የትህዴን ርዕሠ አንቀጽ
በአሁኑ ግዜ በአገራችን ህዝብን የሚወክልና በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሳይኖረን ይህንን እድል ለመፍጠር አጋጣሚውን ያገኙ ቡድኖች ሆኑ ግለሰቦች ከህዝብ ፍላጎት እና ከሃገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን‘ና የባእዳኖችን ፍላጎት በማስቀደም ያገኙትን የተለያዩ አጋጣሚዎች በመጠቀም የህዝብን ስልጣን እየነጠቁ ለህዝብ እና ለሃገር የቆሙትን እየገፉ እና እየገደሉ በጉልበት መንግስት ነን በማለት እስካሁን ስልጣን ላይ ይገኛሉ።
የኢህአዴግ አመራሮች ህዝብን የማገልገል ስራ ሳይሆን የየራሳቸውን ጥቅም በማስጠበቅ እና ስልጣን ላይ ወጥተው የህዝብን ሃብት ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ፤ ህዝብን እንዳሻቸው እየጨቆኑ፤ እያንገላቱና እየጨፈጨፉ ባጠቃላይ ለትውልድ የሚተርፍ መጥፎ ታሪክና የማይረሳ የጥፋት አሻራ ጥለው እያለፉ መሆናቸው ግልፅ ነው።
የደርግ ስርዓት በህዝብ ልጆች መስዋእትነትና የአካል-መጉደል ከተደመሰሰ በኃላ ስልጣን የሙጥኝ ያለው ፀረ ህዝብ የኢህአዴግ ስርዓት ፋሺስታዊው የደርግ ስርዓት ለሃገር እና ለህዝብ የቆሙትን ንፁኃን ዜጎች በመጨፍጨፍ እንደሚታወቀው ሁሉ አሁን በአገዛዝ ላይ ያለው የኢህአዴግ ስርዓትም በፖለቲካ አመለካከታቸውና ደስ አላሰኙኝም በሚል ንጽሁሃን ዜጎች በድብቅና በግልፅ ብመጥፋት የራሱ የሆነ ጸረ ህዝብ እና ጸረ ሃገር የሆኑ መለያዎች አሉት።
የኢህአዴግ ስርዓት ካለፉት ጨቋኝ ስርዓቶች ለየት የሚያደርጉት በርካታ እኩይ ባህሪያቶች እዳሉት ግልጽ ነው። ስርአቱ የሚታወቅበት መቼም ሊለወጥ እና ሊሻሻል የማይችል አያሌ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ህዝብ አጀንዳዎች እንዳሉ ሆነው በተጨማሪም አለቆቹ በባእዳን የተነገረውን ትእዛዝ ለማስከበር ሲሉ ለባእዳኖች ባለመገዛቱ የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለመበቀል፤ኢትዮጵያን ለመበታተን’ና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተዘጋጀውን የተሳሳተ ታሪክ ይዞ በተለይም ለስርዓቱ አልገዛም ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቂም ይዞ ለመበቀል ከፍተኛ በጀት እና የሰው ሃይል መድቦ ለጥፋት መነሳቱ የስርዓቱ ባህሪ ነው።
እንደሚታወቀው በመሳሪያ ጋጋታ እና በአፋኝ ህግ ብዛት ሃሳቡን እና ተቃውሞውን እንዳይገልጽ የተከለከለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለስርዓቱ ያለውን እምቢተኝነት እና ተቃውሞ ባገኘው አጋጣሚ እየገለጸና ከዛም አልፎ የስርዓቱ አስመሳይ የምርጫ ሂደት ላይ ባለመሳተፍና ባለመምረጥ በስርዓቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጿል። በመሆኑም የኢህአዴ ስርዓት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በስልጣን መቆየቱ የቂሙን ደረጃ የት ያደርሰዋል? ስልጣኑንስ የሚጠቀመው እውነት ሃገር እና ህዝብን ለመጥቀም ነው? ወይስ የተነሳለትን ኢትዮጵያን ህዝቧን የመበታተን ዘመቻውን አጠናክሮ ለማስቀጠል?
ለማኛውም! አጥፊ እና ጠፊ አብረው መኖር እንደማይችሉ ሁሉ መቼም ቢሆን ህዝብ ከኢህአዴግ ስርዓት ጎን ሊቆም አይችልምና ህዝቡ ለኢህአዴግ ባለመምረጡና ከህወሓት-ኢህአዴግ ጎን ባለመቆሙ ምክንያት የተለመደ የኢህአዴግ ቂም በቀል እርምጃ በእጥፍ መቀበሉ አይቀሬ ነው፤ ወያኔ በስልጣን እስካለ ድረስ በህዝቡ ላይ የሚደርሰው የጥፋት ዘመቻ፤ እስራት፤ ድብደባ፤ አፈና፤ በኑሮ ውድነት መሰቃየት፤ ከኖረበት መፈናቀሉ ሌላም ሌላም በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል።
በኢህአዴግ ስር ሁኖ እየተሰቃየ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደደም ጠላም ይህ ስርዓት እስከቀጠለ ድረስ መስዋእትነት መክፈሉ አይቀርም ምክንያቱ የእኛ ከኢትዮጵያውያን ታሪክ አንጻር ሲታይ ለውጭ ወራሪውችም ሆነ ለውጥ ጸረ ህዝብ ስርአተወች አሜን ብሎ ተገዝቶ ኣይውቅም ስለዚህ መቼም ቢሆን አይቶ እንዳላየ መሞትን ይመርጣል ተብሎ አይገመትም።
ስለሆነም ማንኛው ኢትዮጵያዊ በሚከተለው ዓላማና በፖለቲካ አስተሳሰቡ ህይወት መክፈሉ ላይቀር እራሱን መስዋእት አድርጎ ብሄራዊ ክብሩን ለማስመለስና በሃገራችን ውስጥ እውነተኛና ያልተገደበ ዴሞክራሲ ለመገንባት፤ ለህዝብና ለሃገር ተቆርቋሪ የሆነ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለመመስረት በሚደረገው ትግል ላይ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል፣ ምክንያቱም ለማይቀረው መስዋእትነት ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ክብርን ያጎናፅፋልና።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45748#sthash.MV5Ni22F.dpuf
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar