lørdag 29. mars 2014

የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፈኑ “ወያኔ እጅ ገብተዋል”

የጋምቤላ ክልልን ሲመሩ ቆይተው ባለመስማማት የኮበለሉት የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸው ተጠቆመ። ዜናው በገለልተኛ ወገን ባይገለጽም ኖርዌይ በስደት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ በኢህአዴግ በጥብቅ የሚፈለጉ ሰው ነበሩ።
በመለስ ዜናዊ ውሳኔ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ወደ ደቡብ ሱዳን ከማምራታቸው በፊት ኬንያ እንደነበሩ፣ ከኬንያ ወደ ደቡብ ሱዳን ለምን እንደተጓዙ የዜናው ምንጮች በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ስማቸው እንዲደበቅላቸው የጠየቁ የጋምቤላ አስተዳደር ባልደረባ ለጎልጉል የአካባቢው ዘጋቢ እንደተናገሩት አቶ ኦኬሎ ደቡብ ሱዳን ሆቴል በተቀመጡበት መታፈናቸውን አረጋግጠዋል። “ወያኔ እጅ ገብቷል” ሲሉ ያከሉት እኚሁ ሰው “አቶ ኦኬሎ ብረት በማንሳት ወያኔን ለመታገል ከተነሱ ጋር ተቀላቅለዋል በሚል ስማቸው መመዝገቡንና ወደ ደቡብ ሱዳን ማቅናታቸው በመታወቁ ህወሃቶች እጅ ሊወድቁ ችለዋል” ብለዋል። ምንጩ ይህንን ይበሉ እንጂ አቶ ኦኬሎ አክዋይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀኑበትን ምክንያት በርግጠኛነት ሃላፊነት ወስዶ የገለጸ ወገን አልተደመጠም። ኢህአዴግም ቢሆን የቀድሞውን ሹመኛ ስለመያዙ ይፋ ያደረገው ነገር የለም።
ከደቡብ ሱዳን ቀውስ ጋር በተያያዘ የኑዌር ተወላጅ ከሆኑት ሬክ ማቻር ጦር ጋር በመሰለፍ የሳልቫ ኪርን ሃይል ሲወጉ ከተገደሉ ወታደሮች መካከል የኢህአዴግን ሰራዊት መለያ የለበሱ ኑዌሮች መገኘታቸው ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ያመለከቱት ምንጭ “ደቡብ ሱዳን እየወጋት ካለው ኢህአዴግ ጋር አብራ የቀድሞውን የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር ከምድሯ ላይ እንዲታፈኑ መፍቀዷ ቅሬታ ያስነሳል” ብለዋል።
ከቤተሰባቸው ተነጥለው በስደት ከሚኖሩበት ኖርዌይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያመሩት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ደቡብ ሱዳን በህወሃት ሙሉ ቁጥጥርና ፈቃድ የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን እያወቁ ወደዛ ማቅናታቸውን ባሥልጣኑ “ታላቅ ጥፋት” ብለውታል። ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በቅርቡ አቶ ኦሞት ኦባንግ መኮብለላቸውና በብዙዎች ዘንድ አውሮጳ እንዳሉ ቢነገርም በትክክል ያሉበት አገር በይፋ አለመታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar