mandag 12. mai 2014

የወያኔ መንግስት በዩኒቨርስቲዎች ስለተከሰተው ተቃውሞ ትንፍሽ ሳይል መሰንበቱ ያሳስባልና እናስተውል!

እንጠንቀቅ! ይህች አገር የብልፅግና ተስፋና የመናጋት አደጋ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች

እናስተውል! ስልጡን ጎዳና ከያዘች የሚያስቆመን አይኖርም፤ ከተናጋችም መመለሻ የለንም
መንግስት፣ በዩኒቨርስቲዎች ስለተከሰተው ተቃውሞ ትንፍሽ ሳይል መሰንበቱ ያሳስባል
ተቃውሞውና ረብሻው የብሄር ብሄረሰብ ቅኝት መያዙም፣ የዘመናችንን አደጋ ያመለክታል
በአንድ ቀን ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸው 9 ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች መታሰራቸው ያሸብራል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ ጎላ ጎላ ያሉ ችግሮችንና ውዝግቦችን ተመልከቱ። አንዳንዶቹ፣ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዙ ቀውሶች ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ፤ ከጎሰኝነት ወይም ብሔረተኝነት ጋር የተቆራኙ። የብዙዎቹ መነሻ ግን ጭራና ቀንዱ የማይታወቅ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ነው፡፡ የሦስቱን ቀውሶች ግንኙነታቸውን ለማየት፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስን በማንሳት ልጀምር። 
“ጥቃቅንና አነስተኛ” በሚል ተደራጅተው ከመንግስት ብድር እየወሰዱ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል። ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ በርካታ ስደተኞች ገና አንድ አመት እንኳ ሳይሞላቸው ተመልሰው ለመሄድ በረሃውንና ባህሩን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ምን ማለት ነው? መንግስት የስራ እድል ለመፍጠር በሚል ለብድርና ለድጐማ የሚያወጣው ገንዘብ በከንቱ እየባከነ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ለጊዜው ከበቂ በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት የሚችሉ ግድቦች ተገንብተው እያሉ፤ ነጋ ጠባ ኤሌክትሪክ የሚቋረጥ መሆኑስ ምን ሊባል ነው? ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ መንግስት የያዘው ቢዝነስ የትም አገር አይሳካም፡፡ እንዲያውም የግል ኢንቨስትንም ያሰናክላል፡፡ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ብቻ አንድ የግል ፋብሪካ በአመት 200 ሚ. ብር ኪሳራ እንደሚደርስበት በመንግስት ሚዲያ ጭምር ሲገለፅ፣ የችግሩ ስፋት ምን ድረስ እንደሚዘልቅ አስቡት። ከእጥፍ በላይ ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የኢንዱስትሪ ምርት፤ ብዙም ፈቅ አለማለቱስ? በየአመቱ በመቶ ሺ እና በሁለት መቶ ሺ የሚቆጠር የስራ እድል እንደተፈጠረ በሚነገርባት በአዲስ አበባ፤ አሁንም የብዙ ስራ አጦች ከተማ የመሆኗ እንቆቅልሽስ? የቅይጥ ኢኮኖሚ ባህርይ ነው፡፡ “ድሆችን ለመደገፍና ሰፊውን ህዝብ ለመጥቀም ወይም አገርን ለማልማት” በሚሉ ሰበቦች መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ እየገነነ ሲመጣ፣ ሃብትን ከማባከን ያለፈ ውጤት አይኖረውም፡፡ በዚያውም ሙስናን ያስፋፋል፡፡  
አምናና ዘንድሮ በጉልህ ከታዩት ክስተቶች መካከል፣ የሙስና ክሶች ትልቅ ቦታ ነበራቸው። ከአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ያ ሁሉ ሃላፊ ሲታሰር… ከዋና ዳሬክተርና ከምክትል ጀምሮ፣ የቅርንጫፍ መስሪያ ቤት መሪዎችና ዋና ዋና የክፍል ሃላፊዎች በሙስና ሲከሰሱ ምን ማለት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። በቅይጥ ኢኮኖሚ ውስጥ፤ የሙስና እድል በስፋትና በቀላሉ የሚገኝ መሆኑን ይጠቁማል። ስንዘረዝር ውለን ስንዘረዝር ልናድር እንችላለን፡፡ ግን ጠቅለል ልናደርገው እንችላለን “የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ” በሚል ስያሜ፡፡ አስገራሚው ነገር፣ ቀውሱ የኛ አገር ብቻ አይደለም።
 ኢትዮጵያን የመሰሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሻል ያሉትንም አገራት፣ እንዲያውም ወደ ብልፅግና ደጃፍ የደረሱትንም ጭምር፣ ከዚያም አልፎ የበለፀጉ ተብለው የሚታወቁትንም አገራት እየተፈታተነ የሚገኝ የ21ኛው ክ/ዘመን ልዩ ቀውስ ነው – የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ። ለወራት ሳያቋርጥ የሚካሄድ የስራ ማቆም አድማ በዱላና በገጀራ ማጀብ የተለመደባት ደቡብ አፍሪካን ተመልከቱ። በጎማ ጭሽ የታፈኑና በድንጋይ ክምር የታጠሩ የቬኒዝዌላ ጎዳናዎችንም እይዋቸው። የነዳጅ ገንዘብ ተገኘ ተብሎ መድረሻው ያልታወቀ የባቡር መስመር መዘርጋትና የዩፎ ሙዚዬም መገንባት የተጀመረባት ብራዚልም ከዚሁ ተርታ የምትመደብ ናት። ለምልክት ያህል አንድ ዩፎ ሳይኖር፤ ለዩፎ ሙዚየም ግንባታ ሃብት ማፍሰስ እብደት ነው? የብራዚል መንግስት ለእነዚህና ለበርካታ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ብዙ ሃብት አፍስሷል፡፡ ግን እብደት አይደለም፡፡ የቅይጥ ኢኮኖሚ ባህርይ ነው፡፡ መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ ከገነነ ብዙ ብዙ ጉድ ይታያል፡፡  75 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ኢራን ውስጥ፤ በየወሩ የ15 ዶላር ድጎማ ለመውሰድ 77 ሚሊዮን ሰዎች መመዝገባቸውም ሊያስገርም አይገባም። የቀውሱ አካል ነው – መንግስት በየአመቱ ከ65 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጎማ ይሰጣል። 
በናይጄሪያ፣ ከነዳጅ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ገቢ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው (ከሃያ ቢሊዮን ዶላር በላይ) የት እንደገባ አይታወቅም በማለት የገንዘብ ሚኒስትሩ መናገራቸው ሳያንስ፤ ሚኒስትሩ ብቃት የላቸውም ተብለው መባረራቸውን አስቡት፡፡ ሌላዋ ሚኒስትር ደግሞ በሹመታቸው ማግስት 3 ሚሊዮን ዶላር (60 ሚ.ብር ገደማ) በጀት በመመደብ ሁለት የቅንጦት መኪኖችን አስገዝተዋል፡፡ 
ግብፅም የራሷን ጉድ ይዛለች፤… በአገሪቱ ውስጥ ያለው የመንግስት ተቀጣሪ ወይም በላተኛ ከ7 ሚሊዮን ይበልጣል – ከሰራተኛው ይልቅ በላተኛው የበዛባት አገር ልትሏት ትችላላችሁ። እንዲያም ሆኖ፤ እነዚህ “ጉደኛ” አገራት እንደ ጉድ መታየት የለባቸውም። ያን ያህልም ከሌሎቹ አገር የተለየ ነገር አልሰሩም። የመጠንና የደረጃ ልዩነት ነው እንጂ፤ ከእነዚህ ሻል በሚሉት አገራትም መንግስታት ኢኮኖሚውን ማቡካታቸውና ሃብት ማባከናቸው አልቀረም። ለነፋስ ተርባይን ድጎማ፣ የባህር ዳርቻ ላይ ቪላ ለሚገነቡ ድጎማ፣ አመት ሁለት አመት ስራ ለሚፈቱ ድጎማ… ይሄ በአውሮፓ አገራት የተለመደ ነው። 
ከአምስት ከስድስት አመት በፊት፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ ከመፈንዳቱ በፊት፣ አውሮፓ ውስጥ ሃይለኛ ዘመቻ ይካሄድበት የነበረው ትልቅ የኢኮኖሚ ጥያቄ ምን መሰላችሁ? በሳምንት ውስጥ መደበኛው የስራ ጊዜ 40  ሰዓት ነው፡፡ ይህንን ወደ 35 ወይም ወደ 30 ልንቀንሰው ይገባል የሚል ነበር ትልቁ አጀንዳ። እንደቁም ነገር ጥያቄው መነሳቱ ሳያንስ፤ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱ! በአንድ በኩል ለድጐማ ገንዘብ እንደዘበት መርጨት በሌላ በኩል ደግሞ የስራ ሰዓትን መገደብ! የአውሮፓ መንግስታት በእዳ ክምር መዋጣቸው ምን ይገርማል? በእርግጥ ሁሉም የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ናቸው ማለት አይደለም። ግን ምን ዋጋ አለው?  ከሌሎች አገራት ሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጀርመን፣ እንግሊዝ … አሜሪካም ጭምር፤ ከተመሳሳይ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ የፀዱ አይደሉም። 
ከመቶ አመታት በፊት ከጠቅላላ የሕዝቡ አመታዊ ገቢ ውስጥ በተለያዩ የታክስ አይነቶች አማካኝነት በመንግስት የሚወሰደው 10 በመቶ አይሞላም ነበር። ዛሬ ብዙዎቹ የአውሮፓ መንግስታት፤ ከሕዝቡ አመታዊ ገቢ ውስጥ 50 በመቶ ገደማ ይወስዳሉ። የእንግሊዝም ወደዚያው ተጠግቷል። የአሜሪካም 40 በመቶ ደርሷል። ከዚያስ? አብዛኛው ሃብት የሚውለው ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የድጎማ አይነቶች ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ፣ ልጅ ያላት አንዲት ወጣት፣ በአስተማሪነት ወይም በሽያጭ ሰራተኛነት ከመቀጠር ይልቅ፣ ቤቷ ተቀምጣ ድጎማ ብትወስድ የተሻለ ገቢ ታገኛለች። ቢያንስ ቢያንስ በወር 2ሺ ዶላር ታገኛለች – ከሽያጭ ሰራተኛ ጋር የሚቀራረብ ገቢ መሆኑ ነው። በአንዳንድ ግዛቶች ደግሞ እስከ 4ሺ ዶላር የሚደርስ ድጎማ ልታገኝ ትችላለች። ስራ ልግባ ብትል፣ ድጎማው ይቀርባታል። ገቢዋ ይቀንሳል፡፡ ስራ መጀመር ጉዳት ሲሆን ይታያችሁ፡፡ ኢኮኖሚ ውስጥ መንግስት ገናና እየሆነ በሄደ ቁጥር፣ አስገራሚ ጉዶች እየተበራከቱ ይመጣሉ፡፡  
በበርካታ የአውሮፓ አገራትም፣ ገበሬዎች ድጎማ የሚከፈላቸው ምርታማ እንዲሆኑ አይደለም። ማሳቸውን ለእርሻ ምርት የማይጠቀሙበት ከሆነ ነው ድጎማ የሚከፈላቸው፡፡ ብዙ የማይታረስ ማሳ ያለው ገበሬ ብዙ ድጎማ ያገኛል ያለ ስራ ስለተቀመጠ። ታዲያ እያንዳንዱን ማሳ እየመረመሩና እየለኩ የድጎማ ክፍያ የሚወስኑ መዓት ቢሮክራቶችም እንዲሁ ክፍያ ይወስዳሉ። ለአንድ ገበሬ 6ሺ ዶላር ክፍያ ለመፈፀም፤ ከ3ሺ ዶላር በላይ የስራ ማስኬጃ ወጪ ያስፈልገዋል – ለቢሮክራቱ፡፡ መንግስታት ኢኮኖሚ ውስጥ እጃቸውን ሲያስገቡ፤ ቀስ በቀስ ነገረ ስራቸው ሁሉ የቅዠት አለም እየመሰለ ይመጣል። 
በኢትዮጵያም ቢሆን፤ የግብርና ምርታማነትን ያሳድጋል እየተባለ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚመደበውን  በጀት ተመልከቱ፡፡ ዛሬ፤ ግማሽ ያህሉ በጀት፣ ለምርታማነት ሳይሆን ለእርዳታና ለድጎማ የሚውል ሆኗል። የሆነ ሆኖ፤ መንግስታት ስራዬ ብለው የዜጎችን ሃብት በእልፍ መንገድ ማባከንን ከተያያዙት፤ እዳ መቆለሉ፣ ሙስና መስፋፋቱ፣ ኢንቨስትመንት መንቀራፈፉ፣ የሰራ እድል መጥፋቱ፣ ኑሮ መክበዱ የማይቀር ነው። የቅይጥ ኢኮኖሚ የቀውስ አዙሪት!
ደረጃውና መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ በእንዲህ አይነት ቀውስ ያልተነካ አገር የለም፡፡  አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ ተዘፍቀውበታል – ሻል ያሉትም ግን አላመለጡም። ለምን ቢባል፣ ደረጃውና መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ ሁሉም አገራት በቅይጥ ኢኮኖሚ አዙሪት ውስጥ ገብተዋል። መንግስት ጠቅላላ ኢኮኖሚውንና ሁሉንም ንብረት የሚቆጣጠርበት የሶሻሊዝም ስርዓት ዛሬ ብዙም የለም፤ ድህንነትንና ረሃብን ሲፈለፍል ቆይቶ በመጨረሻ ፈራርሷል። ነገር ግን፤ ብልፅግናንና ምቾትን የሚያጎናፅፍ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የሰፈነበት የካፒታሊዝም ስርዓትም በጉልህ አይታይም። መንግስት ከዜጎች ገቢ ላይ ግማሽ ያህሉን ዘግኖ የሚወስድ ከሆነ ምኑ ነፃ ገበያ ይሆናል? የለየት ሶሻሊዝምም አላዋጣም፤ የተሟላ ካፒታሊዝምም አልተፈለገም። የሁለቱ ቅልቅል ቅይጥ ኢኮኖሚ የነገሰበት ዘመን ነው  – 21ኛው ክፍለዘመን። ከዚሁም ጋር ነው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩ ቀውስ የተፈጠረው – በየአገሩ እንደምናየው። 
ችግሩ ምን መሰላችሁ? ለቀውሱ መፍትሄ አልተገኘለትም። ግራ የሚያጋባው ነገር ምን መሰላችሁ? መፍትሄ ፍለጋ መጣጣር እንኳ እየቀረ ነው። ግን አለምክንያት አይደለም፡፡ ሶሻሊዝምን እንደገና መሞከር፣ የኢኮኖሚ ውድቀትን መጋበዝና እድሜን ማሳጠር ነው። ግን ደግሞ፤ “ሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ፤ ድሃውን ሕብረተሰብ ለመደገፍ፤ የአገር ለማልማት እያንዳንዱ ሰው መስዋእትነት መክፈል አለበት፡፡ ከራስ ጥቅም በፊት የሌሎችን ጥቅም አስቀድሞ” የሚለው የሶሻሊዝም መፈክር ዛሬ ድረስ አልተሻረም። ብዙዎቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ዛሬም ድረስ የሚያምኑበት መፈክር ነው። 
በተቃራኒው መስዋዕትነትን የሚያስቀር የካፒታሊዝም መርህን አይፈልጉትም። ራስን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ (ለምሳሌ “ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን” በሚል ሰበብ የደሞዝህ 50 በመቶ ያህል በመደበኛ ታክስና በቫት ለመንግስት ማስረከብ) አልያም በሌሎች መስዋዕትነት ተጠቃሚ ለመሆን መሞከር (ለምሳሌ ድጎማ ይሰጠኝ፤ የሃብት ክፍፍል ይካሄድ ብሎ መጠየቅ፣ ማመፅና ሕግ ማውጣት) …በካፒታሊዝም ነውር ነው፤ ከዚያም አልፎ ወንጀል ይሆናል መዘረፍንና መዝረፍን ስለሚከለክል ብዙዎቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ካፒታሊዝምን አይፈልጉትም። “በራስ ጥረት የራስህን ኑሮ የማሻሻል ነፃነት፤ የንብረት ባለቤትነት መብት…” የሚባሉ የነፃ ገበያ መርሆች እንደ ቅዱስ ሃሳብ አይታዩም። ግን ደግሞ፤ ለየትኛውም መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሕልውና ጉዳይ እየሆነ ስለመጣ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የነፃ ገበያ ስርዓትን ይፈልጉታል። ያለ ነፃ ገበያ፣ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ አይቻልማ። እና ምን ተሻለ? 
ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች በሶሻሊዝም መፈክር ያምናሉ፤ እምነታቸውን መለወጥና ማስተካከል የሞት ሞት ሆኖ ይሰማቸዋል። የካፒታሊዝምን ብልፅግና ደግሞ ይፈልጋሉ፤ የሕልውና ጉዳይ ሆኖባቸዋል። ስለዚህ ሁለቱንም በማቀላቀል ዘመኑን የቅይጥ ኢኮኖሚ ዘመን አደረጉት፡፡ እናም በቅይጥ ኢኮኖሚ የቀውስ አዙሪት ውስጥ ከመሽከርከር ውጭ ምንም መፍትሄ አይታያቸውም። ለቀውሱ መፍትሄ ለመፈለግ መጣጣር ያቆሙትም በዚህ ምክንያት ነው። ገዢ ፓርቲዎችና ባለስልጣናት በየቦታው የቀውስ ምልክቶች ጉዳዩ በፍርሃት ከመባነን ውጭ ምንም መፍትሔ አማራጭ አይገለጥላቸውም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ደግሞ፤ “አለሁ፤ አለን” ከማለት ውጭ መፍትሔ ለማምጣት በመሪነት የመሰለፍ አቅም አይኖራቸውም። በአረብ አገራትም ሆነ በዩክሬንና በታይላንድ፣ በቬኒዝዌላም ሆነ በአውሮፓ አገራት፣ አብዛኞቹ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው ያልቻለው በዚህ ምክንያት ነው – የቅይጥ ኢኮኖሚ ሰለባ ናቸው።
ግን ደግሞ፤ “መፍትሄ የሌለው ችግር ነው” ብሎ አርፎ መቀመጥ አይቻልም። ከድህነት የሚያወጣና ከዝርፊያ የራቀ የብልፅልግና ተስፋ፣ ከሰው ተፈጥሮ ሊነጠል የማይችል መሰረታዊ ፍላጎት በመሆኑ፤ በእንጥልጥል ሲቀር ሁሉም ሰው ዝም ይላል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ከአፈናና ከፍርሃት ተገላግሎ በነፃነት የማሰብና የነፃነት አየርን የመተንፈስ ምኞት እንዲሁም፤ ከውርደትና ከአገልጋይነት በመላቀቅ አንገትን ቀና አድርጎ የእኔነት ክብርን ተላብሶ የሕይወትን ትርጉም የማጣጣም ፍላጎት፤ መሰረታዊ የሰው ልጅ ቅዱስ ፍላጎቶች ናቸው። 
ከቅይጥ አስተሳሰብ በሚመነጩ፣ ቅይጥ ፖለቲካ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚና ቅይጥ መንፈስ የተነሳ፤ ሶስቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች (የነፃነት፣ የብልፅግናና የእኔነት ክብር ፍላጎቶች) በእንጥልጥል ሲቀሩ፤ አብዛኛው ሰው እስከ ወዲያኛው በዝምታ አይቀጥልም። እምንነቱ በግልጽ የማይታወቅ “ለውጥ” ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አይጠፉም። መፍትሄውን ባያውቁት እንኳ፣ በአንዳች ተዓምር መፍትሄ ይገኝ ይሆናል ብለው ድምፃቸውን የሚሰሙ ይኖራሉ። 
ግን ምን ዋጋ አለው? ከሰው አእምሮና ከጥረት የሚገኝ መፍትሔ እንጂ፤ በአንዳች ተዓምር የሚመጣ መፍትሄ የለም። ይሄኔ ነው፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወደ ሌሎቹ ሁለት የዘመናችን ቀውሶች የሚመነዘረው – የጎሰኝነት (የብሔርተኝነት) ቀውስ እና የሃይማኖት አክራሪነት ቀውስ። በሌላ አነጋገር፤ ከቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው የዩክሬን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ  ብዙም ሳይቆይ በዘር እና በሃይማኖት የተሰባሰቡ ቡድኖች የገነኑ የመጡት በአጋጣሚ አይደለም። 
የሊቢያና የግብፅ፣ የሶሪያና የኢራቅ፣ የሴንትራል አፍሪካና የናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካና የኮንጎ ግጭቶችና ትርምሶች… በሙሉ ከቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የተሳሰሩ ቢሆኑም ውለው አድረው የጎሰኝነት ወይም የብሔረተኝነት ቀውስ እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁት በአጋጣሚ አይደለም። በአጭሩ፤ ሶስቱ ቀውሶች፤ (የቅይጥ ኢኮኖሚ አዙሪት፣ የጎሰኝነት (የብሔረተኝነት) አባዜ እና የሃይማኖት አክራሪነት)፤ አለምን ከዳር ዳር ያዳረሱ የ21ኛው ክፍለዘመን መለያ ቀውሶች ናቸው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ቀውሶች ውጭ አይደለችም። ከሌሎቹ አገሮች አትለይም።
ቀውሶቹን ለመከላከል ወይም ለመግታት እያንዳንዱ አገር ውስጥ በሚከናወን ዝግጅትና ጥረት ነው ልዩነት የሚመጣው። የኛ አገር ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። ዝግጅትና ጥረት ሊከናወን ይቅርና፤ አደገኛዎቹን ቀውሶች በቅጡ መገንዘብም ለብዙዎች አቀበት ሆኖባቸዋል። የቀውሶቹን ምንነትና አደገኛነታቸውን የተገነዘብን ጊዜ ግን፤ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ለማወቅ አይከብደንም። 
ትልቁ ሃላፊነት የመንግስትና የገዢው ፓርቲ ነው – ሦስቱ የሰው መሰረታዊ ፍላጎቶችን (የነፃነት፣ የብልፅግናና የእኔነት ከብር ፍላጎቶችን) የሚያሰናክሉ የአፈና፣ የቁጥጥርና የውርደት ድርጊቶች እንዳይባባሱ መጠንቀቅ፤ ቀስ በቀስም እየቀነሱ እንዲሄዱ በትጋት መጣር ይገባቸዋል። ለራሳቸው ሕልውናም ይበጃል። ለምሳሌ ጋዜጠኞችንና ፀሐፊዎችን በገፍ ከማሰር፤ ያንንም ያንንም በአሸባሪነት ከመፈረጅ፣ ጥይት ለመተኮስ ከመቻኮል ቆጠብ ማለት! በሌላ በኩልም፣ የቢዝነስ ሰዎችን ማንገላታትና ማብጠልጠል ይብቃቸው፡፡ በዘፈቀደ  ህጎችና መመሪያዎችን እየፈለፈሉ የሰዎች ምርትና ንብረት ላይ ፈላጭ ቆራጭ መሆን ይቅርባቸው። የፓርላማና የክልል ምክር ቤት ምርጫ 99.9 በመቶ አሸነፍኩ የሚባለው ጨዋታ፤ ከአመት አመት ተረት ሆኖ እንዲቀር ዘዴ ይፍጠሩለት። 
ዜጎች፣ ምሁራን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም ሃላፊነት አለባቸው። በቅድሚያ ግልፅ መፍትሄ በማበጀት እንጂ፤ በአንዳች ተዓምር መልካም ለውጥ እንደማይመጣ በመገንዘብ፤ ቀውሶችን ከማባባስ መቆጠብና መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ወይም በሃይማኖት ተከታይነት ምክንያት የሚወረስ የጋራ አእምሮና አካል የለም። እናም፣ በጅምላ “ትግሬ ተገለለ፤ አማራ ተሰደበ፤ ኦሮሞ ተፈናቀለ … ምናምን” በማለት ጭፍንነትን ከማራገብ እንራቅ! ኢህአዴግን ለመቃወምና ለመተቸት እልፍ ትክክለኛ ምክንያቶች ይኖራሉ። ኢህአዴግን ለመቃወም ሲባል፣ አክራሪነትንና አሸባሪነትን ወይም ጎሰኝነትንና ብሔረተኝነትን መደገፍ ይቅርና በዝምታ ማለፍም ነውር እንዲሆን እናድርግ።
መንግስትና ገዢው ፓርቲ፤ እንዲሁም ዜጎችና ምሁራን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች የየራሳቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ከተሳናቸው፤ ወይም ፈቃደኛ ካልሆኑ፤ ይባስ ብለው በጭፍን የእልህ ስሜት የሚቀጥሉ ከሆነስ? አትጠራጠሩ፤ ያኔ በዘር የተቧደኑ የጎሰኝነት (የብሔረተኝነት) መዓተኞችና የሃይማኖት አክራሪ ሽብርተኞች እግር ስር እንወድቅና መመለሻ ወደሌለው የጥፋት ቀውስ እናመራለን።
addis admas

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar