søndag 27. oktober 2013

“ኢቴቪ” የዜና መረጃዎችንና የሰዎችን መልክ ይደፈጥጣል


በኢቴቪ የምናያቸው ቪዲዮዎችና ምስሎች፣ የተደፈጠጡና የተጣመሙ ሆነዋል – ስንት ወሩ? አልተስተካከለም።
በኢቴቪ የሚሰራጩ የተዛቡና የተሳሳቱ ዜናዎች ወይም ዘገባዎች ያሳፍራሉ፤ ደግሞም መላ ያለው አይመስልም።
አንዳንዴ፣ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የሚሰራጩ ዜናዎችን መስማት ያሳቅቃል፤ ወይም ያዝናናል። በሌላ በኩል ደግሞ ቀሽም ስህተት ስለሆነ ያዝናናል። ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ የአገሪቱ ብቸኛ የቴሌቪዥንና የሬድዮ አንጋፋ ድርጅቶች መረጃ ሲሳሳቱና ሲያዛቡ ማየት ያሳቅቃል። 
ባለፈው ረቡዕ ምሽት የተሰራጨውን ዜና መጥቀስ እችላለሁ። በአፍጋኒስታን የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሃይል አገሪቱን ለቅቆ የሚወጣበትን የጊዜ ገደብ ለመቁረጥ እንዳልቻለ የሚገልፅ ነው ዜናው። ሰላም አስከባሪው ሃይል ወደ አፍጋኒስታን የተሰማራው፣ በእርስበርስ ግጭት መነሻነት እንደሆነም ዜናው ይጠቅሳል። የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ጦር ሃይል ወደ አፍጋኒስታን ለምን እንደተሰማራ ተረሳ ማለት ነው? አስር አመት ያስቆጠረ ዘመቻ ስለሆነ ኢቲቪ አያስታውሰው ይሆናል፡፡ ግን፤ እንዴት እንዴት የቢን ላደንና የአልቃይዳ ሽብር ሊረሳ ይችላል? በኒውዮርክና በዋሺንግተን የ3ሺ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ የሽብር ጥቃት መፈፀማቸውስ እንዴት ይዘነጋል? ከዚያ በኋላ፣ በአሜሪካ መሪነት፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አፍጋኒስታን መዝመታቸውን መላው አለም ያውቀዋል፡፡
ለኢቲቪ እንዴት እንደተሰወረበት እንጃ! አናስታውስም? ለአመታት በመንዛዛቱ “ዘመቻነቱ”ና ውጤታማነቱ ቢደበዝዝም፣ በጊዜው ትክክለኛ እርምጃ ነበር። 
የሆነ ሆኖ፣ የአሜሪካ ዘመቻ ቢን ላደንን ለመግደል፣ አልቃይዳን ለመውጋትና ጥላ ከለላ የሆናቸውን የታሊባንን ሃይል ከስልጣን ለማስወገድ እንጂ፣ “ሰላም ለማስከበር” የተካሄደ ዘመቻ አይደለም። በአጭሩ፣ ለጦርነት ነው፣ አሜሪካና አጋሮቿ ወታደሮቻቸውን ያዘመቱት። በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወታደሮቹ ቁጥር ቀንሷል። ነገር ግን፣ ዛሬ ከአስር አመት በኋላም፣ ገሚሶቹ ከአሜሪካ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሌሎች የኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ ወደ መቶ ሺ የሚጠጉ ወታደሮች በአፍጋኒስታን እንደተሰማሩ ናቸው። ሰላም አስከባሪ የሚሰማራው ደግሞ፣ “ሰላም ሰፍኗል” ተብሎ ሲታሰብ ነው – “ሰላምን ለመጠበቅ”። የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ሶማሊያ ያልተሰማራው ለምን ሆነና? በአገሪቱ ሰላም የለም፣ ሰላም ከሌላ ሰላምን ማስከበር አይቻልም በሚል ነው። ታዲያ የአፍሪካ ህብረት፣ ለምን “ሰላም አስከባሪ ሃይል” አሰማራ? “የተወሰነ ሰላም ተገኝቷል” ብሎ ስላመነ ነዋ። 
በአፍጋኒስታን ግን፣ የሰላም አስከባሪ ሃይል የማሰማራት ሃሳብ በጭራሽ ተነስቶ አያውቅም። ሰሞኑን ስለ አፍጋኒስታን እና ስለ አሜሪካ ወታደሮች የሚያወሱ በሺ የሚቆጠሩ ዜናዎችና ዘገባዎች ቢሰራጩም፣ በአንዳቸውም ላይ “ሰላም አስከባሪ ሃይል” የሚል አባባል አታገኙም – በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በተሰራጨው ቀሽም ዜና ካልሆነ በቀር። በእርግጥ፣ ዜናውን የሰራው ጋዜጠኛ ቀሽም ላይሆን ይችላል። ደግሞም፣ በዜናው የተካተቱ በርካታ መረጃዎች ሲታዩ፣ ጋዜጠኛው ቀሽም እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ቀሽም ስህተት እንዳይፈጠር የሚከላከል አሰራርና ባህል በድርጅቱ ውስጥ አለመኖሩ ይመስለኛል – ዋናው ችግር።
“የሜርከል ፓርቲ አሸነፈ፣ ፓርቲያቸው ተሸነፈ”
በቅርቡ በጀርመን በተካሄደው ምርጫ በአብላጫ ድምፅ ያሸነፈውና በአንጌላ ሜርከል የሚመራው ፓርቲ፤ አዲስ መንግስት ለመመስረት ውይይት እያካሄደ ነው። ሲዲዩ የተሰኘው ፓርቲ ከነአጋሩ፣ በምርጫው 42 በመቶ ድምፅ አግኝቷል። ታዲያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዜና ምን ይላል አትሉም? ቀደም ብሎ እንደተጠበቀው የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በምርጫው ሲያሸነፍ፣ ተፎካካሪው ሲዲዩ ፓርቲ 42 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተሸንፏል ይላል ዜናው። ትክክል ይመስላል። ከሃምሳ በመቶ በታች ድምፅ ያገኘ ፓርቲ በተሸናፊነት መጠቀሱ አይገርምም። ቀሽሙ ስህተት ምን መሰላችሁ? ሲዲዩ የአንጌላ ሜርከል ተፎካካሪ ፓርቲ አይደለም፤ አንጌላ ሜርከል የሚመሩት ፓርቲ ነው። አሸነፈ እንጂ አልተሸነፈም፡፡ በኢቴቪ አዘጋገብ…”አቶ ኃይለማርያም የሚመሩት ፓርቲ በምርጫው ሲያሸንፍ ኢህአዴግ ተሸንፏል” እንደማለት እኮ ነው፡፡
የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ (ሲዲዩ) ከነአጋሩ 42 በመቶ ድምፅ በማግኘቱ ነው፣ በአብላጫ ድምፅ አሸናፊ ለመሆን የቻለው። ዋናው ተፎካካሪ ፓርቲ (ኤስፒዲ) ደግሞ 25 በመቶ ገደማ ድምፅ አግኝቷል። 9 በመቶ፣ 8 በመቶ፣ እና ወደዚያው ገደማ ድምፅ ያገኙ ሌሎች ፓርቲዎችም አሉ። የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በአሸናፊነት የሚጠቀሰው፣ መንግስት ለመመስረት ከአንድ ፓርቲ ጋር ጥምረት መፍጠር ስለሚበቃው ነው። ተቀናቃኛቸው ኤስፒዲ ፓርቲ ግን፣ ከአራት ወይም ከአምስት ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ካልፈጠረ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል አቅም አይኖረውም። እንግዲህ፣ የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በአብላጫ ድምፅ ሲያሸንፍ፣ ተፎካካሪው ሲዲዩ ፓርቲ 42 በመቶ ድምፅ ተሸንፏል የሚለው ዜና፤ በቀሽም ስህተት ሳቢያ ምን ያህል መረጃውን ሁሉ እንዳዛባው አያችሁ?
የአካባቢው ጥበቃ ሟርትና የዩኤን እዬዬ 
በዚሁ ወር የተሰራጨ ሌላ ዜናም ልጥቀስላችሁ። “ከአካባቢ ጥበቃ” ጋር. በተያያዘና የአለም የሙቀት መጠንን በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር፣ በየጊዜው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርት አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ድርጅት አለ። በእርግጥ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ፣ በአመዛኙ “ከፖለቲካ እምነት” ጋር እንጂ፣ “ከሳይንሳዊ እውነታ” ጋር ብዙም አይዛመድም። ምን ለማለት እንደፈለግኩ ልንገራችሁ፡፡ “ሟርት” ማስተጋባት የማይሰለቻቸው የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፤ ከሰላሳ አመት በፊት፣ “አለም በቅዝቃዜ ደንዝዛ በበረዶ ትሸፈናለች” በማለት ነበር ዘመቻ የሚያካሂዱት። ነገር ግን፣ የተነበዩለት “Global Cooling” በእውን አልተከሰተም። ግን ሌላ ትንበያ አላጡም። አለምን የሚያሰጋት፣ የበረዶ ቅዝቃዜ ሳይሆን፣ የዓለም ግለት “Global Warming” ነው ተባለ።
በእርግጥም፣ የአለም አማካይ ሙቀት፣ በመቶ አመታት ውስጥ በግማሽ ሴንቲግሬድ እንደጨመረ የተለያዩ የሳይንስ ምርምሮች ይመሰክራሉ። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ግን፣ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ ሳይሆን፣ ከሟርት ያልተለየ ትንበያ ላይ ነው የሚያተኩሩት። በመቶ አመታት ውስጥ የአለም ሙቀት እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምራል በማለት አለምን የሚያስበረግግ “እዬዬ” ማስተጋባት፣ የቡድኖቹ የእለት ተእለት ስራ ነው። “እዬዬ”ውን በአስለቃሽነት እያስተባበረ የሚመራው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው – በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርቶች። 
የ“ሟርት” ነገር! ዩኤን እና የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች የተነበዩት ያህል የአለም ሙቀት አልጨመረም። በተለይ ባለፉት 20 አመታት፣ ከቁጥር የሚገባ ጭማሪ አላሳየም። ለዚህም ይመስላል፣ “የአለም ግለት” ከሚለው ስያሜ ይልቅ፣ በደፈናው “የአየር ንብረት ለውጥ” “Climate Change” የሚል ፈሊጥ ያመጡት። አምስተኛው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርት በቅርቡ የተሰራጨውም፣ በዚህ ድፍን ስያሜ ነው። ከቀድሞዎቹ ሪፖርቶች ብዙም የተለየ አይደለም፤ ትንሽ ለየት የሚለው፣ ባለፉት 20 አመታት የአለም ሙቀት እንደተጠበቀው አለመጨመሩን ለመካድ አለመድፈሩ ብቻ ነው። ከተጠበቀውና ከተተነበየው ጋር ሲነፃፀር፣ ከሶስት እጥፍ በታች ነው የሙቀት ለውጥ የተመዘገበው። ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘ የተሰራጩ ዓለማቀፍ ዘገባዎችም፣ ይህንን አወዛጋቢ መረጃ በስፋት ጠቅሰውታል። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ግን፣ ጨርሶ ጉዳዩን አላነሳም። እናስ ምን ዘገበ? በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት የሚሰራጨው ሪፖርት ውስጥ የተካተቱ የዓለም ግለትን የሚመለከቱና ዓለምን የሚያስበረግጉ ወሬዎችን ነዋ። ግን ምን ዋጋ አለው? የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እነዚህን ጎደሎ መረጃዎችንም ቢሆን በትክክል አልዘገባቸውም። እንዴት በሉ።
እንደሚታወቀው፣ በዩኤን እና በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ድምዳሜ መሰረት፣ የአለም ግለት መንስኤ የሰዎች አኗኗር ነው። በተለይም በነዳጅ አጠቃቀም የሚፈጠረው ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ለአለም ግለት ዋነኛ መንስኤ ነው ይላሉ።
ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ ተብለው ሲጠየቁ፣ በአብዛኛው እርግጠኛ ሆነናል የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጡት። ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ፣ “በጣም እርግጠኞች ነን፤ 90 በመቶ እርግጠኞች ነን” ወደ ማለት ደረሱ። በዘንድሮው ሪፖርት ደግሞ፣ “እጅግ በጣም እርግጠኞች ነን” ወደ የሚል ደረጃ ተሸጋግረዋል። የአለም ግለት በሰዎች አኗኗር ሰበብ እንደተከሰተ 95 በመቶ እርግጠኞች ሆነናል ይላል ሪፖርቱ። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ግን፤ የአለም ግለት 95 በመቶ ያህሉ በሰዎች አኗኗር ሰበብ የሚከሰት ነው ብሎ ዘገበው። ምን እንደማለት መሰላችሁ? “የእገሌ ቡድን የተሸነፈው በተጨዋቾች አሰላለፍ ሳቢያ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፤ 95 በመቶ እርግጠኛ ነኝ” ሲባልና፣ “የእገሌ ቡድን ለሽንፈት የተዳረገበት ምክንያት 95 በመቶ ያህሉ ከተጫዋቾች አሰላለፍ የመነጨ ነው” ሲባል ልዩነት የለውም?
ምናልባት ይህንን ልዩነት ማወቅ ይከብድ ይሆናል። አንዳንዴ ግን፣ የኢቴቪ ቀሽም ስህተቶች የሚመነጩት ካለማወቅ ብቻ አይደለም። ይህችን ቅንጣት ስህተት ተመልከቱ። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በኒውዮርክ ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ስለኢንቨስትመንት እድሎች ገለፃ አድርገው አልነበር? በውይይቱ የተሳተፉ አንድ ባለሃብት፣ ለኢቴቪ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ በገለፃው “intrigued” ሆኛለሁ አሉ – በእንግሊዝኛ። በኢቲቪ ሲተረጎም፣ “በገለፃው ተደስቻለሁ” ተብሎ ቀረበ። የባለሃብቱ አነጋገር ግን፣ “ገለፃው ትኩረቴን ስቧል”፤ “ገለፃው፣ የማወቅ ጉጉት አሳድሮብኛል” ከሚል ሃሳብ ጋር የጥርጣሬ ስሜትንም ጭምር የሚያስተላልፍ ነው። “ገለፃው ጥያቄ አጭሮብኛል” እንደማለት አይነት። ይሄ ነው፤ “በገለፃው ተደስቻለሁ” ተብሎ የተተረጎመው። የአላዋቂነት ስህተት ነው ወይስ ከፕሮፓጋንዳ ፍቅር የሚመነጭ ስህተት? የሆነ ሆኖ ስህተት ነው።
እንግዲህ፣ በጥቂት የዜና ስርጭቶች ውስጥ የታዘብኳቸው ቀሽም ስህተቶችን ነው ያካፈልኳቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን ስህተቶች ማስተካከል ለኢቴቪ ይከብደዋል? ላይ ላዩን ስታዩት ከባድ አይመስልም። ነገር ግን፣ ወጣትና ጎበዝ ጋዜጠኞች የሚያጋጥሟቸው ቀሽም ስህተቶችን ማስተካከል የሚቻለው፣ ሙያውንና ሙያተኛውን የሚያበለፅግ አሰራር በማዳበር ነው። ይሄ ደግሞ ከባድ ነው። የረዥም ጊዜ ጥረትንና ፅናትን ይጠይቃል። ታዲያ ይሄ ነገር ኢቴቪ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል? አይመስለኝም። የመንግስት ድርጅት ነዋ፡፡ 
ሌላውን ተዉት። ኢቴቪ የዜና እና የዘፈን ክሊፖችን ሳይቀር፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን እየደፈጠጠ ማሰራጨት ካዘወተረ ስንት ወሩ ነው? የተለያዩ የቪዲዮ ፎርማቶች፣ በቁመታቸውና በወርዳቸው እንደሚለያዩ ማወቅኮ፣ የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ‘ሀሁ’ ነው። በአንዱ ፎርማት የተዘጋጀ ቪዲዮ፣ በሌላ ፎርማት ከተሰራጨ… ወይ የተደፈጠጠ ድንክ ይሆናል ወይም ወደ ላይ የተመዘዘ ሞላላ ሆኖ ይታያል። ያው እንዳያችሁት የስንቱ ሰው መልክና ቁመና፣ በኢቴቪ ሲደፈጠጥ ከርሟል። አሁን፣ ቪዲዮዎችን በትክክለኛ ፎርማት ማሰራጨት ትልቅ ስራ ሆኖ ነው? ግን ለወራት አልተስተካከለም። ይህችን ለማስተካከል የሚበቃ የአፍታ ጥረትና ፅናት ካልተገኘ፤ ሌሎችን ስህተቶች ለማረም የረዥም ጊዜ ጥረትና ፅናት ከወዴት ይመጣል?

addis admas 

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar