tirsdag 26. november 2013

ጠጉረ ልውጦች ከአራት ኪሎ እንጅ ከሶማሊያ ወይንም ከኢራቅ ይመጡ ይሆን?

………
ሰሞኑን በኢቲቪና በሬዲዮ፣ እንዲሁም ህዝቡን እየሰበሰቡ ‹‹ጠጉረ ልውጥ ሰው ካያችሁ ጠቁሙን!›› ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
ጠጉረ ልውጥ ማለት አገሪቱን አሊያም ህዝቡን የማያውቅ ማለት አይደለም፡፡ እሱማ ፈልጎም ሆነ አፈላልጎ ወደዛው ደርሷል፡፡ ጠጉረ ልውጥ የሚገኝባት አገርም ሆነ ህዝብ በውል የማያውቁት በዕድ ማለት ነው፡፡
አሁን ወደ ጥቆማው እንግባ፡፡ በእርግጠኝነት ጠቁሙ የተባልነው የውጭ አገር ዜጎችን አይደለም፡፡ እንደዛ ከሆነማ ቻይናዎቹንም አናውቃቸውም፡፡ የሶማሊያ ስደተኞችንስ ስናሳስር ልንውል ነው እንዴ? እኔ እንደሚመስለኝ እነሱ ጠጉረ ልውጥ ብለው ያተኮሩት ከ90 ሚሊዮኑ ህዝብ መካከል ነው፡፡ ስለሆነም ማተኮር የፈለኩት እዚሁ አገር ውስጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለተለያዩ ጉዳዮች በአገሪቱ ይዘዋወራሉ፡፡ በተለይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መነሃሪያ ነች፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች አዲስ አበባ ትንሽ መንደር አይደሉም፡፡ ሰውን እንዲሁ ‹‹ጠጉረ ልውጥ›› መሆን አለመሆን ማወቅ አይቻልም፡፡ ‹‹መንግስት›› የፈለገው ይህኛውን አይደለም፡፡ በተቃራኒው ከእሱና ከደጋፊዎቹ አንጻር ‹‹ፖለቲካ ልውጥ››፣ ‹‹ ብሄር ልውጥ››፣ ‹‹እምነት ልውጥ›› ያላቸውን ነው ጠቁሙን የሚለው፡፡ ሽብር እንዲህ በወሬ ሳይጦዝ ከ30ና 40 አመት በላይ የኖሩትን አርሶ አደሮች ‹‹ጠጉረ ልውጥ›› አድርገው አባርረዋቸዋል፡፡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ከጥቂቶቹ በስተቀር ኢትዮጵያውያን እስር ቤት ውስጥ ሊታጎሩ ነው፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም አካባቢ ይምጣ፣ የትኛውንም ቋንቋ ይናገር፣ የትኛውንም ብሄር ይምረጥ፣ ……ጠጉሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የከሳ፣ የጠቆረ፣ የተጎሳቆለ ከሆነ እሱ በድህነት የሚማቅቅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የተናደደ፣ አንገቱን የደፋ፣ ፊቱ ላይ በደል የምታይበት አንዳንዴም ጨርቁን ጥሎ ያበደ ከሆነ እሱ የተገፋ፣ አገሩን የተቀማ የአገርህ ሰው ነው፡፡ እነዚህን ኢትዮጵያውያን የበደል፣ የስቃይ፣ የጭቆና ጠጉር አንድ ያደርጋቸዋል፡፡
‹‹ስለ እውነት›› እያወራ የሚያፍረው፣ ስለ ‹‹ማንነቱ›› እየተናገረ የሚደነግጠው፣ ስለ ነጻነት እየተሰበከና እየሰበከ የሚገዛው፣ ስለ አንድነት እያወራ የሚከፋፈለው እሱ ዘመኑ የፈጠረው፣ ስርዓት ያበላሸው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህኛው በአንድ በኩል በጭቆናው ከጭቁኑ ያልተላቀቀ በሌላ በኩል ከገዥው ጋር በኪሱ የተገናኘ የዘመኑ ሆድ አደር ካድሬ ነው፡፡ አገሩም፣ ህዝቡም፣ ስርዓቱም፣ እራሱም ላይ እምነት እንደሌለው ግንባሩም፣ አይኑም፣ ድምጹም ላይ ትለይበታለህ፡፡ ይህ አንድ ደረጃ ከፍ ሲል ግን ጠጉሩን ይለውጣል፡፡
እንገቷን በደፋችው አገር በማን አለብኝነት ደረቱን የሚነፋው፣ ስታለቅስ የሚደሰተው፣ ስታነባ የማይጨንቀው፣ ስትራብ የሚያበሰናው፣ ኩርምት ባለችበት የሚቦርቀው፣ እንቅልፍ ባጣችበት ለሽ ብሎ የሚተኛው ይህ ኢትዮጵያ የማትለየው፣ ዜጎቿ ጋር ተገናኝቶ የማያውቅ ጠጉረ ልውጥ ነው፡፡ በቆረቆዘችበት የለማ፣ በጨለመችበት የበራው፣ በተጠማችበት የረካውና የሰከረው በምስኪኗ ኢትዮጵያና ዜጎቿ ዘንድ የማይታወቅ ባዕዳና ጠጉረ ልውጥ ነው፡፡
እነዚህ ጠጉረ ልውጦች ከአራት ኪሎ እንጅ ከሶማሊያ ወይንም ከኢራቅ አይመጡም፡፡ እንደ ሶማሊያውያኑ አሊያም ሌሎች መንገድ ላይም አናገኛቸውም፡፡ ከማያውቃቸው ህዝብ ለመራቅ መንገድ ዘግተው፣ ሰራዊት አሰልፈው የሚውሉት እነሱ ‹‹ጠጉረ ልውጦች›› ናቸው፡፡
አዎ! ሁሌም ባይሆን በአብዛኛው ጠጉረ ልውጥ ይሰርቃል፣ ያሸብራል፣ ይገድላል፡፡ የእኛዎቹ ጠጉረ ልውጦችም ግን ተግባራቸው ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በእርግጥ ስለ እነሱ መጠቆም መጠቋቆም አያስፈልግም ‹‹ቤተ መንግስት›› የሚሉት አገር ውስጥ መሽገዋል፡፡ ‹‹መንግስት›› የሚሉት ቡድን አቋቁመው ኢትዮጵያውያን የማያውቁት ጸጉር አከናንበውታል፡፡ ምን አልባትም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ጠጉረ ልውጥ በግል ሳይሆን በቡድን ያደማት፣ ያሸበራት፣ የዘረፋት አገር መሆኗ ነው፡፡ Getachew Shiferaw
source: freedom4ethiopian

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar