fredag 21. august 2015

ወጣቶቹን እየበላ ያለው ስርዓት … (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

ግርማ ሠይፉ ማሩ
  • 116
     
    Share
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በቀጣይ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተመረጡ እና የተለመዱ ፊቶችን ስብስበው ጥያቄ ሲያቀርቡና ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር፡፡ የእኔን ቀልብ የሳበው ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ወጣቶችን እየበላ ያለ ስርዓት ባለቤት እና መሪ መሆናቸውን የገለፁበት አስተያየት ከታዳሚው ሞቅ ባለ በተደጋጋሚ ጭብጨባ መታጀቡ ነው፡፡ ባለፈው የኦባማ ጉብኝት ወቅት ዲሞክራሲ ማላት ምርጫ በስላም ማጠናቃቅ ብቻ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞችን አክቲቪሰቶችን እስር ቤት እያወረዱ አማራጭ ፖለቲካን እየከለከሉ ዲሞክራሲ የተሟላ አይሆኑም ብለው ሲሞልጯቸው በጭብጨባ ያጅቡ ነበር፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ነው የሆነብኝ፡፡
ይህን ፅሁፍ ከመለጠፌ በፊት ግን በእስር ላይ ያሉ ጓዶቻችን ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት መበየኑን ሰምቻለሁ፡፡ ንፁህ ናችሁ ብሎዋቸዋል፡፡ ንፁህ ነበሩ እና አይገርምም፡፡ ይህን ማበረታታት አለብን፡፡ እነ አንዱዓለም፣ ናትናኤል፣ እስክንድር፣ ተመስገን ደሳለኝ ፣ ወዘተ መለቀቅ አለባቸው፡፡ ይህን ጥሩ እርምጃ ኦባማ ተቆጥቷቸው ነው እያሉ ከማንቋሸሽ ይህን እያጣጣምን ተጨማሪ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለማነኛውም ለቤተሰቦች ዕዳ ሆነው የነበሩት ታጋዮች ነፃ ወጥተዋል፡፡ ከቂሊንጦ!!! እንኳን ደስ ያላችሁ ደስ ያለን!!!
ወደ ተነሳሁብ ነጥብ ሰመለስ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጉቦ የሚበላባቸው መስሪያ ቤቶች እንዳሉ ማወቅ ብቻ አይደለም ወጣቶችንም ጉበኛ አድርጎ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስልጥኖ ወደ ተግባር እንደሚያስገባ በግልፅ ነግረውናል፡፡ በተጨማሪ ምንም ዓይነት የተሟላ ማስረጃ ቢኖረን ጉዳያችንን መጨረስ የማንችልባቸው የመንግስት ተቋማት እንዳሉም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጠንቅቀው ያውቃሉ እነዚህም ተቋሞች የሰለጠኑ አዲስ ምሩቃን ወጣቶች ስራ እንዲሰሩ ሲመደቡላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ጉዳይ ማለቅ እንደሌለበት ጠንቅቀው ይማራሉ፡፡ ይህንንም በተግባር ይፈፅሙታል፡፡ እነዚህ መስሪያ ቤቶች የመንግስት አገልግሎት መስጫ ነው፡፡
ባለጉዳይን በአግባቡ እና በስርዓት ያለማስተናገድ በእርሰቸው ቃል አመናጫቂና አንጓጣጭ መስሪያ ቤቶችም እንዲሁ የተመደቡላቸውን ወጣት ምሩቃን በፍጥነት ቀይረው ተገዶ አገልግሎት ፍለጋ የመጣውን ተገልጋይ ያመናጭቃሉ፣ ይሳደባሉ፡፡ ይህን ስስማ የጤና ባለሞያዎቻችን ወላዶችን በምጥ ወቅት ማን አርግዥ አለሽ አትጩሂ ሲሉ ተሰማኝ፡፡ ሌሎች የሚሉትን ፀያፍ ቃል ለዚህ ፅሁፍ ስለማይመጥን ዘልየው ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ገቢ ኦዲተሮች እና ገማቾች በግብር ከፋይ ዜጎች ላይ ያላቸውን “ቬቶ ፓውር” ማወቅ ብቻ አይደለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትረ ተሰፋ የቆረጡበት ሁኔታ ያለ የሚመስል አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ ሂሳብ ሰርታችሁ ካልመጣችሁ እንደፈለጉ ያድርጓችሁ የሚሉን ይመስላል፡፡ ለአፋቸው እንኳን እነዚህን ልክ ማስገባት አለብን የሚል ተሰፋ አልሰጡንም፡፡ እኔ በግሌ የሀገር ውስጥ ኦዲተር ብሆን ስራ አቆም ነበር፡፡ ደግነቱ እግዜር አንድኖኛል፡፡ በእኛ ሀገር መስሪያ ቤቱ ሲሰደብበት ኃላፊነቱን የሚለቅ ባለስልጣን ስለሌለን ነው፡፡ እራሴ እለቅ ነበር ያልኩት፡፡
እነዚህን ሁሉ ወጣቶችን የሚበሉ መስሪያ ቤቶች የሚተዳደሩት በመንግሰት በጀት፣ በምርጫ አሸንፌ ስልጣን ያዝኩ በሚል መንግሰት በሚሾሙ የፖለቲካ ሾመኞች መሆኑን የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ ደግሞ መፍትሄው የታጋይ ዜጋ መኖርና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው በማለት አስቀምጠው፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በተመለከት ጠንካራ ፓርቲና አመራር በመኖሩ ተገባራዊ ማድረግ ይቻላል በሚል አሹፈውብናል፡፡
ይህን ፕሮግራመ የተከታተልን ሰዎች ታጋይ ዜጎችን በእኔ ትርጉም እንቢ ሙሰኝነት ….. ያሉትን፣ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የጮሁትን እና የዘመሩትን፣ መንግሰት ይህን ጉዳይ የማያውቅ ከሆነም እንዲገባው የጦመሩትን፣ የፖለቲካ ሙሰኝነት እንዲቀር እንቅልፉን አጥቶ ጋዜጣና መፅሄት በማዘጋጀት የሚተጉትን ጋዜጠኞችን እስር ቤት እያጎሩ እንዴት ታጋይ ዜጋ እንደሚፈራ አልታይህ አለኝ፡፡
ታጋይ ዜጋ እንዳይፈራ ዜጎችን አንገት እያስደፉ ፖለቲከኞች በሚፈነጩበት ሀገር ኪራይ ስብሳቢነት አንገቱን እንዴት እንደሚደፋ ማወቅ አይቻልም፡፡ ታጋዮችን አንገት አስደፍቶ ሌቦች ፖለቲከኞችን ቁርጠኞች ናቸው ማለት ፌዝ ነው፡፡
ታጋይ ዜጋ እናፍራ – ታጋይ የሆነ ዜጋ ጉቦ አይከፍልም በዚህ ጊዜ ኪራይ ስብሳቢነት ይደፈቃል ነው ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ጉቦ አልሰጥም የሚል ዜጋ ለማፍራት፣ ከፖለቲከና ዱላ የሚጠብቅ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ጋዜጠኛ የግድ ይለናል፡፡ ፍርድ ቤት ያስፈልገናል፡፡ ያስቸገሩንን ወሰደን የምንገትርበት፡፡ የመርጊያ በቃናን ውሳኔ የሚያፀና ፍርድ ቤት አለን ብለን ጉቦ አንከፍልም በሉ ብለን እዝቡን ለጅብ አንሰጥም፡፡ መልዕክቴ ስርዓቱ ከፖለቲካ ሙሰና ከፀዳ እርገጠኛ ይሁኑ ሌሎች ሙስናዎች ተራ ናቸው፡፡ ለማነኛውም ይህ ወጣቶችን እየበላ ያለው የፖለቲካ ስርዓት ይገራልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!!!!! ዛሬ ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!!!!
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/9727#sthash.PyNQLVuH.dpuf

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar