በ1997ቱ ሚያዝያ መጨረሻና ግንቦት መጀመሪያ ላይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታና ተስፋ ተሞልቶ ነበር። የሚያዝያ 30 ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ እና የግንቦት 7 ጨዋነት የተላበለው ምርጫ የፈጠሩት ተስፋ ቃላት ሊገልጹት በሚችሉት በላይ ነበር። ሆኖም በህወሓት የተመራው የሰኔው ጭፍጨፋ ያንን ሠናይ ስሜት አደፈረሰው፤ አጨለመው።
በዘረኝነት፣ በአፍቅሮተ ንዋይና አፍቅሮተ ሥልጣን የታወረው ወያኔ ከራሱ አባላት ሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው መኖሩ አይታየውም። በህወሓት ጎጠኞች እሳቤ መሠረት ወጣት ሽብሬ፣ ህፃን ነቢዩ፣ ወ/ሮ እቴነሽ፣ ሌሎች እናቶችና አባቶች ሰዎች አይደሉም። ስለሆነም ያለአንዳች ምክንያት ተገደሉ። እስከዛሬ ድረስም ከገዳዮች መካከል አንዱ እንኳን ተጠያቂ አልሆነም። በግልባጩ ገዳዮች በመግደላቸው ተሾሙ፤ ተሸለሙ። ይህ ሁሉ ያሳምማል።
የሰኔ 1997 ሰማዕታትን የምናስባቸው በጥልቅ ሃዘን ብቻ ሳይሆን በቁጭትና እልህ ጭምርም ነው። ወገኖቻችን እንደሰው ባለመቆጠራቸው ተገደሉ። አሁንም እንደሰው የማይቆጠሩ በመሆኑ ሙት ዓመታቸውን መዘከር ወንጀል ነው። መቸ ነው ይህ ውርደት የሚያበቃው?
ሰማዕታት ወገኖቻችን የሕይወት ዋጋ ከፍለው ዘረኝነትን የማስወገድ ሸክም እኛ ላይ ጥለዋል። እኛስ ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም ብቁዎች ነንን? እያንዳንዳችን የገዛ ራሳችንን እንጠይቅ።
ዘላለማዊ ክብር ለሰማዕቶቻችን !!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar