søndag 10. november 2013

ያለ ፕሬስ ከሚኖር መንግሥት ያለ መንግሥት የሚኖር ፕሬስ እመርጣለሁ››

ቶማስ ጃፈርሰን

Posted: November 9, 2013 in Uncategorized

 
በብዙ ሺ ወጣት ኢትዮጵያውያን ደም ወደ ሥልጣን የመጣው ኢህአዴግ የሚሊዮኖች ተስፋ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትን ወደ ጎን በማለት የጥቂት ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት መገንቢያ ከሆነና ሥርዓቱ ከዴሞክራሲያዊነት ይልቅ የአምባገነንነትን መስመር ከተከተለ 21 ዓመታት አልፈዋል፡፡
በዚህ 21 ዓመታት ውስጥ ሥርዓቱ የፈፀማቸውን በርካታ ህገ-ወጥ ድርጊቶች መዘርዘር የሚገድ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ከመሠረቱ ባህሪው ዴሞክራሲያዊ ባይሆንም የቀዝቃዛውን ጦርነት ማክተም ተከትሎ የሶቭዬት ጎራ በመፈራረሱ ሳይወድ በግድ ወደ ምዕራባዊያን መጠጋቱና እንዲሁም የዓለም እርዳታ ሰጪዎች፣ አበዳሪ ባንኮች በመፈለጉ እውነተኛ ባህሪውን ደብቆ የዴሞክራሲ ለምድ በማጥለቅ የነፃ ገበያ አራማጅ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ባለሟል መስሎ መታዬቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ሥርዓቱ ወደ ገዢነት በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ህገ-መንግሥት በማጽደቅ የማይፈጽማቸው ግን ደግሞ የፖለቲካ ትርፍ ሊያገኝባቸው የሚያስችሉ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስጠብቁ አንቀፆች በስፋት ማካተቱ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዜጎች በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት እንዲችሉ ጉልህ ሚና የሚጫወተው አንዱና ዋናው ነፃ ሚዲያ (independent media) በመሆኑ ይህንኑ መፈቀድና የሳንሱር ህግን ማስቀረት አንዱ ነው፡፡ ሚዛናዊና አስተዋይ አዕምሮ ላለው ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ሆኖ የሚታየው ግን ነፃው ፕሬስ የሚደረስበት እስር እንግልት ወከባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ከመሄዱ በአሻገር በአሳሪ የፕሬስ ሕግ እግር ከወርች ተጠፍሮ ሥራውንና ኃላፊነቱ እንዳይወጣና እንዲሽመደመድ መደረገ ነው፡፡
የፕሬስ ሥራ ፍፁም ነፃነት እንደሚያስፈልገው መድረክ አጥብቆ ያምናል፡፡ ነፃ ፕሬስም ለልማትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑም እውነት ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሰፈኑባቸው አገራት ነፃ ፕሬስ አራተኛው የመንግሥት አካል ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ልክ እንደ ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈፃሚውና እንደ ፍርድ ቤቶች ሁሉ፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው ነፃ ፕሬስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሕግ የበላይነት መጠበቅ ለግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራር ወሳኝ ሚና እንዳልው ነው፡፡ ኢህአዴግ በነፃው ፕሬስ ላይ ጥላቻ ያደረበትና ሰለባው ያደረገው ያለምንም ጥርጥር በዴሞክራሲ ስለማያምን ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግ ነፃ ፕሬስ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን መብቶች በጠራራ ፀሐይ ይነጥቃል፤ በርካታ ጋዜጦችና ጋዜጠኞችን አምባገነናዊ በትሩን አሳርፎባቸዋል፡፡ ጋዜጦች ታይተው እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ ጋዜጠኞች ለሰደት ተዳርገዋል፡፡
ኢህአዴግ ዓይን በአወጣ መልኩ በነፃው ፕሬስ ላይ የህግ ጥሰት መፈፀም የጀመረው ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ነው፡፡ የ97 ዓመቱን ምርጫ በጉልበት የነጠቀው ኢህአዴግ የእሱን ዓላማ የማያራምዱትንና ነፃ ናቸው የሚባሉ ጋዜጦችን በጠቅላላ በመዘጋት እና ጋዜጠኞችን በማሰር ሠፊና ሕገ ወጥ ርምጃ ወስዷል፡፡ ፕሬስም ትልቅ ፈተና ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ ለአብነትም የ1997 ዓም ምርጫን ተከትሎ በተለያዩ ጫናዎች ከ23 በላይ የግል ጋዜጦች እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡ በመቀጠልም ጣም እውቅ ከሆኑ ነፃ ጋዜጦች መካከልም አዲስ ነገር፣ አውራምባ ታይምስና ሌሎችም ጋዜጦች ከህትመት እንዲወጡ በማድረግ እና ዜጎች እንዳይገቡ ፈቃድ በመከልከል ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን ሚና አደናቅፈዋል፡፡
ኢህአዴግ ከልማታዊ ወሬዎች ውጭ ጠንካራ የፖለቲካ ትችቾችን በመፍራቱ አዲስ ነገርን፣ አውራምባ ታይምስንና ፍትሕን በጠላትነት ማየት የጀመረው ገና ከማለዳው ነበር፡፡ እግር ሳያወጡ መቁረጥ በሚል የተበላሸ ፖሊሲውም የመንግሥት ሚዲያ የሆኑትን አዲስ ዘመንንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በመጠቀም ዘመቻ ተከፍቶባቸው ነበር፡፡ ከጋዜጠኞቹ እንደሚሰማው ዛቻና ክትትሉ የተለመደ ነበር፡፡ እናስራችኋለን የሚል አይን ያወጣ ማስፈራሪያም ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይህ ጫና የበረታባቸው የአዲስ ነገርና የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኞች ለጊዜውም ቢሆን ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች ‹‹ከኢትዮጵያ ውጭ ሀገር የለንም›› የሚል ጠንካራ ሀገራዊ መፈክር በማንሳትና ሥርዓቱ እንዲስተካከል የሚረዱ ፖለቲካዊ ትችቶችንና ትንታኔዎችን ለኢትዮጵያውያን በማቅረብ በጽናት ስራቸውን ቀጥለው ነበር፡፡
መሰደድንም አንቀበልም፣ መፃፍ ማሳተምንም አናቆምም ያሉትን በጽናት የቆሙትን የፍትህ ባለቤትና ጋዜጠኞችን መንግሥት ህገ-ወጥ ርምጃ ወስዶባቸዋል፡፡ የሐምሌ 13 ቀን 2ዐዐ4 የፍትሕ ጋዜጣ ሕትመት በፍትሕ ሚኒስቴርና በአቃቢ ህግና መስሪያ ቤት አማካኝነት እንዳይሰራጭ ተደርጓል፡፡ በዚህም ሳያበቃ በሳምንቱ ሐምሌ 2ዐ ቀን ለሕትመት የተዘጋጀውን ጋዜጣ ብርሃንና ሠላም የተባለው የመንግሥት ማተሚያ ድርጅት ማተም አልችልም በማለት ህጋዊ ኃላፊነቱን ወደ ጎን በመተውና የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ በመዘንጋት ‹‹ፍትሕ ሚንስቴር በደብዳቤ አትሙ ካላለ አላትምም›› የሚል የሚል መልስ በመስጠት የሕግ ጥሰቱ ተባባሪ ሆኗል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴርም ለማተሚያ ቤቱ ተገቢውን መመሪያ በመስጠት ህትመቱ እንዲቀጥል በማድረግ ፈንታ ‹‹የከለከልነው አንዱን ህትም ብቻ ነው›› በማለት በእጅ አዙር መንገድ ክልከላው ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጉን ከጋዜጣው አዘጋጆች ተረድተናል፡፡ በሌላ በኩልም ፍትሕ ሚኒስቴር የተከለከለው ህትመት የሐምሌ 13 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ብቻ መሆኑን ለማተሚያ ቤቱ ደብዳቤ እንዲጽፍ ሲጠየቅ እምቢ ማለቱ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡
በጠቅላላው በነፃው ሚዲያ ላይ በተለይም ደግሞ በፍትህ ጋዜጣ ላይ እየተወሰደ ያለው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ርምጃ የሥርዓቱን ፍፁም አምባገነንነት፣ ማን አለብኝነትና ለዜጎች ክብር የማይሰጥ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለሆነም መድረክ ፍትሕ ጋዜጣ ወደ መደበኛ ህትመት በአስቸኳይ እንድትመለስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ ገዢው ፓርቲ በነፃ ጋዜጦች ላይ የከፈተውን የማጥፋት ዘመቻ እንዲያቆም እንጠይቃለን ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ህገ-ወጥ ድርጊት እንዲቃወም ጥሪ እናስተላልፋለን››፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ሐምሌ 25 ቀን 2ዐዐ4 ዓም
አዲስ አበባ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar