søndag 30. august 2015

ጎሳን ለይቶ የሚደረግ ጥቃትን ለማስወገድ መሰረታዊ ለውጥ ያሻል

 shengo 
አንድ መንግስት ልማታዊ ሊባል የሚችለው የሚመራውን ሕዝብ ከዃላ ቀርነትና ከድህነት አሮንቓ መንጥቆ ሲያወጣ፣የህዝቡን አንድነትና መልካም ግንኙነት ሲያጠናክር፣የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ዳር ድንበር ሲያስከብር ነው።
ሕዝብ በኑሮ ክብደት የሚሰቃይበትና የበይ ተመልካች በሆነበት፣ወጣቱ ተስፋ ቆርጦ ለስደት ሲዳረግና እግረመንገዱን ለተለያዩ አደጋዎች የሚጋለጥበት፣የጎሳ ስሜት ነግሶ አንዱ ሌላውን እንዲጠላና ሰላም እንዲናጋ፣ዜጋ ለዘመናት ከኖረበት ቦታና መሬት በሃይል እየተፈናቀለ እንዲበታተን የሚያደርግ ስርዓት ያሰፈነ ቡድን የሚመራው መንግስት ጥፋታዊ እንጂ ልማታዊ ተብሎ ሊጠራ አይገባውም።
የሕዝቡን መብት ገፎ፣የአገሩን ሃብትና ንብረት፣ለም መሬት ጭምር ለባዕዳን አሳልፎ እየሰጠ፣እየሸጠና ተባብሮ እየመዘበረ በውጭ አገር ባንክ የሚያካብት ቡድን ስልጣን ላይ ባለበት አገር ውስጥ ልማታዊ መንግስት አለ ብሎ ማመን ቀርቶ መናገሩ የስህተት ስህተት ነው።
ብሔራዊ ስሜትና የአገር ፍቅር፣ለራሱ ሕዝብ አክብሮት የሌለው ቡድን ኪራይ የሚሰበስብባቸው ታላላቅ ሕንጻዎች ስለሰራ፣የውጭ አገር ተባባሪዎቹን ለማስተናገድና ለመሳብ ሆቴሎችንና መንገዶችን በመገንባቱ ብቻ ልማታዊ ነው ብሎ መቀበልና ማስተጋባት ስለልማት ሁለንተናዊነት ሊኖር የሚገባውን ግንዛቤ ይጻረራል።ልማት በአጭሩ ሲተረጎም የሕዝብ ኑሮ መሻሻልን፣የሰብአዊ መብት መከበርን፣የዜጎችን ደህንነትና ሰላማዊ ኑሮ ዋስትና መኖርን፣የዴሞክራሲና የዜጎች መብት መረጋገጣቸውን ማሳየት ይኖርበታል።ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የማይመክርበት፣የማይወስንበት ሁኔታ ካለ ትርጉም የሚሰጥ ልማት ሊኖር አይችልም።ልማት ማለት የትቂቶችን ከርስ ሞልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን በህዝብ ውስጥ የመንፈስ እርካታም ጭምር ሲኖር ነው።የአገር ዜግነትና ባለቤትነትም በተግባር ሲገለጽ ነው።
ይህ ከዚህ በላይ በጥቅሉ የቀረበው መንደርደሪያ የህወሃት/ኢሕአዴግን ፖሊሲወች ምንነት ለመግለጽ ከሚያስችሉት አንኳር ነጥቦች ጥቂቱ ሲሆን፣ሰሞኑን ደግሞ አንድ መንግስት አለ ተብሎ በሚገመትበት አገር ቀርቶ ወራሪ ጠላት በሚያስተዳድረው አገር ውስጥ እንኳን ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ድርጊት፣ሰው ሰውን ቀቅሎ የሚበላበት ፈቃድና ድርጊት መፈጠሩ የስርዓቱን ምንነት በጉልህ ያሳያል።
ዛሬ በጉሙዝ ክልል ውስጥ በአማራነታቸው ተቀቅለው የተበሉት ወገኖች እንደ ወንጀል የተቆጠረባቸው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና ሁሉንም ማህበረሰብ እንደራሳቸው ቆጥረው አብረው ለመኖር መወሰናቸውና መኖራቸው ነው።
በጉሙዝ ክልል ውስጥ ለተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት ሀገርን አሰተዳድራለሁ የሌለው ክፍል በቴሎቪዥን መስኮት ቀርቦ የአዞ እንባ ከማፍሰስ አልፎ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሁሉ መንጥሮ እያወጣ በይፋ ለህግ ማቅረብ  ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት ደግሞ ከሁሉም ባለድርሻወች ጋር መወያየት ይኖርበታል፣ጉዳት የደረሰባቸውንም ወገኖቹን ለመካስና ተመሳሳይ አውሬያዊ አድራጎት እንዳይፈጸምባቸው ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል። በተጨማሪም ስርአቱ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የኢትዮጵያ ምድር በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ መብታቸውን ማክበርና ሁኔታውን ማመቻቸት ይኖርበታል።
ሸንጎ የአማራው ማህበረሰብን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊ  ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ግፍና መከራ ሲያጋልጥና ሲያወግዝ ቆይቷል። ላለፉት ግፎች ምንም አይነት ሕጋዊና መሰረታዊ መፍትሔ ስላልተገኘላቸው አሁን የደረሰው ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት እንዲከሰት ዕድልና በሩን የከፈተው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ፖሊሲና ተግባር እንደሆነ በማመን ከማጋለጥ በላይ በዓለም አቀፍ ሕጋዊና  ሰብዓዊ መብት መድረኮች ላይ ጉዳዩን ለማቅረብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ የሚገኙት ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ድርጊቱን በማውገዝ ከሚጠቁት ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጎን እንዲሰለፍና አስፈላጊውን ዕርዳታና ድጋፍ እንዲለግሳቸው ለደህንነታቸውም ዋስትና በሚሰጠው መንገድ ሁሉ እንዲተባበር ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar