ዲቦራ ለማ/ ከኖርዌይ
ኦገስት 31, 2014
ኦገስት 31, 2014 በኖርዌ ዋና ከተማ ኦስሎ የግንቦት 7 ለፍትህ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱን በተሳካ ሁኔታ አደረገ። የግንቦት 7 ለፍትህ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በተለያዩ ከተሞች እያደረጋቸው ካሉት ህዝባዊ ስብሰባዎች አንዱ የሆነውና በኦስሎ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ በተጋባዥ እንግድነት በስፍራው የተገኙ ሲሆን ይህንን ስብሰባ ያዘጋጀው የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ነው።
ዝግጅቱ በኖርዌጂያን የሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 1500 ላይ የተጀመረ ሲሆን የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የመክፈቻ ንግግ አድርገው ባለፉት 23 አመታት በወያኔ የግፍ አገዛዝ ህይወታቸው ላጡ ንፁሀን ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማስደረግ ዝግጅቱን በይፋ አስጀምረዋል። በመቀጠል የግብረኃይሉ ዋና አስተባባሪ የሆኑት ጠንካራ ሶስት መልክቶችን አስተላልፈው የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እራእይና አላማን እንዲሁም የትግሉን ደረጃ በቪዲዮ የተደገፈ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከዚህ በመቀጠል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ ዋና ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዮሐንስ አለሙ ይህን ዝግጅት ድርጅታቸው በማዘጋጀቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው እስከዛሬ ከሄድንባቸው የትግል ስልቶች ትግሉን አንድ ደረጃ በማሳደግ የተግባር ስራ መስራት እንደሚገባና ወያኔን ከስልጣን ለማውረድ ሁለገብ ትግላችንን ያለማቋረጥ በተከታታይ ማድረግ እንዳለብን እንዲሁም ያለንበት ሰአት የተግባር ስራን የሚጠይቅ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የሁላችንንም ቆራጥነት የሚጠይቅ መሆኑን በማሳሰብ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበሩም በተያዘላቸው ሰአት የትግሉን ደረጃና የግንቦት 7ትን ራእይና አላማ ለህዝቡ በዝርዝር በማስተላለፍ በተለይ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ወደ ትግሉ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል። በቀረበው ጥሪ መሰረት በርካታ ሰዎች የድርጅቱን ፎርም በመሙላት ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ግንቦት 7 ትን ተቀላቅለዋል። በስብሰባው መሃልም የአርበኞች ግንባር፣ የትግራይ ህዝብ ንቅናቄ እንዲሁም የግንቦት 7 ህዝባዊ ኃይል ኃላፊዎች በስልክ ለታዳሚው መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በቀጣይ አንዳርጋቸው ፅጌ ማን ነው የሚል የአንዳርጋቸውን ስራዎችና የህይወት ታሪኩን የሚዘክር ቪዲዮም ቀርቧል።
በመጨረሻም የአንዳርጋቸውን ፅጌን ምስል የያዘ ፎቶ ግራፍ ለጨረታ ቀርቦ ህዝቡ በከፍተኛ የገንዘብ መጠን ፉክክሩል አሳይቷል። ከፍተኛውን ገንዘብ በመክፈል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ጨረታውን በማሸነፉ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ምስል ከአቶ አበበ ቦጋለ እጅ ተረክብዋል። ለዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ሎተሪዎች፣ መፅሀፎት፣ ትኬቶች ምግብና መጠጥ እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ከሽያጩም ከፍተኛ ገቢ ተገኝትዋል። በመቀጠል የግንቦት 7 ምክትል ሊቀመንበሩ ከተሰብሳቢው ጋር የጥያቄና መልስ ውይይት አድርገዋል። በማጠቃለያም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ም/ሊቀመንበር የመዝጊያ ንግግር አድርገው በህዝባዊ ኃይሉ መዝሙር ስብሰባው በተያዘለት ሰአት በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar