(ዘ-ሐበሻ) “ወደ ፍቅር ጉዞ” በሚል መርህ ቴዲ አፍሮ በሰሜና አሜሪካ የሚያደርገው የሙዚቃ ኮንሰርት ትናንት በሲያትል ዋሽንግተን ተጀመረ። በሺህዎች የሚቆጠሩ የቴዲ አፍሮ አፍቃሪዎች ይህን ኮንሰርት የታደሙት ሲሆን ቴዲም ሲያስደስታቸው እንዳመሸ ከሲያትል ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከሥራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ በዋሽንግተን ዲሲና በዳላስ ቴክሳስ ይደረግ የነበረው ኮንሰርት መሠረዙ የሚታወስ ሲሆን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ድምጻዊው የሥራ ፈቃዱን በማግኘቱ ትናንት በሲያትል የደመቀ ምሽት አሳልፏል።
ቴዲ ወደ ፍቅር ጉዞ በሚል የጀመረው የሙዚቃ ኮንሰርት ጁላይ 3 በሳንሆዜ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ የሚቀርብ ሲሆን ጁላይ 4 ለአሜሪካ የነፃነት ቀን ከአፍሪካ ድምጻውያን መካከል ተመርጦ ይዘፍናል።
ከዚያ ቀጥሎ ጁላይ 12 በሚኒሶታ የሚያደርገው ዝግጅት በጉጉት እየተጠበቀ እንደሚገኝ ዘ-ሐበሻ ከደረሷት መረጃዎች ለማረጋገጥ ችላለች።
ቴዲ አፍሮ የፍቅር ጉዞውን ወደሚኒሶታ ጁላይ 12 ካደረገ በኋላ በሰሜን አሜሪካና በካናዳ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያቀርብ ሲሆን ከዚያም ወደ አውሮፓ እንደሚያቀና ይጠበቃል። ዘ-ሐበሻ እንደደረሳት መረጃ ከሆነ በላስቬጋስ ለኢትዮጵያ አዲስ አመት ሥራውን እንደሚያቀርብም ነው።
የኢትዮጵያው ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሰሰ እግርን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ የነገሠው ቴዲ አፍሮ በቅርቡ አንድ ነጠላ ዜማ እንደሚለቅና ሙሉ የአልበም ዝግጅቱን እንደጨረሰም የዘ-ሐበሻ ምንጮች ጠቁመዋል።
Ze-Habesha Website
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar