ምንሊክ ሳልሳዊ ብሎግ |
ጌታቸው ሽፈራው Getachew Shiferawgetcholink@gmail.com
ከፖለቲካ ለመራቅ መሞከር ሰው የመሆንን ማንነት መካድ፣ ሰው ከሚባለው ማንነት መውጣት ያህልን ከባድና የማይቻል ነው፡፡ ይልቁን የማይርቁትን ነገር ለመራቅ ከመሞከር ይልቅ የሰውነት ክብርን ማጠናከር፣ ማንነትን፣ ክብርን ማስከበር የመሰለ ነገር የለም፡፡ ይህን አልችልም የሚል እንኳ ትርፉ ባርነት ነው፡፡ በፈቃዱ ከተጨቆነ ሰው(ባሪያ) ወጥቶ ውሻ ወይንም ዶሮ ለመሆን ቅንጣት አቅም ያለው ‹‹የፖለቲካ እንሰሳ›› የለምና፡፡
እንደ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ቃላት ሁሉ ‹‹ፖለቲካ›› ራሱ ምንጩ ከግሪክ ነው፡፡ በግሪካዊያኑ ቋንቋ ፖለቲኮስ (politikos) ለዜጎች ወይንም ከዜጎች ጋር የተገናኘ የሚል ትርጉም አለው፡፡ ግሪካዊ ትርጉሙ በዜጎች ጉዳይ ላይ በህዝብን ወይንም በግለሰቦች ዘንድ ተቀባይነት፣ ይሁንታቸውን፣ ትኩረታቸውን የማግኘትና የመሳብ ተግባር ወይንም ንድፈ ሃሰብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ከግሪኮቹ ዜጎች በቀጥታ የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊና የከተማ መንግስት አልፎ አገራት ሲጠናከሩና አምባገነን መንግስታት ስልጣን ላይ ሲወጡ ‹‹ፖለቲካውን›› የሚዘውረው መንግስት፣ ፓርቲ፣ ግለሰቦች ብቻ ወደመሆን ቢያቀኑም በውስጡ ግን ያለ ዜጎች ተሳትፎ ሊሆን አልቻለም፡: የፖለቲካ ስርዓቱ የሚመራው ዴሞክራሲያዊም ሆነ አምባገነን መንግስታት ‹‹ፖለቲካ›› መቸውንም መኖሩ አይቀርም፡፡ በካድሬዊ፣ ወታደራዊ አሊያም ሌላ መንገድ የመሳብ፣ የህዝብን ይሁንታ የማግኘትም ይሁን በሌላ መልኩ ህዝብ በፖለቲካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ነው፡፡
ነገር ግን ይህ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚፈጥረው ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ስርዓት ‹‹ፖለቲካ›› አለመኖን ሊያሳይ አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ባልሆኑ አገራት ህዝብ ተታልሎ፣ ተገዶ፣ ተገፍቶም ቢሆን ከመንግስት ጎን ይቆማል፡፡ አሊያም ይከተላል፡፡ አሊያም በዝምታው ሌሎች በስልጣን ላይ እንዲፈነጩ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ይህኛውን ያልፈለገና የተመረረው ደግሞ ከተቃዋሚዎች አሊያም አማጺያን ጎን ለመቆም ይገደዳል፡፡
‹‹ፖለቲካ›› የሰዎች ብቻ ተግባር ………… ፖለቲካ ሰዎች ከሌሎች እንሰሳት በተለየ እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት መስተጋብር የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ በእርግጥ ሌሎች እንሰሳትም የእርስ በእርስ መስተጋብር አላቸው፡፡ አብረው ይኖራሉ፡፡ ግጭት ውስጥም ይገባሉ፡፡ አንዱ የሌላኛው የበላይ ይሆናል፡፡ ሆኖም ይህ የሰው ልጅ እንደሚያደርገው በስልት፣ በስትራቴጅ፣ በእቅድ የተመራና ውስብስብ አይደለም፡፡ በርካቶቹ እንሰሳት የሰው ልጅ እንደሚያደርገው በበላይነት ለመግዛት፣ የራሳቸው ነው የሚሉትን አገር ስለመገንባት የሚያስቡ አይደሉም፡፡ ዛሬን በማገናዘብ፣ ነገን በማለምም ላይም የሰው ልጅ ብቸኛው እንሰሳ ነው፡፡ ስለዚህም ይመስላል ፈላስፋው አርስቶትል ‹‹ሰው ፖለቲካዊ እንሰሳ ነው!›› የሚል ታላቅ አባባልን ጥሎ ያለፈው፡፡
ፖለቲካ የመተዳደር፣ የማስተዳደር ብቻ ሳይሆን የማንነት፣ የክብርም ጉዳይ ነው፡፡ ፖለቲካ የክብርም ጉዳይ ጭምር ነው ካልን እንደ ሰው ለክብሩ የሚጨነቅ እንሰሳ ደግሞ አናገኝም፡፡ ሰው ስለ ‹‹ዘር ግንዱ››፣ ቋንቋው፣ የስልጣን እርከኑ፣ ፖለቲካው፣ ማህበራዊ ደረጃው፣ ስሙ ብቻ ስለሁለመናው የሚጨነቅ ብቸኛው እንሰሳ ነው፡፡ አህያ፣ ውሻ፣ ዶሮ፣ አሳማ እነዚህ ማንነቶች የሏቸውም፡፡ አሊያም በድምጻቸው፣ በመልካቸው…….አንዱ ሌላኛውን ሲንቅ አይተይም፡፡ ወይንም ሌላኛው በተሰጠው ‹‹ማንነት›› አያፍርም፡፡ ለማስመለስ አይጥርም፡፡ ይህን ያህል ስለ ማንነት የማያውቀው ህጻን እንኳ ሲሰድቡት የሚያለቅሰው፣ የሚያኮርፈው ገና ከልጅነቱ ‹‹የፖለቲካ እንሰሳ›› በመሆኑ ነው፡፡ እናም ፖለቲካ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የሚተገብረው ዋነኛው መገለጫ ነው፡፡ ፖለቲካና ብልሹ ፖለቲካ ………… ፖለቲካ የዜጎችን ጉዳይ ጋር የተያያዘ፣ የክብር፣ የማንነት ጉዳይ እንደመሆኑ በተለይ በአምባገነኖች ከመርህ ውጭ ይጠቀሙበታል፡፡ ሆኖም ይህ የአምባገነኖች ተግባር ፖለቲካ እንደሌለ የሚያሳይ አይደለም፡፡ አሊያም ፖለቲካን በጅምላ ጭፍጨፋ፣ አምባገነንነት፣ የራስን ጥቅም ማሳደድ፣ ጦርነት፣ ሙስና………የመሳሰሉት ብልሹነቶች ጋር አያመሳስለውም፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ስርዓቶች የሚኖረው ፖለቲካ ብልሹ ፖለቲካ ነው፡፡ ስርዓቶቹ ፖለቲካን በመልካም ጎኑ መጠቀም ሲገባቸው ለራሳቸው ጥቅም አውለውታል፡፡ ዜጎችን ቀስቅሰው፣ አሳትፈው አገር መገንባት፣ ጥቅማቸውንና ደህንነታቸውን ማስከበርና ማስጠበቅ ሲኖርባቸው የራሳቸውን ብቻ ጥቅምና ክብር አስጠብቀውበታልና ፖለቲካው ተበላሽታል፡፡ ብልሹ ፖለቲካ በሰፈነባቸው አገራት ዜጎች ‹‹ፖለቲካን›› በጥቅሉ አሉታዊ አድርገው ሲፈርጁት ይታያል፡፡ በእነዚህ አገራት ፖለቲካ ማለት ንቅዘት፣ አምባገነንነት፣ ጦርነት፣ ማስገደድ፣ አፈና፣ ……..እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ከፖለቲካው ይርቃሉ፡፡ ይጠሉታልም፡፡ ይህን ተከትሎ ነው እንግዲህ ፖለቲካ አልወድም፡፡ የሚሉት የሚበረክቱት፡፡ አብዛኛዎቻችን ‹‹ፖለቲካን አንወድም!›› ስንልም መለየት የተሳነን በፖለቲካና በብልሹ ፖለቲካ መካከል ያለውን ልዩነት ነው፡፡ ፖለቲካ ከሙስና፣ ንቅዘት፣ ውሸት፣ ፕሮፖጋንዳ፣ …..እና መሰል ብልሹ ፖለቲካዎች ጋር ከሚመሳሰልባቸው አገራት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዚህም አብዛኛው ህዝብቻን ‹‹ፖለቲካ አልወደም፣ አታነካኩኝ….›› ማለቱ የተለመደ ሆኗል፡፡ ፖለቲካን ከጠሉት……. ………… ፖለቲካ ‹‹በዜጎች ጉዳይ ላይ በህዝብን ወይንም በግለሰቦች ዘንድ ተቀባይነት፣ ይሁንታቸውን፣ ትኩረታቸውን የማግኘትና የመሳብ የመሳብ ተግባር ወይንም ንድፈ ሃሰብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡›› ብለናል፡፡ በመሆኑም በብልሹ ፖለቲካ ምክንያት ‹‹ፖለቲካን አልወድም፣ ምን ያደርግልኛል፣ ይቅርብኝ!›› የሚሉ ከሆነ በዜጎችና በመንግስት ጉዳይ ያለው ማንኛውም ጉዳይ፣ ተግባር፣ ሂደት ላይ ምንም አያገባኝም እንዳሉ ይቁጠሩት‹‹ የአርስቶትልን አባባል ስንወስደው ደግሞ ይበልጡን ከዚህ አዙሪት እንደማይወጡ ይረዱታል፡፡ ‹‹ሰው ፖለቲካዊ እንሰሳ ነው›› ብሏል አርስቶትል፡፡ ከዚህ ማዕቀፍም የለሁበትም ካሉ ሲሰደቡ፣ ሲዘረፉ፣ ሲዘለፉ፣ ሲጨቆኑ፣ ሲበዘበዙ………… ምንም አይነት ሰዋዊ ስሜት፣ ቅሬታ፣ ሊሰማወት አይገባም፡፡ የሌሎች ሰዎች በደል፣ አገር ግንባታ ችግር፣ የመንግስት አስተዳደር፣ ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነት፣ ሰቆቃ፣………ብቻ በሰውና በአገር ብሎም በዓለም የሚከሰቱ ሰው ሰራሽም ሆነ ሌሎች ክስተቶች ምንም ሊያስጨንቅወት፣ ሊያሳዝንወት አይገባም፡፡
ፖለቲካ ምንወትም ካልሆነ ባርነት ምንዎትም አይሆንም፡፡ አህያ ይጫናል፡፡ በሬ ይታረሳል፡፡ አህያ የሚጨንቀው የሰው ንብረት መሆኑ፣ ለጭነት የሰዘጋጀ መሆኑ አይደለም፡፡ የሚጨነቀው ሲጫንና ሲከብደው ብቻ እንጅ ማህበራዊ ደረጃው፣ የሚሰጠው ክብር፣ ምግብ (ኢኮኖሚ)፣ ከሌሎች ጋር ያለበት መድሎ (ለምሳሌ ከፈረሰም ቢሆን) አይደለም፡፡ በቃ ጭነቱ ካልከበደው ለእሱ ሁሉም ነገር መልካም ነው፡፡ ጭነቱ በዝቶበትም ቢሆን ከጭቆና፣ ከአህያነት ደረጃ አያየውም፡፡ ከመሰሎቹ ጋር ተደራጅቶም ሆነ በግል ነጻ ለመውጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡ ለአህያ የማንነትና የክበር ነገር ተብሎ አይታሰበውም፡፡
እናም ‹‹ፖለቲካ አልወድም›› እያሉ የሚሸሹ ከሆነ የሚወጡት ከሰውነት ደረጃ ነው ማለት ነው፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ክብር፣ ማንነቱና አሊያም እነዚን ማንነቶች በበላይነት በመቆጣጠር አሊያም በማስመለስ ደረጃ መጠመዱ ከሆነ ዝምታን የመረጠ ከፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ‹‹ከሰውነትም›› ለመውጣት የመታገልን ያህል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሰውን ሰው ያደረገው ፖለቲካ ነው ማለትም ሳይቻል አልቀረም፡፡ ለአብነት ያህል በአንጻራዊነት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚኖሩቱ ዜጎች የዜግነት ደረጃቸው በአምባገነንነት ስርዓት ውስጥ ከሚኖሩት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው፡፡ ይህን ያደረገውም ዜጎቹ በፖለቲካው ያላቸው ተሳትፎና ከብልሹ ፖለቲካ የተሻለ ስለሚሆን ነው፡፡ ቢያንስ የተሻለ ሰው አድርጓቸዋል፡፡ ብልሹ ፖለቲካ በነገሰበትም ቢሆን ከማይጠይቁት ይልቅ የሚጠይቁት ቀድመው ዜግነታቸውን ክብር ያስጠብቃሉ፡፡ አሊያም ቢያንስ እስር ቤትም ሆነው ቢሆን የመንፈስ ልዕልና ያላቸው፣ ለነጻነትና ክብራቸው የማይፈሩ ይሆናሉ፡፡
ስለሆነም ከፖለቲካ ለመራቅ መሞከር ሰው የመሆንን ማንነት መካድ፣ ሰው ከሚባለው ማንነት መውጣት ያህልን ከባድና የማይቻል ነው፡፡ ይልቁን የማይርቁትን ነገር ለመራቅ ከመሞከር ይልቅ የሰውነት ክብርን ማጠናከር፣ ማንነትን፣ ክብርን ማስከበር የመሰለ ነገር የለም፡፡ ይህን አልችልም የሚል እንኳ ትርፉ ባርነት ነው፡፡ በፈቃዱ ከተጨቆነ ሰው(ባሪያ) ወጥቶ ውሻ ወይንም ዶሮ ለመሆን ቅንጣት አቅም ያለው ‹‹የፖለቲካ እንሰሳ›› የለምና፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar