tirsdag 18. februar 2014

ኢህአዴግ ራሱ ባወጣው አፋኝ ሕግ ታፈነ

ለተፈጥሮ ሃብት የጠየቀው ዓለምዓቀፋዊ እውቅና ውድቅ ሆነ
eiti
ኢህአዴግ የተፈጥሮ ሃብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለአገራት እውቅና የሚሰጠው The Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) ለተሰኘ ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ማመልከቻ ከተገመገመ በኋላ መመዘኛዎቹን ማሟላት ባለመቻሉ መውደቁ ተሰማ። ኢህአዴግ የእውቅና ማመልከቻ በድጋሚ ማስገባቱን አስቀድሞ ያወቀው ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት (Human Rights Watch) ጉዳዩን ከሚከታተሉ ጋር ባገኘው መረጃ ኢህአዴግ የEITI መስፈርት የማያሟላና በሰብአዊ መብት ጥሰት የተወነጀለ ድርጅት መሆኑንን ማስረጃ አስደግፎ በመጥቀስ መሟገቻ ደብዳቤ ለድርጅቱ አስገብቶ ነበር።
EITI የዛሬ 11ዓመት አካባቢ የተቋቋመ በተፈጥሮ ሃብት ዙሪያ ዕውቅና የሚሰጥ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የተፈጥሮ ሃብት የህዝብ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ማንኛውም የተፈጥሮ ሃብት – ማዕድን፣ ዘይት፣ ብረታብረትና ጋዝ – ከመሬት በሚወጣበት ጊዜ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚኖረውን ያህል ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለባቸው አገራት ድርጊቱ ለሙስና እና ግጭት በር እንደሚከፍት ይናገራል፡፡ በመሆኑንም ድርጅቱ አገራት ለሚያቀርቡት የዕውቅና ጥያቄ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልማትና እድገት በሚል ሰበብ የሕዝብ ሃብት የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት በማውጣት የህዝባቸውን መብት ለሚረግጡ አገራት የሚያቀርቡትን የዕውቅና ማመልከቻ ውድቅ ያደርጋል፡፡
የጎልጉል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ምንጭ እንደጠቆሙት ኢህአዴግ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ውድቅ መደረጉ እውነት ነው። ምንጩ እንዳሉት ኢህአዴግ በውሳኔው በመበሳጨት ይግባኝ ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ ነው። ድርጅቱ (EITI) አንድ አገር ለሚያቀርበው የእውቅና ማመልከቻ በመስፈርቱ መሰረት ግምገማ ካካሄደ በኋላ እውቅና እንዲሰጥ ሲያምን በራሱ ድረገጽ ላይ የዚያን አገር ስም በመመዝገብ ተጠቃሹ አገር ከተፈጥሮ ሃብት ጋር በተያያዙ ኢንቨስትመንቶች የሚገኘው ትርፍ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ያደርጋል የሚል እውቅና በመስጠት ምስክርነቱን ያሰፍራል፡፡
ኢህአዴግ የመጀመሪያው የማመልከቻ ጥያቄ ያቀረበው በአውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ2009 አካባቢ ነበር፡፡ ከEITI አምስት መስፈርቶች መካከል አንዱ፤ ማመልከቻ የሚያቀርቡ አገራት ከመያዶች (መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) ጋር ለመስራት ያላቸው ፍላጎት ተጠቃሽ ነው፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ በመያዶች ላይ አፋኝ ሕግ አውጥቶ የነበረ በመሆኑ እውቅና ሰጪው ድርጅት – EITI – የኢህአዴግን ማመልከቻ ውድቅ አድርጎታል፡፡ የEITI ቦርድ ይህን ዓይነት ውሳኔ ሲያስተላልፍ ያሰፈረው ነገር ኢትዮጵያ በእጩ አባልነት ለመመዝገብ በመጀመሪያ በመያዶች ላይ ያወጣችውን ሕግ ማስወገድ አለባት የሚል እንደነበር የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት በድረገጹ ላይ አስቀምጦታል፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ይህ ብያኔ በEITI እውቅና አሰጣጥ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ እንደሆነ ተጠቁሞም ነበር፡፡
የEITI ዕውቅናን ለማግኘት ቋምጦ የነበረው ኢህአዴግ በድርጅቱ ውሳኔ ባለመደሰት ጥቂት ዓመታትን ቆጥሮ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በአቶ ሃይለማርያም በመመራት በድጋሚ ዕውቅና የማግኘት ዘመቻውን ማጠናከር ጀመረ፤ በይፋም እንቅስቃሴውን ቀጠለ፡፡ የማዕድን ሚ/ር መ/ቤትም ዕውቅና ማግኘቱ በጣም የሚያስፈልግ እንደሆነ በይፋ በመናገር ዘመቻውን አጧጡፎ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ለዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን አሠራር በዓለምአቀፉ ድርጅት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ኢህአዴግ Ethiopia Revenue Transparency Initiative (ERTI) የሚባል “ተለጣፊ” ተቋም በመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለEITI በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጾዋል፡፡
ጉዳዩን በቅርብ ይከታተሉ የነበሩ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ኢህአዴግ በአውሮጳውያኑ አቆጣጠር 2013ዓም በድጋሚ ማመልከቻ የማቅረብ ዓላማ እንዳለው ለዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አሳወቁ፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ ማሻሻያ እያደረጉ ነኝ የሚል ማስመሰያ ለማቅረብ የሞከረ ቢሆንም የመያዶችና የጸረ አሻባሪነት አፋኝ ሕጎቹ በተጨማሪ በቴሌኮሙኒኬሽን በኩል በስልክና ኢንተርኔት የሚያደርውን ህዝብን የመሰለል ተግባር አጠናክሮ የቀጠለበት እንደሆነ በመጥቀስ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ክፍሎች EITI ዕውቅና እንዳይሰጥ መወትወታቸውን ተያያዙ፡፡
እነዚሁ ወገኖች በተደጋጋሚ ያደረጉት “የወረቀትና የፔቲሽን ትግል” እየተባለ የሚቃለለው ትግል ውጤት በማምጣት ኢህአዴግ በደጋሚ ያስገባው የአባልነት ማመልከቻ ሰሞኑን ውድቅ መደረጉ ተሰምቷል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ EITI ማመልከቻ በሚመዝንበት በሁሉም መስፈርቶች ኢህአዴግ ወድቋል፡፡
አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙና ኢህአዴግ “ልማታዊ” የሚላቸው ኢንቨስተሮች ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሚመደብ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ ባለሃብቶች ኢንቨስት የሚያደርጉበትን አገር ለመምረጥ የመጀመሪያው መለያቸው የEITI ድረገጽ የአባል አገራት ዝርዝር እንደሆነ ስለ አሰራሩ የሚያውቁ ይናገራሉ። ኢህአዴግም አስፈላጊውን የምዝገባና የማመልከቻ መስፈርት በማሟላት የተቋሙን እውቅና የጠየቀው በድርጅቱ ድረገጽ ላይ ለመመዝገብ ነበር። የሁለት ጊዜ ሙከራው መክሸፉ ኢህአዴግ ራሱ ባወጣው አፋኝ ህግ መታፈኑ የሚያመላክት እንደሆነ የሚጠቅሱ ክፍሎች፤ ከኢህአዴግ ከፍተኛ ፍላጎት አኳያና ሰሞኑን በተለያየ አቅጣጫ እየተወጠረ ከመምጣቱ አንጻር ሁኔታው አጣዳፊና ፋታ የማይሰጥ በሽታ ምልክት እንደሆነ በምጸት ይናገራሉ፡፡
ስለEITI ውሳኔ ባጭሩ እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው ባለሙያ እንዳሉት “አንድ ዩኒቨርሲቲ ህንጻ በማስገንባቱና አስተማሪዎችን በመቅጠሩ ብቻ ዩኒቨርስቲ ተብሎ ሊጠራ አይችልም። ዩኒቨርስቲው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ተገምግሞ እውቅና የሚሰጠው መስፈርቶቹን በሙሉ አሟልቶ ስለመገኘቱ ምርመራ ተደርጎበት ፈተናውን ሲያልፍ ብቻ ነው። በዚሁ መሰረት አልፎ እውቅና ያላገኘ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ መማር የተሳትፎ ያህል ነው። መስፈርቱን አሟልተው እውቅና ካገኙት ጋር መወዳደር ስለማይችል ተመራጭ አይሆንም። በተመሳሳይ Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) የተባለው ድርጅትም ከየአገራቱ እውቅና እንዲሰጥ የሚቀርብለትን ጥያቄ /ማመልከቻ/ የሚመዝንበት መስፈርቶች አሉት። ኢህአዴግ የተፈተነው በዚሁ አቅልጦና አንጥሮ በሚያወጣው መመዘኛ ነው ብለዋል፡፡”
ስለጉዳዩ የተጠየቀው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ የህዝብ ግንኙነት ግብረ ኃይል ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቀውና ገና ከጅምሩ ሲከታተል የቆየው መሆኑን በመግለጽ በበርካታ ፈርጆች ከሚያካሂደው ትግል አንጻር በዕቅድ ሲያከናውነው የቆየ መሆኑን አመልክቷል። የህዝብ ግንኙነት ክፍሉ ለጎልጉል እንዳለው ከሆነ “የEITI ውሳኔ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ውሳኔው ኢህአዴግ በራሱ ግትረኝነትና እብሪት ያመጣው ጣጣ በመሆኑ የራሱን ተግባር ተከትሎ የተወሰነው ውሳኔ በአገሪቱ ላይ በማንኛውም መልኩ ለሚያደርሰው ኪሳራ ተጠያቂው ኢህአዴግና ህወሃት ናቸው” ብሏል። በማያያዝም የጋራ ንቅናቄው ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ በማውጣት አስፈላጊ ናቸው ለሚላቸው ወገኖች እንደሚበትንና ተቋሙ በውሳኔው እንዲጸና የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ለተሰማሩ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ አመልክቷል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar