lørdag 12. oktober 2013

“አዲሱ ፕሬዚዳንት ከኢህአዴግ ማዕቀፍ ወጥተው የራሳቸውን አሻራ ማኖር አለባቸው”

ናፍቆት ዮሴፍ፤(addisadmass)

“አዲሱ ፕሬዚዳንት ከኢህአዴግ ማዕቀፍ ወጥተው የራሳቸውን አሻራ ማኖር አለባቸው”

እኛ ስራ እንሰራለን እንጂ ከኢህአዴግ ጋር አተካራ ውስጥ አንገባም – የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ
ባለፈው ሰኞ ላለፉት 12 ዓመታት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተሰናብተው አዲስ በተመረጡት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተተክተዋል፡፡
በፓርላማ የአዲሱን ፕሬዚዳንት በእጩነት መቅረብ ተከትሎ በምክር ቤቱ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት “አገራዊ መግባባትን ያመጣሉ ብለን ተስፋ በማድረግ ሙሉ ድጋፍ ሰጥተናል” ሲሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በአዲሱ ፕሬዚዳንት አመራረጥና በስልጣን ዘመናቸው በሚጫወቱት ሚና እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ግርማ ሰይፉ ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

አዲሱን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ምን ያህል ያውቋቸዋል?
መቼም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያለው ሰው ሁሉ ያውቃቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሚኒስትር ዲኤታም ነበሩ፡፡ በብዙ ሀላፊነት ላይ ስለነበሩ አውቃቸዋለሁ።
እሳቸው ፕሬዚዳንት ሆነው እንደሚሾሙ ቀድመው ሰምተው ነበር?
መልሴ አዎም አይም ነው የሚሆነው፡፡ ለምን ብትይ — ከነበሩት ግምቶች አንፃር ዶ/ር ሙላቱ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ መገመት ቀላል ነበር፡፡
እንዴት ማለት?
መጀመሪያ ሲገመቱ የነበሩ ሰዎች በትክክል ወደ ቦታው የሚያደርሱ ግምቶች አልነበሩም፡፡
የተገመቱት ሰዎች ለቦታው አይመጥኑም ማለትዎ ነው?
በፍፁም! ለቦታው ማንም ሰው ይመጥናል፡፡ ቦታው የሚፈልገውና የቦታው ተግባር ግልፅ ነው። ነገር ግን አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ– ዶ/ር አሸብር ወዘተ — እየተባሉ የሚነገሩ ግምቶች ትክክል አልነበሩም። በአጠቃላይ መሰረት የሌላቸው ግምቶች ነበሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ የተሳሳተ አመለካከት ይዘው ነበር ግምት የሚናገሩት፡፡ አንድ ጊዜ የግል ተወዳዳሪ ፕሬዚዳንት ሆኖ ስለተመረጠ፣ አሁንም በግላቸው ተወዳድረው ምክር ቤት የገቡት ዶ/ር አሸብር ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ እርግጠኛ እስከመሆን የደረሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሁሉ አጉል ግምት በኋላ ዶ/ር ሙላቱ ላይ ግምቶች ሲያነጣጥሩ፣ እኔም ግምቶች ወደ እውነቱ እንደቀረቡ ተረዳሁ። ከግምት ባሻገር ቀድመሽ ለማወቅ ግን ኢህአዴግ መሆን አለብሽ፡፡
የዶ/ር ሙላቱ ሹመት ድንገተኛነት “ኢህአዴግ የበለጠ ምስጢረኛ ፓርቲ መሆኑን ያስመሰከረበት ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ምስጢረኛነቱ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴጐች ህዝቡን “ከእናንተ የበለጠ እኛ እናውቅላችኋላን” እያሉ መሆኑን ያረጋገጡበት ነው፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ የያዛቸው ሶስት እጩዎች ቢኖሩ፣ እነዛን እጩዎች በተለያየ መንገድ ለህዝብ ይፋ አድርጐ፣ ምንም እንኳን የመጨረሻውን ውሳኔ የሚወስነው ገዢው ፓርቲ ቢሆንም የህዝቡን አስተያየት ለመስማት ጆሮውን መክፈት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ማን ፕሬዚዳንት ሊሆን ይችላል በሚለው ዙሪያ በጋዜጣ፣ በፌስቡክና በሬዲዮ ሲወያይ ከርሞ ኢህአዴግ ሌላ ሰርፕራይዝ ይዞ መምጣቱ ምን ያህል ለህዝብ ድምፅ ጆሮ እንደማይሰጥ የሚያሳይ ነው፡፡
ዶ/ር ሙላቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች እጩ ሆነው ሲቀርቡ፣ እርስዎ የሰጡትን የድጋፍ አስተያየት በተመለከተ ከወከለዎት መድረክ ፓርቲ ጋር ተወያይተው ነበር ? ወይስ —
ከመድረክ ጋር ለመመካከር ማን እንደሚመረጥ አይታወቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ለፓርቲው ይጠቅመዋል ብዬ ያሰብኩትን ነገር በራሴ መወሰን እችላለሁ፡፡ ሁልጊዜ ወደ ምክር ቤት እየመጣሁ ስሰበሰብ በየጉዳዩ ላይ ከመድረክ ጋር እየተመካከርኩ አይደለም፡፡ ምክር ቤት ውስጥ የተቀመጠ አንድ የምክር ቤት አባል በህገ-መንግስቱ የተቀመጠ ሀላፊነት አለበት። እነዚህ ሀላፊነቶች ምን ምን ናቸው ያልሽ እንደሆነ —- ተገዢነቱ ለህሊናው እና ለህገ-መንግስቱ ነው የሚሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እናም ከመድረክ ጋር አጀንዳ ይዘን የትኛው ፕሬዚዳንት ቢሆን እንደግፋለን፣ የትኛው ቢሆን እንቃወማለን አላልንም፡፡ በመርህ ደረጃ አሁን የተሰየሙትን ፕሬዚዳንት ብቃወም የምቃወምበት ምክንያት ያስፈልገኛል፡፡ ስደግፍም እንዲሁ ምክንያት ያስፈልገኛል ማለት ነው፡፡
እስቲ የደገፉባቸውን ምክንያቶች ይግለፁልኝ—
የደገፍኩበት ምክንያት አሁን የተመረጡት ፕሬዚዳንት በእድሜም በጤንነት ሁኔታም ቀድመው ከነበሩት ፕሬዚዳንት ይሻላሉ፡፡ ቀድመው የነበሩት ፕሬዚዳንት ግርማ የተመረጡ ዕለት በማግስቱ ነው ለህክምና ወደ ውጭ የሄዱት፡፡ ከዚያ በኋላ 12 አመቱን ያሳለፉት በህክምና ክትትል ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ጥብቅ የሆነ የጤና ክትትል ላይ ያለ ፕሬዚዳንት እና በአንፃራዊነት በተሻለ ጤናና እድሜ ላይ የሚገኝ ፕሬዚዳንት ሊሰራው የሚችለው ነገር የተለያየ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በፕሬዚዳንትነት ብዙ ሀላፊነት ስለሌለ፣ በህገ መንግስቱ የተሰጡ ሀላፊነቶችም ውስን በመሆናቸው አዲሱ ፕሬዚዳንት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ለአገር ሊጠቅም በሚችል ስራ ሊያሳልፉት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በአገራችን መግባባት እንዲኖር ተቃዋሚና ገዢው ፓርቲን ተግባብተው በመስራት በአገር ጥቅም ላይ አንድ ግንባር እንዲፈጥሩ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ቢሰሩ ይህ አንድ ተስፋ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ተግባራዊ አደረጉትም አላደረጉትም በእጃቸው ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ “አይ እኔ ከፖለቲካ ውጭ ሆኜ እንደ ቀድሞው ፕሬዚዳንት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ብሰራ ይሻለኛል” ካሉም ይችላሉ፡፡ “አይ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በአረጋዊያን ላይ እሰራለሁ” ካሉም ምርጫቸው ነው፡፡ ጊዜያቸውን የትኛው ቦታና ዘርፍ ላይ ቢያውሉት አገርና ህዝብ ይጠቀማሉ ብለው ማሰብና መምረጥ የእሳቸው ፋንታ ነው፡፡
እርስዎ ፕሬዚዳንቱ የትኛው ዘርፍ ላይ ቢያተኩሩ የበለጠ ይሻላል ይላሉ?
እኔማ ለሹመት ምክር ቤት ሲቀርቡ ይጠቅማል ያልኩትን ተናግሬአለሁ፡፡ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ያለመግባባት ክፍተት በማስወገድና አገራዊ መግባባት ላይ ቢሰሩ ለአገሪቱም ለህዝቦቿም የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ለማድረግ በህገ-መንግስቱ ስልጣንና ሀላፊነት አላቸው?
እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀም በህገ-መንግስት የሚሰጥ ሀላፊነት አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከፈለገ መሞከር ይችላል፡፡ እሳቸው ግን ይህን ነገር ለመሞከር በተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የፕሬዚዳንትነት ቦታ በሚይዙበት ጊዜ “ያለ አድልዎ የኢትዮጵያን ህዝብ አገለግላለሁ” ብለው ከተነሱ፣ ይህንን ለማድረግ የሚከለክላቸው የህግ-ድንጋጌ የለም፡፡
ከአገራዊ መግባባት ውጭ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በጤናም ሆነ በዕድሜ ጫና አልሰሩትም የሚሉትና ከአዲሱ ፕሬዚዳንት የሚጠብቋቸው ተጨማሪ ተግባራት ምንድን ናቸው?
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምንም ስላልሰሩ፣ ይሄኛውን ያኛውም ማለት አይቻልም፡፡ ይህን ሰርተዋል፣ ያን አድርገዋል የምለው ነገርም የለም፡፡ እሳቸው ጥሩ የጡረታ ጊዜ ነው በቤተ-መንግስት ያሳለፉት፡፡ አዋጅ ላይ ለመፈረምና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተጨባጭ በሆነና ሊታይ በሚችል መልኩ እንዲህ አድርገዋል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ከአዲሱ ምን ይጠብቃሉ ላልሽው— ይሰራሉ አይሰሩም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ብዙ ነገር ሊጠበቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸውን በምን ያሳልፋሉ? የቀድሞው ጤናቸውን ሲያስታምሙና ሲከታተሉ ነው የኖሩት፡፡ ከዚህ በላይም አይጠበቅባቸውም፡፡ ምክንያቱም አንድ በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ ያለ ሰው ምንም ያህል ብሩህ አዕምሮና እውቀት ቢኖረውም ምንም አይጠበቅበትም፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት በዋናነት በአገራዊ መግባባት ላይ ሰርተው ለሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ጊዜ ቢሰጡ የተሻለ ነው እላለሁ፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት በስንብት ንግግራቸው ላይ ለገዢው ፓርቲና ለተቃዋሚዎች የለገሱትን ምክር በተመለከተ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንደኔ እንደኔ ይህን ምክር ገና ሲሾሙ ለግለሰው ለተግባራዊነቱ ቢንቀሳቀሱ መልካም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ እንድትቆሙ ያስፈልጋል፡፡ (ታማኝ ተቃዋሚ ያሉትንም በኋላ ሊያብራሩት ይገባ ነበር) ግን ደግሞ ችግራችሁ ምንድን ነው? በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን አብራችሁ አትሰሩም? ማለትና ማድረግ ሲችሉ፣ እሳቸው ግን ይህን በ12 አመት ውስጥ አንድ ጊዜም አድርገው አያውቁም፡፡ ምክሩን መጀመሪያ አድርገውት ሁኔታውን ቢከታተሉ አንድ ነገር ነበር፡፡ “አይ የሚፈለገውንና ያቅማቸውን ጥረት አድርገዋል” እንድል ጠብቀሽ ከሆነ በጣም ተሳስተሻል፡፡ አሁንም ደግሜ የምነግርሽ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከእድሜ፣ ከጤና፣ ከትምህርት ዝግጅትና ካላቸው ልምድ አንፃር ብዙ ለመስራት እድል አላቸው፡፡ አይ ጭልጥ ብዬ ካድሬ ሆኜ እቀጥላለሁ ሊሉ ይችላሉ፣ መፅሀፍ መፃፍ እፈልጋለሁ ብለው ቁጭ ብለው ሊፅፉ ይችላሉ፣ ምርጫው የእርሳቸው ነው፣ ችሎታም ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የትኛው ነው ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚበጀው፣ እኔንም ታሪካዊ ሰው የሚያደርገኝ የሚለውን ያስቡበታል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እርግጥ ፕሬዚዳንት መሆን በራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ወርቃማ ስራን ሰርቼ የማልፈው በየትኛው ዘርፍ ነው የሚለውን በጥልቀት ሊያስቡበት ይገባል እንጂ ኢህአዴግ ሰፍሮ በሚሰጣቸው ስራ ላይ ብቻ ከተወሰኑ የራሳቸው አሻራ አይኖራቸውም፡፡
የራሳቸውን ታሪክ አሻራ የማስቀመጥ ፍላጐት ሊኖር የሚችለው ከፈለጉ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሰው በጉትጐታ ፍላጐቱን ሊያመጣላቸው አይችልም፡፡ እኔ በበኩሌ ከኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ወጥተው የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ፣“በእርሳቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን እንዲህ አይነት መልካም ውጤት ተከናውኗል” የሚያስብል ጉልህ ስራ ቢሰሩ ደስ ይለኛል፡፡
ግን እኮ የቀድሞው ፕሬዚዳንት እሳቸው በቀጥታ ተሳታፊ በነበሩበት ዘመን ብዙ ውጤቶች እንደተመዘገቡና በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
እርግጥ ነው እንደዚያ ብለዋል፡፡ እሳቸው ቀጥተኛ ተሳታፊ በሆኑበት ድል ተገኝቷል ካሉን፣ እሳቸው ቀጥታ ተሳታፊ በሆኑበት ጊዜ ለጠፋውም ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸውን ማመን አለባቸው፡፡ ለተገኘው ድል ብቻ ሳይሆን ለጠፋውም ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸውን መግለፅም ነበረባቸው፡፡ በእኔ እምነት ግን የተገኘም ድል ካለ እርሳቸው የሉበትም፡፡ የጠፋም ጥፋት ካለ — ባይሆን እሱ ላይ ሀሳብ ባለመሰንዘራቸው ምናምን ሊባል ይችላል፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ፕሬዚዳንቱ ድንገት በተገኘ ድል “እኔም አለሁበት” ማለት ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት በአገሪቱና በህዝቧ ሊረሳ የማይችል ከፍተኛ እንቅስቃሴና ውጤት ማስመዝገብ አለባቸው ነው፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሰፊ እድል አላቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን እርስዎ በፓርላማ የወከሉት “መድረክ” በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
እኔ የመድረክ ተወካይ አይደለሁም፡፡ ይህን ጥያቄ ለመድረክ አመራሮች ነው ማቅረብ ያለብሽ፡፡
እንዴት? መድረክን ወክለው ተወዳድረው አይደለም እንዴት ምክር ቤት የገቡት?
እኔ የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የአንድነት አባል ነኝ፡፡ እርግጥ ም/ቤት አባል የሆንኩት መድረክን ወክዬ ተወዳድሬ ነው፡፡ ያ ማለት ግን መድረክ ውስጥ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የማደርግ ተሳታፊ ነኝ ማለት አይደለም፡፡ በመድረክ የአንድነት ተወካይ ሌላ ሰው ነው፡፡
“አንድነት” ለሶስት ወር ባቀደው ንቅናቄ ውስጥ በተለይ በሰላማዊ ሰልፎች አካባቢ ብዙ እንቅፋቶች እንደገጠሙት እየገለፀ ነው፡፡ በቀጣይ እንቅስቃሴው በምን ላይ ያተኩራል?
እንግዲህ ከላይ በጠቀስሻቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ችግሮች እንደነበሩ መግለጫ አውጥተናል፡፡ በቀጣይ ከአሁኑ በተሻለ ጥንካሬ ትግሉን ለመቀጠል እቅድ ካለ ዝርዝሩን ወደፊት ይፋ እናደርጋለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ያለውና ሰፊ ትኩረት የሰጠነው የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪያችን ላይ ነው፡፡ በቅድመ-ዝግጅቱ ላይ በስፋትና ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከዚያ በተረፈ አዲስ የሚመጣው አመራር፣ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ሀይል የተሻለ ትግል እንዲቀጥል ስራዎች ከወዲሁ እየተሰሩ ነው፡፡ ጊዜያቸውን ጠብቀው በዝርዝር መግለጫ ይሰጥባቸዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተወሰዱ ንብረቶችና የደረሱ እንግልቶችን በተመለከተ ክስ እንመሰርታለን ብላችሁ ነበር—
የወሰዱብንን ንብረቶችና ያጠፉብንን እቃዎች መልሱልን አንላቸውም፡፡ የህግ ጥሰት የተፈፀሙባቸው ሁኔታዎች ላይ በህግ ለመፋረድ ማሰባችንን በመግለጫ አሳውቀናል፡፡ በዛው መንገድ እንሄዳለን፡፡ በተረፈ እኛ ስራ እንሰራለን እንጂ ከኢህአዴግ ጋር አተካራ ውስጥ አንገባም፡፡ ይሄው ነው፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar