(አንዱ ዓለም ተፈራ፤ የእስከመቼ አዘጋጅ)
ከዝግጅት ክፍሉ፡ “በህወሃት ውስጥ የዕርቅ ሃሳብ መነሳቱ ተሰማ” በሚል ርዕስ ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ላቀረበው የዜና ዘገባ አቶ አንዱ ዓለም ተፈራ የሚከተለውን የአጸፋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በቅድሚያ ጊዜያቸውን ወስደው ይህንን ምላሽ ስለጻፉ እያመሰገንን ይህንን ዓይነቱን ባህል ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሚያደፋፍር መሆኑን እንወዳለን፡፡
በኢትዮጵያዊያን ዘንዳ፤ ይቅር ለፈጣሪ ብሎ ከተጣሉት ጋር እንዲታረቁ፤ ከልበ ሙሉዎች፣ ከባህል አካሪዎችና ለነገ ግምት ካላቸው ሰዎች ይጠበቃል። እናም አመዛዛኝ የሆኑ፤ አክብሮት፣ ርጋታና ፍቅር ያላቸው፤ ለእርቅ ምን ጊዜም በራቸው ክፍት ነው። አጉል የሆኑት ደግሞ፤ እኔ ስህተት አልሠራም፣ እኔ ምን ጊዜም ትክክለኛ ነኝ፤ ስለሚሉና ሌላው ሁሉ ለነሱ ሰግዶ እንዲልመጠመጥ ስለሚፈልጉ፤ ለእርቅ በራቸው ዝግ ነው። አጉል የሆኑ ማለት፤ እብሪተኞች፣ ፈሪዎች፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ የግልና የአሁን ሕይወታቸውና ጥቅማቸው እንጂ፤ የኅብረተሰብ ወይንም የሀገር ጉዳይ የማይዋጥላቸው ናቸው። ትናንት በጎልጉል ገፅ፤ በህወሃት ውስጥ የዕርቅ ሃሳብ መነሳቱ ተሰማ፤ – “የኢህአዴግ የአፈና ገመድ ነትቧል፣ ድርጅቱ ተናግቷል” በሚል ርዕስ አዘጋጆች የጻፉትን ደጋግሜ ተመለከትኩትና እኔ ይኼን በሚመለከት፤ የትም የሚደርስ አይደለም በማለት ሀሃስቤን እንደሚከተለው አቅርቤአለሁ።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሀቅ ለማንኛውም ሰው ዓይን የሚያስፈጥጥ፣ የሚረብሽና እረፍት የሚነሳ ነው። ይኼን በምንም መንገድ ቢያዩት፤ የነገውን አስፈሪ መጪ ሊያስበረግገው አይችልም። አስፈሪ ነገ ከፊታችን ላይ ተገትሯል። እንግዲህ ጥያቄዎቹ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ይኼን እንዴት ሊያየው ይችላል? ነው። ማየቱ ብቻ ሳይሆን ምን ያደርጋል? ነው።
አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ሀቅ አለ። ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነው። ይህን ግን ግንባሩ አይቀበለውም። እናም መፍትሔ ፍለጋ የሚሮጠው ከዚህ ተነስቶ አይደለም። እናም ዕርቅ አይዋጥለትም። በተመሳሳይ መንገድ፤ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለሕዝቡ ትንሽ መፈናፈኛ የሥልጣን መንገድ አለመክፈታቸውን፤ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከሱ ሌላ አዋቂና መፍትሔ ሠጪ የለም ብሎ ማመኑን፤ በተመሳሳይ ምንገድ ደግሞ መለስ ዜናዊ የዚሁ ቅጂ መሆኑን ማጤን ይኖርብናል። ሶስቱም ገዥዎች ከራሳቸው በላይ ነፋስ ብቻ ባይ እንደነበሩ ሁላችን እናውቃለን።
አንዳንዶቻችን የራሳችንን ኃላፊነት ወደ ሌላው በማሻገር፤ ህወሃት በራሱ ፈርሶ ወይንም በፈቃዱ ሥልጣን ሊያጋራ እንደሚችል ማስረጃው ሳይሆን ምኞቱ አለን። ደግ! ምኞት ብለን መቀበል አንድ ነገር ነው። ምኞት ብቻ ነው ብለን መቀበል አለብን። ከዚያ አያልፍም። በርግጥ የሕዝቡ እየደፈረ መምጣትና በተለያዩ ቦታዎች የሚነሱት ጥያቄዎች የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች ሊያቁነጥንጥ ይችላል። መቀመጫዎቻቸውን ከማደላደል ያለፈ ግን፤ የሚያደርጉት እንደሌለ መረዳት አለብን። ከደረስብን ግፍና በደል ተነስተን፤ ምኞታችን በዝቶ አስተሳሰባችንን እየጋረደው፤ ምኞታችንን ሀቅ እያደረግን የምንዋዥቅ ሞልተናል። ግን ታሪክ የሚያስተምረን፤ ከእባብ እንቁላል እርግብ እንዳንጠብቅ ነው።
በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች መካከል ዕርቅ ለውይይት ሊነሳ ይችላል። ይኼን መቼም አይደረግም ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር አልችልም። በመካከላቸው አንድነት ስለሌለ፤ አንዳንዶቹ ያገኙትን ጥቅም ይዘው የተደላደለ የወደፊት ኑሮ ከፊታቸው ብልጭ ሊልባቸው ይችላል። እነዚህ ግን አቅራቢዎቹ ግለሰቦች ብቻ ናቸው። ወሳኙ ደግሞ ተሰባስበው በአንድነት የሚስማሙበት ብቻ ነው። እናም ማተኮር ያለብን፤ የጠቅላላ ስብስቡ ቅኝት ላይ ነው። የጠቅላላ ስብስቡ ቅኝት ደግሞ ከራሱ ታሪክና ከሌሎች መሰሎቹ ታሪክ የተጻፈ ስለሆነ ማወቁ አይቸግርም። ታሪክ ታስተምራለች ሲባል፤ ማገናዘቡን ለኛ ትታ ነው። ከታሪክ የማንማር ከሆን፤ አሁንም በዚያው ስንዳክር ለወጪዎቹ በሽታችንን እናተላልፍላቸዋለን። ትጥቅ መፍታት እንዳይሆን መገንዘብ አለብን።
እርቅ ወርዶ ሀገራችን በሰላም የወደፊቷን የምትጀምር ከሆነ፤ ከማንም በማያንስ ደረጃ ደስተኛ እሆናለሁ። በምኞት ፈርስ ግን መጋለቡን እስከዛሬ አድርገነዋልና የዚያ ፈረስ ጥላውም ከኔ ጋር የለም። ፈረሱ ደክሞት ሕይወቱን ጨርሶ ሞቷል። ጥላውም አብሮ ተቀብሯል። የሀገራችን አደጋ ከባድ ነው። የተመሰቃቀለ ነው። እንዲያው አንድ ቀን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተነስቶ ከዛሬ በኋላ ሁሉ ነገር ተለውጧል! የሚልበትና የሚቀየርበት እውነታ ገና መጻፊያ ቀለሙ አልተበጠበጠም።
እንዲህ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች ዕርቅ ይፈልጋሉ ብለን ስንጀምር፤ ከኛ ምኞትና እምነት ሳይሆን መነሳት ያለብን፤ ከነሱ እምነትና እውነታ ነው። መመልከቻ መነፅራችን የነሱ መሆን አለበት። ለምን ይፈልጋሉ? በነሱ እምነት፤ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም። ሥልጣኑ ሁሉ በጃቸው ነው። ሀብቱ ሁሉ በጃቸው ነው። ጉልበቱ ሁሉ በጃቸው ነው። መንግሥታዊ መዋቅሩ ሁሉ በጃቸው ነው። የውጭ ሀገር መንግሥታት ሁሉ የሚያውቋቸው እነሱን ብቻ ነው። ብዙ የድርጅት አባላት ያሏቸው እነሱ ብቻ ናቸው። በሌላ በኩል እኛ ይኼ ሁሉ ገለባ እንደሆነ እናውቃለን። ለዚህ ነው፤ እንዲህ ስለሆነ፣ ያ በዚያ ሰለመጣ . . . እያልን የምንደራርተው። ይኼንን የተረዱ፣ የሚይውቁትና የሚቀበሉት ቢሆን ኖሮ፤ ብዙ አምባገነን መሪዎች ቀድመው እርምጃ ይወስዱ ነበር። አላደረጉም። የኛዎቹ አምባገነኖች ከሌሎች ተለይተው አዋቂና ጥንቃቄ ይወስዳሉ ማለት፤ የምኞትን ቦታ ለእውነታ ማስረከብ ነው። አልፎ ተርፎም፤ ማንም ሳይጠይቀን ራሳችን ራሳችንን ትጥቅ እያስፈታን እንዳይሆ አፈራለሁ።
አሁንም አንድ ታሪክ የሚያስተምረንን ቁም ነገር እዚህ ላይ ልጥቀስ። እንደሌሎቹ አምባገነኖች ሁሉ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች ሁሉ፤ ለሁሉም ጥያቄዎች ያላቸውና የሚሠጡት መልስ፤ በጉልበት መደምሰስ ነው፤ ከሕዝቡም በኩል ይምጣ ከራሳቸው መካከል። ይልቁንስ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ሆነን፤ አንድ አጀንዳ ብቻ ይዘን፤ ከሕዝቡ ጎን በመሠለፍ፤ እውነተኛ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ አብረን እንፈልግ።
የኢትዮጵያን ነገ የሚወስነው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚያደርገው ወይንም የማያደርገው ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተገብረውና የሚጽፈው ብቻ ነው። የየካቲት ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምህረት ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ መነሳት እንጂ፤ የንጉሠ ነገሥት ዝም ማለት አይደለም። የደርግም የመጨረሻ ታሪክ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምቢታና የታጠቁ ኃይሎች ደርግን መደምሰስ እንጂ የደርግ ተግባር አልነበረም። አሁንም በድጋሜ፤ የነገው ታሪካችን የኢትዮጵያ ሕዝብ መነሳት እንጂ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተግባር አይደለም የሚጻፈው። ሲጀምርና ሲጨርስ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተነስቶ በማመፅ፤ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ደመሰሰ!” ነው የሚለው።
አስከመቼ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar