ጌታቸው ሽፈራው Getachew Shiferaw
getcholink@gmail.com
ትናንትና ኢቲቪ ‹‹የእኛ ጉዳይ›› ብሎ ስለ አልሻባብ ውይይት አቅርቧል፡፡ በእርግጥ እነ ኃ/ማሪያም ለገንዘብ ማግኛም ይሁን ለኢህአዴጋዊ ጀብድ በየ መድረኩ ‹‹አልሻባብ ተንኮታኩቷል›› ከሚሉት በተቃራኒ አልሻብብ አሁንም አስፈሪ፣ ስራ አጥነት መቅረፍ የግድ መሆኑን፣…..ሌላም ሌላም ከኢቲቪ የተለዩ የሚመስሉ ሀሳቦች በተወያዮቹ ተነስተዋል፡፡ እውን እነ ኃ/ማሪያም ከሰሙ ‹‹የአሸባሪዎች ስልታቸው እንጅ ጥያቄያቸው ተገቢ (ሌጅቲሜት) ነው››ም ተብሏል፡፡ ነገሩ ተወያዮቹ ከነ ሽመልስ፣ በረከት፣ ኃ/ማሪያም እንደሚሉዩ ማየት የሚቻለው ስለ ኢትዮጵያ ‹‹ሽብርተኛ›› ብዙም አለማለታቸው ነው፡፡
ሆኖም በስተመጨረሻ ‹‹ሽብርን ለመግታት አስቀድሞ መረጃ ስለመስጠት፣ ከፖሊስ ጋር ስለመስራት….›› የተሰጠው ማሳሰቢያ ከእነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጉትጎታ ጋር የው ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የኮሚኒቲ ፖሊስ፣ ደህንነትም ሆነ ሌሎቹ ‹‹አሸባሪ›› ብለው መረጃ አሰባሰብን ብለው ያሰሯቸው ኢትዮጵያውያን ፈንጅ ለማፈንዳት ይቅርና ፈንጅ እንኳን በእጃቸው ነክተው የማያውቁ ናቸው፡፡ እስክንድር ነጋ የታሰረው ፌስ ቡክ ላይ እየጻፈ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ርዕዮት አለሙ አሸባሪ ተብላ የተያዘችው ‹‹በቃ!›› በሚል አዲስ አበባ ውስጥ የተለጠፈን ጽሁፍ ፎቶ ስታነሳ በመገኘቷ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ አቡበክርና ሌሎች የኮሚቴው አባላት፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ…… ይልቅ የኢህአዴግ ታጋይና ካድሬዎች ለፈንጅና ሽብር ቅርቦች ናቸው፡፡
እውነቱን ለመናገር ፌስ ቡክ ወይንም ድህረ ገጽ ላይ ጽሁፍ ሲለጥፍ አሊያም ሲያነብ የተገኘን ሁሉ ይጠቆም ማለት ሌላ መንግስታዊ ሽብር፣ ሌላ እብደት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በይፋ ኢንተርኔትና ኢንተርኔት ቤቶችን መዝጋት ይቀላል፡፡ ካልሆነ የአቶ መለስን ፎቶ ለማየት፤ አይጋ ፎረፍም፣ ኢርታን አሊያም ሌላ የፓርቲውን ፕሮፖጋንዳ የሚያሰራጩትን ለማንበብ የሚገባ ጀማሪ ካድሬም ካልሆነ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡
በእርግጥ ‹‹መረጃ የማሰባሰቡን›› ስራ ከጀመሩት ቆይተዋል፡፡ ኢንተርኔት ቤት ባለቤቶችና ሰራተኞቻቸውን ‹‹የተለየ ነገር የሚጽፍ ሰው ካጋጠማችሁ ሪፖርት አድርጉ!›› እንደሚሏቸው ብዙዎቹ አረጋግጠውልኛል፡፡ እንግዲህ የተለየ የሚጽፈውን ለማወቅ ‹‹ቻት›› የሚያደርገውን ሁሉ ለአልሻባብ ይሆን ለሌላ መሆኑን ማለት ሊኖርባቸው ነው፡፡ ፌስ ቡክ፣ ቲውተር…ብቻ ኢንተርኔት ላይ የተለየ የሚጽፍን ሰው እንዴት ማወቅ ይቻላል? ራሱ የተለየ ማለትስ ምን ማለት ይሆን? መቼም ደህንነቶቹ ስለ ሽብር ከሚያወራ ይልቅ የባለስልጣናትን አስቂኝ ፎቶ የለጠፈን ‹‹አሸባሪ!›› ብለው ከረቼሌ እንደሚከቱት አያጠራጥርም፡፡
ታዲያ በአዜብ መስፍን፣ አባዲላ፣ በረከት፣ ሽመልስ…….የቀለደ፣ ፎቷቸውን ያጣመመ፣ ያጣመሙት ሀሳብ ላይ ትችት ያቀረበ ሁሉ ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ መረጃ ከተሰባሰበበት የሚቀረው ማን ነው? የሴቶች፣ የወጣቶች…..ሊግ አባላትማ ከፌስ ቡክ ይልቅ ስብሰባ ማዕከል፣ ቀበሌ ውስጥ ነው ተሰብስበው የሚውሉት፡፡ ተዘግቶም ቢሆን ኢቲቪን ቢያፈጡበት ይወዳሉ፡፡ እንዲያው ኢንተርኔት ቤት ቢያዘወትሩስ ማን መረጃ ያሰባስብላቸዋል? ሌላ አካባቢስ ማን ጆሮ ይጠባላቸዋል? የድጋፍ ሰልፉስ? አሸባሪነት ካድሬ በመሆንና ባለመሆን፣ ድምጽን ከፍ አድርጎ በመጠየቅና ባለመጠየቅ፣ ስለ ሰብአዊነት በመቆምና ባለመቆም መካከል የተቀመጠ ማሸማቀቂያ ካልሆነ በስተቀር ምን ሊባል ይችላል?
‹‹በቃ›› የሚልን ብቻ ሳይሆን ፈንጅ የሚያጠምድን አሸባሪ ፎቶ ማንሳት ወይንም ስለ ጉዳዩ መጻፍ የጋዜጠኛ ስራ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ጉዳይ መረጃ መስጠት የሚደፍር ጤነኛ ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ መስጠትም አያስፈልገውም፡፡ መስጠት ቢያስፈልግ ግን አሸባሪ መባል ያለባቸው ለምን ‹‹በቃ›› ተብሎ እንደተጻፈ ሳያውቁ ጉዳዩን ሽብር አድርገው የሚቆጥሩት ናቸው፡፡ እውነተኛና ሽብርን የሚዋጋ መንግስት ቢሆር ‹‹በቃ›› ያለውን ሲያጡ በንዴት ፎቶ ግራፉን የሚያነሱትን ጋዜጠኞች የሚያስሩት ካድሬዎች ላይ ነው መረጃ መሳባሰብም መጠቆምም ያስፈልግ የነበረው፡፡
በግልጽ የሚታየው ‹‹አሸባሪነት›› መጀመሪያ መቀረፍ ይኖርበታል፡፡ ይልቁንስ ‹‹በቃ›› ከሚባለውና ለኢህአዴግ ከፈንጅም በላይ ከሚያስበረግገው ጉዳይ በስተጀርባ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጭቆና እና ኢፍትሃዊነት ጥቆማ መስጠት ቢቀድም የተሻለ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ስለ አሸባሪ ማውራት ይቻል ይሆናል፡፡ ምዕራባዊያን ዜጎቻቸው ትምህርት ቤትም ሆነ ሌላ ቦታ ሰው ሲፈጁ ንክ፣ እብድ እንጅ አሸባሪ ብለው አይጠሯቸውም፡፡ አንድ ከመካከለኛው ምስራቅ የመጣ ሸክ መስጊድ ውስጥ ምዕራባዉያንን የሚያጥላላ ሰበካ ሲያደርግ ግን አሸባሪ ይሉታል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ወደ ተቃዋሚና አባልነት አውርዶታል፡፡ ከወራት በፊት ባህርዳር ላይ ንጹሃንን የጨፈጨፈው ፖሊስ ለስርዓቱ የቀመ ስለነበር አሸባሪ አልተባለም፡፡ ለፖለቲካው ይጠቅም ዘንድ የሸክ ኑሩ ሞት ሽብር ተደረገ፡፡ ድራማ ነው የሚባለው እንዳለ ሆኖ ኢህአዴግ ባህርዳር ላይ ንጹሃንን የቀጠፈው ፖሊስ አንድ ቀን ከተቃዋሚዎች ስብሰባ ላይ መገኘቱ መረጃ ቢሆረው ተቃዋሚዎቹን በቀጥታ ከአልቃይዳ ጋር አገናኝቶ ለመውቀጥ ጊዜ አይፈጅበትም ነበር፡፡ የባህርዳሩም ሆነ የሸህ ኑሩው ድራማ ላለመሆኑ ምንም ማስረጃ አልተገኘም፡፡ ሽብርተኝነትን በንጹሃን ላይ የሚተውነውንና ‹‹ጠቁሙን›› የምትሉንን ሽብርተኛ በምን መለየት እንችላለን? ለኢህአዴግን የስልጣን ጥያቄ፣ ሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲ፣ የአገር ጉዳይ፣ የሀይማኖት ጉዳይ፣ ሰላማዊ ሰልፍ…..ማንሳት ሽብርተኝነት ነው፡፡ ከእስክርቢቶ ውጭ ይዘው የማያውቁትን ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ሰልፈኞችና ሌሎችም ፈንጅና መሳሪያ ከያዙት በላይ ያስፈሩታል፡፡ አገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚዎች ይልቅ በየ ቀኑ ‹‹ ተስማማ፣ ተፈራረመ…›› ሲባል የምንሰማው መሳሪያ አንግተው አብረውት ካደጉት ኦብነግና ኦነግ ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አይነት ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ይግባባሉ፡፡ አልሻባብም ቢሆን ለመደራደር ስላልፈለገ ይሆናል እንጅ ኢህአዴግ ከሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ ቀድሞ ሊደራደረው እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ የኦብነግንና የኦነግን መሪዎች ‹‹ምህረት›› ተደርጎላቸው፣ ቤትና መኪና ተሰጥቷቸው እየኖሩ እነ ርዕዮት፣ በቀለ፣ እስክንድር፣ አቡበክር ላይ ጥቆማም ሆነ እስራት ሲደረግ ‹‹ሽብር›› ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ልክ እንደ እነ ርዕዮት፣ በቀለ፣ አንዱአለም፣ አቡበክር፣ እስክንድር የሰብአዊ መብቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል፡፡ በእምነቱ ጣልቃ የሚገቡበትን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ፍትህ ይፈልጋል፡፡ መብቱ እንዲከበርለት ይከራከራል፡፡ ይህን ሁሉ ታዲያ ጮህ ብሎ ሲናገር ለኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ መብት ጠያቄ፣ የፌስ ቡክ፣ ቲውተር፣….ኢንተርኔት ተጠቃሚ ላይ እንዴት ጥቆማ ማድረግ ይቻላል? ስንቱን አሸባሪ ላይ መረጃ ተሰጥቶበት ያልቃል? ለምንስ ተብሎ?
የሚያሳዝነው ደግሞ እንዲህ አዘናግተውን፣ እንዲህ የሽብርን ትርጉም አጥፍተውብን እውነተኛዎቹ አሸባሪዎች ሲመጡ የምንጎዳው እኛው መሆናችን ነው፡፡ መቼም መንገድ አስዘግተው የሚጓዙት ባለስልጣናት ላይ ፈንጅ ሊፈነዳ አይችልም፡፡ ቤተ መንግስት ውስጥም ቢሆን የፓርቲው ልዩነት ካልሆነ በስተቀር (ሲጠበቅ በጣም ዘገየ) ፈንጅ አይፈነዳም፡፡ እነሱማ ምን ይሆናሉ?
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar