torsdag 10. oktober 2013

መስከረም 19 ቀን 206 ዓ.ም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በጠራው ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የተደረገ ንግግር

የተከበራችሁ የሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚዎች፤
የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤
የተከበራችሁ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች፤
ክቡራንና ክቡራት!
አስቀድሜ የማክበር ሰላምታየን እያቀረብኩ መብታችንን አደባባይ ወጥተን ለምንጠይቅበት፣ ያልተሸራረፈ ነፃነታችንን ለማረጋገጥ ጉዞ ወደቀጠልንበት ታሪካዊ ቀን ሁላችንንም እንኳን አደረሰን፡፡

በመቀጠልም ለዚህ ዝግጅት መሳካት የተባበሩንን፣ የረዱንን፣ ያገዙንንና በቅስቀሳ ወቅት መስዋዕት ከፍለው ለዚህ ላደረሱን የአንድነትና የ33ቱ አባላት፣ አመራሮችና ደጋፊዎቻችን ከፍ ያለ ምስጋናየን ከአክብሮት ጋር ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በስትራቴጅው መሰረት በመጀመር፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በማንቀሳቀስ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማከናወኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነገር ግን ሕጋዊ መብቱን ሳያስነካ፤ መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በመክፈልና በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት ከአባላቱና አመራሩ ጋር በመሆን በማከናወን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መመኪያ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ዛሬ የተሰለፍንበት ዋና ምክንያትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሰለፈለትን፣ የሞተለትን፣ በአጠቃላም አንድ ትውልድ ትልቅ ዋጋ የከፈለለትን ግን ደግሞ እስካሁን መረጋገጥ ያልቻሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ የሰፈነባት የሁላችን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲደረግ የቆየውን ትግል በማያዳግም መልኩ ከህዝቡ ጋር በመሆን እውን ለማድረግ ነው፡፡

የምንታገለው ለመብታችን መከበር፣ ለነፃነታችን መረጋገጥ፣ ለሀገር ሉዓላዊነታችን፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ የታሰሩ የፖለቲካና ህሊና እስረኞች እንዲፈቱና ማንም ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ፣ በእምነቱና ሃሳቡን በነፃነት ስለገለፀ የማይታሰርባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲሁም የፀረ-ሽብር ህጉ መሰረታዊ ዜጎችን መብቶችና ሕገ-መንግስቱን በግልፅ የሚንድ በመሆኑ የሚሊዮኖችን የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሰረዝ ለማድረግ ነው፡፡

ዛሬ የተሰለፍነው ኢህአዴግና የኢህአዴግ መንግስት እንደሚከሰን ሁከት ለመፍጠር አይደለም፣ ሽብር ለመፍጠር አይለም፣ አሸባሪዎች ስለሆንን አይደለም፣ የአሸባሪዎች መደበቂያ ስለሆንንም አይደለም፣ የሻዕቢያ መልዕክት አድራሾች ስለሆንን አይደለም፣ በአቋራጭ የመንግስት ስልጣን ለመያዝም አይደለም፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በገዥው ፓርቲ የተነጠቅናቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስመለስ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በአመለካከታችን የማንታሰርባት ኢትዮጵያ ስለምታስፈልገን ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በጉልበትና አፈና መግዛት እንዲበቃና እንደሌሎች ሀገሮች ሀገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንድትሆን ነው፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
ፓርቲያችን አንድነት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚገባትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ በሰላማዊ የትግል መስመር ለማረጋገጥ ትግል ከጀመረ አምስት ዓመቱን ይዟል፡፡ በነዚህ ዓመታትም ፓርቲያችን ወደ ፍፁም አምባገንነት እየሄደ ያለውን ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ አካሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጠቃ እንዲቆም አጥብቆ ታግሏል፣ እየታገለም ይገኛል፡፡

በትግሉ ሂደትም ስርዓቱ በግልፅና በስውር ፓርቲያችን ላይ ጥቃት ፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል፡፡ አመራሮቻችንና አባሎቻችንም ስለ ቁርጠኛ ዓላማቸው ያለምንም ማፈግፈግ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ስለ ዴሞክራሲና ነፃነት ሲሉ ጨለማ ክፍል የተጣሉትን ወጣት የፖለቲካ አመራሮች፣ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ እስር ቤት የተጣሉ ጋዜጠኞችና የዕምነት ጣልቃ ገብነትን የተቃወሙ የሙስሊም ወገኖች መፍትሄ አፈላላጊ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቀለን፡፡ ዜጎችን ለማሰር እያገለገለ ያለው የጸረ-ሽብር አዋጅም በአስኳይ እንዲሰረዝና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እየሰሩ ያሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ውይይት እንዲጀመርና በሀገራችን ጉዳይ ላይ መፍትሄ እየሰጠን እንድንሄድ፤ ለዚህም ገዥው ፓርቲ ፈቃደኛም፤ ቁርጠኛም እንዲሆን ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ በኢህአዴግ ብቻ አይፈታም፡፡ በሌላ አንድ ፓርቲ ብቻም ይፈታል ብለንም አናምንም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመተባበር፣ በመቀናጀትና ውህደት በመፍጠር ትልቅ የፖለቲካ አቅም መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

የተከበራችሁ ሰላማዊ ሰልፈኞች!

አሁንም ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ለውጥና ማሻሻያ ለማድረግ ፍላጎትም አቅምም የለውም፡፡ በ3 ወር ህዝባዊ ንቅናቄችን ያረጋገጥነው ይሄንኑ ነው፡፡ ምክንቱም አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዥ ሀይል በሰላማዊ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ አሁንም ለጥያቄ አቅራቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ቢሆን ህዝባችን ጋር ለመድረስና ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለማሰማት ችለናል፡፡ ይሄው በማሰማት ላይም እንገኛለን፡፡ ሰላማዊ የተቃውሞ ትግላችንን አጠናክረን በመቀጠል አምባገነኖችን በሚያንቀጠቅጥ የተቃውሞ ትግል እንደምናሸንፍ አልጠራጠርም፡፡

በጎንደርና ደሴ ከተማ በ7/11/2005 የጀመርነው የተቀውሞ ሰልፎች በባህርዳር፣ በአርባምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማ፣ በፍቼ በተሳካ ሁኔታ የተካሄዱ ሲሆን በመቀሌና ባሌ ሮቤ በከፍተኛ ጫናና ህገወትነት ሳካሄዱ ቀርተዋል፡፡ በወላታ ሶዶና አዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡ ከላይ በጠቀስናቸው ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ ደብድበዋል፣ አዋክበዋል፡፡ ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን አግተዋል፣ የተለጠፉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማካሄዳቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅና በጉልበት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ችለናል፡፡

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን!

ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ተቋምና የፍትህ ስርዓት ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የፖሊስና የደህንነት ተቋምም ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተና የዴሞክራሲ ተቋማትም መፈጠር አለባቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ተቋማት የሚፈጠሩት ግን በልመና አይደለም፡፡ እነዚህን ተቋማት ነጻ ሆነመው እንዲፈጠሩ የምታደርጉት እናንተ ናችሁ፡፡ ነፃነት ከፍርሀት አይገኝምና፣ በሀገር ጉዳይ አይፈራምና ነፃነታችንንና መብታችንን የሚነጥቁንን እምቢ ማለት አለብን፡፡ አትችሉም ማለት አለብን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ገዥዎችን የምንፈራብ ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ ገዥ ህዝቡን ይፈራል እንጅ ሕዝብ ገዥዎችን አይፈራም፡፡

ከላይ የተናገርኩትን የሚያጠናክር መረጃ ላቅርብ፡፡ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይያዛሉ፣ አስገድው በአካል ፈሳሽና ናሙና በመውሰድ ምርመራዎች ይካሄዳሉ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ በውሸት ማስመስከርና አስገድዶ መረጃ ማውጣጣት፣ ቶርቸር፣ ዜጎች በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ ማስገደድና ሌሎች የማሰቃያ ዘዴዎች አገዛዙ ፍርሃት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ስርዓቱ ዜጎች ካላግባብ ከየመኖሪያ ቀያቸው በገጠርም ሆነ በከተማ በግፍ እንዲፈናቀሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄው ሀገራዊ ይዘት ያለው ማፈናቀል ሦስት አይነት መልክ ያለው ሲሆን በዘር ላይ ተመሰረተ ማፈናቀል፣ በልማት ስም ማፈናቀልና ለመሬት ወረራ ማፈናቀል ናቸው፡፡ ዘርን መሰረት ያደረገው ማፈናቀል በቅርቡ ብቻ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎችና ሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተው ነው፡፡ በልማት ስም የሚከናወነው ማፈናቀል በአብዛኛው በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው መሰረቱ የገዥው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡ መሬት በባለቤቱ ፈቃድ የሚሸጥና የሚለወጥ ባለመሆኑ ያለበቂ ካሳና ማስጠንቀቂያ ለማህበራዊ ትስስር ቁብ ሳይኖረው ልማት የሚል ስም ብቻ በማንሳት ዜጎች የሚፈናቀሉበት ነው፡፡ ሌላው የማፈናቀል አይነት ደግሞ ከመሬት ወረራ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና በእርሻ መሬት ሰበብ ዜጎች እየተፈናቀሉ ለውጭና ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በጥቂት ሳንቲም የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄም በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በስፋት የታየና እየታየ ያለ ነው፡፡ ሀገራቀፉን ማፈናቀል አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በአስቸኳይ እንዲቆምም እንጠቃለን፡፡

ከመፈናቀሉ በተጨማሪም ቅጥ ያጣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ ያስነካው የዋጋ ግሽበት ዋና መንስኤው ስርዓቱ የሚከተለው የተሳሳተ አጠቃላይ ፖሊሲ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ የወለደው ነገር ቢኖር ሀገራችን በታሪኳ አይታ የማታውቀው ስደት ነው፡፡ ዜጎች ከፊት ለፊት ሞት እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ተጋፍጠው ለስደት የመነሳታቸው መንስኤ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር የነፃነት እጦት ሲታከልበት የችግሩን መልክ ውስብስብ አድርጎታል፡፡

የንግዱን ማህበረሰብም ስንመለከት ከመቼውም በባሰ ሁኔታ ነጋዴ መሆን ወንጀለኛ መሆን የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ በተጨማሪም አንድ ፓርቲ ነጋዴና አንድ ፓርቲ ህግ አውጭ በሆነበት ሁኔታ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ስለዚህ የግሉ ሴክተር የልማት ሚና አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ካላግባብና በግምት የሚጣል ታክስ መክፈል ሃገራዊ ግዴታ የመሆኑን ለዛ አሳጥተውታል፡፡ አንዳንዱ በብልጣብልጥነት ስርዓቱን እንደመታወቂያና ከለላ በመጠቀም፣ ከባለስልጣናት ጋር በመሻረክ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሀብት ማማ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን፡፡ ይሄም በንፁህ ንግድ ላይ ያልተመሰረቱ ለበርካታ ዜጎች አደጋ ነው፡፡ ከዚያም ልቆ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሃዊ የንግድ አሰራር እንዲኖር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ማስገንዘብ የምወደው በሀገራችን የስልጣን ሽግግር ታሪክ እንዱ እንዱን በአፈሙዝ እየገደለ፣ መንድም ወንደሙን ጠላት እያደረገ ነው፡፡ ይህም የርስ በርስ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ትውልድ ብቻ ሁለት አብዮቶች ተካሂደዋል፡፡ በአገራችንንና በትውልዱ ላይም በገንዘብ የማይተመን ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ዛሬም በተለይም ወጣቱ ትውልድና ዋጋ የከፈሉ አባቶች ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ምኞታችን ከፍተኛ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ እየዘጋው ያለው ዴሞክራሲያዊ መንገድና ዜጎች እየደረሰባቸው ካለው ስቃይ አንፃር ወደ ሕዝባዊ አመፅ ተቀይሮ ወደ ሶስተኛው አብዮት ቢገፋ ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክትም ምንም እንኳ የወረሳችሁድ ዕዳ ብዙ ቢሆንም በቁርጠኝነት ታግላችሁ ሀገራችንን እንደሰለጠኑት ሀገሮች እንደምታደርጉ ተስፋ አለኝ፡፡ ከ50 ዓመት በላይ ዋጋ የተከፈለበት ዴሞክራሲ እውን እንድታደርጉ አደራ እያልኩ እንደምታሳኩትም ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar