fredag 9. mai 2014

የህወሃት ደጋፊ ኦህዴዶች ከተቀረው የኢህዴድ አባላት ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ታወቀ


 ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባና የዙሪያዋ ኦሮሚያ የተቀናጀ የጋራ ልማት መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን ከስድስት በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በተቀጣጠለው ተቃውሞ ምክንያት የኦሮሞ ተማሪዎች በአጋዚ ልዩ ኃይልና በፌዴራል ፖሊስ አባላት መገደላቸው ኦህዴድን ለሁለት ሊከፍል የሚችል ክስተት ሆኖ ብቅ ማለቱን ምንጮች ገልጸዋል።
በኦህዴድ ድክመት ምክንያት ስለማስተር ፕላኑ አስቀድሞ ሕዝቡ ተወያይቶበት ውሳኔ ሳይሰጥበት ወደ ትግበራ መገባቱ የመጀሪያውና ትልቁ ስህተት ነው ያሉት ምንጮቻችን ፕላኑ ወደ ትግበራ ሲተላለፍ በርካታ የኦህዴድ አባላትና አንዳንድ ከፍተኛ ካድሬዎች ጭምር ደስተኛ እንዳልነበሩ ጠቅሰዋል።
ብዙዎቹ የኦህአዴድ አባላትና ካድሬዎች ዘንድ ኦሮሚያ ከአዲስአበባ ማግኘት ያለባት ጥቅም ሳይረጋገጥ እንደገና በአዲስአበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን ወደ አዲስአበባ ለማካለል የማሰቡ ጉዳይ እንዳልተዋጠላቸውና በዚህም ምክንያት በየመድረኩ ቅሬታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን፣ በአንጻሩ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሩ ይህንን ቅሬታ በመከላከል ሲያዳፍንና ቅሬታ አቅራቢዎችን በኦነግነትና በጠባብነት እየፈረጀ ሲያሸማቅቅ መኖሩን ያስታወሱት ምንጫችን፣ በዚህ ምክንያት በኦህዴድ ውስጥ በሚታይ መልኩ ከአዲስአበባ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ጥቅም መጠበቅና መረጋገጥ አለበት በሚል እና ይህን ጥያቄ በሚቃወሙ የህወሃት ደጋፊ የኦህዴድ አመራሮች መካከል ግልጽ ሽኩቻ እየታየ መሆኑ ድርጅቱን ለሁለት ሊሰነጥቀው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኦህአዴድ ከፍተኛ አመራሮች ለችግሩ መንስኤ የኦነግ አባላትና የውጪ ኃይሎች ናቸው በሚል ውጫዊ ምክንያት እየደረደሩ መሆኑ ውስጣዊ ችግራቸውን ለመሸፋፈን ሆን ብለው ያደረጉት ነው ያሉት ምንጫችን፣ የውስጥ ሽኩቻቸው አድጎ የደሃውን ገበሬ ልጆች ሕይወት መቅጠፉ እጅግ አሳዝኝ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል፡፡
ሰሞኑን ከስድስት በላይ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በአምቦ፣ በነቀምት፣ በሐረማያ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በመደወላቡ፣ በተቀሰቀሰው አመጽ ወደ70 የሚጠጉ ተማሪዎች መገደላቸውን የተለያዩ ምንጮች ሲገልጹ ፣ መንግስት የሟቾችን ቁጥር ወደ 10 ዝቅ በማድረግ ሰዎች መሞታቸውንና መንስኤውም ጸረ ሰላም ኃይሎች መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዘጠነኛ መሪ ፕላን የአገልግሎት ዘመኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ አሥረኛውመሪ ፕላን በመዘጋጀት ላይ ሲሆንየመሪ ፕላን ዝግጅቱ የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያየሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን ማለትም ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ መናገሻ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ገላን፣ ዱከምና ሰበታበዚሁ እንዲካተቱ ተደርጎ ፕላኑ እየተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ቀጥሎአል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar