søndag 17. august 2014

እንደገና ይድረስ ለሠራቱ


“የትግሬ” ነፃ አውጪ ነኝ ብሎ ራሱን የሠየመው የዘረኞችና የዘራፊዎች ቡድን አገሪቷን እያጎሳቆለ ያለው ከሠራዊቱ ጀርባ ተንጠላጥሎ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የዘረኞችና የዘራፊዎች ቡድን የተሸከመውን ሠራዊት ሳይቀር በጉስቁልናና በድንቁርና እንዲኖር ፈርዶበታል። ህወሃት ሠራዊቱ እንዲማር፤ ዘመኑ ከሚፈቅደው የቴክኖሎጂ እውቀት ጋር ራሱን እንዲያዋህድ እና በራሱ የሚተማመን የዘመነ ሠራዊት እንዲሆን ፍላጎት የለውም።አሜሪካን በአገሯ በሚገኙ የጦር ትምህርት ተቋማት ውስጥ ወታዶሮችን ለማሰልጠን ፍላጎት ብታሳይም ሳሞራ የኑስና መለስ ዜናዊ እምቢ ማለታቸውን አብዛኛው የሠራዊቱ አባላት የሰሙት አይመስልም። አሜሪካን በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ 42 ወታደሮችን አገሯ ወስዳ ለማስለጠን በጠየቀች ግዜ ሳሞራ የፈቀደው 13 ወታደሮች ብቻ ሂደው እንዲማሩ ነው። እነዚህም ከህወሃቶች መካከል ፊደል የቆጠሩ ተፈልገው በመገኘታቸው መሆኑም ታውቋል። በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም የትምህርት እድሉን ተከልክለዋል።
ህወሃት ከራሱ ውጪ ያሉት ሌሎች ላይ ምንም ዕምነት እንደሌለው በተለያየ አጋጣሚ ተናግሮታል። የትምህርት ዕድሉን ለምን መጠቀም እንዳልፈለጉ ሲጠየቅ ሳሞራ የኑስ “ሌሎችን አናምናቸውም አሜሪካን ሂደው ይቀራሉ” ብሎ መልስ መስጠቱም ተመዝግቦ ይገኛል። 11ኛ ክፍልን ያልዘለለው የህወሃቱ ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስ ሠራዊቱን ታማኝና የማይታመኑ በሚል ይከፍላቸዋል። የህወሃት አባል የሆነ ወታደር ታማኝ ፤ ሌሎች የሠራዊቱ አባላት የማይታመኑ።
አሁንም የሠራዊቱ አባላት ስሙ !
እናንተ ምንም ያክል ጥሩ ዜጋ ለመሆን ብትጥሩ በህወሃቶች ዘንድ የምትታመኑ አይደላችሁም። ህወሃቶች ከእነርሱ ውጪ ባሉ ሌሎች ላይ ጥርሳቸውን እንደነከሱ እስከ ዛሬ አሉ። በሌሎች ዜጎች ላይ የመዘዙት የበቀል ሰይፍም ወደ ሰገባው የሚመለስ አልሆነም። በሁለት ዓመት ውስጥ 42 ወታደሮችን አሜሪካን ወደ አገሯ ወስዳ ለማስልጠን ብትጠይቅም 13ቱን ብቻ ተቀብለው 29ኙን አንፈልግም ማለታቸው የተመዘዘው የበቀል ሰይፋቸው አንዱ አንጓ መሆኑን የትምህርት ዕድሉን የተነፈገው የሠራዊቱ አባል ልብ ሊለው ይገባል። እነ ሳሞራ የኑስ ከእነርሱ ውጪ ያሉ ሌሎች ዜጎች በድንቁርናና በችጋር እየተሰቃዩ ይኖሩ ዘንድ ፈርደውበታል። በእንዲህ ሁኔታ እንዲኖር የተፈረደበት ሠራዊት፤ ውጪ አገር ሂዶ እንዳይማር የተከለከለ ሠራዊት፤ ዘር ሃረጉ እና ድርጅታዊ ታማኝነቱ እየታየ ለሹመት የሚበቃው የሠራዊት አባል ይህን ውስኔ ለወሰነበት ለመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ከሚያገኛት ከወር ደመወዙ ላይ ቆርጦ እንዲከፍል ይደረጋል። እንዲህ ዓይነት በደል በየትኛውም አገር ታይቶ አይታወቅም።
በችጋር እንድትኖሩ ከምታገኟት ከወር ደመወዝችሁ ላይ ይወሰዳል፤ ተምራችሁ ራሳችሁን እንዳትቀይሩ በነፃ የሚገኘውን የትምህርት ዕድል እንኳ እንዳትጠቀሙ ተከልክላችኋል። በዚህ ሁኔታ እንድትኖሩ ከተፈረደባችሁ በኋላ የገዛ ወገኖቻችሁን ደም በከንቱ እንድታፈሱ ትደረጋላችሁ። የቀደመው ትውልድ በደሙ ያቆመው ድንበር ፈርሶ እና ዜጎች ተፈናቅለው መሬቱ ለባዕድ ሲሰጥ አናንተ ቁማችሁ ትመለከታላችሁ። ያ የሚፈሰው ደም የራሳችሁ ደም፤ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ የሚወድቀው የገዛ ወገናችሁ መሆኑን ለማሰብ እንኳ ነፃነት ያጣችሁ ትመስላላችሁ። የህፃን ደም በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ሲፈስ ለምን ስትሉ አልተሰማም፤ ጋምቤላዎች ለዘለዓለም ከኖሩበት መሬት ተፈናቅለው መሬታቸውን ሌሎች ሲቀራመቱት ይሄ አይሆንም ለማለት የያዛችሁት ነፍጥ የሸንበቆ ምርኩዝ ሁኖባችኋል። በኦጋዴን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀም ተባባሪ ትሆናላችሁ። ህወሃቶች በዚያች አገር ለሚፈፅሙት ማንኛውም ወንጀል እናንተ የእነርሱ በትር ሁናችሁ ታገለግላላችሁ። ከዚያች አገር ከሚገኘው ሃብት ግን ተካፋይ አትሆኑም። እነርሱ ሚሊየነር ሁነው የሚያደርጉትን ሲያጡ፤ አናንተ የሠራዊቱ አባላት ግን በችጋር ከነ-ቤተሰቦቻችሁ ትሰቃያላችሁ። ይሄ ሁኔታ ማብቃት የኖርበታል።
የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ራዕይ ተብሎ የተነገረህ እንዲህ ይላል “. . . ለህገ-መንግስቱ እና ለህዝቡ ፍፁም ታማኝ የሆነ . . . የሃገራችን ህዝቦች ተምሳሊት የሆነ . . . የእውቀት መፍለቂያ የሆነ ሠራዊት መገንባት “
ምንም እንኳ ጥሩ ራዕይ ተቀርፆ የተቀመጠ ቢሆንም አንተ የሠራዊቱ አባል ግን የዚህ ራዕይ ተካፋይ አይደለህም።አንተ የምትካፈልው መከራውን እንጂ መልካሙን ራዕይ አይደለም። ለህገ-መንግስቱ እና ለህዝቡ ፍፁም ታማኝ የሆነ ሠራዊት መገንባት የሚለውን ራዕይ መልሰህ መልሰህ እንድታስብ እንመክርሃለን። በእኛ በኩል ግን ህወሃት በአገሪቷ ጫንቃ ላይ ከተቆናጠጠ ዘመን ጀምሮ ህዝቡን ሲያዋርድ ኖረ እንጂ ለህዝብ ታማኝ ሲሆን አልታየም። ህገ-መንግስት ብሎ ራሱ እዚያ ጫካ ሁኖ የፃፈውን ራሱ ሲያፈርሰው ኖረ እንጂ ሲያከብረው አላየንም። ህወሃት ለህገ-ማንግስቱ እና ለህዝቡ ታማኝ ሁኖም አያውቅም። ወደ ፊትም ራሱን ከህዝብ እና ከህግ-በታች አድርጎ እንዳይኖር እሰከ ዛሬ ሲፈፅመው የኖረው ወንጀል የሚያስችለው አይሆንም። ህወሃቶች ከነ እድፋቸው ወደ ማይቀረው መቃብራቸው መሄድን የመረጡ ስለሆነ ሠራዊቱ ራሱን ከእነዚህ ነውረኞች ለይቶ ለህገ-መንግስቱና ለህዝቡ ፍፁም ታማኝ መሆኑን ማስመስከር ይጠበቅበታል።
ሌላው ከህወሃት ውጪ ያላችሁ የሠራዊቱ አባላት ልታስቡበት የሚገባው ዓቢይ ነገር ደግሞ ‘የሃገራችን ህዝቦች ተምሳሊት የሆነ ሠራዊት መገንባት ‘ የሚለውን ራዕይ ነው። ሃገራችን ከ80 በላይ ብሄሮች የሚኖሩባት መሆኑ ይታወቃል።ለዚህች አገር ምሳሌ ሊሆን የሚችል መከላከያ ኃይል መገንባት እንደ ራዕይ የተቀመጠ ቢሆንም በተግባር የሆነው ግን ሌላ ነው። አሁን ባለው የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ውስጥ ያሉ የጦር አዛዦችን ቀና ብለህ አይተህ እውነት መከላከያ ሃይሉ የህዝቦቿ ተምሳሊት የሆነ ሠራዊት መሆኑን ራስህ እንድትመልስ እንጠይቅሃለን። በአገሪቷ የተሾሙ ጄኔራሎች ከአንድ ጎጥ እና መንደር የተሰባሰቡ መሆናቸው በምን መልኩ የሃገራችን ህዝቦች ተምሳሊት የሆነ ሠራዊት ሊሆን እንደሚችል ህወሃቶችን ደግሞ ደጋግሞ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል።
በመጨረሻም ‘የዕውቀት ምንጭ የሆነ ሠራዊት መገንባት’ የሚል ራዕይም በጉልህ ተፅፎ ተቀምጧል። የህወሃት የጦር አበጋዞች ከ7ኛ ክፍል ያልዘለሉ፤ካርታ ይዘው የቆሙበትን ሥፍራ እንኳ ለማሳየት የሚደናበሩ መሆናቸው የታወቀ ነው። እነዚህ ፊደል ቆጥረው ያልዘለቁ ቡድኖች የሚመሩት ተቋም እንደምን ሁኖ የዕውቀት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል የሚያውቅ የለም። የህወሃቶች እውቀት የንፁሃን ደም ማፍሰስ፤ የድሃ ሃብት መዝረፍ፤ እኔ ብቻ ባይነት እንጂ ከዝህ የዘለለ ሌላ እውቀት ያላቸው አይደሉም። እነርሱ ባለመማራቸው የጎደለባቸው ነገር አለመኖሩን እያዩት ለትምህርትና ለተለየ ዕውቀት ዋጋ ይሰጣሉ ማለት አይቻልም። ሌሎቹም ተምረው እውቀት እንዲገበዩ ለማድረግ ስብዕናቸው አይፈቅድላቸውም። በዚህም ምክንያት ከውጭ አገራት በነፃ የሚገኘውን የትምህርት ዕድል እንኳ ወታደሩ ተጠቅሞ ራሱን በእውቀት እንዳያዳብር ይከለክላሉ። እንዳይማር የተከለከል የሠራዊት አባል እንደምን ሁኖ የዕውቀት መፍለቂያ ሊሆን እንደሚችል የሠራዊቱ አባላት የሽፍቶቹን ቡድኖች መጠየቅ ይኖርባችኋል።
የሠራዊቱ አባል የህዝብ አካል መሆንህን አትርሳው። ነገ ዞረህ የምትገባውም እዚያው ከወጣህበት ህዝብ መሆኑን እኛ ልናስታውስህ እንወዳለን። አሁን ባለው አካሄድህ የወጣህበትህን ድንኳን፤ በዚያች ድንኳን ውስጥ ሁነህ ያሳደጉህ ወገኖችህን እያሳደድክ መሆንህን አስታውስ። የወጣህበትንም ድንኳን እያፈረስክ ነው። ድንኳንህንም አፍርሰህ ከጨረስከው ነገ ዞሮ ማረፊያ እንደማይኖርህ ደግሞ እኛ ልናስታውሰህ እንፈልጋለን። ጥሪያችንን መስማት ከማንም በላይ ለራስህ ይበጅሃል። የወገኖችህን ጥሪ ሰምተህ በወገኖችህ ላይ የተመዘዘውን የበቀል ሰይፍ ለማቆም ከህዝብ ጎን መሆንን አልመርጥ ካልክ መጨረሻህ አያምርም። እነ ሳሞራ የኑስ ጠላቶችህ እንጂ ወገኖችህ አይደሉም። እነ ሳሞራ የኑስ አንተንና ልጅ ልጆችህን ጭምር በድንቁርና አዘቅት ውስጥ አኑረው ቀጥቅጠው ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት ወሰን እንደሌለው ማወቅ ይኖርብሃል። የተሸከምከው መሣሪያ ለፍትህ ለእኩልነት፤ ለነፃነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሚሆኑትን የሚፋለም ሊሆን ይገባዋል እንጂ እነዚህን ጥያቄዎች ባነሱ ወገኖች ላይ የሚያነጣጥር መሆን አይኖርበትም።
እንግዲህ ምን እናድርግ እያላችሁ የምትጠይቁን አላችሁ። ለዚህ ጥያቄ መልሱ ያለው ከእናተው ደጅ ነው። እኛ ያነሳነውን ጥያቄ ባላችሁበት ሁናችሁ ማንሳት ትችላላችሁ። አብዛኛው ሠራዊት ጥቂት ዘረኞችንና ዘራፊዎችን ተሸክሞ የሚኖሩበት ሁኔታ ለመቀየር ሦስትም አራትም እየሆናችሁ እምቢ ማለት መጀመር አለባችሁ። ህወሃቶችን ተሸክማችሁ፤ የህዝባችሁ ጠላቶች ሁናችሁ፤ አገራችሁንና ህዝባችሁን አዋርዳችሁ የምትኖሩት ኑሮ ኑሮ አይደለምና እምቢ አይሆንም ማለት ጀምሩ። ለዘረኞቹና ለዘራፊዎቹ ህወሃቶች ከመሞት ይልቅ ለፍትህ፤ ለእኩልነት እና ለነፃነት ብላችሁ ብትሠው መሥዋእትነታችሁ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል፤ ስማችሁም ከመቃብር በላይ ይሆናል።ፍፃሜያችሁም የጀግና ፍፃሜ ይሆናል።
ፍፃሜያችሁ የጀግና ፍፃሜ እንዲሆን ለፍትህ፤ ለነፃነት እና ለእኩልነት ዘብ የምትቆሙ ሁኑ እንጂ የአንድን ዘረኛና ዘራፊ ቡድን እድሜ ለማራዘም የምትቆሙ አትሁኑ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar