lørdag 12. oktober 2013

አንዷለም አራጌ ለህገ ወጥ ድርጊት ባለመተባበሩ ጎብኚ እንዳይኖረው ተደረገ

October 11th, 2013
993428_527514320666840_1681692550_nበሽብርተኝነት ተከስሶ ዕድሜ ልክ እስራት ተበይኖበት በቃሊቲ ቅጣት ቤት የሚገኘው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ በጎብኚዎች እንዳይታይ መደረጉ አንድነት ፓርቲን አሳስቧል፡፡አንዷለም ፍርድ ከተላለፈበት በኋላ በማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ከጨረሱ እስረኞች ጋር መቀላቀል ይገባው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ሆን ተብሎ እርሱን ለመጉዳት ጊዜያዊ እስረኞች በሚገኙበት ‹‹ቅጣት ቤት ››ውስጥ እንዲታሰር መደረጉም ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
አንድነት መስከረም 19/2006 ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ለተገኙ ሰዎች በደብዳቤ መልእክቱን በሰደደው አንዷለም የተበሳጩ የሚመስሉት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ‹‹አንዷለምን መጠየቅ የሚችሉት ቤተሰቦቹ ብቻ ናቸው በማለት ጠያቂዎችን ሲያጉላሉ ከቆዮ በኋላ ከትናንትና መስከረም 29/2006 ጀምሮ በይፋ ማንንም አናስገባም ማለት ጀምረዋል፡፡
ከማረሚያ ቤቱ ባገኘነው መረጃ መሰረት የእስር ቤቱ ሃላፊዎች አንዷለምን ወደ ቢሮ በመጥራት ‹‹እንዲጠይቁህ የምንፈቅደው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነው፣ስለዚህ በጣም ቅርቤ የምትላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በመጻፍ ስጠን›› ይሉታል፡፡ሰላማዊው ታጋይ በበኩሉ በጠያቂዎች መጎብኘት ህገ መንግስታዊ መብቱ መሆኑን በመጥቀስ የማንንም ስም ጽፎ እንደማይሰጣቸው በመንገር ወደ ማረፊያው ተመልሷል፡፡
የአንዷለምን ምላሽ የሰሙ ሃላፊዎችም ማንኛውም (የአንዷለም) ጠያቂ ከበር እንዲመለስ የሚያደርግ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡በጉዳዮ ዙሪያ የፓርቲውን አቋም ያንጸባረቁት የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊው አቶ ዳንኤል ተፈራ ‹‹ድርጊቱ የመጀመሪያቸው አይደለም፣ የሆነ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር እንዲህ አይነት እርምጃዎችን ይወስዳሉ፣ሽብርተኛ በማለት ያሰሩት ሰው ምን ያህል ህገ መንግስታዊ መብቶቹን ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑንም እግረ መንገዱን አሳይቷቸዋል፡፡የአንዷለም ቁርጠኝነትና መብቴን አላስነካም ማለቱ እንደሁልግዜው አርአያችን ሆኖ ይቀጥላል ››ብለዋል፡፡ የእስር ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ እንዲህ አይነት ውሳኔ የተላለፈው ለእስረኞች ደህንነት ተብሎ ነው ብሏል፡፡አንዷለም አራጌ ከዚህ ቀደም በእስር ቤቱ ውስጥ ደረቅ ወንጀል በመፈጸም በታሰረ እስረኛ መደብደቡ አይዘነጋም፡፡
posted by Daniel tesfaye

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar