ሀገር ወዳድ መሆን እኮ ጦርነትን በሀገር ላይ ማሰብ አደለም፤ ሀገር ወዳድ እኮ መንግስት ህዝቡን ሲበድለው የራስን ኑሮ ደልቀቅ አድርጎ ማየት አደለም፤ ህዝብ ሲራብ ቆሞ ማየት አደለም፡፡ ምን አልባትም ችግርን አብሮ መጋፈጥ ትልቅ እሴት አለው
‹‹ ደረጃ ዜሮ ›› በገለልተኛ ጥናት ያልታገዘ የፀረ ሙስና ትግል
የዛሬ የጽሑፌ ማጠንጠኛ በአገሪቱ ያለው የፀረ ሙስና ትግል በጥናትና ምርምር፣ ብሎም በሕዝብ ምክክርና ተሳትፎ ገና ያልዳበረ መሆኑን መሞገት ነው፡፡ መንግሥት በተለይም ‹‹የሕዝቡ ተሳትፎ ጨምሯል›› ቢልም በሌላው ዓለም ኅብረተሰቡ ሙስናን ከሚታገልበት ሁኔታ አንፃር እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ገለልተኛ የዘርፍ ተቋማትና ምሁራን በጥናት ላይ የተመሠረተ የፀረ ሙስና ትግል ተሳትፏቸው ‹‹ዜሮ ደረጃ›› ላይ የሚገኝ የሚባል ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?
በጥናት ላይ የተመሠረተ ትግል የተሟላ ውጤት ያስገኛል
ከስድስት ወራት በፊት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ያወጣው አንድ መረጃ በስፔን የክልል ፕሬዚዳንቶችንና ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ300 በላይ የሚሆኑ ባለሥልጣናት በሙስና መዘፈቃቸውን ይፋ አደረገ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራሆይ መንግሥት በሙስና እንዲታማ በዋናነት አስተዋጽኦ አድርገዋል የሚባሉት የቀድሞው ሕዝባዊ ፓርቲ ዓቃቤ ንዋይ ሉዊስ ባርሲናስ ነበሩ፡፡ 22 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ በስውስ ባንክ ደብቀው በማስቀመጣቸው ማለት ነው፡፡ ይህና ሌሎች በርካታ የሙስና በደሎች መፈጸማቸውን ያረጋገጠው ግን ጠንካራው ጥናትና ጥርስ ያለው የሕትመት ሚዲያ ነበር፡
፡
፡
የሙሪካ ዩኒቨርሲቲ የሙስና ወንጀሎች ኤክስፐርት ፈረናንዶ ኤሚኔዝ ‹‹የሙስና ቅሌቱ ከኢኮኖሚ ችግር ጋር ተቀላቅሎ በአገልግሎት አሰጣጥና በማኅበረሰቡ ላይ የፈጠረው የከፋ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝባዊ ፓርቲው በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለሙስና እጃቸውን መስጠታቸው አስተዋፅኦ አድርጓል፤›› ብሏል፡፡
እንደ አሚኔዝ ገለጻ ባለፉት 10 ዓመታት በአገሪቱ የተከሰተው ሙስና በአመዛኙ የተፈጸመው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በተሟሟቀበት ወቅት በግንባታና በከተሞች መሪ ዕቅድ ላይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለሕዝብ አስተዳደርና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጥ ልገሳና ድጎማ እንዲሁም የኮንትራት አሰጣጥ ላይ ነው፡፡ ይህን የጥናት ግኝት መሠረት ያደረገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የስፔን ባለሥልጣናት ድፍረት የተሞላባቸውን በርካታ ዕርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል ነው ያለው፡፡ በእርግጥም መላው ሕዝብና ፓርቲው ከባድ የፀረ ሙስና ትግል ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልወሰዱም፡
፡
በአገራችን ባለፉት 11 ዓመታት የፀረ ሙስና ትግል ውስጥ የትኛው ገለልተኛ ወገን በሙስና ላይ ጥልቅ ምርመራ አድርጓል በማለት መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአነስተኛ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በከፍተኛ ሙስና ጉዳዮች ላይ አንዳችም ጥናት ወይም ምርመራ አልተካሄደም፡፡
ይህም ሆኖ ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥናት በአገሪቱ ፈጣን ዕድገት ውስጥ አስደንጋጭ የሙስና ዝንባሌ እንዳለ አረጋግጧል፡፡ እንዲያውም ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለዓመታት ‹‹በአገሪቱ የከፋ ከፍተኛ ሙስና የለም›› ይለው የነበረውን አስተያየት የሚቀረን ጥናት እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ጥናቱ ያመለከታቸው የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የመሬትና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፎች መንግሥትም ትኩረት አድርጎ የሚከታተላቸው ናቸው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያም ቢሆን ይህ ነው የሚባል የምርመራ ጥናት አድርጎ የሙስና ሥጋቶችን እንዳላመለከተ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናት ምርመራም ሚስጥራዊ (Confidential) ባህሪ ያለው ነው፡፡ እንዳስፈላጊነቱ ከብሔራዊ መረጃ መረብ ደኅንነትና የፀጥታ ዘርፍ ጋር አልፎ አልፎም በራሱ የማያጠናቸው የሙስና ጉዳዮች እንዳሉ ከተቋሙ የወጣ መረጃ ያስገነዝባል፡፡ ክፍተቱ ግን በአንድ በኩል ጊዜ የሚወስድ መሆኑ፣ ሁለተኛ ኮሚሽኑ ራሱ የመንግሥት ተፅዕኖ ያለበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል እጅግ ውስን የሚባሉ ጉዳዮችን የሚመረምር በመሆኑ ነው፡፡ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ፍርድ ቤት ካስቀጣ በኋላ ሌሎችን በሚያስተምር መንገድ ለሕትመት ማብቃቱን ግን የሚወዱት አሉ፡፡
‹‹የአገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አገር ሊጠብቅ የሚችል የፀረ ሙስና ትግል አጋር የሆነ ጥናት ከማጥናት ይልቅ ራሳቸውም በሙስና የተተበተቡ ናቸው፤›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አጋጥመውኛል፡፡ በተቋማት ግንባታ፣ በመንግሥት ግዥና ክፍያ፣ በትምህርት አሰጣጥና መድልኦ፣ በመልካም አስተዳደርና መሰል የለውጥ እንቅፋቶች የታሰሩ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እጆች ደፍረው የፖለቲካ መሪዎችንና አጠቃላይ የመንግሥታዊ ሥርዓቱን የሙስና ጉዳይ ለመመርመር አቅም እንደማይኖራቸው በመጠቆም፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ፣ ትላልቅ የሙያ ማኅበራት፣ የሲቪክ ማኅበራትና ሕዝባዊ ተቋማትም ሚናቸው አልታየም፡፡ በዚህ ረገድ የትናንቷ ደቡብ ሱዳን የተሻለ ተሞክሮ አላት፡፡ ገና ሦስት ዓመት ያልሞላው መንግሥታዊ ሥርዓቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ወደ ገደል እየወረወረ መሆኑን የሙስና ገመናውን በማጋለጥ ያወጡት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የአገር ውስጥ ሲቪክ ማኅበራት የተሠሩ ጥናቶች ናቸው፡፡ በእርግጥም ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሙስና መዘረፉን የተረዱት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጠንከር ያለ ዕርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡ መጨረሻው ካማረላቸው!?
ከእነዚህ እውነቶች አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛ በሆኑ ምሁራን የአገሪቱን የሙስና ደረጃ ማስጠናት ይጠቅመዋል፡፡ ከፖለቲካ መዋቅሩ ትግልና ሲቪል ሰርቪስ የለውጥ መሣሪያዎችን እንዲተገብር ከማድረግ ጎን ለጎን ኃላፊነትና ተጠያቂነት መጠናከር አለበት፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃን መጠቀም ደግሞ ለሁለት ነገር ይጠቅማል፡፡ አንደኛው ችግሩን ከተደበቀበት ዋሻ ለማውጣት ያስችላል፡፡ ሁለተኛው ግን በግምት ከሚነገረው ያነሰ ሙስና ከሆነ በአገሪቱ ያለውን የመንግሥት ንፅህና አፍ ሞልቶ ለመናገር ያስችላል፡፡
ጥናት የሚጠላ የሚዲያ ባህላችን መቀየር አለበት
በአገሪቱ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በርካታ የሕትመት ሚዲያዎች በግል፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሲቪክ ማኅበራትና በመንግሥት ባለቤትነት ሲታተሙ ቆይተዋል፣ አሁንም እየታተሙ ነው፡፡ ብዙዎቹ ታዲያ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአገሪቱን የሙስና ገጽታ በተከታታይነት አለማቅረባቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይስማሙበታል፡፡ ለዚህ ችግር ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚዲያዎቹ አበቃቀል በአሉባልታ ላይ መመሥረት፣ የፋይናንስና የክህሎት ውስንነት፣ የመንግሥት አካላት በጎ ፈቃደኝነት መታጣት፣ ሥራው የሚጠይቀው አድካሚነትና ጊዜ ምክንያት በሚዲያው ጠንካራ ትግል ሙስና ሥሩ ሊነቀል አይችልም፡፡
ለምሳሌ ቀደም ሲል በተጠቀሰው የስፔን ሙስና መጋለጥ ላይ ኤልፕይስ የሚባለው የአገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ጋዜጣው ‹‹የባርሲናስ ሚስጥራዊ ወረቀቶች›› በሚል ርዕስ በቀድሞው የፓርቲው ገንዘብ ያዥ በእጅ የተጻፉ 14 ወረቀቶችን ያጋለጠ ሲሆን፣ ወረቀቶቹ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከመድረክ ጀርባ በሚያደርጉት ድርድር ሕገወጥ ጥቅም ማግኘታቸውን አረጋግጧል፡፡ ጋዜጣው እንደዘገበው የወረቀቶቹ ሚስጥር ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ በርካታ ባለሥልጣናትን እንደሚያካትት አሳይቷል፡፡ ከእነርሱም መካከል በአሁኑ ወቅት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ማሪያ ዴ ሎሪስ ዶ ኮስፒዳልና አንዳንድ ሚኒስትሮች እንደሚገኙበት ትስስሩን አጋልጧል፡፡ ጋዜጣው በተከታታይ ባወጣቸው ጽሑፎች የፓርቲው ሕዝባዊ ተቀባይነት በአሥር በመቶ እንዲቀንስ ያደረገው ዋነኛው ችግር ሙስና መሆኑን በራሱ ጥናት ማረጋገጡን ጽፏል፡፡
ይህን ማንሳት የተፈለገው እንዲሁ አይደለም፡፡ የአገራችን የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር በመንግሥትና በሕዝብ ትግል ብቻ እንደማይፈታ ለማመላከት ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችን ጨምሮ በጥናትና በምርመራ ላይ የተመሠረተ ዘገባ (Investigative Report) እንዲሠሩ ማበረታታትና መደገፍ አለበት፡፡ ራሳቸው የሚዲያ ተቋማቱም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ባልፀዳ መንገድ ‹‹ወዲያ ወዲህ›› ከማለት ወጥተው፣ ሕዝብና አገርን ሊጠቅም የሚችል የጥናትና ምርምር ብሎም የምርመራ ዘገባ መልመድ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን፣ የመረጃና ነፃነት አዋጅ 590/2000 የሚያግዝ ይሆናል፡፡ በምንቸገረኝ ካልተተወ በስተቀር፡፡
ዕውቁ የ‹‹ዘ ሰን›› ጸሐፊ ዴቪድ ኢድስ (አሁን የቢቢሲ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢ ነው) በምርመራ ዘገባ ላይ እንደጻፈው፣ ‹‹ሙስና በመንግሥታት ትግል ብቻ በምንም ተዓምር ሊቀር አይችልም፡፡ ቢያንስ በጠንካራ ሚዲያዎችና ገለልተኛ አካላት ጥናት፣ ምርመራና በሕዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ መታጀብ አለበት፤›› ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር የፀረ ሙስና ኮሚሽን ብዙ ማሰብ ያስፈልገዋል፡፡
አንዳንድ የሚዲያ አካላት ኮሚሽኑ ለጋዜጠኞች የሚሰጣቸው አጫጭር ሥልጠናዎች ቢኖሩም፣ አደፋፍረው ወደ ምርመራ ጋዜጠኝነት የሚያስገቡ አይደሉም ይላሉ፡፡ በዘጋቢዎች ጥበቃ (Protection) ረገድም ምንም የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ሥርዓትም ቢሆን የሚጠብቀው ‹‹ራሱ ትግሉ›› ነው ማለቱ ለምርመራ ጋዜጠኝነት በቂ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የግል ባንኮች፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና መሬት ጉዳይ ላይ ተጀምረው የተቋረጡ ዘገባዎችንም በመጥቀስ የሚያስረዱ አሉ፡፡
የሕዝቡ የፀረ ሙስና ትግል በቂ አይደለም
እዚህም ላይ አንድ የውጭ ምሳሌ ቀድሞ መጥቀስ ነገሩን ይበልጥ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ለህንድ አሥራ ሁለት የመከላከያ ሔሊኮፕተሮችን የሸጠ የፊንሜካኒካ ኩባንያ የተባለ ድርጅት ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረዋል፡፡ ህንድም ከስድስት ወር በፊት ግዥው ሙስና ተፈጽሞበታል በሚል ጥርጣሬ 720 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የሔሊኮፕተር ግዥ ለመሰረዝ መዘጋጀቷን ወዲያውኑ ነበር ያስታወቀችው፡፡
በዚህ የሙስና ወንጀል ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ እንዴት ተንፀባረቀ የሚለውን ለማየት ከግዥ ኮሚቴው ያፈተለከውን መረጃ ያገኘችው አንዲት ወጣት እንስት ነበረች፡፡ በፆታዊ ግንኙነት ቁንጅናዋን ተጠቅሞ የተጠጋትን የሙስናው ተባባሪ ግለሰብ መረጃ በመቀበል ‹‹አገር ለማዳን›› ተጠቅማበታለች፡፡ በእኛ አገርስ በዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኙ ዜጎች አንስቶ፣ ደላሎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ መላው ሕዝብና በራሱ የመንግሥት ኃላፊዎችና ፈጻሚዎች የሚታዩ የሙስና ድርጊቶችንና ዝንባሌዎችን ያውቃሉ? ያያሉ? ምን ያህሉን ያጋልጧቸዋል? የሚለው መታየት አለበት፡፡ በእርግጥ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕዝቡ ተሳትፎ ጨምሯል ለዚህ ማሳያው በየጊዜው የሚመጣው ጥቆማና አስተያየት ብቻ ሳይሆን፣ ጉቦ ለመክፈል በሚል እጅ ከፍንጅ የሚያስይዘውን ዜና ይጠቅሳል፡፡ ይኼ በበጎ ጎኑ ሊወሰድ ቢችልም በሌሎች አገሮች ሙስና ከፍ በሚባልባቸው መሥሪያ ቤቶች ላይ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ፣ አንዳንድ ኃላፊዎች በመረጃ ላይ በተመሠረተ ጥቆማ ከሥልጣን እንዲወርዱ የመሳሰለውን ዓይነት ገጽታ የለውም፡፡
በተለይ ማኅበረሰቡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለውን ሰንካላ ተረት በመተው፣ ሙስናን በማጋለጥ ይበልጥ መነቃቃት እንዳለበት ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚናገሩት፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን ብቻ ‹‹የሚቀበላቸው›› ጥናቶች ጉዳይና አሳሳቢው እውነታ
ኮሚሽኑ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2003 ዓ.ም. የተጠና የተፅዕኖ ትንተና፣ በኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል በ2004 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ሁለተኛው አገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናትና በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በ2005 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ግሎባል ባሮ ሜትር ጥናት ውጤቶችን ይጠቅሳል፡፡
እንደ መረጃው ጥናቶቹ በሙስና ዙሪያ በአስተሳሰብና በእውነታው ደረጃ ሰፊ ክፍተት እንዳለ በግልጽ ቢያመለክቱም፣ ሙስና በአገሪቱ ላይ የሚያስከትለውን ዘርፍ ብዙ አደጋ ሳያሰምሩበት አላለፉም፡፡ ከወራት በፊት የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሙስናን ሁኔታ ለመረዳት ‹‹Diagnosing Corruption in Ethiopia›› በሚል ያሳተመውን መጽሐፍ ኮሚሽኑ ደጋግሞ ያነሳል፡፡ ነገር ግን የዓለም ባንክ ትኩረት በአንድ በኩል በአገሪቱ የልማት አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርጉባቸው (በትምህርት፣ ጤና፣ የመጠጥ ውኃ) ላይ የወፍ በረር ጥናት ማድረጉ፣ በሌላ በኩል የአገሪቱ መንግሥታዊ ሥርዓት ከሌሎች ደሃ አገሮች በተሻለ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የማልማት አቅም እንዳለው በማረጋገጡ የቀረበ ሪፖርት መሆኑን ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እነዚህን ጥናቶችና የዓለም ባንክ መረጃን ይወስድና የሙስናን አስከፊ ጥፋት ይናገራል፡፡ አሁንም ግን ‹‹በአገሪቱ ትልልቅ ሙስና የለም፤ የከፋ ደረጃ ላይ አይደለንም፤›› የሚለው ፖለቲካዊ አገላለጽ እንዳያዘናጋን የሚሰጉ አሉ፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑ ይህን በተናገረ የወራት ዕድሜ የሆነውን ሁሉ ያስታውሳሉ፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አንዳንድ ባለሀብቶችና ደላላዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሚገመት የሕዝብ ሀብት መከሰስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የትራንስፎርመር ሕገወጥ ግዥ ከ430 ሚሊዮን ብር የማያንስ ክስ ምን ሊባሉ ነው? ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደምስ 95 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጥፍጥፍ ባሌስትራ ‹‹ወርቅ›› ሆኖ የተሸጠው፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን የ100 ሚሊዮኖች ብር ሙስና የት አገር የተካሄደ ነበር? የሚሉ ጥያቄዎችን አፍ ሞልቶ መመለስ አይቻልም፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ከ4.5 ቢሊዮን ብር የማያንስ መሬት በሕገወጦች (ባለሥልጣናትና ግብረ አበሮቻቸው) አልተዘረፈምን? በኦሮሚያና በደቡብ ያለው የመሬት ጉዳይ ጉምጉምታ ትንሽ ሙስና ይባል ይሆን? ይልቅ መድኃኒቱ ከመዘናጋት መውጣት ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡
በታዳጊ ክልሎች አካባቢ ያለው አደጋም እንደ ቀላል የሚታይ እንደልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቀድሞውን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች በሚሊዮን የሚገመት ሀብት ዘርፈዋል በሚል ተጠርጥረው በክስ ሒደት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ‹‹በቴሌቪዥን ንግግራቸው ብፅአን›› የነበሩ ሲሆኑ፣ ለሕዝቡ የሚያስቡ መስለው ባልተወለደ ልጃቸው ‹‹ስም›› ጭምር ቦታና ሀብት ሲያከማቹ እንደነበሩ በክሱ ሒደት ተሰምቷል፡፡
ይህን ምርምር ከፌደራሉ ፀረ ሙስና ጋር ሠርቶ ለውጤት ያበቃው የክልሉ ኮሚሽነር ግን እንደ አገር ጠንካራ ታጋይ ተደርገው በኮሚሽኑ ቢሸለሙም ክልሉ አላመሰገናቸውም፡፡ ይልቁንም የአሁኑ ካቢኔ ገምግሞ ከኃላፊነት እንዳነሳቸው ሰምተናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አካሄዱ ሕጉን ያልጠበቀና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ተቀባይነት ያላገኘ በመሆኑ በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ እንግዲህ ትግሉ መከናወን ያለበት ከውስጥም ከውጭም እንደሆነ መረዳት የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በገለልተኛ ጥናት ያልታገዘ የፀረ ሙስና ትግል የትም አይደርስም የሚባለው፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar