onsdag 25. desember 2013

ህወሓቶች ጊዜያዊ ‘ዕርቅ’ ፈፀሙ!

Wednesday, December 25, 2013

ህወሓቶች ለሁለት ተከፍሎው የደብረፅዮን (የአዲስ አበባ) ና የአባይ ወልዱ (የትግራይ) ቡድን ተሰይመው ሲነታረኩ መቆየታቸው ይታወቃል። ከወራት በፊት ጀምሮ ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ‘ለማስታረቅ’ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰን ነበር።
አሁን አቶ ስብሃት ነጋ (ከቢተው በላይ ጋር በመሆን) ሁለቱም ባላንጣ ቡድኖች ‘ማስታረቅ’ ችለዋል። ዕርቁ የተፈፀመው በነ ደብረፅዮን ቡድን አሸናፊነት ነው። የነ አባይ ወልዱ ቡድን በመሸነፉ ምክንያት አቶ አባይ ወልዱ ከነ ስብሃት ነጋ ጋር እንዲስማማ ምክንያት ሁነዋል። የነ አባይ ቡድን የተዳከመበት ምክንያት ለሁለት በመከፈሉ ነው። አቶ አባይ ወልዱ ከአቶ ቴድሮስ ሐጎስ፣ ኢያሱ ተስፋይ፣ ተክለወይኒ አሰፋ፣ ኪሮስ ቢተው፣ በየነ መክሩ ወዘተ መግባባት ባለመቻሉ ከአዲስ አበባዎቹ ጋር ለመስማማት ተገደዋል።

በስምምነቱ መሰረት ህወሓት በአዲስ አበባዎቹ ፕላን ይጓዛል። በ’መለስ ራእይ’ ስም ህዝብ መጀንጀን ይቀራል። በሙስና ሰበብ ባለስልጣናት ማሳሰርም ይቀራል። ከአሁኑ በኋል ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት በሙስና ሰበብ አይታሰሩም። በቀጣዩ የኢህአዴግ ጉባኤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ከህወሓት እንዲሆን ጥረት ይደረጋል (ዶር ቴድሮስ አድሐኖም)።
ይህ የህወሓቶች የ’ዕርቅ ሂደት’ ባብዛኛው የብአዴን አመራር አባላትና በተወሰኑ የኦህዴድ መሪዎች ቅሬታ አስነስተዋል። ህወሓቶች ለመታረቅ የተገደዱበት ምክንያት በተቃዋሚዎች ስልጣን እንዳይነጠቁ በመስጋት ነው። ዓረና ፓርቲ ለህወሓቶች ትልቅ ስጋት በመፍጠሩ ነው። የፀጥታ ሃይሉ መፈራረስም ሌላ ህወሓቶች ያስደነገጠ ጉዳይ ነው። በዕርቁ ሂደት ከፍተኛ ሚና የተጫወተው አቶ ስብሃት ነጋ ነው።
የዕርቅ ሂደቱ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል። ኢህአዴግ በዉስጥ ለውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት የሚዳከምበት አጋጣሚ መፈጠሩ አይቀርም። ዕርቁ ግዝያዊና ስትራተጂካዊ ብቻ ነው። የታረቁት መግባባት ስለ ፈጠሩ ሳይሆን የጋራ ጠላትን ለመከላከል ብቻ ነው።

አብርሃ ደስታ ከትግራይ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar