onsdag 2. juli 2014

ግንቦት7 አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለማስፈታት ጥረቱን መቀጠሉን አስታወቀ

ኢሳት ዜና :-የንቅናቄው የስራ አስፈጻሚ አባልና የህዝባዊ እምቢተኝነት ዘርፍ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ የየመን የጸጥታ ሃይሎች አቶ አንዳርጋቸውን በአስቸኳይ ይለቁት ዘንድ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ደብዳቤ ከመጻፍ ጀምሮ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፎችን እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉበትን መንገድ እያመቻቹ ነው።
ግንቦት7 ለየመን ፕሬዚዳንት ፊልድ ማርሻል አብዱ ራቡ ማንሱር ሃዲ እኤአ ሰኔ 30፣ 20014 በጻፈው ደብዳቤ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታፈን ህገወጥ በመሆኑ የየመን መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታው ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችንና መንግስትን የሚተቹትን ሁሉ አስሮ የሚያሰቃይ መሆኑ በአለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ፣ የየመን መንግስት የአቶ አንዳርጋቸውን ተላልፎ ያለመሰጠት መብቱን እንዲያከብር ጠይቋል።
እስካሁን ድረስ የየመን መንግስት በይፋ ለንቅናቄው መልስ ባይሰጥም ከዲፕሎማሲው ማህበረሰብ በተገኘው መረጃ አቶ አንዳርጋቸው አሁንም በየመን የጸጥታ ሃይሎች እንደታገቱ ይገኛሉ።
አቶ አንዳርጋቸውን ለማስፈታት ያስችል ዘንድ በተለያዩ አህጉራት የተቃውሞ ሰልፎችን ለማዘጋጀት የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን አቶ አበበ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአቶ አንዳርጋቸው መታገት ቁጣውን እየገለጸ መሆኑን አቶ አበበ ገልጸዋል
ግንቦት7 ባወጣው መግለጫ ፣ የየመን መንግሥት የአገሪቱን የወደፊት የረዥም ጊዜ ጥቅም አስልቶ አቶ አንዳርጋቸውን በአስቸኳይ ካልፈታወይም የአካል ጉዳት ቢደርስ ወይም ለወያኔ አሳልፎ ቢሰጥ የመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የማይሽር ቂም ውስጥ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል።
ግንቦት 7 በመግለጫው ” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ተላልፎ ቢሰጥ በአካሉና በሕይወቱ ለሚደርሰው ሁሉ የወያኔ ፋሽስቶችን ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ከአሁኑ እናስጠነቅቃለን። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስና ሕይወት ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቃት ለነፃነታቸው ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆኑ እልፍ አዕላፍ ታጋዮችን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለንም። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስ እና ሕይወት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ሁሉ በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ቦታ የምንበቀል መሆኑንና ብዙ የወያኔ ሹማምንት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሚሆን እንዲያውቁት እናስጠነቅቃለን” ብሎአል።
ከአቶ አበበ ቦጋለ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ ይቀርባል። በአቶ አንዳርጋቸው ዙሪያ የየመንን የውጭ ጉዳይ መልስ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሰካልንም

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar