onsdag 26. mars 2014

ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ትብብር መፈራረሟ አነጋጋሪ ሆኗል

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለፈው እሑድ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈጸሙን ‘ሱዳን ትሪቡን’ በሰኞ እትሙ ዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ ‘ወዳጅ’፣ የግብፅ ደግሞ ‘ጠላት’ ተደርጋ የምትታሰበው ደቡብ ሱዳን ድርጊት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግሥታዊ ቴሌቪዥንን ዋቢ አድርጎ እንደተጻፈው ዘገባ ከሆነ፣ አዲሱ ስምምነት የተፈጸመው በመከላከያ ሚኒስትሩ ኩዎል ማን ያንግ ጁክ የሚመራ የደቡብ ሱዳን ልዑካን ቡድን በካይሮ ጉብኝት ካደረገ በኋላ ነው፡፡ 
ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጁክ በተጨማሪ የልዑካን ቡድኑ ከብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ከጄኔራል ማቡቶ ማሙር ማቴ፣ ከወታደራዊ ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተሩና በግብፅ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር የተውጣጣ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ከግብፅ ፕሬዚዳንት አዲል መንሱር ጋር በተገናኙበት ወቅት ግብፅ በደቡብ ሱዳን እያደረገች ያለችው ትብብርና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለአገሪቱ ግንኙነት መጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጉን በመጥቀስ፣ ለግብፅ ምሥጋና ማቅረባቸውም ተገልጿል፡፡ ጁክ አክለውም የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የጋራ ጥቅምን በተመለከተ የግብፅ ወሳኝ አጋር ለመሆን ደቡብ ሱዳን ያላትን ቁርጠኝነት ለግብፅ ባሥልጣናት ማረጋገጫ መስጠታቸውም ዘገባው ያመለክታል፡፡
የግብፅ ፕሬዚዳንት አዲል መንሱር በበኩላቸው፣ የደቡብ ሱዳንና የግብፅ መንግሥታት በጋራ ለሚያከናውኗቸው ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መንግሥታቸው ገቢ ማግኛ መንገዶችን ለማፈላለግ ያለውን ቁርጠኝነት እንደገለጹም ተጠቁሟል፡፡
በዘገባው የወታደራዊ ትብብር ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ያልተገለጹ ቢሆንም፣ ምንጮች ግን ወታደራዊ ኤክስፐርቶችን በጋራ የመጠቀም፣ ልዩ ኃይሎችን የማሠልጠንና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በጋራ መሳተፍን እንደሚያካትት መግለጻቸውን ዘግቧል፡፡
የግብፅ ወታደራዊ ኃይሎች በደቡብ ሱዳን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ያመቻቻል የተባለው ይህ ስምምነት፣ ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራል እየተባለ ነው፡፡ ግብፅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ እንድታቋርጥ ለማድረግ በተከታታይ እያደረገች ያለው ጫና አንድ አካል ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ደቡብ ሱዳን የዓባይ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) እንድትፈርም ለማድረግ የማግባባት ሥራ እየሠራች ላለችው ኢትዮጵያ፣ ይህ ዜና ጥሩ ስሜት እንደማይፈጥርላት ተንታኞች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃነቷን እ.ኤ.አ. በ2011 እንድትቀዳጅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተች ቢሆንም፣ በቅርቡ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስና ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር እያጠናከረች ከመጣችው ግንኙነት ጋር ተዳምሮ ለግብፅ ክፍተት እንደፈጠረላት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኞች ያመለክታሉ፡፡
የአፍሪካ የደኅንነት ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አየለ የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ግልጽ ባይሆኑም፣ የተለያዩ መረጃዎች ግን ‘ቀላል’ (Soft) ሊባል የሚችል ይዘት እንዳለው እንደሚጠቁሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ ሥልጠናና የባለሙያዎች ልውውጥ ላይ ማተኮሩ ለዚህ እንደ ማስረጃ ሊቀርብ እንደሚችል ያመላከቱት ዶ/ር ሰለሞን፣ ስምምነቱ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ቢሆንም በኢትዮጵያ ላይ ስለሚያስከትለው ተፅዕኖ ለመናገር ግን ጊዜው ገና መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ስምምነቱ ሊያስነሳ ከሚችላቸው ጥያቄዎች መካከል ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን  ስትጫወተው የነበረውን ከፍተኛ ሊባል የሚችል ሚና ሊያዳክም ይችላል ወይ? ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን የእርሰ በርስ ጦርነት ለማስቆምና የፖለቲካ ቀውሱን ለማረጋጋት እየሠራች ያለችው ሥራ ወዴት ያመራል? የሚሉት ወሳኝ መሆናቸውን ዶ/ር ሰለሞን አፅንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ጉዳዩ ሊያሳስብ የሚችለው ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም፤›› ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፣ ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አፅንኦት ሰጥተው ሊከታተሉት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ያለፈ እንቅስቃሴ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ የሚያስፈልግም ከሆነም ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ከደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር ነው፤›› በማለትም ዶ/ር ሰለሞን አክለዋል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን የስምምነቱ ተፅዕኖ ቀላል መሆኑ የሚያቆመው የግብፅ ወታደሮች ወደ ሱዳን በመግባት ከሁለቱ ወገኖች አንዱን የሚረዱ ከሆነና ወታደራዊ ሠፈር (Base) የሚያገኙ ከሆነ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ስምምነቱ በግልጽ እነዚህን ተጨባጭ የሆኑ አሉታዊ አንድምታዎች በግልጽ የሚያሳይ ባይሆንም፣ ግብፅና ኤርትራ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ፕሬዚዳንት ተቃዋሚ ለሆኑት ለሪክ ማቻር ይረዳሉ የሚለውን ሐሜት እውነት ሆኖ እሱን ለመቀልበስ አለመፈጸሙን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን እያጤነው እንደሆነ ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ ለጊዜው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar