mandag 30. juni 2014

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን ባለሥልጣናት እገታ ላይ መሆኑን በማስመልከት የወጣ መግለጫ


ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቷል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን የጉዞው መዳረሻ አልነበረም፤ ከየመን ጋርም የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ አልነበረውም። የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አግቶ ለአንድ ሰዓት እንኳን ለማቆየት ምንም ምክንያት የለውም። በዚህም ምክንያት ያለአግባብ የታገተብን የንቅናቄያችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። እንዲያውም የየመን ባለስልጣናት አምባገኑን ወያኔ ለመርዳት ባለው ፍላጎት ሳቢያ መሪያችንን አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ፤ ዝግጁነቱንም በተግባር ያሳየ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። የየመን መንግሥት ከዘረኛውና ፋሽስታዊው ወያኔ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋይ መሪያችን ላይ እየፀመ ያለውን ደባ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የንቅናቄዓችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል።
ትግላችን መስዋትነት እንደሚያስከፍል እናውቃለን። ከዚህ በፊትም ብዙ ጓዶቻችን መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ወደፊትም ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። አሁን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰውና ወደፊትም ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ምሬታችን በማብዛት፣ ቁጣችንና ዝግጁነታችን ከማጠንከር በስተቀር ቅንጣት ታክል እንኳን ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ እንደማያደርገን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለአባሎቻችንና ለደጋፊዎቻችን ሁሉ መግለጽ እንወዳለን።
መንግሥታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ኢትዮጵያና የመን ግን ጎረቤታሞች ሆነው መቆየታቸው የማይቀር ነው። የየመን መንግሥት የወያኔ እድሜ አጭር መሆኑ የተገነዘበ አይመስልም። በዚህም ምክንያት የየመን መንግሥት የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የቆየ ወዳጅነት የሚያደፈርስ እርምጃ ወስዷል። የየመን መንግሥት የየመንን የወደፊት የረዥም ጊዜ ጥቅም እንዲያሰላና ያገተብንን መሪ በአስቸኳይ እንዲፈታ እንመክራለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመሪያችን ላይ ጉዳት ቢደርስ ወይም ለወያኔ አሳልፎ ቢሰጥ የመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የማይሽር ቂም ውስጥ የምትገባ መሆኑን የየመን መንግሥት አውቆ በጥብቅ እንዲያስብበት እናስጠነቅቃለን።
በየመን መንግሥት አልሰማ ባይነት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ተላልፎ ቢሰጥ በአካሉና በሕይወቱ ለሚደርሰው ሁሉ የወያኔ ፋሽስቶችን ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ከአሁኑ እናስጠነቅቃለን። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስና ሕይወት ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቃት ለነፃነታቸው ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆኑ እልፍ አዕላፍ ታጋዮችን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለንም። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስ እና ሕይወት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ሁሉ በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ቦታ የምንበቀል መሆኑንና ብዙ የወያኔ ሹማምንት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሚሆን እንዲያውቁት እናስጠነቅቃለን ።
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ጊዜ የማይሠጥ ሀገራዊ ጥሪ አለብን!

June30/2014
እስከመቼ ባለንበት እንረግጣለን?
eskemechie


ራሱን “የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሰየመው ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት (ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት)፤ ሀገራችንን ዕለት ከዕለት ወደ ባሰ አዘቅት እንድትገባ እየጎተታት ነው። የፖለቲካ ፍልስፍናውና የአስተዳደር መመሪያው የሀገራችንን ሕልውና በንጥልጥል ላይ እንዲቀመጥ ሌት ከቀን እየጣረ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ለኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ በመቆም፤ በተለያዩ ድርጅቶች ከፍተኛውን መስዋዕትነት በመክፈል፤ ከዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተዋደቁ ያሉ ታጋዮች አሉ። ይህ በዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል እየተደረገ ያለው ግብግብ፤ ለረጅም ዘመን እንዳለ ሆኖ፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊው መንግሥት የፈለገውን እያደረገ ያለበትና፤ በታጋዩ ወገን ያለው ክፍል ደግሞ ላለፉት ፳ ፫ ዓመታት ባለበት የሚረግጥበት ሁኔታ አልተለወጠም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠናወተው ክፍል እየበዛ፤ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ ይኼው ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ሊቆጣጠረው በማይችልበት ቀውስ ውስጥ ልትገባ አዝምማለች። ከዚህ እንድታቀና ሁላችን እንፈልጋለን። ይኼን ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ማስወገድ ሁላችን እንፈልጋለን። እስካሁን የደከምንባቸው መንገዶች ውጤታቸው አመርቂ ስላልሆነ፤ አዲስ መንገድ መቀየስ አለብን። የሀገራችን ችግርና መከራ፣ በምኞት አይቀረፍም። ይህ በትግላችን የሚከናወን ነው። ይኼን ለማሳካት እንዴት እንደምንበቃ ምርጫ የሌለው አንድ መንገድ አለን። ሁላችን እናውቀዋለን፤ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተነስተው ሀገራችን እያሉ እንደሆነ ሁሉ፤ እኛም በያለንበት ለኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው ቆመን፤ ሀገራችንን አስቀድመን፣ በአንድ ተሰልፈን መነሳት ነው። የዚህ መንገድ ጠቃሚነቱ፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊውን መንግሥት ማስወገዱ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ቀጥሎ ለምትመሠረተው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አስተማማኝ መሆኑ ነው። በዚህ ሂደት ሁሉም ድርጅቶች ባለቤቶች ናቸው። በዚህ ሂደት እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት ባለቤት ናት። በዚህ ሂደት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባለቤት ነው። ትኩረቱ፤ በሚሰቃየው ወገናችን፣ የጋራችን በሆነችው ሀገራችን፣ እና በጠላታችን ፀረ-ኢትዮጵያዊው መንግሥት ላይ ነው። ይህ የጋራችን ፈተና ነው። ማናችንም ከዚህ ውጭ አይደለንም። ከሀገር መለስ ብዙ የምንለያይባቸው ጉዳዮች አሉ። ነገር ግን ክብደታቸው ከሀገር ነፃነት ጋር ሲነፃፀር፤ ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ስለሆነ፤ ቅድሚያን ለሀገር እንድርግ። በመካከላችን ያለው ልዩነት የዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚጠይቅና በዚያው መንገድ የሚፈታ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፤ ከተለያየ ቦታና የተለያየ ተመክሮ ያለን ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን፤ ከድርጅት አባል መሆን አለመሆን ይልቅ፤ የወገናችንን ብሶት ማስወገድና የሀገራችንን ሕልውና ማስጠበቅን በማስቀደም፤ በአንድነት በመቆም፤ የትግሉን ሂደትና መደረግ ያለበትን ተረድተን፤ በሀገራዊ ጥሪው ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን እንድንሰባሰብ ነው። ይህ ብዙዎቻችንን ያሰባስባል። ይህ በአንድነት ለተግባር ያሰልፈናል። ይህ፤ የምናደርገው ጥረት ለሀገራችን መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ በፍጥነትና በተጠናከረ ጉልበት ለወገናችን እንድንደርስ ያደርገናል።
ውድ አንባቢ፤
በሀገራችን ላለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ፤ ላንዴና ለመቼውም መፍትሔ ለማስገኘት የመጨረሻው ደወል ተደውሏል። ሀገራችን ስላለችበት የፖለቲካ ሀቅ እርስዎም ሆነ እኔ ነጋሪ አያስፈልገንም። ኢትዮጵያዊያንን ለረጅም ዘመን አቆራኝቶ የያዘንን የኢትዮጵያዊነት ትስስር ለመበጣጠስ የተነሳን ድርጅት፤ በምንም መመዘኛ ብንለካው ፀረ-ኢትዮጵያዊ ከመሆኑ ሌላ፤ ምንም ገላጭ ቃል አይገኝለትም። በመካከላችን ያለውን አንድነት ሰብሮ፤ እርስ በርሳችን በጥርጣሬ እንድንተያይ ያደረገን፤ ይኼው ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ሀገራችንን እየገዛ ያለው ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት፤ ሀገራችንን እየወሰዳት ያለበት አዘቅት፤ አደገኛና መመለሻ የሌለው ነው። ዴሞክራሲያዊነት፣ ፍትኅን አክባሪነት፣ ለሕዝብ ተቆርቋሪነት፣ ለድሃ ቋሚነት፣ ሀገር ወዳድነትና ለሕግ ተገዥነትን የወደደ፤ የትውልድ ቆጠራን ከውሉ አያስገባም። እኒህ፤ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት ባላቸው ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን እጅ ያሉ ጥበቦች ናቸው። ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተገኘን ወገኖች፤ በምን መንገድ ተለያይተን ልንተያይ ነው? ኢትዮጵያዊ ብለን በእኩልነት ካልተቀባበልን፤ መበታተኑ ማንን ነው የሚጠቅመው? የየተንገንጣዩ ልሂቃን ሥልጣን ይዘው የገነጣጠሉንን ወገናቸውን ለመግዛትና ኪሳቸውን ለማሳበጥ ከመሯሯጥ ውጪ፤ ለኛ ለተራ ግለሰቦች ምን ሊያስገኙልን ይችላሉ? ዴሞክራሲ ለየብቻ ስንሆን ብቻ ነው የሚሠራው ያለው ማነው? ትናንት በኤርትራ የደረሰውን ለምን እንረሳለን? አሁንም የተያዘው ጉዞ፤ ሀገሪቱ አንድነት አጥታ መገዛት የማትችልበት ሁኔታ እንዲፈጠርና፤ ስግብግብ የሥልጣን ጥመኞች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። በሀገራችን ያለውን የጨቋኝና የተጨቋኝ ጉዳይ “የብሔር ጥያቄ ዋነኛው የሀገራችን ቅራኔ ነው” ብሎ የተነሳው ይሄ ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት፤ ይህ ቅኝቱ አሁን ሀገራችን እንደ አንድ ሀገር እንዳትቆምና ሕዝቧም እንደ ኢትዮጵያዊነቱ ሕልውናውን እንዲያጣ ቀን በመቁጠር ላይ ነው። ለሥልጣን መወጣጫና በሥልጣኑ መስንበቻ የቀመረው ጉዳይ፤ አድሮ በራሱ ላይ ተጠምጥሞ መታነቂያው ሆኗል። በየክልሉ ያሉ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈጠሩ ያሰላውና የየክልሉ ነዋሪዎች፤ ሌሎችን “መጤዎች” በማለት እንዲያባርሩ ያፋፋመው ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት፤ ኢትዮጵያን ወደ ማጥፋቱ አምርቷል። በአንፃሩ ግን፤ ኢትዮጵያዊያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ሀገራችን አንድ ናት ብሎ ተነስተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የፖለቲካ ጉዳይ፤ ከጀርባው ኢትዮጵያን ለማጥፋት በደንብ የተቀመረ እርምጃና አራማጅ አለው። ይህ በፀረ-ኢትዮጵያዊው መንግሥት የሚተገበረው ጥፋት፤ ከጀርባው የውጭ ሀገር እጅ ያለበት ለመሆኑ ማናችንም ጥርጥር ሊኖረን አይችልም። በፖለቲካ ምንም ነገር ለብቻው የሚሄድ የለም። በምንም መንገድ የውጭ ሀገር መንግሥታት ለኢትዮጵያዊያን ጥቅምና ለዴሞክራሲ ይቆማሉ ብለን ማሰብ የለብንም። እነሱ የቆሙት ለሀገራቸው ጥቅምና ከኛ የሚያገኙትን ጥቅም ለማብዛት ነው። ከአሜሪካ አንስቶ እስከ ኤርትራ ድረስ፤ ለዴሞክራሲ ወይንም ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመመሥረት የቆመ የለም። ባለቤቶችም ሆን ባለዕዳዎቹ፤ ታጋዮችም ሆን አሳልፎ ሠጪዎቹ፤ እኛው ነን። የኢትዮጵያን መንግሥታዊ ሥልጣን በውጭ መንግሥታት ፈቃድና ቡራኬ ለመቀበል የተዘጋጁ የድርጅቶች መሪዎች፤ ምን ያህል ሀገር ወዳድ ናቸው? የውጪ ሀገሮች አደግዳጊ የሆነ ቡድን በሀገራችን የሥልጣን ወንበር ከተቀመጠ፤ አሁንም ፖለቲካችን እንቧለሌ ዙሪያ ነው የሚሆነው፤ ወጣቶቻችንን ለጦርነት፣ የሀገራችንን ሀብት ለጥቂት ግለሰቦች፣ ድህነትና ረሃብን ለወገናችን ማውረስ ነው። የአክራሪዎች (ቴረሪስት) ተግባር የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ችግር አይደለም። የአሜሪካ ችግር ነው። የኛ ችግር ፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት በላያችን ላይ መጫኑ ነው።
የምንታገለው ለሚከተሉት የትግል ዕሴቶቻችን ነው፤
ሀ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነቱ ተከብሮ፤ ሕዝቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ፤
ለ) ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ፤ ለሙ መሬቷና ዳር ድንበሯ ለኢትዮጵያዊያን እንዲሆን፤
ሐ) በሀገራችን ኢትዮጵያ፤ በሕዝቡ የጸደቀ ሕግ-መንግሥት ኖሮ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፤
መ) የእያንዳንዷ ኢትዮጵያዊትና የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግለሰብ መብት በሕግ እንዲደነገግና በተግባር እንዲገለጥ፤
እነዚህ ናቸው የምንታገልላቸው። እኒህ ደግሞ በማንኛውም ታጋይ ደርጅት ዘንድ ተቀባይነት አላቸው። በተግባር ላይ እንዲውሉ ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ድርጅት የኔ ብሎ መነሳት አለበት። ሀገራችንን ከዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ለማስለቀቅ በሚደረገው ትግል፤ በዚህ መለስተኛ በሆነው ሀገራዊ ጥሪ ለመሰባሰብ፤ የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸው ወይም አዳዲስ መፈጠራቸው አስፈላጊ አይደለም። ይልቁንስ የሚያስፈልገው ሁላችንም ወደ አንድ የምንመጣበት መንገድ ነው። አሁን በታጋዮች ወገን ያለው ሀቅ አያኮራም። ከአንደኛው የፖለቲካ ዝማሜ እስከሌላው ጫፍ ድረስ ተዘርግቶ ያለው የፖለቲካ ድርጅቶች ስምሪት፤ የፖለቲካ ማኅደሩን ከማጨናነቅ ያለፈ፤ አመርቂ ውጤት አላሳየም። እናም ሊቀጥል አይገባውም። ከዚህ መውጣት አለብን። ለሥልጣን በመሰለፍ ላይ እግራቸውን የተከሉ ሁሉ፤ የኢትዮጵያን ዘለቄታ ጥቅም ስላላዘሉ፤ ውጤታማ ቢሆኑም፤ ለኢትዮጵያዊያ መልሶ እምቦጭ ነው።
ነገ እንድትመጣ የምንፈልገዋን ኢትዮጵያ፤ በአንድነት ልናረጋግጥበት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው። ከሺ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሶስቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ከሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለው ትግል፤ ይኼንኑ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው አንግቦ የዘመተው። ሕዝባዊ ያልሆነ ሥልጣን ያባልጋል። በቀላሉ አይለቀቅም። መንገዱን ሁሉ በማጥበብ ዘለቄታን ይሻል። እናም አምባገነን ነው። መንግሥቱ ኃይለማርያምን ማጥናቱ የበለጠ ያረጋግጣል። ኢሳያስ አፈወርቂን ያየ ሌላ አይሻም። መለስ ዜናዊን ያየ ሌላ መረጃ አይጠይቅም። የሀገራችን ምጣኔ ሀብት ሥምሪት ዘግናኝ ነው። ጥቂቶች ከመጠን በላይ ባለሀብቶችና፤ እጅግ በጣም ብዙዎች መንገድ አዳሪዎች ያሉበት ሀቅ ነው። ሥራ ፈላጊው ቁጥሩ እየጨመረ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታገሉ ወገኖቻችን ስንመለከት፤ በየጊዜው በሚለዋወጥ ሕግ እጅና እግራቸው ተፈጥርቆ፤ ይኼን ካደረጋችሁ እንዲህ ትደረጋላችሁ እየተባሉ፤ ከፍተኛውን መስዋዕትነት በመክፈል ይገኛሉ። ሆኖም ግን መሠሪ በሆነው የገዥው ቡድን ተንኮልና የስለላ ድር ተሸብበው እንቅስቃሴያቸው ውስን ሆኗል። ደስ የሚል የትብብር ጅማሬ እየታዬ ነው። ይበርታ እንበል። ሆኖም ግን፤ አሁንም አንድ የሆነ ማዕከል ኖሮ፤ ሁሉም በአንድነት የሚሰለፉበት መንገድ ካልተፈጠረ፤ ከሚገኘው ድል ይልቅ መስዋዕትነቱ እየበለጠ፤ የታጋዩን ቁጥር ለጊዜውም ቢሆን እንዳያሳሳው ያሰጋል። እናም የአንድነት ጥሪው አሁንም መጠንከር አለበት።
በውጭ ሀገር ያለን ኢትዮጵያዊያን ለረጅም ጊዜ በያለንበት ስንታገል ብዙ ዓመታት አሳልፈናል። በአንድነት ሕብረትን ፈጥረን፤ አንድ ሀገር፤ አንድ ራዕይ፤ አንድ ትግል ብለን ካልተነሳን፤ አሁንም ዓመታትን ከመቁጠር ሌላ የረባ ልንሠራ አንችልም። ትግል ሥነ ሥርዓት አለው። ትግል መስዋዕትነት አለው። ትግል ታታሪነትን ይጠይቃል። ትግል ቀጣይነትን ይጠይቃል። ሲያመቸንና ደስ ሲለን የምንቀላቀለው፤ ደስ ያላለን ጊዜ ደግሞ ንቀን የምንተወው ከሆነ፤ የትም አይደርስም። ቆራጥነትን፣ ታታሪነትን፣ አልቸነፍም ባይነትን ይዘን ነው ወደፊት መሄድ የሚገባን። ለዚህ ደግሞ አሰባሳቢና አነሳሽ ራዕይ ያስፈልጋል። ፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት በሀገራችን ቆሞ፣ ሕዝቡ ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮው እያሽቆለቆለ፣ ጥቂቶች ሀብታቸውን ሽቅብ አጉነው ባለንበት ሀቅ፤ ሀገርን ከዚህ ፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት ነፃ ለማውጣት ከታጋዩ ሕዝብ ጎን አብረን መሰለፉ ይገባናል።
አሁን ምን እየሠራን ነው? እያንዳንዳችን መጠየቅ ያለብን ራሳችንን ነው። ዛሬ፣ ትናንት፣ የዛሬ ሳምንት፣ ያለፈው ወር፣ ባለፈው ዓመት፣ ባለፈው አምስት ዓመት ምን ሠራን ብለን ራሳችንን እንጠይቅ? ከዚህ ተነስተን ሌሎች የሚያደርጉትን መገመትና መገምገም እንችላለን። ታዲያ ወገናችንን ማፍቀራችንን እና ሀገራችንን መውደዳችን የት ላይ ነው? እኛስ ካልታገልን ማን ታግሎ ነፃ እንዲያወጣን እንጠብቃለን? በውጭ ያለን ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ መድረኮች አሉን። ሃሳቦቻችንን ልንለዋወጥባቸው የሚያስችሉን፤ ድረገፆች፤ የመወያያ ክፍሎች፣ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ እና ሌሎችም አሉን። እኒህን በመጠቀም አንድነትን እያራመድን፤ ትግሉን ማጠናከር እንችላለን። ይህ ፍላጎቴ አይሠራም ወይንም ትክክል አይደለም የምትሉ ካላችሁ፤ የናንተን የሚሠራ አቅርቡና ልከተላችሁ። ዋናው ነገር ተግባራዊ ሆነን መገኘታችን ነው።
አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለማቋቋም ያለው መንገድ፤ በአንድነት ሁላችን ተሰባስበን የምንመሠርተውና የምንቆምለት ድርጅት እየመራን፤ ይኼን ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥት ከሥሩ ስንመነግለው ነው። ጊዜ ባለፈው የአፄው ዘመነ መንግሥት የታጋዮች ጥያቄ፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነበር። ለዚህም ከፍተኛውን መስዋዕትነት በመክፈል ትግሉን ወደፊት ገፍተውታል። በሰው በላው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አምባገነን መንግሥት ዘመን የታጋዮች ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነበር። ያንን አረመኔ መንግሥት በማፋጠጥ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከትንሹ እስከ ትልቁ ከፍለው ትግሉን ወደፊት ገፍተውታል። በፋሽስቱ ጣሊያን ወራሪ መንግሥት የታጋዮች ጥያቄ የሀገራችን ነፃነት ነበር። ለሀገር ነፃነት በአንድነት ሁሉም ሀገሬ ብሎ ተነስቶ፤ ለጦርነት ተጉዘው ያልተመለሱ አርበኞቻችን ሀገራችንን ለኛ አትርፈውልናል። በሀገራችን አሁን ያለው መንግሥት የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን የምናቀርብለውት መንግሥት አይደለም። ሕግን የሚያከብር መንግሥት አይደለም። እኩልነትን የሚቀበል መንግሥት አይደለም። የሕዝብን ድምጽ የሚያከብር መንግሥት አይደለም። በኢትዮጵያዊነት እየገዛ አይደለም። ፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት ነው። እናም እንደፋሽስቱ የምንታገለው መንግሥት ነው። ለፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ መልሱ በአንድነት ሀገሬ ብሎ መነሳት ነው። በዚህ ሂደት፤ ብዙ የተለያዩ አጀንዳዎች ሊነሱ ይችላሉ። በቅድሚያ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ወደ አንድ መምጣት አለባቸው። ጠላታችንን እንዴት እንደምናፈልሰው አንድነት ሊኖረን ይገባል። ከጠላታችን መፍለስ በኋላ መከተል ስላለበት የመንግሥት አመሠራረትና አካሂያድ አንድነት ሊኖረን ይገባል። ይህ ደግሞ ከፍ ባለ ትክክለኛ ተራማጅ ድርጅት መዋቀርና መመራትን ግድ ይላል። ሁሉም ከሀገር መለስ ያሉት ጉዳዮች ከሀገር መዳን በኋላ የሚነሱ ሁለተኛ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር ለመወያየትና አብሮ ለመነሳት ፈቃደኛ ነኝ። አብሬህ አለሁ በማለት እንድንወያይ የምትፈልጉ በ(eske.meche@yahoo.com ) ጻፉልኝ።

søndag 29. juni 2014

መዝገቦቹ መልሰው ተቀራረቡ የእምነት ክህደት ቃል በኃይል አስፈርመዋቸዋል

ጽዮን ግርማTsion Girma's photo.
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በስድስቱ ጦማሪያንና በሦስቱን ጋዜጠኞች ላይ የፌደራል ፖሊስ የተለያየ ምክንያት እየሰጠ ቀጠሮ የሚያራዝመውን ሁለት መዝገብ አንዴ ሲያቀራርበው መልሶ ደግሞ ሲያራርቀው ቆይቶ አሁን ደግሞ መዝገቦቹን መልሶ አቀራርቧቸዋል፡፡እስረኞቹ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ኹኔታ ፖሊስ ያረቀቀውን የእምነት ክህድት ቃል ተገደው እንዲፈርሙ አድርጓቸዋል፡፡
የሦስቱ ብሎገሮች አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ቀጠሮ ለዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ የሚል የነበረ ሲኾን ከጠዋት ጀምሮ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ቤተሰብ፣ጓደኞቻቸው፣ጋዜጠኞች፣ዲፕሎማቶችና የወጣቶች ደጋፊዎች በአጠቃላይ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ ሰው ከችሎት ውስጥ የሚሰማውን አዲስ ነገር ለመጠበቅ በግቢው ውስጥ ቆመው ነበር፡፡ ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ የእስረኞቹ ጠበቃ አቶ አመኃ መኮንን ተጠርተው የመዝግብ ቤት ጸሐፊዋ ስለሌለች ችሎቱ ለከሰዓት በኋላ እንደተዛወረ ይነገራቸዋል፡፡ እርሳቸውም ችሎቱን ለመከታተል ለቆመው ሰው መልዕክቱን ያስተላልፋሉ፡፡ ጥቂት ሰዎችም ይህን መልዕክት ሰምተው ግቢውን ለቀው ይወጣሉ ብዙኃኑ ግን እዛው እንደቆሙ መጨረሻውን ለማየት መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡
ሠላሳ ደቂቃ ያህል እንደተቆጠረ የእስረኞቹ መምጣት በጉምጉምታ መወራት ጀመረ፡፡ሁሉም ሰው ወደ ጓሮው በር ዐይኑን ተክሎ ቀረ፡፡ አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ ማኅሌት ፋንታሁ ከካቴና ውጪ ኾና እንደተለመደው በከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ ታጅበው ወደ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ግቢው ፊታቸው ላይ የጥንካሬ መንፈስ የነበረ ሲኾን ተሰበሰበውም ሕዝብ በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው፡፡በዚህ መካከል እስረኞቹን አጅበው የመጡት ፖሊሶች ወደተሰበሰበው ሰው ዘለው በመግባት ፎቶ ስታነሳ ነበር ያሏትን ምኞት መኮንንን (የሰማያዊው ፓርቲ አባል) የተባለች ወጣት የያዘችውን ስልክ ቀምተው እየጎተቱ ወሰዷት፡፡ፖሊሶች በወጣቷ ላይ የሚፈጽሙት ማንገላት ያስቆጣው ዮናታን ተስፋዬ የተባለ ሌላ ወጣት ድርጊቱን በማውገዝ ለመገላገል ሲጠጋ እርሱንም ጨምረው ወስደውታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ይህን ችሎት ማየት ከጀመረ ወዲህ እስረኞቹን አጅበው የሚመጡት ፖሊሶች ቀጠሮ ባለ ቀን ሁሉ ችሎት ለመከታተል የሚመጣውን ሰው ሲያንገላቱ፣ሲሰድቡና ሲዘልፉ ልክ እንደ መብታቸው የሚቆጥሩት ሲኾን እዛ ግቢው ውስጥ የተገኘው ሰው ችሎት ውስጥ ገብቶ በሚገባ መቀመጫ ቦታ ተሰጥቶት ችሎት የመከታተል መብት እንዳለው ቅንጣት ታክል አስበውት የሚያውቁ አይመስል፡፡ እንዲኹም ከችሎቱ ውጪ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥም ቢኾን ‹‹ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው›› የሚል ማስጠንቀቂያ እስካልተለጠፈ ድረስ ከሁለት ሰው በላይ የኾነ ማንም ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ላይ ፎቶ የማንሳት ሙሉ መብት እንዳለ የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ በአጠቃላይ በዛ ቦታ ላይ ከእነርሱ ውጪ ሌላ ሰው የመቆም መብት ጭምር እንደሌለው ጠንቅቀው ስሚያውቁ ወደ ተሰበሰበው ሰው ተመልሰው፤‹‹ሁላችሁም ግቢውን ለቃችሁ ውጡ›› ሲሉ ትእዛዝ ሰጡ፡፡
ከፊት ለፊት ቆመው የነበሩት ሰዎች ከግቢው ላለመውጣት እንቢተኝነታቸውን አሳዩ፡፡በተለይ በእስር ላይ የምትገኛው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እህት እስከዳር ዓለሙ፣አባቷ አቶ ዓለሙ እና ሌሎች ወጣቶች አንድ ላይ ኾነው ግቢ ውስጥ መቆም መብት እንዳላቸው በመግለጽ ለመውጣት ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀሩ፡፡ የፖሊሶቹ ማስፈራሪያና ዘለፋ ግን ቀጠለ ሕዝቡ ግቢውን ለቆ የማይወጣ ከኾነ አድማ በታኝ ፖሊስ እንደሚጠሩ ጭምር በመግለጽ ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ፎቶ ማንሳት የተከለከለ እንደኾነ እና እንኳን ሰውን መሬቱንም ጭምር ማንሳት እንደማይቻል በማስፈራራት ጭምር በመግለጽ ሰውን ከግቢው ውስጥ ገፍተው ወደ ውች አስወጡት፡፡
ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2006 ዓ.ም ውሎ በነበረውና ከዚያም ቀጥሎ በነበረው ችሎት ላይ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወከለው ቤተሰብ አባል ወደ ችሎት እዲገባለት ተደርጎ የነበረ ሲኾን አሁን ግን ይህም መብት ተከልክሎ ችሎት ውስጥ በእስረኞቹ በኩል ከጠበቃቸው ከአቶ አመሐ መኮንን በስተቀር ማንም ችሎት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ችሎት ከገቡም በኋላ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጠማሪ ሃያ ስምንት ቀን እንዲፈቀድለት የጠየቀ ሲኾን ፍርድ ቤቱ፤‹‹ከዚህ በኋላ የሚሰጣችሁ ሃያ ስምንት ቀን የለም ዐሥራ አራት ቀን ይበቃችኋል፡፡ ችሎቱም ከዚህ በኋላ እሁድ ስለማይሰየም ቀኑ አንድ ቀን ተቀይሮ ሰኞ ሐምሎ 7 ቀን 2006 ዓ.ም›› ሲል ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የጊዜ ቀጠሮው መዝገብ ሲከፈት የአቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና የማኅሌት ፋንታሁንን ጉዳይ የያዘው መዝገብ ከሌሎቹ ከስድስቱ አስረኞች ጋራ በአንድ ቀን ይለያይ የነበረ ሲኾን በመካከሉ አንዲት ዳኛ የሃያ ስምንት ቀን ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ጉዳዩ በዐሥራ አምስት ቀን ተለያይቶ እንደነበር ይታወሳል አሁን ደግሞ መዝገቦቹ መልሰው ተቀራርበዋል፡፡ የስድስቱ ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን ይታያል የሦስቱ ደግሞ ሰኞ ሐምሌ ሰባት ቀን፡፡
በዛሬው ቀጠሮ በፍቃዱ ኃይሉ ያላመነበትን የእምነት ክህደት በኃይል እንዲፈርም መገደዱን ተናግሯል፡፡ እንደምንጮች ገለጻ ከኾነ አብዛኞቹን እስረኞች በከፍተኛ ጫናና በድብደባ በመርማሪ ፖሊሶች የተረቀቀውንና በእነርሱ ሐሳብ የተዘጋጀ የእምነት ክህደት ቃል ላይ ‹‹የሰጠሁት ቃል የኔ ነው ጥፋተኛ ነኝ›› ብለው እንዲፈርሙ ተደርጓል፡፡
የፍርድ ቤቱ መዝገቡን ማጠጋጋትና የእምነት ክህደት ቃሉ ፊርማ እስረኞቹን ለመክሰስ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ማሳያዎች በሚል በሕግ ባለሞያዎች ተገምቷል፡፡

lørdag 28. juni 2014

እያበበ የመጣዉ ህዝባዊ ትግል


ኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት እንወድሀለን በሚሉት ነገስታት ተረግጧል፤ ህብረተሰብዓዊነት አመጣንልህ ባሉት ወታደራዊ አምባገነኖችም ለ17 አመት እጅና እግሩን ታስሮ ተገዝቷል። እነዚህ ሁለት ለህዝብ ደንታ የሌላቸዉ መንግስታት ተራ በተራ በህዝብ ትግል ተንኮታኩተዉ የታሪክ ቅርጫት ዉስጥ ገብተዋል፤ ሆኖም ሁለቱንም መንግስታት በመራራ ትግል አሸንፎ የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግሉን ዉጤት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ይህ ኃያልና የረጂም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነ ህዝብ ዛሬም ነፃ አወጣንህ በሚሉት ዘረኛ አምባገነኖች እየተረገጠ ነዉ። አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም እየተረገጠ ነዉ። ዛሬም አየታሰረ ነዉ። ዛሬም እየተገደለ ነዉ። ዛሬም ይህንን ሁሉ በደል የሚያደርሱበትን የአንድ ወንዝና የአንድ መንደር ምርት የሆኑ ዘረኛ አምባገነን ገዢዎችን ከጭንቅላቱ ላይ ለማዉረድ እየታገለ ነዉ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ከምን ግዜም በተለየ መልኩ የወያኔን ዘረኛ አገዛዝ አምርሮ እየታገለ ነዉ፤ በተለይ በዚህ በያዝነዉ አመት ወያኔንና ሃያ ሁለት አመት ሙሉ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐቱን ለመደምሰስና ኢትዮጵያ ዉስጥ በፍትህና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዐት ለመገንባት የሚደረገዉ የሞት የሽረት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ወያኔ እግሩ አዲስ አበባን ከረገጠበት ግዜ ጀምሮ የጭቆና ተቋሞቹን በየቦታዉ ተክሎና ተደላድሎ ህዝብን እንዳሰኘዉ መርገጥ እስከጀመረበት ግዜ ድረስ አንዴ ሰዉ በላዉን የደርግ ስርዐት አስወገድኩላችሁ እያለ ሌላ ግዜ ደግሞ ፌዴራል ስርዐት መስርቼ ብሄር ብሄረሰቦችን ነፃ አወጣሁ እያለ ለተወስነ ግዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ያ በፌዴራሊዝም፤ በዲሞክራሲና በይስሙላ ምርጫ የተሸፈነዉ የወያኔ አስቀያሚ ገበና ይፋ እየሆነ መጥቶ ወያኔ አርግጫዉንና ግድያዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ትግሉን፤ እስሩንና ስደቱን ተያያዙት።
የወያኔን መሰሪ አላማ ገና ከጧቱ የተረዱ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ይህንን መሰሪ አገዛዝ በተደራጀ፤ ባልተደራጀ፤ በተባበረና በተበታተነ መልኩ ሲታገሉ ቆይተዋል። ሆኖም የአገራችንን የፖለቲካና የኤኮኖሚ መዋቅሮች ሙሉ ለሙሉ ከሚቆጣጠረዉ ወያኔ ጋር በቁጥር፤ በአይነትና በይዘት የሚመጥን ትግል ማካሄድ ባለመቻላቸዉና እንዲሁም ብትራቸዉን ወያኔ ላይ ብቻ ከመሰንዘር ይልቅ እርስ በርስ ስለሚላተሙበት ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ በሌለዉ ወያኔ ላይ የትግል የበላይነት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ወያኔም እኛዉ ዉስጥ ከመካከላችን የበቀለ እሾክ በመሆኑና ደካማ ጎናችንን በሚገባ ስለሚያዉቀዉ በዚሁ ደካማ ጎናችን እየገባና እርስ በርስ እያባላን የስልጣን ዘመኑን እስከዛሬ ማራዘም ችሏል።
ወያኔ የአንድን አካባቢ ህዝብ ከሌላዉ አካባቢ ህዝብ፤ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል ከሌላ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሆነዉ ባልሆነዉ ምክንያት እየፈጠረ ማጋጨቱን አሁንም አላቆመም፤ እንዲያዉም ይበልላችሁ ብሎ በስፋት እንደቀጠለበት ነዉ። ዘንድሮ ግን ህዝብ፤ የተቃዋሚ ኃይሎችና በወያኔ ተንኮል ተታልለዉ የእርስ በርስ ሽኩቻ ዉስጥ ገብተዉ የነበሩ የህዝብ ወገኖች ሁሉ የወያኔን የከፋፍለህ ግዛዉ ደባና ሴራ በሚገባ ያወቁ ይመስላል። ለምሳሌ በቅርቡ አምቦና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ ከፍተኛ ፀረ ወያኔ የተቃዉሞ ሰልፍ በተካሄደ ግዜ የወያኔ ካድሬዎች የኦሮሞ ህዝብ ቁጣና መነሳሳት አቅጣጫዉን ቀይሮ በትግል አጋሩ በአማራ ህዝብ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ያልፈነቀሉት ዲንጋይ አልነበረም። ሆኖም ወያኔን ከስልጣን ለማባረርና የአገራቸንን ወደፊት በህዝብ እጅ ላይ ለማስቀመጥ ቁልፉ መተባባርና አንድ ላይ መቆም መሆኑን የተረዳዉ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ቁጣ ይበልጥ በወያኔ ላይ ነደደ እንጂ አንደቀድሞዉ ለወያኔ የተንኮል ሴራ እጁን አልሰጠም።
ወየኔን በተለያዩ የትግል ስልቶች የሚፋለሙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በፀረ ወያኔ አቋማቸዉና በአላማቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ከጎናቸዉ እንዳለ እንኳን እኛ ወያኔም በሚገባ ያዉቃል። ህዝብን የመሰለ እንደ ዉኃ ማጥለቅለቅ የሚችል ኃይል ከጎናቸዉ ያሰለፉ ድርጅቶች ደግሞ ወያኔን የመሰለ ምንም ህዝባዊ መሰረት የሌለዉን ኃይል ቀርቶ ፊታቸዉ ላይ የቆመን ምንም አይነት ኃይል ከማሸነፍ የሚገታቸዉ ምንም ነገር የለም።
ሆኖም ዉኃም ቢሆን ምን ያክል ኃይለኛ መሆኑ የሚታወቀዉ ተገድቦ ወደ ተፈለገበት አቅጣጫ እንዲሄድ ሲደረግ ነዉና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችም ከጎናቸዉ የቆመዉን ህዝብ አስተባብረዉ አገራችንን ወደ ድል መምራት የሚችሉት መጀመሪያ እነሱ ተባብረዉ ህዝብን በአንድ አላማና በአንድ አመራር ስር ማሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነዉ። ዛሬ በሁሉም አካባቢዎች ባይሆንም አገር ዉስጥና ካገር ዉጭ በተለያዩ አካባቢዎቸ ይቅናችሁ በሚያሰኝ መልኩ ጎልተዉ የሚታዩ ብዙ የትብብርና የትግል ቅንጅት ጅምሮች አሉ። በገበሬዉና በሰራተኛዉ፤በወጣቱና በወታደሩ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ብሄረሰቦችና በተለያዪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከመለያየት ይልቅ የመቀራረብ፤ ከመወቃቀስ ይልቅ የመወያየት ከመጠላለፍ ይልቅ የመተቃቀፍ አዝማሚያዎች በብዛት እየታዩ ነዉ።
ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ጀምሮ እስከቅርብ ግዜ ድረስ የተቃዋሚዉን ጎራ በተለይም አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኙትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልህቃን ለሁለት ከፍሎ ሲያጨቃጭቅ የከረመዉ ወያኔን በህዝባዊ አመጽ ወይስ በህዝባዊ እምቢተኝነት ታግለን እናዉርደዉ የሚለዉ ጥያቄ ዛሬም ድረስ አዎንታዊ እልባት ባያገኝም ዛሬ ሌላ ቢቀር እንደቀድሞዉ የተቃዋሚዉን ጎራ ለሁለት ከፍሎ የወያኔ መጠቀሚያ ማድረግ አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብም እኔ ያለሁት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉና ወይ ተደጋግፋችሁ አዉጡኝ አለዚያም በቻላችሁትና በሚታያችሁ መንገድ አዉጡኝ ነዉ የሚለን እንጂ በኛ መጨቃጨቅ የሱ የጉድጓድ ዉስጥ ቆይታ ዬትየለሌ እንዲሆን አይፈልግም። ዛሬ ይህንን ተደጋግፋችሁ ነጻ አዉጡኝ የሚለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ሰምተዉ በየጫካዉና በየበረሃዉ ከወያኔ ጋር የሞት የሽረት ትግል ለማድረግ የቆረጡ ኃይሎች የሚያደርጉት መሰባሰብና በተባበር ወገንን እጅግ የሚያበረታታ ጠላትን ደግሞ ያንኑ ያክል የሚያንቀጠቅጥ መልካም ጅምር ነዉ።
ከተለያዩ የአገራችን ኣካባቢዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተዉጣጥተዉ ወያኔን በሚገባዉ ብቸኛ ቋንቋ ለማነጋገር ቆርጠዉ የተነሱት የኢትዮጵያ ልጆች ወያኔን አንከባልለዉ የሚጥሉት ባነገቡት ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን በህብረታቸዉና በአላማ ጽናታቸዉ እንደሆነ በሚገባ ያዉቃሉ። ለዚህም ነዉ ዛሬ እነዚህ ጀግኖች ባሉበት ጫካና በረሃ ሁሉ የሚሰማዉ መዝሙር . . . . ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ . . . ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ደሜን የማፈሰዉ የሆነዉ።
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከዘረኞችና እነሱ ከገነቡት ዘረኛ ስርዐት ለማላቀቅ ዉስብስብነት ገብቷቸዉ ይህንን ዉስብስብ ትግል ከመታግል ዉጭ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለ ተረድተዉ የትግል ህብረትና አንድነት የጀመሩ ብዙ ወገኖች አሉ። ይህ የሚያበረታታና ተስፋዉ የለመለመ ጅምር የሁላችንም ድጋፍና ተሳትፎ የሚያስፈልገዉና አለንልህ ሊባል የሚገባዉ አገራዊ ጅምር ነዉ። በዚህ ጅምር ዉስጥ ትንቅንቅ አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ መስዋዕትነት አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ ድል አለ። በህዝባዊ እምቢተኝነቱ ጎራ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በብዙ የኢትዮጵያ ከተማዎች ዉስጥ ህዝቡ የወያኔን ግልምጫ፤ እስርና ድብደባና ግድያ ከምንም ባለመቁጠር በየአደባባዩ ወያኔን ፊት ለፊት መጋፈት ጀምሯል። ወያኔን በብዕራቸዉ የሚታገሉ ወጣቶችም ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት ይሻለናል ብለዉ በሰላ ብዕራቸዉ ህዝብን እንዳስተማሩ ቃሊቲ ወርደዋል። በህዝባዊ አመጹ ጎራ ደግሞ የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም ቆርጦ የተነሳዉ የኢትዮጵያ ወጣት አዲሱን የኢትዮጵያ የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት ታሪክ በደሙ ለመጻፍ የከተማ ኑሮ በቃኝ ብሎ የጫካና የበረሃ ኑሮዉን ተያይዞታል።
ዛሬ ይህንን እንዳባቶቹ ዱር ቤቴ ብሎና ጠመንጃቸዉን አንግቦ ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ የጀመረዉን ህዝባዊ አርበኛ የብሄረሰብ ስብጥር የተመከለተ ማንም ሰዉ የአገራችን ኢትዮጵያ ዳግማይ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑን በሙሉ አፉ ደፍሮ መናገር ይችላል። ወያኔ በነጋ በጠባ ከሚያስረዉና የወደፊቱን ካጨለመበት ወጣት ጀምሮ ገዳማቸዉን ካፈረሰባቸዉ መነኮሳትና ቤ/ክርስቲያናቸዉን አስካረከሰባቸዉ ካህናት ድረስ የትግሉ ጎራ ሁሉንም አይነት ኢትዮጵያዉያን በብዛት አካትቶ ይዟል።
ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በሚቆይባት በእያንዳንዷ ቀን ተጨማሪ ወጣቶች እንደሚታሰሩ፤ተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፈኞች እንደሚገደሉ፤ተጨማሪ ጋዜጠኞች ሽብርተኞች ተብለዉ እንደሚታሰሩ፤ ተጨማሪ ምሁራን አገራቸዉን ለቅቀዉ እንደሚሰደዱና የአገራችን የኢትዮጵያም አንድነት የበለጠ እየላላ እንደሚሄድ ሁላችንም በሚገባ እናዉቃለን። በሌላ አነጋገር ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የመቆየት አንድ ተጨማሪ ቀን በሰጠነዉ ቁጥር የኛም ሆነ የአገራችን ህልዉና በቀላሉ የማናበጀዉ እጥፍ ድርብ ችግር ዉስጥ ይወድቃል። ይህ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነዉ ችግርና መከራ ገና ከጧቱ የታያቸዉ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ አመታት የየራሳቸዉን እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት ዉስጥ አንዳንዶች ዉድ ህይወታቸዉን ገብረዋል፤ ሌሎች ደግሞ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፤ አገር ለቅዉ ተሰድደዋል። እዚህ ላይ አንድ ሁላችንም በትክክል ልንገነዘበዉ የሚገባን ሀቅ አለ፤ እሱም የኢትዮጵያ ችግር የአንድና የሁለት ሰዉ ችግር አይደለም፤ በአንድና በሁለት ሰዎች የሚፈታ ችግርም አይደለም። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፤ ችግሩም የሁላችንም ነዉ፤ ወያኔን በቆራጥነት ታግለን አገራችንን ከመበታተን ህዝባችንን ደግሞ ከዘረኝነትና ከድህነት ማላቀቅ ያለብንም እኛዉ ነን። ወያኔ ስለጠላነዉ፤ ስለሰደብነዉ ወይም ስለጮህንበት ብቻ በህዝብና በአገር ላይ በደል መፈጸሙን አያቆምም:፡ እነዚህ በደሎችና ችግሮች የሚቆሙትና የኢትዮጳያ ህዝብ የሰላም አየር መተንፈስ የሚችለዉ ወያኔ ከስልጣን ሲወገድና በምትኩ ኢትዮጵያዉያንን በእኩልነት የሚያስተናግድ መንግስት በኢትዮጵያዉያን ተመርጦ ስልጣን ሲይዝ ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰብዓዊ መብቱ፤ ለነጻነቱና ለእናት አገሩ አንድነት መከበር ትናንት ካደረገዉ ትገል የዛሬዉ እጅጉን የሚያበረታታ ቢሆንም አሁንም ይህንን ህዝባዊ አደራ ከተሸከሙ ኃይሎች የሚጠበቅ ብዙ ስራ አለ። ከላይ ከፍ ሲል ደጋግመን እንደጠቀስነዉ ከወያኔ ጋር በሚደረገዉ የትግል ሂደት ዉስጥ የህዝብ ኃይሎች የሚመኩበት ትልቁ ኃይል ህብረታቸዉና ከጎናቸዉ የተሰለፈዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ። የተቃዋሚ ኃይሎች አለመተባበርና አለመግባባት ከጎናቸዉ በተሰለፈዉ ህዝብ ዉስጥም አለመግባባትና አለመተባበር ይፈጥራል:፡ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ እየተቃወምነዉና እየታገልነዉ ዛሬ ድረስ የደረሰዉ እኛ ዉስጥ የነገሰዉ አለመተባበርና አለመግባባት እየረዳዉ ነዉ። ስለዚህ ዛሬ ወያኔን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከተወገደ በኋላም የሚገጥሙንን ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን የመገንባትና ህዝባዊ ስርዐትን የመፍጠር አደራ ጭምር ለመወጣት በህብረትና በአንድነት መቆም አለብን። አንድነታችንና ህብረታችን አንድ ስራ ሰርቶ ወያም አንድ ነጣላ አላማ ከግብ አድርሶ የሚቆም ሳይሆን የእኛን ሀላፊነት ተወጥተን ለልጅ ልጆቻችን የምናስተላልፈዉ ብሄራዊ ቅርስ መሆን አለበት።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

የመቐለ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ተከለከለ! – አብርሃ ደስታ

June 28/2014
ህወሓቶች የመቐለ ህዝብ ዓፈናውን በሰለማዊ ሰልፍ እንዳያሰማ ለማፈን ያህል የነገው የመቐለ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ከልክሏል። በደብዳቤ እንዲያሳውቁን በጠየቅነው መሰረት የደብዳቤው ይዘት ምን መሆን እንዳለበት ለስድስት ሰዓት ያህል ከተወያዩ በኋላ እነሆ ቀኑና ይዘቱ አዛብተው ሰጥተውናል። ስህተት አለው ስንላቸው፤ ዝም ብላቹ ያዙ እሱም በስንት መከራ ነው ብለውናል። ባጭሩ የተቀመጠው ምክንያት ክልላዊና ከተማዊ ዝግጅት ስላለን አይመችም፤ በቂ የፀጥታ ኃይልም የለንም የሚል ነው። ግን ነገ ምንም ዝግጅት እንደሌለ አረጋግጠናል። በቂ የፖሊስ ኃይል እንዳለም የታወቀ ነው። ንፁሃን ዜጎች ለመደብደብና ለማሳሰር ፖሊስ ያላጡ ለሰለማዊ ሰልፍ ኃይል የለንም እያሉን ነው። ደሞኮ ለሚፈጠር ችግር ሓላፊነት ትወስዳላቹ ብለው አስፈርመውናል። ሌላ ደግሞ የፎርም ችግር እንዳለ ፅሑፉ ያትታል። የምን ፎርም መሆኑ አይታወቅም። ለማንኛውም ሰልፉ ለመከልከል ፈልገው በደብዳቤው የሚፃፍ ምክንያት ማጣታቸው ነው የሚያሳየው። ደብዳቤው ለህዝብ እንበትነዋለን ስላልናቸው ‘ሌላ ግዜ የምንፈቅድ መሆኑን እናሳውቃለን’ ይላል ደብዳቤው። ባጠቃላይ ግን ህወሓት የመቐለ ህዝብ ድጋፍ እንደሌለው እንዲጋለጥ አልፈገምና ከልክሎታል። ጨቋኝ ስርዓት የህዝብ ድጋፍ የለውም። የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው እንዲታወቅ ግን አይፈልግም። ሰልፉ ሌላ ግዜም ቢሆን ይደረጋል። ለነገ ግን የመቐለ ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቱ መነፈጉ ግልፅ ሆኗል።

ኑ ፦ ኢትዮጵያዊነትን በኒውዮርክ እናክብር

 ኢትዮጵያዊነትን በኒውዮርክ እናክብር

  • 34
     
    Share
Teddy NYኢትዮጵያዊነት በዘረኛው የወያኔ ስርአት ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ባለንበት ዘመን እውነተኛ ተቆርቋሪ ዜጎች የሆንን ሁሉ በያለንበት ሳንታክት የኢትዮጵያ አገራችንን የአንድነት እና የታሪክ ታላቅነት መስበክ ይጠበቅብናል። አገራችን ኢትዮጵያ በዘር እና ሀይማኖት ሳትከፋፈል ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የያንዳንዳችን ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል፤ ለወጣቱ ትውልድ እና ተተኪ ልጆቻችን የኢትዮጵያዊነትን ፍቅር መስበክ የታሪክ ግዴታችንም ነው።
ይህን አላማ ዘዎትር ሳይታክቱ በሙያቸው ክሚያሳዩ የኪነጥበብ ኮከቦቻችን ጎን በመቆም የአላማ አጋሮቻቸው መሆናችንን ማስመስከር ይጠበቅብናል። በመጪው ቅዳሜ ሰኔ ፪፰፣ ፪፻፮ ( ጁልይ ፭፣ ፳፩፬) ከነዚህ አገር ወዳድ የኪነ ጥበብ ሰዎቻችን አንዱ እና ተወዳጁ የሆነው ቴዲ አፍሮ በኒውዮርክ የሰመር ስቴጅ ፌስትቫል ላይ ኢትዮጵያንን ወክሎ በሚያደርገው የዘፈን ትርኢት ላይ መላው በኒውዮርክ እና አካባቢው የምንገኝ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያኖች በመገኘት ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገን በማድመቅ ለአገራችን ያለንን ፍቅር እንግለጽ።  ስለኢትዮጵያዊነት ፍቅር በሚያዜማቸው ዜማዎች እየተዝናናን ሃገር እና ወገን ወዳድነታችንን እናስመስክር።

መግቢያው ነፃ ነው 
ለተጨማሪ መረጃ አባሪ የሆነውን በራሪ ማስታወቂያ ይመልከቱ።  
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑ

fredag 27. juni 2014

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ



አቶ አቻምየለህ ገሠሠ
አቶ አቻምየለህ ገሠሠ
አቶ አቻምየለህ ገሠሠ በ1946 ዓ.ም በቀድሞው ቤጌምድር ሰሜን ጠቅላይ ግዛት በጋይንት አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ አንሰታ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ ቅድመ አብዮትም ሆነ ድህረ አብዮት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ የሰሩ ሲሆን የፖለቲካ ተሳትፎአቸው በተመለከተ አቶ አቻምየለህ ለለውጥ ባላቸው ፍላጎት የተነሣ በ1992 ኢዴፓን ከመሰረቱት አንዱ በመሆን የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ምክትል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም ቅንጅት ሲመሰረት ከመስራቾች አንዱ በመሆን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሰጥተዋል፤ በ2000 ዓ.ም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሲመሰረትም ከመሥራቾቹ አንዱ በመሆን ኦዲትና ኢንስፔክሽን አባል በመሆን አገልግለዋል፤ በ2006 ዓ.ም ታህሣሥ ወር በተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የብሔራዊ ም/ቤት አባል ሆነው ከመመረጣቸውም በላይ የዲሲፕሊንና ሥነሥርዓት ኮሚቴ አባል ሆነው በመመረጥ ታከተኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማገልገል ላይ የነበሩ፣ ድንገት ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ አርፈዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነሥርዓት የሚፈጸመው ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ የሚፈጸም መሆኑን ከቤተሰቦቻቸው ለፍኖተ ነፃነት ያደረሱን ዜና ያመለክታል፡፡ አቶ አቻምየለህ ገሠሠ ረታ የሁለት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

The Continued Imprisonment of Six Ethiopian Bloggers

by Mayukh Sen
Internet Monitor

This is Zone Nine: The Continued Imprisonment of Six Ethiopian Bloggers

There’s a prison, hidden in the suburbs of Addis Ababa, named Kality. Home to many of Ethiopia’s political prisoners, the prison is divided into eight zones. The last of these zones, Zone Eight, is home to detained journalists, human rights activists, and dissidents.Free Zone 9 Bloggers banner. Original design by Hugh D'Andrade, remixed by Hisham Almiraat.
To some Ethiopian citizens, there is a Ninth Zone – a Zone dedicated to the “proverbial prison in which all Ethiopians live”. In 2012, a group of passionate Ethiopian bloggers launched Zone Nine, a blogging collective that, in its own words, “blogs because it cares”. Zone Nine prides itself on providing a counter to the opinions, voices, and attitudes that dominate Ethiopia’s press.
In April 2014, six of Zone Nine’s bloggers – along with three print journalists suspected of associating with the group – were arrested on the grounds that they were covertly receiving money from foreign human rights organizations to incite violence through social media.
63 days have passed since their detention. The bloggers have appeared in court continually over the past few months while being detained in Addis Ababa’s Maekelawi detention center. No formal charges have been leveled against them as of yet. That said, activists fear that these bloggers and journalists will suffer the same fate that befell Eskinder Nega and Reeyot Alemu, two journalists imprisoned and charged with terrorism (a crime that carries heavy fines and a lengthy prison term) in 2011.
The collective has blogged about numerous political issues affecting the Ethiopian populace, hoping to bolster civic discourse in service of social change. In the wake of Prime Minister Meles Zenawi’s death, for example, Zone Nine penned scathing critiques of Zenawi’s proclaimed economic development achievements, casting doubt on his legacies. They also partnered with Global Voices to launch Global Voices in Amharic in 2012, hoping to make international news accessible to local readers.
Since its inception, Zone Nine has amassed a passionate readership within the country. According to its own bloggers, Zone Nine’s stories have occasionally been picked up by wider-known publications within the country, signaling wider support for the messages it has broadcasted. Outside of Ethiopia, the detention of the Zone Nine bloggers has ignited public furor. Global Voices launched a #FreeZone9Bloggers hashtagging campaign and organized a FreeZone9Bloggers Tweetathon on May 14, while UN High Commissioner Navi Pillay criticized Ethiopia’s increasing frequency of charges against journalists on the grounds of terrorism.
The arrests arrive in the context of what some activists fear is a growingly repressive media milieu in Ethiopia. For years, journalists – on and offline – have been susceptible to governmental terrorism charges. The Committee to Protect Journalists has claimed that more journalists have fled Ethiopia since May 2013 than in anywhere else in the world. An ambiguously-worded anti-terrorism law, mobilized in 2009, gave the Ethiopian government the power to act against any form of political dissent so long as it is deemed “supportive of armed opposition activity”. The passage of this law has led to the arrest and detention of scores of journalists.
Recently, this fight against journalists has moved online, with Ethiopian governmental officials moving to counteract online criticism of their efforts by training blogging recruits to attack any online criticism of the administration (a practice known as astroturfing). The government has trained over 230 bloggers since May, teaching them how to post comments that sing the praises of the regime on social media—a particularly interesting move, given that less than 2% of Ethiopia’s population has Internet access.

ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)


ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ
1040ትናንት ሰኔ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ›› በሚል ርዕስ እኔን ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እና ዳዊት ሰለሞንን የውይይት መነሻ እንድናቀርብ በጋበዘን መሰረት በእኔ በኩል ለውይይት መነሻ ሀሰብ ይሆናሉ ብዬ ያቀረብኋቸውን ሶስት ነጥቦች እንዲህ አቅርቤያዋለሁ፡፡
በመጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ‹‹ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ›› በሚል ርዕሥ የውይይት መነሻ ሀሳብ ከሙያ አጋሮ ቼ ጋር እንዳቀርብ ስለጋበዘኝ በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29
ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ የፈረሙበት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ይህ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 29 (1) እና (2) ላይ ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-

‹‹ማናኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡ ፣ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ-ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ በማንኛውም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡››

1012ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከጓደኛዬ አቤል ዓለማየሁ ጋር
‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃነው መጽሐፍ ውስጥ ይህን ሕገ-መንግሥት አስመልክቶ ዶ/ር ነጋሶን ቃለ መጠይቅ በማድረግ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኩት አንቀጽ 29 መከበር አለመከበሩ ከጥያቄዎቼ መካከል አንዱ ነበር፡፡ ዶ/ር ነጋሶም እሳቸው በምላሻቸው እንዲህ አሉ፡-
‹‹እንደ ጥሩ ምሳሌ የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን እና የእስክንድር ነጋን ጉዳይ መውሰድ እንችላለን፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት፣ ርዕዮት እንደጋዜጠኛ የፈለገችውን ሐሳብ ጽፋ ለየትኛውም ሚዲያ የማቀበል መብት አላት፡፡ ይህ ተጥሶ ‹‹ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላት›› ተብሎ ተፈረደባት፡፡ እስክንድር ነጋ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤታችን ድረስ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ተጋብዞ በመምጣት የቀረበውን ሐሳብ ከተሰብሳቢዎች ጋር ተቀምጬ አዳምጫለሁ፡፡ ሐሳቡን በመግለጹ ‹‹ሽብርተኛ ነው›› ተብሎ ተፈረደበት፡፡ እነ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳ ‹‹ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ጋር ለምን ተነጋገራችሁ?›› ተብለው ነበር የታሰሩት፡፡ በተጨማሪም በአንድነት ፓርቲ ስር ትታተም የነበረችው የ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋዜጣ ያለመታተም ጉዳይ፣ የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ መታገድ፣ የ‹‹አዲስ ነገር›› እና የ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ጋዜጦች የደረሰባቸውን ችግር እናውቃለን፡፡ አንቀጽ 29 እስከአሁን አልተከበረም፡፡››

1045እንግዲህ የተከበራችሁ የዚህ ውይይት ተሳታፊዎች፣ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ፈርመው ያጸደቁት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሕገ-መንግሥቱ አለመከበሩን ጥቂት ምሳሌዎችን በማቅረብ ተናገርው ነበር፡፡ ይህ የሥርዓቱን ህገ ወጥነት እና አደገኝነት የሚያሳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የጊዜው መንግሥታችን ‹‹ሀገርን የማስተዳድርበት ወርቃማ ሕግ አለ፡፡ ይህ ትልቅ ስኬታችን ነው›› በማለት ዘወትር ሲናገር እንዳደምጠዋለን፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 29 በተለያዩ በርካታ ጊዜያትና በተለያዩ መንገዶች ሲንድ፣ ሲሸራርፍና ሲደፍር፤ ናድኩት፣ ሸራረፍኩና ደፈርኩት አይለንም፡፡ ይልቅ ጥቂት የማይባሉ ጋዜጠኞችን ‹‹ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ሲንቀሳቀሱ … ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር በመተባበር የሀገርን መሰረተ ልማቶች በሽብር ለማውደም ሲያሴሩ …ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ጠርጠሮ በመያዝ በፍርድ ሂደትም በተለያዩ ዓመታት የጽኑ እስራት ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡ አሁንም በመሰል አካሄዶች ፖሊስ (በሽብርተኝነት ወንጀል) ሶስት ጋዜጠኞች እና ስድስት ጦማሪያን (ብሎገሮች)ን ‹‹ጠጥሬያቸዋለሁ›› በሚል በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ ከታሰሩ ከ56 ቀናት በላይ አልፏቸዋል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ሕገ-መንግሥቱን አክብረው የሚንቀሳቀሱ ነበሩ ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ዛሬም ሕገ-መንግሥቱን እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሃሳቦችን አንስተን በጋራ ብንወያይ ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱ በመናድ ብሎ ጋዜጠኞችን ፖለቲከኞችንና ዜጎችን በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሁሉ እሱም የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች ሲንድ፣ ሲሸራርፍና ሲደፍር በሕግ እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል? በሚለው ላይ እንነጋገር እና የመፍትሔ ሀሳቦች ይንሸራሸሩ፡፡


ከሕገ-መንግሥቱ በፊት
10441001_ኢህአዴግ 1983 ዓ.ም ላይ የደርግ ሥርዓትን ከገረሰ በኋላ ነጻ ፕሬስ ማወጁ ብዙዎቻችንን የሚያስማማ እና ሊመሰገንበት የሚገባ ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ሥርዓቱ ይህንን በማድረጉ ከሰማይ መና እንዳወረደ ተደርጎ መቆጠር አለበት አልልም፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለይ እራሱ ጠቅልሎ በያዛቸው እና እንደፈለገ በሚዘውራቸው ሚዲያዎች ነጻ ፕሬስ ማወጅ መቻሉን ከሚጠበቀው በላይ በማጋነን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታነት ሲጠቀምበት ተመልክተናል፡፡ ኢህአዴግ በትረ-ሥልጣን ባይይዝ ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ፕሬስ ፈጽሞ አይታወጅም ብሎ መደምደምም ከባድ ነው፡፡ (እንዲህ ብለው የሚያስቡ ስላሉ ነው) በዚያን ጊዜ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመሄድ ኢህአዴግ ነጻ ፕሬስን ማወጁ የውዴታ ግዴታውም ነበር – ከልቡ ቢያምንበትም ባያምንበትም፡፡
ከነጻ ፕሬሱ እወጃ በኋላ ባሉት ዓመታትም፣ እስከአሁን ድረስ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲዳክር መጓዙን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ስለሚሆን አልፈዋለሁ፡፡
አንድ ጉዳይ ግን በውስጤ ብዙ ጊዜ ይብሰለሰላል፡፡ እራሴንም ደጋግሜ ጠይቄ ለራሴ መልስ አግኝቼለታለሁ፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕገ መንግሥቱ ብቻ መሆኑን ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሕገ-መንግሥቱ በፊት ቀዳሚ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህንን የምለው፣ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ በነጻነት እንዲያስብ፣ ሐሳቡን ሐላፊነት በተሞላው መልኩ እንዲናገር፣ እንዲጽፍ፣ በተለያዩ ጥበባቶችና የመግባቢያ መንገዶች እንዲያስተላልፍ እና እንዲቀበል ቀድማ ለግሳዋለች፡፡ ይህንን የላቀ የተፈጥሮ ሕግ ከሕገ-መንግሥት ጋር ተሰናስሎ በሕግ ማዕቀፍ መደገፉ ጥቅሙ የላቀ መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አምባገነን ሥርዓቶችን ያየች ሀገር ቀላል የማይባሉ ዜጎች ተፈጥሯዊውንም ሆነ ሕገ-መንግሥታዊ የማሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ …ወዘተ መብቶቻቸው ተሸብቦ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ መውደቃቸውን አምናለሁ፡፡ ይህም ሥርዓታቱ (ደርግ የለየለት፣ ኢህአዴግ ደግሞ ዴሚክራሲያዊ ካባ የደረበ አንባገነን ነው) ለሥልጣናቸው ማቆያ እና ማራዘሚያ ሲሉ ከእነሱ ሃሳብ በተቃራኒው በሚያስቡ እና በድፍረት በሚናገሩ፣ በሚጽፉ …ዜጎቻቸው ላይ በሚወስዷቸው ኢ-ፍትሃዊ የግድያ፣ የድብደባ፣ የእስር፣ የእንግልት፣ የስደት …እርምጃዎች በዋነኝነት የሚመጣ ነው፡፡ አፋኝ የሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁም ኢትዮጵያኖችን ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን የማሰብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር …መብቶች በእጅጉ የሚጨቁን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በመሆኑም ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ የማክበር እና የማስከበር ግዴታን እንዴት እንወጣው? በሚለው ላይ ብንወያይበት መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡


የእስረኞች አያያዝ እና ሰብዓዊ መብቶች
10483746_በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 18 (1) ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› ይላል፡፡ ይህ ግን በተለያዩ ጊዜያት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በግልጽ እየተጣሰ እንደሚገኝ እየደመጥን ያለነው፡፡ በዚያ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፈጸማል፡፡ ‹‹እመኑ›› ወይም ‹‹በሌላ ሰው ላይ መስክሩ›› ተብሎ ቶርች ይደረጋል፡፡ ዜጎች ይደበደባሉ፣ ውስጥ እግራቸው ይገረፋል፣ ቀዝቃዛ ውሃ ይደፋባቸዋል፡፡ ‹‹ወፌ ላላ›› የተባለ አውጫጭኝ ግርፍ ሰዎች እንደሚገረፉ ይነገራል፡፡ ይሄንን ጋዜጠኛ አና ጦማሪ በፍቃዱ ሐይሉ፣ ጦማሪያኑ አቤል ዋበላ እና አጥናፍ ድብደባ እና ጥፊ የመብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ እኔም ለጥቂት ቀናት ማዕከላዊ ታሰሬ በነበረበት ጊዜ ከብዙ ታሳሪዎች ድርጊቱ እንደሚፈጸም አረጋግጫለሁ፡፡ እኔ ታስሬበት በነበረበት ‹‹8›› ቁጥር ውስጥ ከጎንደር የመጣ ብርሃኑ የተባለ ሰው በድብደባ ብዛት እያነከሰ ነበር የሚሄደው፡፡ ከደቡብ ሱዳን በሽብር ጉዳይ ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል ከአንዱ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት (አቶ ኦኬሎ) በስተቀር መደብደባቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ የተደበበደቡትን የአካላቸውን ክፍል አሳይተውኛል፡፡ ለአራት ቀናት ያህል እንዲቆም የተቀጣ ወጣትም የደረሰበትን በመረረ መልኩ ነግሮኛል፡፡ በማንኛውም መንገድ ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲጣስ ‹‹ያገባናል፣ ድርጊቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እና አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው›› ብለን በድፍረት መናገር፣ የሚመለከተውን አካል መጠየቅና ድምጻችንን በተለያየ መንገድ ማሰማት ይገባናል፣ ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡

በመጨረሻም በጣም በማከብራቸው ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ‹‹ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን ማን ይፈራቸዋል?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ የማረከኝን ሀሳብ በመውሰድ የውይይት መነሻ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡

‹‹ …ለእኔም ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሌሉበት ገዥ አካል ከሚኖር ወይም ደግሞ ገዥ አካል በሌለበት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዓላማ በጽናት የቆምኩ፣ ለምሰራው ትክክለኛ ሥራ ሁሉ ኩራት የሚሰማኝ፣ ላመንኩበት ዓላማ ከልብ እና በወኔ የቆምኩ፣ ዓላማዬን ለማስፈጸም በከባድ እርምጃ ወደፊት የምገሰግስ፣ ላልሰራሁት ወንጀል ይቅርታን የማልጠይቅ፣ በምሰራው ሥራ ሁሉ የማላፍር፣ ቆራጥ እና የማያወላውል ባህሪን የተላበስኩ የኢትዮጵያ ጦማሪ ነኝ፡፡››

ኃይል ለነጻ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ጦማሪያን!

torsdag 26. juni 2014

የፊታችን ቅዳሜ በመቐለ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ይካሄዳል

አብርሃ ደስታ ከመቀሌ
ዓረና መድረክ ቅዳሜ ሰኔ 21, 2006 ዓም በመቐለ ከተማ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ያካሂዳል። ለሰልፉ የሚሆን ሙሉ ዝግጅት ተጠናቋል። የመቐለ ህዝብ በሰልፉ ለመሳተፍ ተዘጋጅቷል። ቅዳሜ ጥዋት ከአምስት ሺ በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።
mekele
ሰልፉ የጠራንበት ዋነኛ አጀንዳ መድረክ በአዲስ አበባና በክልሎች ዋና ከተሞች እያደረገው ካለው የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ አካል ሲሆን የሰልፉ ዋነኛ አጀንዳዎች ደግሞ የፍትህ እጦት፣ የነፃነት እጦት፣ የዉሃ ችግር፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ የመሬት ጉዳይ፣ የግብር ጉዳይ፣ የማዳበርያ ጉዳይ ወዘተ ናቸው።
ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትም ሰለማዊ ሰልፍ በማድረግ ይረጋገጣል። የትግራይ ህዝብ እስካሁን ድረስ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ተነፍጎ ይገኛል። በአላማጣ፣ ኲሓ፣ አይናለም፣ መቐለ (ገፊሕ ገረብ)፣ ሓውዜን፣ ዓዲግራት ወዘተ ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ መክረው በፌደራል ፖሊስ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል። ስለዚህ ቅዳሜ ጥዋት ሰለማዊ ሰልፍ የሚጀመርበት ታሪካዊ ቀን ይሆናል። በመቐለ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የተፈቀደ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ይደረጋል ማለት ነው።
ስለዚህ የመቐለው የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ከዉሃ ጥያቄ የዘለለ ነው። የዉሃ ጥያቄ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ሁኖ ሌሎች አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እየተገደሉ ነው። በሌሎች ክልሎችም እየተገደሉብን ነው። ንፁሃን ዜጎች ያለ ፍርድ እየታሰሩ፣ በድንጋይ እየተወገሩ፣ በፖሊስ እየተደበደቡ፣ በመርማሪዎች እየተገረፉ፣ ያለ ምንም ወንጀል በሽብር እየተከሰሱ ነው። ከዚህ በላይ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ የሚጠይቅ ጉዳይ የለም።
ከሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከመገረፍ፣ ከመታሰር፣ ከመገደል በላይ ምን ሊያደርጉን ይችላሉ? በሌሎችስ ከዚህ በላይ ምን ተደረገ? ስለዚህ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ በቂ ምክንያት አለን። የመቐለ ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ በሰለማዊ ሰልፍ ማክበር አለበት። የመቐለ ህዝብ እንደነ አዲስ አበባዎች፣ ባህርዳሮች፣ ደሴዎችና ሀዋሳዎች የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ሊከበርለት ይገባል።
የመቐለ ህዝብ ነፃነት ይፈልጋል። ስለዚህ ይሰለፋል። የቅዳሜ ሰልፍ በገዥው መደብ ካልተስተጓሆለ በቀር ኃይለኛ ሰልፍ ይደረጋል። በአደባባይ ስለሚደረግም ማንም ሰው አይቶ ይመሰክራል። የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ እንዳልሆነ ያስመሰክራል። ፎቶዎችና ቪድዮች እንቀርፃለን። ትመለከታላቹ።
ሰልፉ ቅዳሜ ጥዋት በ3:00 ሰዓት ከአደባባይ ዘስላሴ (ባዛር) ተነስቶ በሓውዜን አደባባይ አልፎ ሮማናት አደባባይ አቋርጦ አብርሃ ካስትል ሆቴል ከደረሰ በኋላ ወደ ናሽናል ሆቴል ታጥፎ በጤና ጣብያ በኩል ላዕለዋይ ፍርድቤት ደርሶ ሮማናት አደባባይ ላይ ይጨረሳል። የመድረክ መሪዎች ንግግር ያደርጋሉ። በ6:00 ሰዓት ይጠናቀቃል።
ህወሓት የሀዋሳውን፣ የባህርዳሩን፣ የአዲስ አበባውን ወይ የደሴውን ያህል ከፈቀደልን የቅዳሜ ሰልፍ በእርግጠኝነት የተዋጣለት ይሆናል። እስቲ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ሰልፍ ከፈቀደ እንይ። መቐለ ሰልፍ ልትጀምር ነው። ህዝብ ዓረና መድረክ ያለውን ድጋፍ ባደባባይ የሚገልፅበት ቀን: ቅዳሜ።
ህወሓት ሰልፉ እስኪጠናንቀቅ ድረስ ፀጥታ ካስከበረ ህወሓትን በፅሑፍ ነው የምናመሰግነው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ አስከብሮለታል ማለት ነውና። ሰለማዊ ሰልፍ መፍቀድ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሰልፍ ለትግራይ ህዝብ ተአምር ነውና። ምክንያቱም ተፈቅዶልን አያውቅም።
እስቲ ህወሓት ትፈተን። እስቲ ህወሓት የህዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ የሚተማመን ከሆነ ሰልፉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሰልፉን ለማየት ዝግጁ ይሁን።
ለማንኛውም ቅዳሜ እንገናኝ። የዉስጥ ለውስጥ ቅስቀሳው አልቋል። ነገ ዓርብ ፎርማል ቅስቀሳ ይደረጋል። በህዝብ ያለን ድጋፍ ለማወቅ ተከታተሉን።

የወያኔን የጥፋት ድግስ እናምክን!

ኢትዮጵያን የሚገዛው ጉጅሌ ሀገራችንን እየወሰደበት ያለው አደገኛ አቅጣጫ አሳሳቢ ከመሆን አልፎ የአደጋውን መራራ ፍሬ ማየት ከጀመርን ሰነበትን። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ወሳኝ ከሆነው የወደፊቱ የጋራ ጥቅማቸውና ህልውናቸው በበለጠ ልዩነታቸውና ያለፈ ታሪካቸው እንደዋናው ነገር እየተቆጠረ ለሚሰበከው ስብከት የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ብዙ ጥፋት በደረሰ ነበር።
ህወሃት በህዝቡ ውስጥ የኖረውን ልዩነት የጠብ፣ የግጭትና የመፈራራት መሰረት በማድረግ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ምኞት የተነሳ በመደዴ ካድሬዎቹ አማካኝነት ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ በማቃቃር እኩይ ተግባር ላይ ተጠምዶ ይገኛል።
ህወሃት ይህን የማጋጨት ስራ በተለይ በስልጣን የመቆየት ፍርሃት ባባነነው ቁጥር የሚጠቀምበት መሳሪያ አድርጎታል። በባህርዳር ላይ የብሄረሰቦች ኳስ ጭዋታ ውድድር ምክንያት አድርጎ፣ መደዴ ካድሬዎቹን አሰማርቶ ስታዲዮም ውስጥ ኦሮሞዎች እንዲሰደቡ ካደረገ በኋላ ነገሩን ከማረጋጋት ይልቅ በኦሮሞኛ የቴሌቪዥንና ሬድዮ፣ ኦሮሞዎች በአማራዎች ተሰደቡ ብሎ ያስነገረው ለምንድን ነው? ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ቁጣና ጠብ ለመቀስቀስ ብሎም በዚህ ጠብ ውስጥ ገላጋይ በመምሰል የአንዱ ብሄር ጠባቂ መስሎ ለመታየት ጉዳዩን ባልተረዱ የዋሆች ውስጥ ለመግባት ይፈልጋል። በአማራ ተወላጆች አካባቢ እኛ ከሌለን ኦሮሞ ይፈጇቹኋል፤ በኦሮምያም በሶማሊያም እንዲሁ በተዘጋ በር ውስጥ በተቃራኒው ዘረኝነትንና መከፋፈልን በመስበክ ንጹሃኑ ህዝብ ከፍርሃት ተነስቶ ተገዥ ደጋፊዎቹ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ መሆኑንም ያልገባቸው የዋሆች ይኖራሉ። ህወሃትንና ባህርዩን በቅጡ ለምናውቀው ወገኖች ግን ይህ ተንኮሉ ትልቅ ሚስጥር አይደለም።
የጉጅሌው ቡድን የራሱን ስልጣንና የዝርፊያ ኢኮኖሚ ኮርቻ ለማደላደል እስከረዳው ወይም የሚረዳው መስሎ እስከታየው ድረስ ደሃ ገበሬዎችን ማፋጀትን፣ ህዝብን እርስበርስ ማናከስን፣ የቂም መርዝ መዝራትን የሚያየው እንደ ፖለቲካ ጥበብ ነው።
ጉጅሌው ብልጠት መስሎት የጎሰኝነትንና የማንነትን ደመነፍስ የሚነካ ፕሮፖጋንዳ በህዝቡ ውስጥ በመንዛት ሊያደርስ የፈለገው ጥፋት በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ስላልሰራለት የራሱን ሎሌዎችና ተካፋይ መደዴ ካድሬዎችን በማሰማራት የጭካኔ ስራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን በብዙ መረጃዎች አረገጋግጠናል። በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚካሄደውን የህዝብ ማፈናቀልና ግጭት የሚመራው ራሱ ህወሃት ያሰማራቸው ካድሬዎች እንጂ በራሱ በህዝቡ ተነሳሽነት እንዳልሆነ ሁላችንም ልናውቅ ይገባል። በዚህ ሳይጣናዊ አካሄድ ለምትደርሰው ለያንዳንዷ ጉዳት ሀላፊነት የሚወስደውም ራሱ ህወሃት መሆኑን ግንቦት 7 አጥብቆ ያምናል።
ህወሃት መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የሚደግስልንን የጥፋት ድግስ ለማምከን የየብሄረሰቡ ልሂቃን ሁሉ አንድ ላይ ሆነን ህዝባችንን እንድንታደግ ግንቦት 7 ለሁሉም የነጻነት ሃይሎች ጥሪውን ያቀርባል።
ግንቦት 7 በዚህ የህወሃት የጨለማ መንገድ ላይ የሚያበራውን የብርሃን ችቦ ይበልጥ በማብራት ላይ ይገኛል። ሁላችንም በምናገኘው የብርሃን ሃይል ጨለማው ላይ እያበራን ከማሳየት አልፈን ወደ መቃብሩ ልንገፋው ይገባል።
ግንቦት 7 በኢትዮጵያ የማንነትና የብሄር ብሄረሰብ ጉዳዮች በሰለጠነ መንገድ እና በመደማመጥ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደረግ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ያምናል። ይልቁንም የወደፊቱ የህዝባችንና የሀገራችን ጥቅም ይበልጥ የሚከበረው በስብጥርነታችን ላይ በምንገነባው አንድነት መሆኑን ያምናል።
የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች የነጻነታችን ጊዜ ቅርብ ነው። ህወሃት መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ ያዘጋጀልንን የጥፋት ድግስ፣ ሀገራችን የጋራ ጠላት በመጣባት ጊዜ ሁሉ እንደምታደርገው በአንድ ላይ ታግለን የጋራ ታሪክ እንሰራ ዘንድ የዘወትር ጥሪያችን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

ምስራቅ እዝ የመከላከያ መኮንኖች መካከል ውስጣዊ ውጥረት መስፈኑ ተገለጸ

ከምኒልክ ሳልሳዊ
በወያኔ መኮንኖች እና በኢትዮጵያ የመከላከያ ስራዊት መኮንኖች መካከል በፖለቲካ እና በጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች ዙሪያ ውስጥ ውስጡን እየተካረረ የመጣው አተካራ ከባድ ውጥረት መፍጠሩን በእዙ የሚገኙ መኮንኖች የተገኘው መረጃ ጠቁሟል። ሕገመንግስታዊ ጥያቀዎችንእና ወታደራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚተይቁ መክንኖች ከየክምፑ ተለቅመው ወደ ሰሜን እዝ እና ወደ ሶማሊያ ከሄደው ጦር ጋር እንዲቀላቀሉ ከተደረገ በኋላ ውጥረቱ እየሰፋ መምጣቱ ታውቋል።
meles and his milltery
ከዚህ ቀደም የተነሱ ሕገመንግስታዊ ጥያቄዎችን የሕወሓት ከፍተኛ መኮንኖች የጥያቄው ባለመብቶችን ወደ ሌላ አከባቢ በመቀየር የቀሩትንም በጥቅም ለመያዝ ቢሞክሩም ያላዋጣቸው ሲሆን ክመሃል ሃገር ሰልጥነው የተመደቡትም ወታደራዊ ደህንነቶች የአንድ ብሄር አባላት ስለሆኑ የመከላከያ ሰራዊቱ የበታች መኮንኖች በጥርጣሬ ስለሚመለከቷቸው የተላኩበትን ግዳጅ በብቃት መፈጸም ባለመቻላቸው ምንም አይነት ውጤት አለማምታታቸው ችግሩ ዳግም እንዲያገርሽ ሆኗል።
በወታደራዊ ደህንነቶች አማካኝነት እንቆጣጠረዋለን ብለው የምስራቅ እዝ ከፍተኛ የሕወሓት መኮንኖች ያሰቡት ጉዳይ ዳግም ውጥረት መፍጠሩ በድንበሩ አከባቢ ስጋት ስለፈጠረ ወደ አከባቢው አዲስ የመከላከያ ሰራዊት አንድ ሻለቃ ጦር እንዲመደብላቸው ጠይቀዋል።
የምስራቅ እዝ ምኮንኖች አብዛኛው ስራቸው የኮንትሮባድ ተግባራትን መፈጸም መዝረፍ እና ሴቶችን መድፈር መሆኑ ይታወቃል። የሕወሓት መኮንኖች ሌላውን አስፈላጊውን ሕግ የሚፈቅደውን ጥቅማ ጥቅም በመከልከል ከፍተኛ በድል እያደረሱ ሲሆን በሶማሊያ ክልል ውስጥ በዘረጉት ከፍተኛ የቢዝነስ ስራ ውስጥ ማንም ሌላ ሰው እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችል ሲሆን እነሱ በሚሰሩ ቢዝነስ ውስጥ የሚገባ ንብረቱ እንደሚወረስ ታውቋል፡፤ የሞባይል ቀፎዎችን እና የኢሌክትሮኒስ ዕቃዎችን በሕገወጥ መንገድ ጭነው ካለፍተሻ ወደ መሃል ህገር በማምጣት በይርጋ ሃይሌ ሕንጻ ካሉ ወኪሎቻቸው ጋር በመተባበር በመላው ሃገሪቱ እንደሚያከፋፍሉ ታውቋል።

እሥረኛው ጠቅላይ ሚንስትር ደሳለኝ ኃይለማርያም በምግብ ራሳችን ችለናል ማለቱ ከምኑ ላይ ነው ስህተቱ?!

June 26, 2014
በጌታቸው ፏፏቴ
መግቢያ፦ ህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ እንደሌለውና ሊኖረውም እንደማይችል ከተቋሙ መሠረታዊ ፕሮግራም በመነሳት ግንቦት 20/1983 በሚል ባቀርብኳት ጦማሬ አስረግጨ አሳውቄ ነበር። እነዚህን የምልበት ምክንያት ከባዶው ተነስቼ ሳይሆን ድርጅቱ ከፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ካለው ፀረ-ሕዝብና አሰቃቂ ዘግናኝ ተግባሮቹ በመነሳት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እወዳለሁ።የዚህ ድርጅት መነሻውም ሆነ የመጨረሻ ግቡ ከተቻለ የህወሃት/ኢህአዴግ ትውልዶች ብቻ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር አለዚያም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ ተራ በተራ እያዘናጉ መጨረስና አገሪቱንም ለባእዳን እንዳወጣች ሸጦ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልነበረች ማድረግ እንደሆነ ለማንም ስውር ሊሆንበት አይገባም።

ድርጅቱ ቀደም ሲል ጫካ ውስጥ በትግል በነበረበት ወቅትም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የፈፀማቸውና እየፈፀማቸው ያሉት አፀያፊ ድርጊቶች ታይተው ያማያውቁ የኢትዮጵያዊነት ሞራልና ስብእና የጎደላቸው ስለመሆናቸው ብዙ የተባለ ሲሆን አንድ ግልጽና ቀላል አስረጅ መጥቀስ የበለጠ እውነታውን ያሳያል ብየ አስባለሁ።

የፌደራል መንግሥት እየተባለ የሚጠራ የይስሙላ መንግሥት ቢኖርም የመንግሥትንም ሆነ የድርጅትን ሥራ ጠቅልሎ የሚያከናውነው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው። በግንባሩ ውስጥ የተካተቱት ድርጅቶች የመወሰንና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ባይኖራቸውም በህወሃት በጎ ፈቃድ የሌሎችን ነፃ ተፎካካሪዎች እድል ለመዝጋት የግል ባንኮችን ኮታው እንዲሸፍኑ ተደርጎ በሥራቸው የሚያንቀሳቅሱት ባንክ አላቸው።እነዚህ ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሥራ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ሆን ብሎ የታቀደ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ሊሰሩ ያሰቡትን ተግባር እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ተንኮለኛ ሴራ ነው።ከነዚህ ከተጠቀሱት የህወሃት አዳማቂ ድርጅቶች ባንክ ብድር ተበድሮ ኢንቨስት ለማድረግ ቢታሰብ ደግሞ አይሞክሩትም እንጅ የግድ መሟላት ያለበት አንድ ነገር አለ። ይኸውም የህወሃት/ ኢህአዴግን የአባልነት ካርድ መያዝ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንቅስቃሴን ለመግታትና የውጭ ምንዛሬ እንዳያገኝ ከማድረጉ አልፎ ባንኩ ራቁቱን እንዲቀር ያደረጉ ሌሎች የተቀነባበሩ ተንኮለኛ ተግባሮችም ተፈጽመዋል እነሱም ከባለ ሥልጣናቱ ቀጭን ትእዛዝ እየተሰጠ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች በኢንቨስትመንት ስም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እንዲበደሩ ይደረጋል። ገንዘቡን ወስደው ከተጠቀሙ በኋላ ለባንኩ መክፈል የሚገባቸውን የተጠቀሙበትን የአገልግሎት ዋጋ(interst) መክፈል ይገባቸዋል ነገር ግን ይህ ሊሆን ይቅርና ዋናውን ብድርም አሻፈረን አንከፍልም ብለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርገዋል።ይህችን ትንሽ ምሳሌ ያቀረብኩት የሌሎቻችሁንም ስሜት ለመቀስቀስ እንጅ ወንጀሉማ ስፍር ቁጥር የለውም እያልኩ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልግባ።

አዎ! አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም በግንቦት 20 ንግግሩ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏን ተናግሯል።ንግግሩን ሰምቸዋለሁ።ነገር ግን ስለማን እንደተናገረ ለማወቅ ለኔ ጊዜ አልወሰደብኝም።የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ወይም የልማታዊ መንግሥቱ መርህ ህወሃት/ኢህአዴግን፤ የግንባሩ አባላትንና ደጋፊዎችን ብቻ የሚመለከት እንጅ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም።ወደፊትም እንዲኖር የሚታሰበው ትውልድም በዚህ ዘረኛ ድርጅት ፕሮግራም ተኮትኩቶ የሚወጣን ትውልድ እንጅ ሌላ ኢትዮጵያዊ ትውልድ እንዲሆን በፍጹም አይታሰብም ይህን ነው ማወቅ ያለብን።

ቀደም ሲል በአንድ ጹሑፌ ላይ ደርግ ከወደቀ በኋላ በሠራዊት ግንባታና አደረጃጀት ጉዳይ ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ ድርጊት ጠቅሸ ነበር። ይኸውም ህወሃት አሰልፎት የነበረው ሠራዊት ከፍተኛ ቁጥር የነበረው መሆኑና የአዲሱ የሠራዊት አደረጃጀት ደግሞ ክልሎች ባላቸው የሕዝብ ብዛት ነው ስለሚል የህወሃትን ሠራዊት ላለመበተን ሲባል የተወሰደው እርምጃ አማርኛ የሚችለው የህወሃት ሠራዊት የመከረኛውን አማራ ሕዝብ ኮታ እንዲሸፍን ማድረግ ነበር ። የቀረውን በትግራይ ሕዝብ ባዛት መጠን ማሰለፍና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሱትን ደግሞ መዳረሻቸውን በማጥፋት ህወሃት ዓላማውን ስኬታማ ለማድረግ ችሏል።አሁን ደግሞ የህወሃት አባላት የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማሩና የኦሮሞውን ክልል በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተወሰደውን አቋምና በየዐረብ አገሩ በዐረብኛ ቋንቋ የሰለጠኑ ወጣቶች ለማፍራትና በየኮሚኒቲውና ኤምባሲው ለመሰግሰግና የስለላ ተግባራትን ለማካሄድ ሲባል የሀገሪቱ ሀብት(ገንዘብ)ለዚህ ወጭ መሸፈኛ እየተመዘበረ ያለበት መሠረታዊ ምክንያት (አንድምታው )ህወሃት ወለድ የሆነ አዲስ ትውልድን የመገንባትና
የመትከል አባዜ ነው።

ህወሃት ጫካ ውስጥ በነበረበት ወቅት ወደ ፊት ድርጅቱ ወደየት እንደሚሄድ የሚያሳይ ማኒፌስቶ በ1976 ዓ/ም ማውጣቱ ይታወቃል።ከ1983ዓ/ም ከደርግ መውደቅ በኋላ ግን ህወሃትን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት በመቁጠር ሕዝቡ የተዘናጋበት ጉዳይ ቢኖር የህወሃትን የመጨረሻ ግብ መርሳቱ ነው።ህወሃት ለ23 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታ ኢትዮጵያዊ በመሆን ሳይሆን እንደ ጣሊያንና ድርቡሽ(የመሐዲስት) ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ መጥፋት ያለበትን ለማጥፋት ሊዘረፍ የሚችለውን የሀገሪቱ ሀብት ለመዝረፍና ኢትዮጵያን በታትኖ በማጥፋት ለትውልደ ህወሃት የሚሆነውን አዲሱን የህወሃት ሥርዎ መንግሥት ለማመቻቸት ነው።

ከአፋር ጀምሮ የኤርትራን አጎራባች ድንበሮች እያጠቃለለ ከሰሜን ወሎ የማይጨው አውራጃን እንዳለ በመውሰድ ሰሜን ጎንደር ጠልምት ወልቃይት ጠገዴን፤አርማጭሆን እያጠቃለለ መተማን ሙሉ በሙሉ ካርታው ውስጥ ያስገባና ሽንፋና ቋራን ዘልቆ እስከ ጋምቤላና ቤንሻንጉል እየመረሸ ወለጋንም ሸረፍ በማድረግ በመውሰድ ”ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ” መገንባት ነው።ይህ ተግባር ባሳለፍናቸው የህወሃት 23ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል። አሁንም ዋናው ግብ እሱ በመሆኑ ሰላዮችን ካድሬውንና የህወሃትን የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በውጭ ያደራጁትን የህወሃት አባል “ከሱዳን ተመላሽ ወገን”በማለት እያሰፈሩ ይገኛሉ። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ይህን መሬት ለሱዳን ሰጥተውት የለም ወይ?የሚል ሊሆን ይችላል።አስቀድሞ ማለቅ ያለበት ተግባር ስለ አለ እንጅ በህወሃት ሰፍሳፋ ተፈጥሮ ይህን የመሰለ ለምና ውሃ ገብ መሬት ለሱዳን? እንዴት ብሎ? ወደ ፊት በሰፊው እናየዋለን።

አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደማይወክልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ አለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም ቢያንስ ሲወራ ሊሰማ ይችላል ብየ እገምታለሁ እዛው ከመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በየሆቴሉ የቆሻሻ መጣያ የተጣለ ትራፊ ምግብ ለማግኘት የሚደክሙትን፤በየትምህርት ቤቱ በርሃብ ጠኔ የሚወድቁትንና መማር አልችል ያሉ ወጣቶች በሞሉባት አዲስ አበባ ፤ከሀገሪቱ ሕዝብ 1/3ኛው ቁጥሩ ከ30ሚሊዮን የማያንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርሃብ አደጋ ላይ ያለ መሆኑን ዓለም አውቆትና የውጭ እርዳታ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት «በምግብ ራሳችን ችለናል» ብሎ መናገር ምንያል ቅጥፈት የተሞላበት ንግግር እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው?

አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ ህወሃት/ ኢህአዴግና የፌደራል መንግሥትን ምንነት ገና የገባው አለመሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮችን ሲናገር ተስተውሏል።ከኤርትራ ጋር ስለሰላም ለመመካከር ዝግጁ መሆኑንና በሌላ ወገን ደግሞ ኤርትራን የአሸባሪዎች ደጋፊ ናት የሚል ክስ መስል ነገር ሲናግርም ተደምጧል ሁለቱ የሚቃረኑ ሃሳቦች መሆናቸውን መመርመር አልቻለም።መራሾቹ ነብሰ ገዳዮች ስብሃት ነጋ ፤ ስዩም መስፍን ፤ አባይ ፀሐየ ፤ አዲሱ ለገሰ ፤ ብረከት ስምኦን ፤ አርከበ እቁባይ ፤ሕላዊ ዮሴፍ፤ታደሰ ካሣ፤ ደብረጽዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም አንብብ ብለው የሚሰጡትን ጹሑፍ ከማንበቡ በፊት ቢያነበው ቢያንስ ለያዘው ሥልጣን የሚመጥን ሀሳብ ባገኘ ነበር ።ነገር ግን ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ አባላትና የጡረታ አማካሪዎቹ እሱን እያጋፈጡ የውስጥ ፍላጎታቸውንና የተነሱበትን ዓላማ እያስፈጸሙ ይገኛሉ። አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የህወሃት ጠቅላይ ሚንስትር ሁሌ ስለአንተ የሚጻፉ ጹሑፎችን አንብባቸው አንድ ቀን ልብ ትገዛ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ስህተቱ ከምኑ ላይ ነው በሚል ርእስ የገባሁት ስህተት አልተናገረም ለማለት ሳይሆን ጹሑፌ ትኩረት እንድትስብ በማሰብ ነው እንጅ ስህተቱንማ ከቁመቱ በላይ በሚደርስ አዘቅት ተዘፍቆበታል። አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ወደታች ወርዶ በቀበሌ የሚኖረውን የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ነዋሪ ኢትዮጵያዊ የሚያይበት እድል ቢኖረው ምን ሊለን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ዳሩ ግን እሱ ራሱ በግዞት ላይ ያለ እስረኛ ስለሆነ ያሳዝነኛል።

የህወሃት እንባ ጠባቂዎች በትክክል በልተው ያድራሉ ። ምክንያቱም ሕሊናቸውን ለሆዳቸው ሲሉ ሸጠውታልና።አባላቱ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ስለሆነ ምን አጥተው? እንኳን ሦስት ጊዜ አስር ጊዜስ ቢበሉስ ምን ጎድሎባቸው? እላይ ያለው ቱባ-ቱባ ባለሥልጣን በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ከሚፈለገው በላይ የጠገቡና የጥጋብ ቁምጣናቸውን በአረቄ ለማወራረድ ሲደፈርሱ የሚያድሩ፤ ሰማይ ውረድ የሚሉ ጥጋበኞች፤ ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ፎቆች ያላቸው፤ሀብት ተብሎ የሚቆጠረው ሁሉ የነሱ ያደረጉ፤ መሬትን የነሱ ያደረጉ፤ የበርካታ ሆቴሎች ባለቤት፤ልጆቻቸው ከፍተኛ ወጭ እየተከፈለላቸው ውጭ አገር ተልከው የሚማሩ፤ የፓርቲ ልብስ የሚገዙት ውጭ አገር ነው፤ ጉንፋን በያዛቸው ቁጥር የሚታከሙትም ውጭ አገር በሚገኙ ሆስፒታሎች ነው።ይህ ሁሉ የሚደረገው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት እየተዘረፈ ነው።

የአቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የግንቦት 20 ቆርፋዳ ንግግር ቢያንስ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ያለበትን ደረጃና ሁኔታ አለማወቅ ራሱን ችሎ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ድናቁርቶች እየተመራች መሆኗን ከማሳየቱም በላይ አምራችና መሬት እንዳይገናኙ የተደረገበትን መሠረታዊ ምክንያት አለማወቁ የግለሰቡን ጥሬነት ያሳያል።ለባዕዳን የተሸጠው መሬት እንዳለ ሆኖ የቀረው መሬት ላይ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተሮችና አርሶ አደሩ ለማምረት እድሉ ቢፈጠርላቸው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ሌሎችን የጎረቤት አገሮች ሊመግብ የሚችል ምርት ማምረት ትችል ነበር።

አብዛኛው ከደቡብ እስከ ምዕራብ ያለውን የሀገሪቱን ክፍል ወስደን ብንመለከት ለም ድንግልና የተለያዩ አዝእርቶችን ሊያመርት የሚችል መሬት እንዳለ ይታወቃል።ከደርግ መውደቅ በኋላ ከ1985 እስከ 1987ዓ/ም በነበረው ወቅት የነበረውን የሕዝቡ ተነሳሽነትና በምእራብ ጐንደርና ምእራብ ጐጃም ብቻ የነበረው የምርት ውጤት ሲታይ ተስፋ ሰጭ ነበር። ሁመራና መተማ ተከማችቶ የነበረውን ማሽላ፤ ሰሊጥና ጥጥ ለማጓጓዝ የነበርውን የተሽከርካሪና የመደብር እጥረት አስታውሳለሁ።ያን ተነሳሽነት ግን ገዥዎቻችን ቀልጥፈው አጠፉት። የመሬት መጠቀሚያና የእርሻ ግብር ክፍያውን እላይ ሰቀሉት ኢንቨስተሩም የሥራ ፈቃዱን መመለስ ጀመረ። ህወሃትን እሰየው አሰኘ ታይቶ የነበረው ተስፋ ጨለመ።

አድንቁረህና አስርበህ ግዛው መሆኑንንም አሳዩን።ያን ተስፋ የተጣለበትን የደቡብ ምእራብና ሰሜን ምእራብ መሬትም ለሱዳን አስረክበው ዛሬ የሱዳን ገበሬዎች በህወሃት የመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ አባቶቻችን ደም አፍስሠው አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩትን መሬት እያረሱት ይገኛል።አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ለማወቅ የተሳነው እንዲህ አይነቱን ሀቅ ነው።በዚህ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመነ መንግሥት በነበረው ፓርላማ ውስጥ እንስጥ አንስጥ በሚል ሃሳብ ተነስቶ አብዛኛው የፓርላማ አባል ለዚህ ቆላማ መሬት ብለን ወዳጅነትን ከሱዳን ከምናጣ ይውሰዱት ሲል ጥቂት የፓርላማ አባላት በድርጊቱ ተቆጥተው ፓርላማው ውስጥ በወንበር መደባደብ እንደተጀመረና ወዲያውኑ ለሱዳን ይሰጥ የሚለው ውሳኔ ተሽሮ ድንበሩ እስከ አሁን የኛው ዘመን ድረስ በጦር ኃይል ሳይሆን በህዝብ የጎበዝ አለቆችና በራሱ ትጥቅ ተከብሮ የኖረ መሬታችን ነው ዛሬ ለሱዳን የተሰጠው።

አሁን ያለው ፓርላማ ፓርላማ ነው ለማለት እንደማይቻል ይታወቃል።የካድሬ ስብስብና እጅህን አውጣ ሲባል ብቻ እጁን እያወጣ ድምጽ የሚያስቆጥር እንጅ በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ወኔ ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ ያመነጫል ተብሎም ተስፋ የሚጣልበት ፓርላማ አይደለም። ለግልጥቅሙና ለሆዱ የተሰለፈውን ህወሃት ከየትም ለቃቅሞ የሰበሰበው ጥርቅም ነው። አንድ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ግን»- እንደ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት መርዙን የተከለ አልነበረም እሱ ወደ መጨረሻው ከተጓዘ በኋላም ዛሬ እየገዙን ያሉት እኩያን “ በመለስ ራእይ” ስለሆነ እነዚህን ስንኩሎች ነቅለን ካልጣልን እፎይ የምንልበት፤በኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚተከልበት፤የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፤ኢትዮጵያውያን ተፋቅረውና ተከባብረው በጋራ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም።

መፍትሔ አልባ የሚፈጠር ችግር የለም። እኛን ለገጠመን ድቅድቅ የጨለማ ዘመን ደግሞ መፍትሔ አለው ብየ አስባለሁ።”የፀደይ አብዮት”በመባል የሚታወቀው የሕዝብ አመጽ የቱኒዚያን፤የግብጽን፤የየመንን፤የሊቢያን፤የሶርያን አሁን ደግሞ የኢራንን መሬቶች እንዳንቀጠቀጠና እያንቀጠቀጠ እንደሚገኝ ይታወቃል።አዎ! ብዙ መስእዋትነት ተከፍሎበታል ቢከፈልበትም ትርጉም ያለው ውጤት ደግሞ አስገኝቷል።በእኛም አገር ትግሉ አፈና የበዛበት ቢሆንም አላቋረጠም።ዳሩ ግን የተከፈለው መስእዋትነትና የተገኘው ውጤት ሲመዘን ብዙ ጎደሎዎችን አሳይቷል።አንደኛ ትግሉ ከየግል ፍላጎት የሚነሳና የተናጠል መሆኑ ፤ሁለተኛ ሁሉንም የሕ/ሰብ ክፍል በአንድ ጊዜ ያነቃነቀ አለመሆኑ፤ሦስተኛ በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም አንድ ቀን ብቻ የሚደረግ ትእይንተ ሕዝብ እንጅ ቀጣይነት የሌለው መሆኑ፤አራተኛ በሕዝብ የሚደረጉት ትእይንተ ሕዝቦች ታክቲክ ለገዥው ቡድን የተጋለጡ መሆናቸው ነው።

የማይሳሳት ቢኖር የማይሰራ ወይም የማይንቀሳቀስ ብቻ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን ህወሃትን ለማስወገድ በተመቸው መንገድ ሁሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል።ስንጓዝ ደግሞ ስህተቶች ተፈጽመዋል ስለሰራን ተሳስተናል ትልቁ ጉዳይ ግን ከስህተት መማርና ከዚያ አደጋ የመውጣቱ ቅልጥፍና ጉዳይ ነው ወሳኙ።አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ከችግር ጋር ያጋፈጠንን ህወሃትን ጡንቻው እንዲያብጥና ጠንካራ ጠላታችን እንዲሆን አብቅተነዋል። ምክንያቱም የጠላትን ጠንካራና ደካማ ጎን መገምገም አልቻልንም። የህወሃት ጠንካራ ጎን እርስ በርሳችን እንድንባላ ማድረጉ ሲሆን ይህን አሜን ብለን ተቀብለነዋል።እስከ መቼ? ደካማ ጎኑ ህወሃት የማይወደው “ሕብረት ወይም አንድነት ስንፈጠር ነው”ካልተሳሳትኩ ቁልፉ እዚህ ላይ ነው ያለው።ወደዚህ እንዳንመጣ ያደረገው ደግሞ ከሥልጣን ጥማት ጋር የተያያዘና እኔ ከሁሉም የላቅሁ ነኝ የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። በዚህ ላይ የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚፈልገውን የመሾም የማይፈልገውን የመሻር ሥልጣኑን የማይቀበል አመለካከት ተሸክመን በመጓዛችን ምክንያት ነው።

ስለዚህ በኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተቻችሎ አንድነትን መገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች በመተሳሰብ በፍቅር በጋራና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ራእይ ይዞ መታገል አግባብ ነው ብየ አስባለሁ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላዓለም ትኑር!!!

እያንዳንዳችን ራሳችን ነፃ ለማውጣት እንታገል!!

በቀጣዩ እስከምንገናኝ ለዛሬ ያለኝን እዚህ ላይ ጨረስኩ።