mandag 30. juni 2014

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን ባለሥልጣናት እገታ ላይ መሆኑን በማስመልከት የወጣ መግለጫ


ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቷል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን የጉዞው መዳረሻ አልነበረም፤ ከየመን ጋርም የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ አልነበረውም። የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አግቶ ለአንድ ሰዓት እንኳን ለማቆየት ምንም ምክንያት የለውም። በዚህም ምክንያት ያለአግባብ የታገተብን የንቅናቄያችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። እንዲያውም የየመን ባለስልጣናት አምባገኑን ወያኔ ለመርዳት ባለው ፍላጎት ሳቢያ መሪያችንን አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ፤ ዝግጁነቱንም በተግባር ያሳየ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። የየመን መንግሥት ከዘረኛውና ፋሽስታዊው ወያኔ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋይ መሪያችን ላይ እየፀመ ያለውን ደባ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የንቅናቄዓችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል።
ትግላችን መስዋትነት እንደሚያስከፍል እናውቃለን። ከዚህ በፊትም ብዙ ጓዶቻችን መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ወደፊትም ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። አሁን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰውና ወደፊትም ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ምሬታችን በማብዛት፣ ቁጣችንና ዝግጁነታችን ከማጠንከር በስተቀር ቅንጣት ታክል እንኳን ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ እንደማያደርገን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለአባሎቻችንና ለደጋፊዎቻችን ሁሉ መግለጽ እንወዳለን።
መንግሥታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ኢትዮጵያና የመን ግን ጎረቤታሞች ሆነው መቆየታቸው የማይቀር ነው። የየመን መንግሥት የወያኔ እድሜ አጭር መሆኑ የተገነዘበ አይመስልም። በዚህም ምክንያት የየመን መንግሥት የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የቆየ ወዳጅነት የሚያደፈርስ እርምጃ ወስዷል። የየመን መንግሥት የየመንን የወደፊት የረዥም ጊዜ ጥቅም እንዲያሰላና ያገተብንን መሪ በአስቸኳይ እንዲፈታ እንመክራለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመሪያችን ላይ ጉዳት ቢደርስ ወይም ለወያኔ አሳልፎ ቢሰጥ የመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የማይሽር ቂም ውስጥ የምትገባ መሆኑን የየመን መንግሥት አውቆ በጥብቅ እንዲያስብበት እናስጠነቅቃለን።
በየመን መንግሥት አልሰማ ባይነት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ተላልፎ ቢሰጥ በአካሉና በሕይወቱ ለሚደርሰው ሁሉ የወያኔ ፋሽስቶችን ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ከአሁኑ እናስጠነቅቃለን። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስና ሕይወት ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቃት ለነፃነታቸው ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆኑ እልፍ አዕላፍ ታጋዮችን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለንም። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስ እና ሕይወት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ሁሉ በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ቦታ የምንበቀል መሆኑንና ብዙ የወያኔ ሹማምንት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሚሆን እንዲያውቁት እናስጠነቅቃለን ።
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar