torsdag 20. august 2015

“በደረሰብኝ በደል ወደ አርበኞች ግንባር ገብቻለሁ” – የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩ ተጠርጣሪዎች

ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው
  • 330
     
    Share
ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው
ሰላማዊ ትግል የማያዋጣ በመሆኑ ከግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባር ጋር በመቀላቀል መንግሥትን በትጥቅ ትግል መገልበጥ እንዳለባቸው በማመን ወደ ኤርትራ ሊሻገሩ ሲሉ፣ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች፣ ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል እየሄዱ እንደነበር ለፍርድ ቤት የእምነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ የተለያየ ኃላፊነት የነበራቸው ተከሳሾቹ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋ፣ ፍቅረማርያም አስማማውና የአርበኞች ግንባር አባል መሆኑን የገለጸው ደሴ ካሳዬ ሲሆኑ፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት ጉዳዩን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡
ሁሉም ተከሳሾች ድርጊቱን መፈጸማቸውን ነገር ግን ጥፋተኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ብርሃኑ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው፣ ‹‹አገሬ ጨቋኝ ሥርዓት ውስጥ ስላለች ይኼንን ለመታገል ግንቦት ሰባት ከተባለ ነፃ አውጭ ድርጅት ጋር ለመገናኘት ጉዞ ጀምሬያለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፡፡ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም፤›› ብሏል፡፡
ኢየሩሳሌምም ድርጊቱን መፈጸሟን አምና ጥፋተኛ አለመሆኗን ገልጻለች፡፡ ሦስተኛው ተከሳሽ ፍቅረ ማርያም ደግሞ ዴሞክራሲ ለማስፈን ድርጊቱን መፈጸሙን ገልጾ፣ ጥፋተኛ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
ትግሪኛ እንጂ አማርኛ እንደማይሰማ የገለጸው አራተኛ ተከሳሽ ችሎቱ አስተርጓሚ እንዲቀርብለት ካደረገ በኋላ በሰጠው የእምነት ቃል፣ ‹‹በደረሰብኝ በደል ወደ አርበኞች ግንባር ገብቻለሁ፡፡ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፡፡ ነገር ግን ጥፋተኛ አይደለሁም፤›› በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ተከሳሾቹ ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነው ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ በመቃወማቸው ምክንያት፣ ዓቃቤ ሕግ ጥፋተኛ ስለመሆናቸው የሚያስረዱለትን ምስክሮች ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያሰማ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/9696#sthash.mZzJmW7B.dpuf

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar