mandag 19. mai 2014

‹‹ሱዳን ከማን ጋር እንደምትነግድ በሉዓላዊነቷ ላይ ማዘዝ አንችልም፤››


ኢትዮጵያ በተዘዋዋሪ መሸጡ አያሳስበኝም አለች
የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ለመግዛት ከተስማማው አንድ መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ መጠኑ ይፋ ያልተደረገ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ ዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ኩባንያን ዋቢ ያደረገው ኢነርጂ ቢዝነስ ሪቪው ድረ ገጽ ባስነበበው ዘገባ መሠረት፣ በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል ከከሰላ ግዛት ተነስቶ ወደ ኤርትራ የሚዘረጋ የ45 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋት ተጀምሯል፡፡ 
ከሁለት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የህዳሴው ግድብ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ግብፅና አሁን ደግሞ ኤርትራ ተጠቃሚ ይሆኑበታል ተብሎ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ኃይል ማሰራጫ መስመርን በጋራ ማስመረቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሱዳን ወደ ኤርትራ ልትሸጥ ዝግጅት መጀመሯን በማስመልከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የኃይል ሽያጭ ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህም ሆኖ ሱዳን ከኢትዮጵያ የገዛችውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማን እንደምታስተላልፍና ከማን ጋር እንደምትነግድ ለመቆጣጠር አንችልም፣ ሉዓላዊነቷም አይፈቅድልንም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሱዳን ከማን ጋር እንደምትነግድ በሉዓላዊነቷ ላይ ማዘዝ አንችልም፤››
(ከሪፓርተር ጋዜጣ የተወሰደ)

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar