችሁ እናውቃለን። ቅምጥሎቹ ጄኔራል ተብየዎች ከድሃ ወገኖቻችሁ ላይ የዘረፉትን ዘርፈው አገሪቷን ጥለው መሄድ ጀምረዋል። ቀሪዎችም የዘረፉትን የድሃ ንብረት ወደ ውጪ አገር እያሸሹ እንደሆነም ይታወቃል።በአጠቃላይ በእናንተ ምርኩዝነት አገራችንን እያፈራረሷት፤ህዝቧንም እያወረዷት ነው።የህዝቡም መከራና እሮሮ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም።እንዲህ አይነቱን ግፍና በደል እያዩ ከንፈር መምጠጥ እያበቃ ነው።እንግዲህ አሁን እኔ ብቻየን ምን አደርጋለሁ የሚባልበት ግዜ እያለፈ ነው።ጋሻ መከታ እና የኋላ ደጀን የሚሆኗችሁ ብዙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን በየቦታው አሉ።ብትወድቁ የሚያነሷችሁ፤ብትደሙ ደማችሁን የሚያብሱላችሁ፤ብትሰው መስዋእትነታችሁን ለትውልድ የሚዘክሩላችሁ ወገን አለላችሁ።አትፍሩ። ከዘረኞቹ መንደር ወጥታችሁ የነፃነቱን ትግል እንድትቀላቀሉ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
ህውሃት ማለት የዘራፊዎች እና የጨካኝ ነፍሰ ገዳዮች ስብስብ መሆኑን ያለምንም ጥርጥር ማመን አለባችሁ።ህወሃት ስንቱን አርዶ፤ስንቱን ገድሎ፤ስንቱን አጥፍቶ፤የስንቱን ኑሮ በትኖ፤ስንቱን ዘርፎ ባዶ እጁን አስቀርቶ በትረ ስልጣኑን እንደያዘ ምስክር የሚያስፈልገን አይደለም።
የህውሃት ዘረኝነትና ዝሪፊያ የቆጨህ እና ለራስህ ክብር ያለህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተነስተህ ትግሉን ተቀላቀል።እነዚህን ግፈኞች የሚፈፅሙትን በደል እያዩ ዝም ማለት ግፉን ከመደገፍ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።እናንተ ለራሳችሁ፤ ለወገናችሁና ለአገራቸችሁ ክብር ያላችሁ ዜጎች ዝም በማለታችሁ ህወሃቶች ዝምታችሁን እንደ በጎ ፈቃድ ቆጥረውት የግፍ ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው ሊመልሱ ፈቃደኞች አልሆኑም።በማን አለበኝነታችውም ፀንተው ቆመዋል።እነዚህን ግፈኞች በቃ ለማለት ግዜው ደርሷልና የነፃነቱን ትግል ሳትዘገዩ አሁኑኑ ተቀላቀሉ።
እኛም ወደ ነፃነት ትግሉ እንድትቀላቀሉ ጥሪ ስናደርግላችሁ ለአገራችን ክብርና ለወገኖቻችን በሰላም መኖር ስንል ቆርጠን የተነሳን መሆናችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።የግንቦት ሰባት ንቅናቄ በምንም ሁኔታ በዘረኞች እጅ ተንቆና ተዋርዶ መኖርን አይቀበልም።እንዲህ ዓይነቱን ውርደት ተቀብሎ ለመኖር ሰው መሆናችን ይከለክለናል።እነዚህን ዘራፊዎች ተሸክመን ከመኖር ከነፃነታችን ጋር አያቶቻችን በተሰውበት ተራራ ላይ ቆመን መሰዋትን እንመርጣለን።አሁን ተነስተናልና የሚያቆመን የለም። እግዚአብሄርም መንገዳችንን ያከናውንልናል። ኑ ሀገርን ለማዳን የነጻነት ትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!