onsdag 27. november 2013

አና ጐሜዝ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ገንቢና ግልጽ ውይይቶችን አደረግኩ አሉ

Posted: November 27, 2013 in Uncategorized

አና ጐሜዝ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ገንቢና ግልጽ ውይይቶችን አደረግኩ አሉ
ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተካሄደው የግንቦት 1997ቱ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረትን በመወከል የምርጫ ታዛቢ የነበሩት ፖርቱጋላዊቷ አና ጐሜዝ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ፡፡
ዛሬ በሚጠናቀቀው የአፍሪካ፣ የካሪቢያን፣ የፓስፊክና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ የፓርላማ 26ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመካፈል አዲስ አበባ የመጡት አና ጐሜዝ፣ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ገንቢና ግልጽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የጋራ ስብሰባው ላይ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ የመጡት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባልና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁት አና ጐሜዝ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ምንም ዓይነት የቪዛ ችግር እንዳልገጠማቸው ገልጸው ይህም አዲስ ዓይነት የፖለቲካ አተያይ እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ በኢትዮጵያ የተለየ የፖለቲካ አተያይ አለ ያሉት አና ጐሜዝ፣ አጠቃላይ የፖለቲካው ምህዳር ግን ከ1997ቱ ምርጫ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የባሰ ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ «ከ1997 ምርጫ ቀደም ብሎ ተስፋ ይታይበት የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ምህዳር በምርጫው ምክንያት በተፈጠረው ቀውስ ከምርጫው በፊት ወደነበረበት አስከፊ ሁኔታ ተመልሷል፤» በማለት መንግሥትን ተችተዋል፡፡
ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት ከምርጫው በኋላ የወጡትን ሕጐች በምሳሌነት በማቅረብ ነው፡፡ «ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት መታሰራቸው፣ የሲቪክ ማኅበራት መፈናፈኛ ማጣታቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የመሳሰሉት ነገሮች በአሉታዊነት የሚነሱ ናቸው፤» በማለት ተናግረዋል፡፡
«ከሁሉም በተለየ ሁኔታ ግን መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ያለአግባብ በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ፀጥ ለማድረግ እያዋለው ነው፤» በማለት አና ጐሜዝ ከፍተኛ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን፣ በዚህም ጉዳይ ላይ ከአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና  ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩ አብራርተዋል፡፡
ምንም እንኳን የውይይቱን ዐበይት ነጥቦች በዝርዝር ከመግለጽ ቢቆጠቡም ውይይቱ ግን ገንቢ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ውይይቱ በዋነኛነት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታት፣ ለሲቪክ ማኅበረሰቡ የምርጫ ሜዳውን ማስፋት፣ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማጠናከር የሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በዝርዝር የተወያዩ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ፣ አና ጐሜዝ ከመንግሥት ወገን ያገኙትን ምላሽ ምን እንደሆነ ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስተዳደር የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አና ጐሜዝ፣ በተለይ ሙስናን በተመለከተ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊበረታታ እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡
የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በጋራ ስብሰባው ጥያቄ መቅረቡን ያመለከቱት አና ጐሜዝ፣ የመንግሥትን ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነም አክለው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ግለሰባዊ ችግር እንደሌለባቸው የገለጹት አና ጐሜዝ፣ ሥራዬን ግን በአግባቡ የመወጣት ግዴታ አለብኝ ብለዋል፡፡
የጋራ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሲሆኑ፣ በአባል አገሮች ሕገ መንግሥታት ላይ የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍንና የፖለቲካ ምህዳሩ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሰፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡን ለመደገፍ፣ ፍትሕና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ ሙስናን ለመዋጋት እንዲሁም የሥነ ዜጋ ትምህርትን ለማስፋፋትና ለማጐልበት ተቋማዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ዙሪያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በጥምረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ግንኙነቱ ግን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡
የአፍሪካ፣ የካሪቢያን፣ የፓስፊክና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ የፓርላማ ስብሰባ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ethiopianreporte
r

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar