Hello, world!
በአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር ቢሮና በሌሎች ተቋማት ላይ ፓርላማ ዕርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ
ዋና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለሕዝብ አቤቱታ መፍትሔ የማይሰጡ ያላቸውን ተቋማት ፓርላማው ዕርምጃ እንዲወስድባቸው አሳሰበ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ እንዲሁም ሌሎች የከተማው ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
ዋና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂዋ ወ/ሮ ፎዚያ አሜን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲያቀርቡ፣ ተቋሙ በምርምራ ውጤት ላይ ተመሥርቶ የተሠሩ ጥፋቶች እንዲታረሙና በደል የደረሰባቸው መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሥራ ኃላፊዎች ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር፣ አብዛኞቹ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሚቀርቡባቸውን አቤቱታዎች እንዲያርሙና የተበደሉ ደግሞ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን በበጐ ጐኑ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በምርምራ ላይ ተመሥርቶ የሚያቀርብላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ ካለማድረጋቸውም በላይ፣ የማይተገብሩበትን ምክንያት እንኳን አይገልጹም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የሕግና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በልዩ ሁኔታ እንዲከታተላቸው ዝርዝር ሪፖርት እንደተላከለትና ኮሚቴውም በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዝርዝር ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ከተላለፉ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይገኙበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ የተጠቀሱት ተቋማት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእንስሳት ሰብልና ገጠር ልማት ቢሮ፣ የሐረር ክልል ፍትሕና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ናቸው፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአሥር ወራት ጊዜ ውስጥ 2,948 የአቤቱታ መዝገቦች የቀረቡለት መሆኑን የገለጹት ዋና እንባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ፣ መዝገቦቹ በአጠቃላይ 17,682 አቤቱታ አቅራቢዎችን ይመለከታሉ ብለዋል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar