torsdag 24. april 2014

የሶማሊያና የአፋር ጎሳዎች ተጋጩ “ፌደራል ፖሊስ ከመጠን በላይ ኃይል ተጠቀመ


የሶማሌ ብሔራዊ ክልልና የአፋር ብሔራዊ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ የሚኖሩ ጎሳዎች መካከል ግጭት ተከሰተ። ግጭቱን ለማረጋጋት ጣልቃ ገብቷል የተባለው የፌደራል ፖሊሲ ለአንዱ ጎሳ በመወገን ከመጠን በላይ የኃይል እርምጃ ወስዷል መባሉን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስተባብሏል።
ባለፈው ቅዳሜ (ሚያዚያ 11 ቀን 2006 ዓ.ም) በተቀሰቀሰው በዚሁ የጎሳ ግጭት የሰው ሕይወትና የንብረት መውደም ማጋጠሙን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ግጭቱ የተቀሰቀሰው በሶማሌ የሐዋያ ጎሳና በአፋር ጎሳዎች መካከል ነው። በግጭቱም በርካታ ንብረት ከመውደሙ ባሻገር ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ከጀቡቲ ወደአዲስ አበባ በሚያቀናው መንገድ የሚጓጓዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችም ለመንቀሳቀስ ተቸግረው እንደነበረም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ ግጭቱን በተመለከተ ተጠይቀው በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተባለው ግጭት መቀስቀሱን አምነው ከሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለማብረድ መሞከራቸውንና በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት የማረጋጋት ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
ከቅዳሜ በኋላ ሁከቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጠቀሱት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ግጭቱን ተከትሎ በርካታ እውነተኛ ያልሆነ መረጃ መናፈሱን፣ በተለይም የፌዴራል ፖሊስ ለአንድ ጐሳ ወግኖ ሌላኛውን አጥቅቷል መባሉ ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቅሰው ፌደራል ፖሊስ ሕዝባዊ ፖሊስ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ከግጭቱ በኋላ የወጡ መረጃዎች ፌዴራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ዘግበዋል። አቶ አበበ ግጭት በሚኖርበት ሰዓት የሰው ህይወትና ንብረት ሊወድም እንደሚችል አስታውሰው ሁለቱ ጎሳዎች መካከል የፀጥታ ኃይሉ እስኪደርስ ድረስ እርስ በርስ በሚፈጠረው ግጭት ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልም ተናግረዋል። መስሪያቤታቸውም በግጭቱ የምን ያህል ሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ምን ያህል ንብረት ወድሟል የሚለውን ለማወቅ ወደ ስፍራው አጣሪ ቡድን መላኩንም አያይዘው ተናግረዋል።
የግጭቱ መንስኤ በአካባቢው የአርብቶ አደሮች አካባቢ እንደመሆኑ መጠን በግጦሽና በውሃ እጥረት ሊቀሰቀስ ቢችልም፤ ሌሎች ከጎሳ ጋር ተያያዥ መቃቃሮች በመኖራቸው ግጭቱ ከግለሰብ ተነስቶ ወደጎሳ መስፋቱን አስረድተዋል። ሁሉም ባይሆንም የአካባቢው ባለስልጣናትም ግጭቱን በማባባስ በኩል ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል።
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የአሁኑ ግጭት በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ የሰው ህይወትና በርካታ ንብረት መውደሙ ይታወሳል።
ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar