NOV 16,2013
ሠሞኑን በሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እየደረሠ ያለው ግፍና ስቃይ እንዳሳዘናቸው የገለፁ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስት እና የኢትዮጵያ መንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ተናገሩ፡፡ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ሣውዲ አረቢያ የራሷንም ዜጐች መብት የማታከብር ሃገር መሆኗን ገልፀው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አሠቃቂ ስራ ግን በ21ኛው ክ/ዘመን የማይጠበቅ ግፍ ነው ብለዋል። በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ድርጊት አስነዋሪ ነው በማለት መወገዝ እንዳለበት የተናገሩት ዶ/ር መራራ፤ ዋናው ተጠያቂ የሳውዲ መንግስት ነው ብለዋል፡፡
“በሌላ በኩል ኢህአዴግ ሃገሪቱን የስደት ሃገር አድርጓል” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ በሜድትራኒያን፣ በየመንና በደቡብ አፍሪካ መስመሮች የሚሰደዱ ዜጐቻችን የአውሬ ሲሣይ እየሆኑ ነው፤ በሃገር ውስጥም በውጭም የዜጐቹን መብት ማስከበር ያልቻለው የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡
በሣውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ በትኩረት እየተከታተሉ መሆናቸውን የሚገልፁት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጐቻችን ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ለመከላከልና ለማስቆም አለመቻሉ መንግስት አልባ መሆናችንን የሚያሣይ ነው ብለዋል፡፡ አቶ አበባው እንደሚሉት፤ የሌላ ሃገር መንግስት ቢሆን ኖሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን እዚያ ሃገር ድረስ ልኮ ሄዶ የዜጐቹን መብት ያስከብር ነበር ብለዋል – አቶ አበባው፡፡ እዚህ ሃገር የውጭ ዜጐች ከቀን ሠራተኛነት ጀምሮ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ መብታቸው ተከብሮላቸው ይኖራሉ ያሉት አቶ አበባው፤ “የኛ ዜጐች በሳውዲ ከሰውነት በታች ተዋርደው ግፍ የሚደርስባቸው ለዜጐች የሚቆረቆር መንግስት ስለሌለ ነው” ብለዋል፡፡ ለዜጐቻችን ሠቆቃ የመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ነው በማለት የሚናገሩት አቶ አበባው፤ ዜጐች በሃገራቸው የስራ እድል የሚያገኙበትን አማራጭ ማስፋት የመንግስት ሃላፊነት ቢሆንም፤ በተቃራኒው በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ብሎኬት የሚሠሩት፣ ሹፌር የሚሆኑት፣ አሣማ የሚያረቡትና የመሣሠሉትን ስራዎች የሚሠሩት የውጭ ሃገር ዜጐች ሆነዋል” ብለዋል አቶ አበባው።
የሣውዲ አረቢያ መንግስት “ከሃገሬ ውጡልኝ” ቢል እንኳ፤ የስደተኞችን ሰብአዊ ክብር በጠበቀ መልኩ ማስፈፀም ነበረበት ያሉት አቶ አበባው፤ “ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ በፖሊስ እየተገደሉና እንደ አውሬ እየተሣደዱ ነውና በዚህም የሣውዲ መንግስት ተጠያቂ ይሆናል” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገፆችና መገናኛ ብዙሃን ላይ የሠላማዊ ሠልፍ ጥሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ መግለጫዎችን ሲሠጥ የነበረው የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ የሚላቸውን ስደተኞች በህገ ወጥ መንገድ ማሠቃየቱ በምንም መዘዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀው፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ደካማነት የሚያረጋግጥና የኢትዮጵያንም ህዝብ የሚንቅ ድርጊት ነው ብለዋል።
የአገራችን ባለስልጣናት ጉዳዩን የተመለከቱበት መንገድ አሣዝኖኛል፤ አሣፍሮኛልም ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ “ጥንታዊ ታሪክና ክብር ካለው ሃገር መሪዎች የሚጠበቅ አይደለም” ብለዋል፡፡ በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ስራ አጥ እየተፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት ኢ/ር ይልቃል፤ ወጣቱን ለስራ ፈጣሪነት የሚጋብዝ ነገር አለመኖሩ አንድ የስደት መንስኤ ነው ብለዋል፡፡ “የተማረና አቅሙ የፈቀደ በቦሌ ይሄዳል፤ ያልተማረው ደግሞ ውሃ ይብላኝ እያለ በረሃ እያቋረጠ ይሄዳል” የሚሉት ኢ/ር ይልቃል፤ “አገር እያደገች ዜጐች ስደትን ይመርጣሉ የሚለው የባለስልጣናት አባባል ውሸት ነው” ይላሉ፡፡ የሣውዲ አረቢያ መንግስት በዜጐች ላይ የፈፀመው አሠቃቂ ድርጊት ሳያንስ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ሚዲያ ለጉዳዩ የሠጡት አናሣ ትኩረት አሳዝኖኛል ብለዋል – የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጐቻችን ሲሰቃዩና የሰው ህይወት ሲጠፋ፣ መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚሉት ኢ/ር ይልቃል፤ የኢትዮጵያ እና የሣውዲ አረቢያ መንግስት በእኩል ደረጃ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል፡፡
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ጉዳዩን በአፅንኦት እየተከታተለው መሆኑን ገልፀው፤ በሳውዲ የተፈፀመው ተግባር በእጅጉ የሚያሣፍር እና የሚያሣዝን ነው ብለዋል። ማንኛውም ሃገር የራሱን ህግና መመሪያ ሊያወጣ ይችላል ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ይሁን እንጂ “ፍቃድ አላሣደሡም” በሚል ሰበብ ዜጐቻችን የሠው ልጅን ክብር በሚያዋርድ ሁኔታ ለስቃይ መዳረጋቸው ብሄራዊ ሃፍረት ነው ብለዋል። ድርጊቱን በፈፀሙት አካላት ላይ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ዶ/ር ነጋሶ ጠቅሰው፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስትና የፖሊስ ሃይሉ በህግ ሊጠየቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
“አሁን ግን በዜጐቻችን ላይ እየተፈፀመ ባለው ድርጊት የአገራችን ሉአላዊነት ተነክቷል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም” ብለዋል ዶ/ር ነጋሶ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጠበቅ ያለ አቋም መውሠድ እንዳለበትና ዜጐች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ በአስቸኳይ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም አሣስበዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነትና የመሣሠሉት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሃገሪቱን ዜጐች ለስደት እየዳረገ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ፤ መንግስት ድክመቱን እንዲያሻሽል ሁሉም ዜጋ ግፊት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
addisadmass
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar