ራሱን የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ብሎ የሚጠራው ድርጅት በከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል። የህወሃትን ዙፋን ከመጠበቅ ባለፈ ምንም ሚና የሌላቸው የብአዴን አመራሮች ያለፉትን ሶስት ወራት በተለያዩ መንገዶች የድርጅቱን አባሎች ሲገመግም ከርመዋል። በግምገማዎች ላይ እንደተረጋገጠው ብአዴን የህወሀትን ዙፋን ሊሸከሙ የሚችሉ ወጣቶችን ኮትኩቶ ለማሳደግ አለመቻሉ ነው። በብአዴን ውስጥ ለሚታየው የውስጥ ትርምስ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ የግንቦት7 አባላትና ደጋፊዎች እየተጫወቱት ያለው ሚና በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ላሉ የንቅናቄው አባላት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነው። የንቅናቄው አባሎችና ደጋፊዎች በድርጅቱ ውስጥ የታቀፉ ወጣቶችን የፖለቲካ ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ ፣ የንቅናቄውን መረብ እስከ ወረዳዎች በመዘርጋት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። ሰሞኑን በገሀድ በየግምገማዎች ላይ ሲነገር እንደነበረው ብአዴን እወክለዋለሁ ከሚለው የአማራ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ተነጥሎ በአየር ላይ የተነሳፈፈ ድርጅት ሆኗል።
ይህን እውነታ ዘግይተው የተረዱት የብአዴን ዙፋን ጠባቂ አመራሮች የሚይዙትን የሚጨብጡትን በማጣት የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው። ታማኝ የሚሉዋቸውን ካድሬዎች በየወረዳዎች በመላክ በግንቦት7 የሚጠረጠሩትን ወይም የግንቦት7 አባሎች ናቸው ተብለው ከሚገመቱ ሰዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት አላቸው ተብሎ የሚታሰቡትን ሰዎች በመያዝና በማሰቃየት ሌላው ወጣት ንቅናቄውን እንዳይቀላቀል ለማድረግ እቅድ ነድፈው ለመንቀሳቀስ አስበዋል። እንዲሁም አንድ ለአምስት የተባለውን አደረጃጀት በመስሪያ ቤቶች፣ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ተቋማት ላይ በስፋት በማውረድ፣ የሰውን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አልመዋል። ወጣቱ አካባቢውን እየለቀቀ ግንቦት7ን ለመቀላቀል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የአካባቢ ፖሊሶችንና የድንበር ጠባቂዎችን በማጠናከር ለመቆጣጠር ውሳኔ አሳልፈዋል።
በድርጅቱ ውስጥ የግንቦት7 ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩትን ወይም ዝንባሌ አላቸው የሚባሉትን ሁሉ ነቅሶ በማውጣት ለብአዴን ነፍስ ለመዝራት ሙከራ እየተደረገ ነው። እነዚህን ውሳኔዎች ያስፈጽማሉ የተባሉ በጭካኔያቸው ፣ በጎጠኝነታቸውና በንቅዘታቸው የሚታወቁትን የእነሱ ታማኝ ካድሬዎችን ወደ ፊት ለማምጣት በማሰብ ሰሞኑን ሹም ሽር አድርገዋል። ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እንደሚባለው የሰዎች መለዋወጥ የብአዴንን ህልውና ከክስመት የሚታደገው አይሆንም።
ለመሆኑ ብአዴን የህወሀትን ዙፋን ከመጠበቅ በስተቀር ባለፉት 22 አመታት እወክለዋለሁ ለሚለው ህዝብ ምን ሰራ? ብአዴን ባለፉት 22 ዓመታት ከሰራቸው አሳፋሪ ስራዎች መካከል ሰፊው የአገራችን መሬት ለሱዳን ተላልፎ ሲሰጥ የስምምነት ፊርማውን ማስቀመጡ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እወክለዋለሁ የሚለው የአማራ ህዝብ ከቦታ ቦታ ሲፈናቀል፣ ለአመታት ህዝቡ በኤድስና በወባ እንደቅጠል ሲረግፍ ፣ ወጣቱ ስራ አጥቶ በአደገኛ እጾች ደንዝዞና ተስፋ ቆርጦ የወጣትነት እድሜውን በከንቱ ሲያሳልፍ ብአዴን ዞር ብሎ ለማየት ፈቃደኛ አልሆነም።
የብአዴን ዙፋን ጠባቂነት የሰለቻቸው የድርጅቱ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የውስጥ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብዙዎች በህወሀትና በተላለኪው ብአዴን የጸጥታ ሀይሎች ተገድለዋል፣ አንዳንዶች ድርጀቱን ለቀው ወጥተዋል፣ አንዳንዶች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብአዴን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላ አገራችን ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ፈቃደኝነታቸውን አሳይተው በግንቦት7 ስር ታቅፈው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት ወጣት አባላት የቀድሞ አባሎች የጀመሩትን ትግል በተደራጀና ስርአት ባለው መልኩ ለማስኬድ የጀመሩት ትግል ንቅናቄው በትኩረት የሚከታተለው ነው። ይህ ትግል ተጠናክሮ በሌሎች ድርጅቶችም ተግባራዊ እንዲሆን ግንቦት7 በተለያዩ የኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ላሉ አባሎቹ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ግንቦት7 መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዘረኛው፣ ዘራፊውና ራዕይ አልባው የህወሀት ጎጠኛ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል እና በምትኩ የሁሉም የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመረውን ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ወሳኝ የትግል ምእራፍ ወቅት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብሎ ንቅናቄው እንደሚያምን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በተለይም በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ታቅፈው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ እውነተኛ የስርአት ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ሀይሎች የብአዴን ወጣት የግንቦት7 አባላት እያሳዩት ካሉት እንቅስቃሴ ልምድ በመውሰድ በውስጥ የሚያደርጉትን ትግል አጠንክረው እንዲገፉበት ንቅናቄያችን ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar