tirsdag 5. august 2014

የብሪታንያ መንግስት የኢትዮጵያን ጉዳይ አስፈጻሚ አስጠርቶ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በጽህፈት ቤቱ አነጋገረ።



ሐምሌ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግንቦት7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ከተያዙ በሁዋላ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ያለፉት 44
ቀናትን በደብረዘይት አየር ሃይል እስር ቤት ውስጥ ካሳለፉ በሁዋላ የብሪታንያ መንግስት የኢትዮጵያን ጉዳይ አስፈጻሚ አስጠርቶ በጽህፈት ቤቱ አነጋግሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሲሞንድስ አቶ አንዳርጋቸው የኮንሱላር አገልግሎት በአፋጣኝ እንዳያገኙ መደረጉ እንዳሳሰባቸው ለኢትዮጵያው ዲፕሎማት ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ  መንግስት ከዚህ ቀደም ለአቶ አንዳርጋቸው የኮንሱላር አገልግሎት እንደሚፈቀድ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ የገባውን ቃል አለማክበሩን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጫ ያመለክታል።ሚ/ር ሲሞንድስ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ የኮንሱላር አገልገሎቱን እንደሚፈቅድ እንዲሁም አቶ አንዳርጋቸው በሌለበት የተላለፈው የሞት ፍርድ ተግባራዊ እንደማይሆን ማረጋገጫ እንዲሰጥ የኢትዮጵያው ዲፕሎማት መልእከቱን ለመንግስት እንዲያስተላለፍ አሳስበዋል።የብሪታንያ መንግስት ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት ወ/ሮ የምስራች ሃይለማርያም ፣ ለህዝብ ይፋ የሆነው መግለጫ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ጠንካራ የሚባል መሆኑን ገልጸው፣ የብሪታንያ መንግስት ተጨማሪ ግፊቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።ከዲፕሎማቶች አካባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የእንግሊዝ መንግስት የኢትዮጵያን ዲፕሎማቶች እየጠራ በተደጋጋሚ ያነጋገረ ሲሆን፣ ዲፕሎማቶችም አቶ አንዳርጋቸው የኮንሱላር አገልግሎት በአስቸኳይ እንደሚያገኙ ቃል ገብተው ነበር። ይሁን እንጅ ቃላቸውን ለመጠበቅ ያልቻሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፣ የብሪታንያ ባለስልጣናት ፊት ሲቀርቡ የሚናገሩት እንደሌላቸውና “መልእክት እናስተላልፋለን” የሚል ቃል ብቻ እንደሚናገሩ ለማወቅ ተችሎአል። በሌላ በኩል ግን አቶ አንድርጋቸው የመጎብኘት ፈቃድ እንዲያገኙ ፈቃድ የሚሰጠው አካል ማን እንደሆነ አለመታወቁ ለዲፐሎማቶች ራስ ምታት መሆኑ ታውቋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለን ቀደም ብለው ኢትዮጵያን ለጎበኙነት የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች የገቡትን ቃል ማክበር የተሳናቸው ሲሆን፣ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ዋናው ፈቃጆች ምናልባትም ከጀርባ ያሉ ሌሎች ስውር ባለስልጣናት ሳይሆኑ አይቀሩም። በኢትዮጵያ ውስጥ ስላጣን ላይ ያለውና ውሳኔ የሚሰጠውን ሰው በትክክል ለማወቅ ባለመቻሉ በርካታ ዲፕሎማቶች ግራ እየተጋቡ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar