ኢትዮጵያ፣የወንጀለኞች መናኸሪያ አገር
July 21, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ቡድን የሆነውን ግንቦት ሰባት የፍትህ፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እየተባለ የሚጠራውን ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንዳርጋቸው ጽጌን በቀን ብርሀን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ፡፡ እንደ ገዥው አካል ዘገባ ከሆነ የኢትዮጵያ የደህንነት አገልግሎት ከአቻው ከየመን መንግስት የደህንነት ጥበቃ አባላት ጋር በመቀናጀት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በየመን ሰንዓ በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ሆነው የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ የየመን ባለስልጣኖች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በቁጥጥር ስር አውለው በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል አሳልፈው ከመስጠታቸው በፊት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእንግሊዝ ኮንሱላር ባለስልጣኖች፣ ከህግ ወኪሎች እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዲችሉ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል፡፡
በገዥው አካል በሚስጥር ተቀርጾ ለ63 ሰከንዶች ያህል በአየር ላይ በዋለው የቪዲዮ ክሊፕ (ቁራጭ) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በገዥው አካል ተጠልፈው መያዛቸውን በማስመልከት በተረጋጋ መንፈስ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በማራኪዎቻቸው ላይ ምንም ዓይነት ቁጣ እንደሌላቸው እና ከእራሳቸው ህሊና ጋር በሰላም እንደሚኖሩ በሙሉ የእራስ መተማመን መንፈስ ተናግረዋል፡፡ እኒህ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰው በእራሳቸው ፈቃድ በነጻነት የሚናገሩት ነው ወይስ ደግሞ በማራኪዎቻቸው አስገዳጅነት የተነገራቸውን እንደ በቀቀን እንዲደግሙ ተገድደው ነው? አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ንግግራቸውን ሲያደርጉ በሚስጥር ለለፕሮፓጋንዳ ትርፍ ሲባል በቪዲዮ ክሊፕ እየተቀረጹ መሆናቸውን አልተገነዘቡም ነበርን? የቪዲዮ ክሊፑ አቶ አንዳርጋቸው በተረጋጋ መንፈስ በነጻነት እራሳቸውን እየተከላከሉ ንግግራቸውን ሲያደርጉ የሚያሰማ ነበር ወይስ ደግሞ በማራኪዎቻቸው ፊት ቀርበው የምህረት ልምምጥ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታዩ ነበር? በቪዲዮ ክሊፑ ተቀርጾ የተለቀቀው ድምጽ የአቶ አንዳርጋቸውን ደጋፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የእንግሊዝን መንግስት ለማታለል ሲባል የተደረገ የመድረክ ትወና ሙከራ ነውን? የአቶ አንዳርጋቸው ማራኪዎች እና አሳሪዎቻቸው አቶ አንዳርጋቸውን በመጥለፍ በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው በፊት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ምን ሲሰሩ ቆዩ? ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ አላገኘሁም ሆኖም ግን በሚሽከመከሙ የጅብ መንጋዎች እና ጥርሳቸውን ባገጠጡ በቀልተኞች ፊት ቀርበው እንደዚያ ባለ በተረጋጋ መንፈስ፣ ሰብዕና እና የመንፈስ ጥንካሬ ሲናገሩ በማየቴ የተሰማኝ አድናቆት ወደር የለውም፡፡
ገዥው አካል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን እ.ኤ.አ ጁን 23/2014 ጠልፎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በይፋ ከገለጸ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የቪዲዮ ክሊፑን ለምን እንደለቀቀ ግልጽ አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ገዥው አካል በአቶ አንዳርጋቸው ንግግር በርካታ የፕሮፓጋንዳ ዓላማዎችን ለማሳካት ጥረት ያደርጋል፣ ከእነዚህም መካከል፣ 1ኛ) ገዥው አካል ብቃት ያለው የስለላ መዋቅር እንዳለው እና ለጠላቶቹ እና ለተቃዋሚዎቹ ቢያንስ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ምንም ዓይነት ነገር ሊያመልጠው እንደማይችል ያለውን ብቃት እና የመፈጸም ችሎታ ለግንቦት ሰባት እና ለሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች አስረግጦ ለመንገር የታለመ ነው፣ (በነገራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በገዥው አካል የደህንነት ኃይሎች ተጠልፈው በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሁኔታ በአንድ ወቅት ከአንድ በአዲስ አበባ ከሚኖር ዘመድኩን ከሚባል ፖሊስ አለቃ ጋር የአሜሪካ ሬዲዮ የአማርኛው ድምጽ የደረገውን ቃለመጠይቅን አስታወሰኝ፡፡ የቪኦኤ ጋዜጠኛ መልዕክቱን በአየር ላይ ካዋለ በኋላ ዘመድኩን ዘጋቢውን ጋዜጠኛ እንዲህ በማለት አስጠነቀቀ፣ “አንተ ዋሽንግተን ወይም ደግሞ መንግስተ ሰማያት ብትኖር ጉዳዬ አይደለም፣ ደንታ የለኝም! ሆኖም ግን አንተን ባለህበት መጥቸ በቁጥጥር ስር አውዬ አመጣሀለሁ፣ ይህንን ልታውቅ ይገባል!!) ገዥው አካል አቶ አንዳርጋቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የዘመድኩንን የእብደት ዛቻ በየመን አገር በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የተገበረው ይመስላል፡፡
ገዥው አካል ጠላቶቹ ዋሽንግተንም ይሁን ወይም መንግስተሰማያት ይኑሩ በየመን ትራንዚት ሲያደርጉ በቁጥጥር ስር ሊያደርጋቸው እንደሚችል በቂ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚችል ለማስረገጥ ጥሯል ፡፡ 2ኛ) በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የአካል ወይም የስነልቦና ስቅይት ያልተደረገ መሆኑን፣ መብታቸው ያልተገፈፈ እና በአግባቡ የተያዙ መሆናቸውን በማሳየት በህብረተሰቡ ላይ ተይዞ ያለውን እምነት ለማስተባበል ነው፡፡ 3ኛ) በእርግጠኝነት አቶ አንዳርጋቸው በደህና ሁኔታ የተያዙ መሆናቸውን እና ክበራቸውም የተጠበቀ መሆኑን ለማሳየት (አቶ አንዳርጋቸው ገጽታቸው የተጎዳ አይመስልም ቢያንስ በፊታቸው ላይ በግልጽ የሚታይ ሰንበር ወይም ሌላ የተጫረ ምልክት አይታይም፡፡) በቪዲዮ ክሊፑ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ሁልጊዜ እንደሚታዩት ሆነው ለፖሊስ ቃለመጠይቅ እንደሚሰጡ የሚመስል የተረጋጋ መንፈስ ይታይባቸዋል፡፡ አሳሪዎቻቸው አቶ አንዳርጋቸውን የተረጋጉ እና ከድሮው የተለየ ሆነው እንዳይታዩ፣ ጭንቀት፣ እና በመጠለፋቸው ምክንያት የተለየ ውጥረት እንዳይታይባቸው ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ 4ኛ) አቶ አንዳርጋቸው በእስር ቤት የማሰቃየት ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል ወይም ደግሞ ሊፈጸምባቸው ይችላል የሚለውን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ትችት አስቀድሞ ለማጥፋት እና አፍ ለማስያዝ የታለመ ነው፣ 5ኛ) ግንቦት ሰባትን እና አመራሩን ለማሸማቀቅ እና ገዥው አካል የድርጅቱን ውስጣዊ ደህንነት ዘልቆ የገባ መሆኑን እና የድርጅቱን ስስ ብልቶች በማውጣት ለመዘገብ እንዲቻል በማስመሰያነት ለመጠቀም ነው፣ 6ኛ) ግንቦት ሰባት የተባለው ድርጅት በጥሩ ሁኔታ የተፐወዘ መሆኑን እና በአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ምክንያት ድርጅቱ አቅመቢስ ሽባ እንደሆነ እና ማንኛውንም መረጃ ከእርሳቸው በማሰቃየት እና በሌላ መንገድ መውሰድ እንደሚችሉ ለማሳየት የታቀደ ነው፣ 7ኛ) በጠቅላላው የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች ተስፋ ለማስቆረጥ እና ገዥው አካል የዓለም አቀፍ ህግን የበላይነት በመጣስ ከዚህ ቀደም ለበርካታ ጊዚያት እንዳደረጉት ሁሉ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች በድብቅ ይሁንታን ለማግኘት የታሰበ ሰንካላ ምክንያት ነው፣ 8ኛ) የሸፍጥ ህልዮት ቀማሪዎች የእራሳቸው የሆነ መግለጫ የሚኖራቸው እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ገዥው አካል አቶ አንዳርጋቸውን በማፈን እና በቁጥጥር ስር በማዋል ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ማሳካት አለማሳካቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የገዥው አካል አባላት የሻምፓኝ ጠርሙስ በመክፈት በማፈኑ እኩይ ተግባር ስኬታማ በመሆን በማታ ቸበርቻቻ ዳንስ ያካሂዳሉ፡፡ ገዥው አካል በአሁኑ ጊዜ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ ባደረገው እኩይ የማፈን ድርጊት ላይ ድልን ተቀዳጅቷልን? ማንም ሰው ቢሆን የአንድ ድርጅታዊ ተቋም ነብስ፣ አካል እና አእምሮ ሊሆን እንደሚችል እጠራጠራለሁ(ከመለስ ዜናዊ በስተቀር)፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው መታፈን በግንቦት ሰባት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚያ ድርጅት መጥፎ ዕድል ሆኖ ጉዳት ያደርስበታል የሚል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አቶ አንዳርጋቸው መረጃ እንዲሰጡ ለማስገደድ የማሰቃየት እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ትክክል ለመሆናቸው ወደፊት ጊዜ የሚነግረን ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የህብረተሰብ ሳይንሳዊ ጥናት መረጃ እና ትንታኔ በግልጽ እንደሚያሳየን በተራ የማሰቃየት የወንጅል ምርመራ እና ልዩ የወንጀል ምርመራ ውሸትን እንጅ እውነትን ሊያመጣ አይችልም፡፡
ለመረጃ ጉዳይ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ተገናኝቸ ወይም ደግሞ ተነጋግሬ አላውቅም፡፡ ከእርሳቸው ጋር በቪዲዮ ቴፕ ተቀርጾ የተለቀቀውን ንግግር ከመስማት እና ስለእርሳቸው በድረገጽ የተለቀቀውን የሰዎች አስተያየት ከማንበብ በስተቀር ሌላ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ገዥው አካል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ በመመስረት የይስሙላው የዝንጀሮው ፍርደ ቤት የሞት ቅጣት ሊበይንባቸው እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ለዚህም ነው ለዚህ ለዝንጀሮው የፍትህ አካል እና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የሚደረገውን ልዩ የወንጀል ምርመራ ዓለም አቀፍ የህግ የበላይነትን ምክንያት በማድረግ ይህንን ትችት ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡
የጸረ ሽብርተኝነትን ህግ በመጠቀም የዓለም አቀፍ የህግ የበላይነትን በመጣስየሚካሄድ መንግስታዊ ሽብርተኝነት እና ውንብድና፣
የማንኛውም የጨነገፈ መንግስት መለያ ባህሪ የህግ የበላይነት አለመኖር ነው፡፡ የጨነገፈ ወንጀለኛ መንግስት መገለጫ ባህሪ የህገመንግስት የበላይነትን እና ዓለም አቀፋዊ ህግን አስከፊ በሆነ መልኩ መደፍጠጥ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ቦኮ ሃራም እየተባለ በሚጠራው በናይጀሪያ በሚንቀሳቀሰው አሸባሪ ድርጅት በናይጀሪያ በ300 ልጃገረዶች ላይ ከሶስት ወራት በፊት በፈጸመው ውንብድና እና በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የወሰደው እብሪተኝነት የተሞላበት አፈና መካክል ትንሽ ልዩነት ብቻ ነው ያየሁት፡፡ ገዥው አካል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አሸባሪ ናቸው በማለት በሌሉበት የጸረ ሽብር ወንጀል (የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2009) እያለ በሚጠራው የዜጎች የማጥቂያ መሳሪያ ክስ በመመስረት የሞት ፍርድ ሊበይንባቸው እንደሚችል ክርክር ሊያቀርብ ይችላል እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በማቀርባቸው ትችቶቸ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ገዥው አካል የፖለቲከ ተቀናቃኞቹን ለማጥቃት በአገር ክህደት እና በሽብርተኝነት በመወንጀል በኢትዮጵያ በይስሙላው ፍርድ ቤት እየተጠቀመ በህግ ሰበብ ሲገድል እና ሲያስር እንዲሁም ሲያሰቃይ ቆይቷል፡፡ አሁንም ይህንኑ እኩይተግባሩን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ በርካታ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመንግስት የሰብአዊ መብት ጥበቃ መምሪያ ዓመታዊ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ ኢላማ ያደረገው ገዥው አካል የፖለቲካ ተቀናቃኞችን እና ተቃዋሚዎቹን፣ አክቲቪስቶችን፣ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን እንደዚሁም የህትመት ሜዲያዎችን መገደብን በመፈጸም በይስሙላው የፍትህ አካል አማካይነት ጥቃቶችን መሰንዘር ነው፡፡ በገዥው አካል በሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው ወገኖች የሞት ፍርድ እንደሚበየንባቸው ጸሐይ የሞቀው እና የታወቀ የገዥው አካል መርህ ነው፡፡ እውነታው ሲታይ ግን በኢትዮጵያ የይስሙላው ፍርድ ቤት አማካይነት በጸረ ሽብር ህጉ በመጠቀም በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚበየነው ኢፍትሀዊነትን የተላበሰው ፍርደ ገምድል ውሳኔ በጅቦች ፍርድ ቤት በአጋዘኖች ላይ ከሚበየነው የሞት ፍርድ ውሳኔ ጋር አንድ እና ተመሳሳይ ነው፡፡ ነጻ የፍትህ ስርዓት ከሌለባት አገር እና ዳኞችም በሚነገራቸው መሰረት ብቻ እንዲወስኑ በሚገደድቡት ሁኔታ የሞት ፍርድ ፍትሀዊነትን ሊያገኝ እና ነጻ በሆነ መልኩ ምርመራ ተካሂዶበት የሚሰጥ ውሳኔ ሊሆን አይችልም፡፡
የገዥውን አካል የጸረ ሽብር ህግ አዋጅን ህግ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ አዋጅ ቁጥር 652 የጫካ ህግ ነው፡፡ የአምባገነን መንግስት አሸባሪ ነው (“Ethiopia: Dictatorship is State Terrorism”) በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ በግልጽ ለመጠቆም እንደሞከርኩት አዋጅ ቁጥር 652 አሁን በህይወት በሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በዘፈቀደ ተፈብርኮ የተረቀቀ እና በይስሙላው ፓርላሜንት የጸደቀ ንጹሀን ዜጎችን ለማጥቃት የወጣ ቀያጅ ህግ ነው፡፡ ያ አስቀያሚ አዋጅ በሁሉም ታላላቅ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውግዘት እና ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አዋጁ በጣም የተለጠጠ እና የትርጉም ግልጽነት የጎደለው እና ንጹሀን ዜጎችን እና የፖለቲካ አመጸኞችን ለማጥቃት የታለመ ነው በማለት ያንን አዋጅ በጥሩ ሁኔታ ተችቶታል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ በጣም አስቀያሚ እና የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ለማጥቃት እና ለማሰቃየት የሚጠቀምበት የማጥቂያ መሳሪያ ነው በማለት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጿል፡፡ የበለጠ የከፋው ነገር ደግሞ በጸረ ሽብር ወንጅል በተጠረጠረ ግለሰብ ላይ መለስ ዜናዊ እና አፈቀላጤዎቹ አስቀያሚ በሆነ መልኩ በጸረ ሽብር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የክስ ሂደቱ እየታየ ባለበት ሁኔታ ከህግ አግባብ ውጭ በማን አለብኝነት የተጠርጣሪዎችን ህግመንግስታዊ መብት በመደፍጠጥ በንጹሀን ዜጎች ላይ የይስሙላው ፍርድ ቤት ኢፍትሀዊ ውሳኔ እንዲሰጥ በማሳሳት እና ስልጣንን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ኢፍትሀዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በሽብር ወንጀል ተጥርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ዋስትና የማግኘት መብታቸውን ተነፍገው በተጠረጠሩበት ጉዳይ ምርመራ በሚካሄድበት ጊዜ ከህግ አግባብ ውጭ መረጃ እንዲሰጡ ለማስገደድ በሚል እኩይ ድርጊት የአካል እና አእምሮ ማሰቃየት ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገዥው አካል በፍርድ ቤቶች ላይ የፖለቲካ ጫና በማድረግ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በአገር ክህደት እና በጸረ ሽብር ወንጀል ተብሎ ብይን እንዲሰጥ ያስገድዳሉ፡፡
ዓለም አቀፍ ህግን ለህገወጦች መስበክ፣
የህግ የበላይነትን በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል መስበክ መናገር እና መስማት ለማይችሉት ዱዳዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሱ ማስተማር እና በባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ያህል ነው፡፡ በአንድ ጆሮ ይገባ እና በሌላው ባዶ ጆሮ ወጥቶ ይበናል፡፡ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እንደሚታገል የህገ መንግስት የህግ ባለሙያ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የህግ የበላይነትን፣ ዓለም አቀፍ ህግን፣ የእራሱን ህገ መንግስት እና ሌሎችንም እንዲያከብር መስበክ እና ማስተማሬን መቀጠል አለብኝ፡፡ ያም ሆነ ይህ ድምጼን ከፍ አድርጌ መናገር አለብኝ ምክንያቱም ይህንን ለማድረግ የሞራል ግዴታ አለብኝና፡፡ ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ የህግ የበላይነት እየተደፈጠጠ እየተመለከቱ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ዝምታን የሚመርጡ የሸፍጠኞች የህግ የበላይነት በትክክለኛው የህግ የበላይነት ላይ ድልን እንዲቀዳጅ የሚፈቅዱና የሚመኙ ከገዥው አካል ጋር የሚሞዳሞዱ ሸፍጠኞች ብቻ ናቸው፡፡
ገዥው አካል ከየመን መንግስት ጋር በመተባበር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ማፈኑ ልዩ “የአፈና ወንጀል” እየተባለ የሚጠራውን የወሮበልነት ወንጀል ፈጽሟል፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ የደህንነት መስሪያ ቤት እየተባለ የሚጠራው አፋኝ ቡድን ከሌላ ሉአላዊነቱ ከተጠበቀ ሀገር ጋር በመመሳጠር በሌላ አገር እስር ቤት ውስጥ በሽብር ወንጀል የተጠረጠረ በሚል እኩይ ድርጊት አንድን ንጹህ ሰው በቁጥጥር ስር ማዋል ከፌዝ ያለፈ ፋይዳ የሚኖረው አይሆንም፡፡ ማሰቃየት በሚፈጸምበት አገር በማሰቃየት የሀሰት በግዴታ የሚሰጥ መረጃ አንዱ መለያ ባህሪ ነው፡፡ ከሎጅስቲክ አንጻር ሲታይ በሽብር ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በውጭ አገር መሬት በባለስልጣኖች በቀጥጥር ስር ውለው ወደ ዘብጥያ በመወርወር ወደ ሌላ መንግስት የማሰቃየት በተመላበት ሁኔታ የአካል እና የስነ ልቦና ሰለባ ለሚያደርግ ምርመራ እና ጥያቄ እንዲዛወሩ ይደረጋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ዜጎችን አፍኖ በመሰወር ወንጀል ልምድ እረገድ አዲስ አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህንን ዓይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም ከማንም በላይ የቀዳሚነቱን ስፍራ የያዘ የማፍያ ቡድን ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ በጠቅላላው ከ100 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪ ሽብርተኞች በሶማሊያ እና በኬንያ በቁጥጥር ስር ውለው በገዥው አካል እና በዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት እና የህግ አስፈጻሚ ባለስልጣኖች ለምርመራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡ ማናቸውም እስረኛ ለተከሰሰበት የምርመራ ጉዳይ ጠበቃ እንዲያቀርብ አልተፈቀደለትም፡፡ አብዛኞቹ እስረኞች በምርመራ ወቅት የአካል እና የስነልቦና ስቅይት እንዲደርስባቸው ተደርጓል፡፡ በተጨባጭ ለማየት ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ያሲር ቲናዊ የተባለውን ወዲያውኑ ወደ ግብጽ እንዲሄድ የተደረገውን እና በቀጣይም ወደ ሶሪያ እንዲተላለፍ የተደረገውን በምርመራ እረገድ አስተናግዷል፡፡ መሀመድ ዓሊ ኢሴ እና ኦማር ቢን ሀሰን የተባሉትም ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ ኢሴ የተባለው የአፈና ሰለባ በኢትዮጵያ መርማሪዎች በኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲሰቃይ ተደርጓል፡፡
ልዩ የአፈና ወንጅል በማንኛውም የሰብአዊ መብት ጥበቃ መጽሐፍ ማንኛውንም ህግ ይደፈጥጣል፡፡ የአፈናው ሂደት የግዳጅ ጠለፋ እና አፍኖ መሰወርን ያካትታል፡፡ የአፈና ወንጀል ሰለባው ከህግ አግባብ ውጭ በውል ላልታወቀ ጊዜ ከማንም ጋር እንዳይገነኝ ሆኖ በእስር እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ በምርመራ እንዲቆዩ ሆኖ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ የአካል እና የአዕምሮ ስቅይት እንዲደርስባቸው ይደረጋል፡፡ የአፈና ወንጀሉ ሰለባ የሆነው ዜጋ ወደ አፈና ወንጀሉ መዳረሻ ከመሄዱ በፊት የህግ አማካሪ የማግኘት ዕድል አይሰጠውም፡፡ የአፈና ወንጀል ሰለባ የሆኑ ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከጤና ሞግዚቶቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ክልከላ ይደረግባቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለብቻቸው በአንድ በሚስጥር በተያዘ እስር ቤት ውስጥ እንዲታሰሩ በማድረግ በቀጥጥር ስር ውለው ለምን ወደ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ እንደቀረቡ የመጠየቅ መብት የላቸውም፡፡
ስለማሰቃየት (ሰቆቃ) ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፤
መንግስታዊ ድጋፍ ካለው የማሰቃየት ድርጊት ነጻ የመሆን መብት መሰረታዊ እና ዓለም አቀፍ መብት ሆኖ በዓለም አቀፍ ህግ ስምምነቶችን አካትቶ የያዘ መርህ ነው፡፡ መንግስታት በፍጹም እና በአስገዳጅ ሁኔታ ውል በመግባት የጥቃት ሰለባ የሆነው ግለሰብ ቅጣት፣ ማሰቃየት፣ ወዘተ ይደርስበታል ተብሎ በሚጠረጠር ቦታ እንዲሄድ አይደረግም፡፡ ይህ ዓይነት ግዴታ ዋና መሰረታዊ ሲሆን በሁሉም መንግስታት ዘንድ የተፈጻሚነት ግዴታ ያለበት ሲሆን ከዚህ ስምምነት ሊወጣ ወይም ደግሞ በተጻራሪ መልኩ ሊቆም አይችልም፡፡ ይህ ጉዳይ የስምምነቱን ፊርማ ቢፈርሙም ባይፈርሙም በሁሉም መንግስታት ዘንድ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
ስለማሰቃየት ያለው ስምምነት እና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው፣ ኢሰብአዊ ወይም ደግሞ የማዋረድ ስምምነት ወይም ቅጣት በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ማርች 14/1994 እና በየመን ደግሞ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 5/1991 ተፈርሟል፡፡ አንቀጽ 3 ዓለም አቀፍ የማሰቃየት ስምምነቶች/ Convention Against Torture (CAT) በተለይ አንድ ግለሰብ በማሰቃየት አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚያስችል በቂ መረጃ እስከተገኘ ድረስ የመንግስት ፓርቲዎች የማስወገድ፣ የመመለስ ወይም ደግሞ አንድን ተጠርጣሪ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መንግስት የማዛወር መብት ይሰጣል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ስለመኖር እና አለመኖር ጉዳይ ተወዳዳሪ ባለስልጣኖች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁሉንም ታሳቢዎች ማለትም በመንግስታት ላይ የብዙሀን ሰብአዊ መብት መረገጥን ያካትታል፡፡ አንቀጽ አንድ ማሰቃየትን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፣ “ከአንድ ሰው ወይም ደግሞ ከሌላ ሶስተኛ ሰው መረጃን በኃይል አስገድዶ ለመውሰድ ወይም ደግሞ ተገድዶ በኃይል እንዲያምን ለማድረግ በመርማሪ ወይም ደግሞ በህዝብ ባለስልጣንነት ደረጃ ላይ ያለ ሰው በሌላ በሚጠረጠር ሰው ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳት ወይም ማሰቃየት ማለት ነው“
ማሰቃየት እና አግባብ ያልሆነ አያያዝ በኢትዮያ ላለው ገዥ አካል ጥሩ የንግድ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ በኢትዮያ በሚሰነፍጠው የማጎሪያ እስር ቤት ለብቻ ማድረግ እና ማሰር በእራሱ ማሰቃየት ማለት ነው፣ እናም በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም አሰቃያሚ ወንጀል ነው፡፡ ማንም ቢሆን በኢትዮጵያ ያለውን አስፈሪውን እና አስደንጋጩን የገዥውን አካል የባርነት የእስር ቤት አያያዝ ስርዓት ለማወቅ በመንግስት ስምምነት መሰረት የእንግሊዝ ዜጋ በሆኑት በኮሎኔል ሚካኤል ዴዋር የተዘጋጀውን የሚስጥር የእስር ቤት ዘገባ ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች የሚፈጸመውን የማሰቃየት እና አግባብ ያልሆነ የእስር ቤት አያያዝን በማስመልከት በተለያየ መልኩ አዘጋጅቶ ዘገባ አቅርቧል፡፡ “በኢትዮጵያ ሰላማዊ አመጸኞችን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና የሽምቅ ቡድን አባላትን ይረዳሉ ተብለው የሚጠረጠሩትን እንዲሁም በሽብርተኝነት የሚጠረጠሩትን ንጸሀን ዜጎች በፖሊስ፣ በወታደር እና በሌሎች የደህንነት አባላት ማሰቃየት እና አግባብ ያልሆነ የእስር ቤት አያያዝ እንዲፈጸምባቸው በመቅጣት የንጹሀን ዜጎችን የሰብአዊ መብቶች በመደፍጠጥ ላይ ይገኛል“ የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡ በማዕከላዊ እና በመንግስት ተወካይ በሆኑት በአዛዦች፣ በጨካኝ ወታደሮች እና በፖሊስ ኃላፊዎች የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና አግባብ ያልሆነ ስልታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ተንሰራፍቶ የሚገኝ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች በሂዩማን ራይትስ ዎች በተዘጋጀው ዘገባ መሰረት ወታደራዊ አዛዦች በግልጽ በሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል”:: የማሰቃየት ስልቶች እና ዘዴዎች የተለያዩ መከሰቻዎች አሏቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ፣ “በተደጋጋሚ እና በአሰቃቂ ሁኔታ በዱላ መደብደብ፣ በኤሌክትሪክ ገመድ መግረፍ፣ በጠብመንጃ አፈሙዝ ና ሰደፍ መደብደብ፣ በብረት ቁራጭ ወይም በሌሎች ጠንካራ በሆኑ የመደብደቢያ ቁሶች መምታት በአብዛኛው የተለመዱ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ማጥቂያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊስ እና ወታደሮች ሌሎች የማሰቃያ ዘዴዎችን ማለትም የጥቃት ሰለባውን ጭንቅላት ዘቅዝቆ በበርሜል ውስጥ ካለ ውኃ ውስጥ መጨመር፣ የጠቃቱ ሰለባዎች ተዘቅዝቀው ባሉበት ወቀት በተደጋጋሚ መደብደብ፣ በጠርሙስ የተሞላ ውኃ በወንዶች ብልት ላይ ማንጠልጠል እና በጠጣር አሸዋ ላይ የጥቃቱ ሰለባዎች ለበርካታ ሰዓት በባዶ እግራቸው እንዲሮጡ ወይም ደግሞ እንዲንከባለሉ ማስገደድ የመሳሰሉትን ይጠቀማሉ፡፡ አንዳንድ የጥቃቱ ሰለባዎች ዘለቄታዊነት ላለው ጉዳት ይዳረጋሉ፣ ጥቂቶች ደግሞ በማሰቃየት ወቅት ህይወታቸው ያልፋል…ኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ያላት እና ለማስገደድ የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ እና አገራዊ ግዴታዎችን የሚወጡ ህጎች ቢኖሯትም በተግባር ላይ የሚውሉት በጣም አናሳ በሆነ መልኩ ነው፡፡ በጣም ጥቂቶች የማሰቃየት ተግባራት ወዲያውኑ እንዲፈጸሙ ይደረጋሉ፣ በጣም አናሳ የሆኑት ብቻ ለህግ ስርዓት ሂደት ይቀርባሉ“
ገዥው አካል በግንቦት ሰባት እና በሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ አባላት እና አመራሮች ላይ ማሰቀየት ይፈጽማል፣ በአንዳርጋቸው ጽጌ ላይ መረጃን በኃይል ለማስወጣት ሲባል የሰብአዊ መብት ረገጣ ይፈጸማል የሚለው በርካታ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን አሳስቧል፡፡ ይኸ ስጋት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ከጫካ ጀምሮ ባለው ታሪኩ በንጹሀን ዜጎች ላይ ማሰቃየት መፈጸም ልምዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በተደጋጋሚ የሚጠቀምባቸውን አራት አስቀያሚ የሆኑ የማሰቃያ ዘዴዎችን እና እስረኛን ከህግ አግባብ ውጭ አያያዝን አቀርባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴት የፖለቲካ አመራር የነበረችው ብርቱካን ሚደቅሳ ለብቻዋ በአንዲት ጠባብ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ሆና ለወራት የስነ ልቦና እና የአካል ስቅይት እንዲደርስባት በማድረግ በሞት በተለየው በመለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2008 እንድትማቅቅ ተደርጋለች፡፡ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2010 ስለብርቱካን ሚደቅሳ የብቻዋን መታሰር ጉዳይ አስመልክቶ ጥያቄ ሲቀርብለት እንዲህ የሚል የቀልድ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፣ “የብርቱካን የጤና ሁኔታ በመጨረሻ እንደሰማሁት ከሆነ በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለ ነው፣ ትንሽ ኪሎ የመጨመር ሁኔታ አሳይታለች፣ ሆኖም ግን ከዚህም በላይ እንቅስቃሴ ከለማድረጓ በስተቀር በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች…“ ብሎ ነበር፡፡ በብርቱካን ላይ መለስ ሲያራምድ የነበረውን አስመሳይ የእስር ቤት አያያዝ በማስመልከት በብርካታ ትችቶቸ ላይ ዘገባዎችን ሳዘጋጅ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል የሆነው እስክንድር ነጋ እና ባለቤቱ የሰርካለም ፋሲል በእስር ቤት ለደረሰባቸው ኢሰብአዊ እና ጭካኔ የተሞላበት የእስር ቤት አያያዝን በማስመልከት ለኮሎምቢያ ዩኒቨርሰቲ ለፕሬዚዳንት ለሊ ቦሊንገር እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ነበር፣ “… በአፍሪካ በመጥፎነቱ በጣም አስቀያሚ በሆነው የዜጎች የማጎሪያ እስር ቤት ምክንያት በሰርካለም አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት በመፈጸም በእስር ቤት የወለደችው ህጻን ከሚገባው ክብደት በታች መሆኑ እና ህይወቱን ለማዳን በሙቀት መስጫ መሳሪያ/incubator እየታገዘ ህይወት የማዳኑ ስራ በእስር ቤቱ ሀኪሞች ከፍተኛ ጥረት አማካይነት እንዲተርፍ የተደረገውን ህጻን አስመልክቶ ገዥው አካል ምንም እንዳልተደረገ ሙጥጥ አድርጎ ክዷል፡፡“
እ.ኤ.አ በ2010 ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተንከባካቢ ኮሚቴ/CPJ ወጣት ሴት ጋዜጠኛ በሆነችው ርዕዮት ዓለሙ ላይ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና ከህግ አግባብ ውጭ የሆነ የእስር ቤት አያያዝ በማስመልከት በእስር ቤት የተፈጸመባትን የሰብአዊ ድፍጠጣ ነቅሶ በማውጣት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣ “ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ ለዓለም አቀፍ ሴቶች ሜዲያ ፋውንዴሽን/International Women’s Media Foundation የሰጠው ዘገባ ከሆነ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ርዕዮት ዓለሙን ባሳየቸው መጥፎ ስነምግባር በሚል ምክንያት ብቻዋን በአንዲት የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ለሁለት ወራት ያህል ለመቅጣት በሚል ታስራ እንድትማቅቅ ከመደረጉም በላይ በእስር ቤቱ የጥበቃ አባላት የሰብአዊ መብቷ እንዲጣስ ተደርጓል፡፡ ሲፒጀ መረጃውን ነጻ በሆነ መልኩ አጣርቶታል፡፡ ርዕዮት በጡቷ ላይ የተከሰተውን እብጠት በሚመለከት ቀዶ ጥገና ከተደረገላት በኋላ በቂ የሆነ ህክምና እንዳታገኝ ተደርጓል… እ.ኤ.አ ማርች 2014 ሰባት ወጣት የሰማያዊ ፓርቲ ሴት አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሴቶች በዓልን ምክንያት በማድረግ በ5 ኪ/ሜ የመንገድ ላይ እሩጫ በማካሄድ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው ብቻ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በገዥው አካል እጅ የስቅይት እና ግርፋት፣ ከህግ አግባብ ውጭ የሆነ የሰብአዊ መብት አያያዝ እና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ያልተፈጸመባቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት፣ ሰላማዊ አመጸኞች፣ የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ሌሎችም ማግኘት እና መግለጽ ያዳግተኛል፡፡
ከገዥው አካል መካከል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ተዋርዶ፣ ተሸማቅቆ እና ክብሩን አጥቶ ማየት የሚፈልጉ እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ በቀልተኝነት፣ ቂምን ቋጥሮ ለመበቀል ጥረት ማድረግ ለእነርሱ ልክ እንደ እናት ጡታቸው ነው፡፡ ገዥው አካል የጠላቶቹን እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን አያያዝ በማስመልከት የጥላቻ፣ የይቅርታ ቢስነት እና መጥፎ አስተሳሰብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ የተሞላበት የሰነድ ጥናት ምርመራ ቢደረግ በማያጠራጥር ሁኔታ በወንጀል ላይ ተዘፍቆ ይገኛል፡፡ ገዥው አካል አባላት የጉዳት ሰለባዎቹ በታላቅ ስቃይ ላይ ሆነው ሲሰቃዩ ማየት ከምንም በላይ ያስደስተዋል ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፡፡ የገዥው አካል ሊቁ ባለ ራዕይ መሪ እና በአሁኑ ጊዜ በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የእርሱን ተቃዋሚዎች ማሰቃየት፣ ማዋረድ እና ስብዕናቸውን ጥልሸት መቀባት ከማናቸውም ነገር ሁሉ ታለቅ እርካታን እና ደስታን ይሰጠው ነበር፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳን ለማዋረድ እና ከሰብአዊነት ውጭ ለማድረግ ሲያደርግ በነበረው እርባናቢስ ስሌት በጣም አዝን እና አበሳጭ ነበር፡፡ መለስ ማንኛውንም የሰብአዊ መብት አብሮነት ክብር፣ ደግነት እና ምህረት በአፍ ጢሙ በመድፋት በተጠናወተው እርኩስ መንፈሱ ብርቱካንን ለመጨቆን እና ለማዋረድ ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ሊጤን የሚገባው ጉዳይ እነዚህ የመለስ ደቀመዝሙሮች የባለራዩን መሪያቸውን ዕኩይ የበቀልተኝነት አምልኮ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ ለመድገም ሸብረብ ከማለት እንደማይቆጠቡ እገምታለሁ፡፡ ዋናዎቹ የገዥው አካል በአቶ አንዳርጋቸው መጠለፍ ብቻ እና መታሰር ይደሰታሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከግንቦት ሰባት ጋር ያላቸውን ጦርነት ማሸነፍ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም ነብስያቸውን የሚያስደስታቸው ጠላቶቻቸውን ይዘው ማሰቃየት፣ ማዋረድ፣ ጥላሸት መቀባት እና ሰብአዊ ክብራቸውን በማዋረድ ስብዕነቸው ኮስሶ ማየት ነው፡፡ ኃይል ስልጣን ባልተማሩ ደንቆሮ በቀልተኛ ቡድኖች እጅ መያዝ አደገኛ ነው፡፡
የየመን የማሰቃየት ስምምነት እዳ፣
አንድ እያወቀ ዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ ሌላ መንግስትን የሚረዳ ወይም እገዛ የሚያደርግ መንግስት (የማፈን ወንጀለኛ) መጥፍ ድርጊትን የመፈጸም ዕዳ አለበት፡፡ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ በኢትዮጵያ ላላው ገዥ አካል በመስጠቷ (አስገድዶ መሰወር እና በሚስጥር በማሰር ማሰቃየት መፈጸም) ገልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ የማሰቃየት ስምምነት ህግን መጣስ ማለት ነው፡፡ የየመን መንግስት እያወቀ በማሰር፣ የሎጂስትክስ ስራ በመስራት እና የማሰቃየት ስራ ሊሰራበት እንደሚችል እያወቀ አቶ አንዳርጋቸውን በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል የደህንነት ኃይል አሳልፎ የመስጠት የወንጀል እዳን በመፈጸሙ ምክንያት ተጠያቂ ነው፡፡
የማሰቃየት ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 3 ሰብአዊ መብትን በመጣስ ረገድ አንድ ሰው በኃይል ታፍኖ በሚወሰድበት ጊዜ ሊደርስበት የሚችለውን ማሰቃየት በሚመለከት በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ የመን ይህንን አስፈላጊ ጉዳይ ወደ ጎን በመተው አቶ አንዳርጋቸውን በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ የየመን መንግስት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል ማሰቃየትን እንዳይፈጽም ዋስትና አልሰጠችም፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 7/2014 የየመን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀሚድ አል አዋዲ ለየመን ታይምስ መጽሔት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ እና የመን እ.ኤ.አ በ1999 የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት ባደረጉት ስምምነት መሰረት ዕቀባ የተጣለበትን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የሆነው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሀፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በአዲስ አበባ ላለው ገዥ አካል አሳልፋ መስጠቷን ይፋ አድርገዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የማሰቃየት ህግ መሰረት የየመን ግዴታ ምንድን ነው? የመን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል አሳልፋ በመስጠቷ አርገድ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ተጠያቂ ወንጀለኛ ናት፡፡
ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር የቬይና ሰምምነት፣
እ.ኤ.አ በ1963 የተፈረመውን የቬይና ስምምነትን ያጸደቁ 177 አገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች ማለትም ቡሩንዲ፣ ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ፓላው፣ ሳን ማሪኖ፣ ሴራሊዮን፣ ሶሎሞን አይላንድስ፣ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ሳይፈርሙ ቀርተዋል፡፡ የመን እ.ኤ.አ ኤፕሪል 10/1986 በመፈረም የስምምነቱ አባል ሆናለች፡፡
የቬይና ስምምነት አንቀፅ 36 አንድ የሌላ አገር ዜጋ በወንጀል ወይም በስደተኝነት ክስ ሳቢያ በቁጥጥር ስር ሲውል ወይም ሲታሰር በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ለተወሰኑ መብቶቹ መጠበቅ ምክር ሊሰጠው ይገባል፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ አንቀጽ 36 መንግስታት ከዚህ ቀጥሎ የሚከተሉትን ተግባራት እንዲፈጽሙ ግዴታ ያስገባል፣ 1ኛ) አንድ በቀጥጥር ስር ስለዋለ ግለሰብ ወዲያውኑ ሳይዘገይ ለተቋቋመው ፍርድ ቤት ማሳወቅ ይኖርበታል፣ 2ኛ) በቀጥጥር ስር የዋለው/ችው ግለሰብ መብታቸውን አውቀው እንዲጠቀሙ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ምክር ይሰጣል፣ 3ኛ) ምክር ቤቱ የኮንሱላር ምክር ቤት ባለስልጣኖች እስረኞችን እንዲጎበኝ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡
የመን ሆን ብላ እና እያወቀች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለእንግሊዝ ኤምባሲ እና በሳና ላለው ኮንሱላር ሳታሳውቅ በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል በመስጠቷ እ.ኤ.አ በ1963 የተፈረመውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የቬይናን ስምምነት ጥሳለች፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል፣ “ከቬይና ስምምነት በተጻረረ መልኩ አቶ ጽጌን በቁጥጥር ስር በመዋላቸው እና ከዚህ ቀደምም የሞት ፍርድ የተበየነባቸው በመሆኑ ጉዳዩ የሚያሳስበን በመሆኑ ከየመን መንግስት ባለስልጣኖች ያልተቋረጠ መረጃ እንጠይቃለን“ የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ከእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተሰጠውን መግለጫ የአዞ እንባ ማንባት እንበለው? ይህንን ጉዳይ በእንግሊዝ መንግስት የግዛት ክልል አፈር ላይ የተወለዱትን እና ሌሎችን የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸውን ዜጎች በአንድ ዓይነት መልኩ ያለማስተናገድ አድሏዊ አሰራር ብለን እንፈርጀው?
በሽብርተኝነት ወይም በዓለም አቀፍ ህግ ላይ ጦርነት ማወጅ?
የጸረ ሽብር ጥረቶች በወሮበሎች ላይ የሚደረግ ትክክለኛ አካሄድ ቢሆንም በሽብርተኝነት ላይ ጦርነት ማወጅ በዓለም አቀፍ ህግ ላይ ጦርነት ማወጅ ሊሆን አይገባም፡፡ ህዝቦች ሽብርተኝነትን የመዋጋት ግዴታ አለባቸው፣ እናም ጉዳት እና አደጋ የሚያደርሱትን አድኖ በመያዝ ወደፊት በሰው ልጆች ደህንነት ላይ የሚሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶችን ማክሸፍ እና ሰላምን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ሽብርተኝነትን ለማሸነፍ እን ድልን ለመቀዳጀትም በህግ አስፈጻሚዎች፣ በደህንነት ሰራተኞች እና በውጭ ግንኙነት ባለስልጣኖች መካከል ዘለቄታነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን እንደዚህ ያሉ ጥረቶች በህገወጥ መንገድ ወይም ደግሞ ስምምነቶችን እና የተለመዱትን ዓለም አቀፍ ህጎች በመጣስ መተግበር የለባቸውም፡፡ የዓለም አቀፍ ህግን መከተል ሽብርተኝነትን ማፋጠን ወይም ደግሞ ለተግባራዊነቱ እገዛ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ የህግ የበላይነትን አጥብቆ መያዝ እና መተግበር እንዲሁም የሰለጠነውን ዓለም ህዝቦች ለህዝብ ደንታ ከሌላቸው ከሽብርተኞች እና ከወሮበሎች የመለየት አካሄድ እንጂ፡፡ መንግስታት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ እና የህግ ሂደታቸውንም ለመከታተል ብዙ ዓይነት የህግ ማዕቀፎች እና መሳሪያዎች አሏው፡፡ ንጹሀን ዜጎች አፍኖ የመውሰድ ወንጀል በዓለም አቀፍ ህግ ፊት ታላቅ ወንጀል ነው፡፡ ማንም መንግስት ቢሆን ማንንም ግለሰብ ቢሆን በሌላ አጥቂ መንግስት የማሰቃየት ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ለማወቅ የሚያስችል በቂ መረጃ እያለው አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም፡፡ ይህ ዓለም ህግ በምንም ዓይነት መልኩ ሊሸራረፍ አይችልም፡፡
ስለዓለም አቀፍ የህግ የበላይነት መከበር የሚደረገው ትግል በኃላቀርነት፣ በጨካኝነት፣ በእጦት እና በኢሰባዊነት ላይ የሚደረግ የስልጣኔ ትግል ነው፡፡ ለህግ የበላይነት እንቅፋት እና ኋላቀር መሆን ለህገወጥ ሽብርተኞች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማሳየት ቃል ለገቡት ወሮበላ ቃል አባዮች ጭምር እንጂ፡፡ አሉታ ኮንቲኑዋ! (ትግሉ ይቀጥላል!)
እንደ ህገመንግስታዊ የህግ ባለሙያነቴ ከዩኤስ አሜሪካ ታዋቂ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ከሆኑት ለሁዊስ በራንዲስ ጋር እንዲህ በማለት ከተናገሩት ጋር ከልብ እስማማለሁ፣ “የእኛ መንግስት ጠንካራ ነው፣ ትግህ መምህር ነው፣ ለደግም ይሁን ለመጥፎ ነገር ሁሉንም ህዝብ በእራሱ አምሳል እያደረገ ያስተምረናል… መንግስቱ ህግ የሚጥስ ከሆነ ህግን የመናቅ አስተሳሰብን ያራምዳል፣ እያንዳንዱ ሰው በእራሱ ህግ እንዲሆን ያደርጋል፣ በዚህም መሰረት ስርዓተ አልበኝነት ይነስራፋል፡፡ የደግ ሰዎችን የሞራል ስብዕና እንዲከስም በማድረግ የመጥፎዎችን እንዲጠናከር ያደርጋል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽብረተኝነት ድጋፍ በመስጠት የደግ ሰዎችን የሞራል ስብዕና ይሸረሽራል፡፡ ህገወጥ መንግስት ሽብርተኝነትን ይጋብዛል፡፡“ በማለት በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ የሌላ አገር ሰላማዊ ዜጋን አፍኖ ለሌላ ወንጀለኛ መንግስት አሳልፎ የሚሰጥ የማፈያ ወሮበላ መንግስት በእራሱ ምሳሌነት ሽብርተኛለትን ይፈጥራል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሀምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar