fredag 27. juni 2014

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ



አቶ አቻምየለህ ገሠሠ
አቶ አቻምየለህ ገሠሠ
አቶ አቻምየለህ ገሠሠ በ1946 ዓ.ም በቀድሞው ቤጌምድር ሰሜን ጠቅላይ ግዛት በጋይንት አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ አንሰታ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ ቅድመ አብዮትም ሆነ ድህረ አብዮት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ የሰሩ ሲሆን የፖለቲካ ተሳትፎአቸው በተመለከተ አቶ አቻምየለህ ለለውጥ ባላቸው ፍላጎት የተነሣ በ1992 ኢዴፓን ከመሰረቱት አንዱ በመሆን የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ምክትል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም ቅንጅት ሲመሰረት ከመስራቾች አንዱ በመሆን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሰጥተዋል፤ በ2000 ዓ.ም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሲመሰረትም ከመሥራቾቹ አንዱ በመሆን ኦዲትና ኢንስፔክሽን አባል በመሆን አገልግለዋል፤ በ2006 ዓ.ም ታህሣሥ ወር በተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የብሔራዊ ም/ቤት አባል ሆነው ከመመረጣቸውም በላይ የዲሲፕሊንና ሥነሥርዓት ኮሚቴ አባል ሆነው በመመረጥ ታከተኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማገልገል ላይ የነበሩ፣ ድንገት ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ አርፈዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነሥርዓት የሚፈጸመው ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ የሚፈጸም መሆኑን ከቤተሰቦቻቸው ለፍኖተ ነፃነት ያደረሱን ዜና ያመለክታል፡፡ አቶ አቻምየለህ ገሠሠ ረታ የሁለት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar