søndag 2. august 2015

አምባሳደሮች ግምገማዊ ሥልጠና ሊገቡ ነው

7418ed7799fa2ae466a00adefbef5112_L



  • 603
     
    Share


የአምባሳደሮችና የቆንስላ ጄኔራሎች ግምገማዊ ሥልጠና ከነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ በሚያካሂደው ግምገማዊ ሥልጠና ለመካፈል በ46 አገሮች የሚገኙ ዲፕሎማቶች በቅርቡ አዲስ አበባ መግባት ይጀምራሉ፡፡
በሚካሄደው ግምገማዊ ሥልጠና አምባሳደሮች፣ ቆንስላ ጄኔራሎችና ዲፕሎማቶች በዓመቱ ውስጥ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስክ ያከናወኗቸውን ሥራዎች ይገመገማሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዲፕሎማቶቹ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ ተወያይተው፣ በቀጣዩ በጀት ዓመት ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መመርያ ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አምባሳደሮቹ በኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ መርህ ወደ አገር እንዲገቡና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቹላቸው ባለሀብቶች ያከናወኗቸውን ሥራዎች ከመዳሰሳቸውም በተጨማሪ፣ ባለሀብቶቹ ያጋጠሙዋቸው አሉታዊና አወንታዊ ጉዳዮች ይታያሉ ተብሏል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ትኩረት ካደረገችባቸውና በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት የቻይና፣ የቱርክ፣ የህንድና የብራዚል በተጨማሪ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ከእነዚሁ አገሮች የተወሰኑ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
አምባሳደሮቹ በእነዚህ አገሮች ኩባንያዎች ፍላጎትና እንዲሟሉ በሚፈልጓቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አዳዲስ መዳረሻ ሊሆኑ በሚችሉ አገሮች ላይ ሊካሄድ ስለሚገባው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ላይ እንደሚነጋገሩ ታውቋል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ታቅዷል፡፡ መንግሥት በተለይ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ በ2008 ዓ.ም. 12 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡
ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተጨማሪ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል፡፡ አዲስ አበባ የሚሰበሰቡት ዲፕሎማቶች የውጭ ኢንቨስተሮችን በጥራትና በስፋት መሳብ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ፣ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
 

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar