tirsdag 23. september 2014

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤክስፐርቶች ኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ትጠቀማለች ሲሉ ከሰሱ

-ተቃዋሚዎች ተገቢ ሪፖርት ብለውታል
United-Nations-01-300x220የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ሁሉን አቀፍ የአቻ ለአቻ ግምገማ የውሳኔ ሐሳቦችን ለመገምገም የተሰበሰበው የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ቡድን መስከረም 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በጀኔቭ ስዊዘርላንድ ባደረገው ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብረተኝነት አዋጁን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብትን ለመጣስ መጠቀሙን እንዲያቆም አሳሰበ፡፡
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ሪፖርትና የሰብዓዊ መብት ይዞታን በአገሪቱ ለማሻሻል የተወሰዱትን ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ተከትሎ፣ አባል አገሮች የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ያደጉ አገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲሻሻል ወይም እንዲሰረዝ የጠየቁት ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ነው፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ሕግና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የመደራጀትና የሰላማዊ ስብሰባ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የዳኞችና የጠበቆች ነፃነትና የኢሰብዓዊ አያያዝና ክብርን የሚያዋርድ ቅጣት መብቶች ልዩ ራፖርተሮች የሆኑት ቤን ኤመርሰን፣ ማይና ካያ፣ ዴቪድ ካዬ፣ ሚቸል ፎርስት፣ ጋብሪኤላ ክናውልና ጁአን ሜንዴዝ በጋራ ያወጡት ሪፖርት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያ የወጡ ሪፖርቶች ማመላከታቸውን ይገልጻል፡፡ ‹‹ግርፋትና ኢሰብዓዊ አያያዝ በኢትዮጵያ ማቆያዎች ውስጥ መስተዋሉ ከፍተኛ የመሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤›› ሲልም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
የኤክስፐርቶች ቡድኑ ሽብርተኝነትን መዋጋት አስፈላጊ ድርጊት ቢሆንም፣ ትግሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶችን ሳይጣረስ መከናወን እንዳለበት ግን አስምሮበታል፡፡ ‹‹ፀረ ሽብርተኝነትን የሚደነግጉ አንቀጾች በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግጋት ውስጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መተርጎም አለባቸው፡፡ ሕጎቹም ላልተገባ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውሉ አይገባም፤›› ሲልም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
ሪፖርቱ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የተከሰሱ ግለሰቦች ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሒደት እያገኙ እንዳልሆነም ይወቅሳል፡፡ በተለይም ከሕግ አማካሪዎችና ከጠበቆች ጋር የመገናኘት መብት እንደማይተገበርም ያስረዳል፡፡ ‹‹ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሒደት የማግኘት መብት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የመደራጀት መብት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አፈጻጸም መጣሳቸው ቀጥሏል፤›› ሲሉም ኤክስፐርቶቹ ያሳስባሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም በዘፈቀደ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ሁሉንም ሰዎች እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት መሪዎች መደበኛና ሕጋዊ ሥራቸውን ያለ ዛቻና እስር ሳይፈሩ እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል፤›› ሲሉም የተመድ ኤክስፐርቶች ጠይቀዋል፡፡ ኤክስፐርቶቹ ኢትዮጵያ የአዋጁን አፈጻጸም ከገባቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ጋር እያገናዘበች እንድታስኬድም ጥሪ አድርገዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመቃወም የሕዝብ ፊርማ እስከማሰባሰብ የደረሰው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር) ሪፖርቱን አስመልከቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ፓርቲያችን አንድነት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የሕግ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድ ነው ያለው ከየትኛውም ፓርቲ ቀድሞ ነው፡፡ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ከኢሕአዴግ የተለየ አቋም የሚያንፀባርቁ ግለሰቦችና ጋዜጠኞችን ለማፈን ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ግዛቸው የሕጉን ተፅዕኖ በማየት ፓርቲያቸው በ2005 እና በ2006 ዓ.ም. ሕጉን ለማሰረዝ ፊርማ የማሰባሰብ ሥራ መሥራቱንም አስታውሰዋል፡፡
የተመድ ኤክስፐርቶች ሪፖርት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ምን ያህል ጠቃሚ ነው በሚል የተጠየቁት አቶ ግዛቸው፣ ተመድ ሕጉ ጉድለት አለበት ስላለ ሳይሆን አዋጁ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ፓርቲያቸው ተቃውሞውን እንደጀመረ ገልጸዋል፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብታቸው በሕገ መንግሥቱ ቢከበርም እነዚህን መብቶች በመጣስ በሕጉ አማካይነት በርካታ የህሊና እስረኞችን ኢትዮጵያ እንዳፈራችም አመልክተዋል፡፡ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል የሚሉ ከሆነ ለምን ጥያቄአቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ለሕገ መንግሥታዊ አጣሪ ጉባዔ እንዳላቀረቡ የተጠየቁት አቶ ግዛቸው፣ ከሕግ ክፍላቸው ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነና በቅርቡ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አንድነት ፓርቲ ሁሉ በአዋጁ ላይ የሰላ ተቃውሞ በማቅረብ የሚታወቀው የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የኤክስፐርቶቹ ሪፖርት የፓርቲያቸውን አቋም እንደሚያንፀባርቅ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም በሪፖርቱ በጣም ደስተኛ ነን፡፡ ኤክስፐርቶቹ ገለልተኛና በጉዳዮቹ ላይ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ ተዓማኒነት ያለው ሪፖርትም በማውጣት ይታወቃሉ፡፡ ይኼ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ከመፍጠር አልፎ ተግባራዊ ዕርምጃ ለመውሰድም የሚያስችል ተፅዕኖ ይፈጥራል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ተጠቅሶ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተከሰው ፍርድ ያገኙ ሲሆን፣ በቅርቡም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በዚሁ አዋጅ ተከሰው ጉዳያቸው በመታየት ላይ ነው፡፡ መንግሥት ግን ይሠሩት ከነበረው ሙያዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በሽብር ተግባር ሲሳተፉ እንደያዛቸው በመግለጽ ራሱን ይከላከላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የህሊና እስረኛ እንደሌለ መግለጻቸውን ባለፈው ረቡዕ ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአሁኑ የተመድ ኤክስፐርቶች ሪፖርት ላይ የመንግሥትን ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar