onsdag 11. juni 2014

የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን ማን ይፈራቸዋል? (ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም)

June 11, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የእስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችን…የዴሞክራሲያዊ መብት የመጠቀም የትግል እንቅስቃሴ ሲመለከት እንደሚዳቋ እየበረገገ የሚስፈነጠረው ማን ነው?Ethiopian government scared of bloggers and journalists
የኢትዮጵያ የነጻው ፕሬስ እና ጦማርያን ቁንጮ የሆነው እስክንድር ነጋ ሀሳቡን በነጻ በመግለጹ ብቻ በአምባገነኑ የወሮበላ ቡድን ስብስብ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት በገዥው አካል የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ሟቹ መለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ስር እንዲውል እና የ18 ዓመቱ የሸፍጥ እስራት እንዲበየንበት ተደርጓል፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ማናቸውም ጋዜጠኞች የበለጠ እስክንድር ነጋን ይፈራዉና ይጠላው ነበር፡፡ ዝሆን አይጦችን “ይፈራል” ከሚለው ኢ-ስነ አመክንዮ አንጻር በተመሳሳለ መልኩ መለስም እስክንድር ነጋን እንደጦር ይፈራው ነበር፡፡
በቅርቡ እስክንድር ከማጎሪያው እስር ቤት ለ8 ዓመት ልጁ ለናፍቆት እንዲህ የሚል ግልጽ ደብዳቤ ጽፏል፣ “እንዲያው ሁኔታውን ሳየው እያለሁ የሌለሁ የዘፈቀደ አባት ሆኛለሁ፣ ምክንያቱም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈረንሳዮች ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍቅር እያሉ ደጋግመው ይጠሯቸው የነበሩትን ሶስት ቀላል ቃላትን በመውሰድ እኔም በሀገሬ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍቅር እንዲሰፍን በማሰብ እነዚህን ቃላት በማስተጋባቴ ነው በሸፍጠኞች ለእስር የተዳረግሁት“ ብሏል፡፡ እስክንድር ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለአብሮነት ፍቅር ጦማሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለእኔ የጀግናዬ ተምሳሌት የሚሆነው!
የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል ጀግናዋ የ34 ዓመቷ ወጣት ርዕዮት ዓለሙ በተመሳሳይ መልኩ በአቶ መለስ ዜናዊ የ14 ዓመታት እስር በይኖባታል፡፡ ይህች ጀግና ወጣት በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ “እውነት ተናጋሪዋ ኢትዮጵያዊት እስረኛ” በመባል ትታወቃለች፡፡ ርዕዮት ለእስር የተዳረገችው የግድብ ፕሮጀክት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በተመለከተ በገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችት በማቅረቧ እና በቅርቡ በህይወት የተለዩት የሊቢያ አምባገነን መሪ ሙአማር ጋዳፊ እና መለስ ዜናዊ ከአንድ ባህር የሚቀዳ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው መሆናቸውን በይፋ በመግለጿ ነው፡፡ ርዕዮት በእስር ቤት ተዘግቶባት እና አፏን ተሸብባ ለመቀመጥ ባለመፍቀድ በድፍረት አንገቷን ቀና አድርጋ ስልጣኖቻቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በህገወጥነት ለሚጠቀሙት ህገወጦች እና ትዕቢተኞች እውነት እውነቱን እንዲህ በማለት እቅጬን ተናግራለች፣ ”የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት እኔ በግሌ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ማበርከት አለብኝ የሚል እምነት አለኝ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ኢፍትሀዊነቶች እና ጭቆናዎች ተንሰራፍተው ስለሚገኙ እነዚህን እኩይ ተግባራት በምጽፋቸው ትችቶቸ ማጋለጥ እና ከንቱ መሆናቸውን መቃወም አለብኝ… ለዚህ በጎ ዓላማ በድፍረት ትግል በማካሂድበት ወቅት ሊያስከፍለኝ የሚችለውን ዋጋ ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ“ በማለት ከእስር ቤት አፈትልከው በሚወጡ የእጅ ጽሁፎቿ ገልጻለች ጀግናዋ ርዕዮት ዓለሙ፡፡ በማይበገረው እና በማይንበረከከው ትክክለኛ የጽናት አቋሟ ምክንያት ገዥው አካል ሰብአዊነት የሚባለውን ክቡር ነገር በመደፍጠጥ የህክምና አገልግሎት እንዳታገኝ ቅጣት ጥሎባታል፡፡ መቀመጫውን ሎንዶን ያደረገ የህግ መከላከል የተነሳሽነት ሜዲያ/Media Legal Defense Initiative የተባለ ተቋም በአልጃዚራ ባቀረበው ዘገባ መሰረት ርዕዮት “በሰውነት አካሏ ላይ የተከሰተ እብጠት የተገኘ ቢሆንም ተገቢ የሆነ ህክምና እየተሰጣት እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የሰመመን መስጫ ማደንዘዣ ሳይሰጣት በጡቷ ላይ የቀዶ ህክምና ስራ በማከናወን የቀዶ ህክምና መስፊያ ክሩ ከጡቷ ሳይወጣ ከዓመት በላይ ከመቆየቱም በላይ ከደህረ ቀዶ ህክምናው በኋላም ቢሆን ተገቢ የሆነ ህክምና የተሰጣት አይደለም“ ብሏል፡፡ ለእኔ ርዕዮት የጀግና ተምሳሌታዬ ናት!
የማይበገረው ጋዜጠኛ እና አርታኢ ውብሸት ታዬ የመናገር አንደበቱን ተሸብቦ በመለስ ዜናዊ ዝዋይ በሚባል አስፈሪ እና ጭራቃዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በእርሱ ላይም የ14 ዓመታት እስራት ተበይኖበታል፡፡ ውብሸት የገዥውን አካል ሙስና እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን አስመልክቶ በጋዜጣ ላይ የሚያቀርባቸውን ትችቶች እና አስተያየቶች በፍጹም አያቋርጥም፡፡ ውብሸት ለሚጠዘጥዝ የኩላሊት ህመም ተጋልጦ የሚገኝ ቢሆንም እርሱም ህክምና እንዳያገኝ ተደርጎ በመሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ በማጎሪያው እስር ቤት ለሚገኙት የህሊና እስረኞች የህክምና አገልግሎት መንፈግ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል እለት በእለት የሚፈጽማቸው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የቅጣት ወንጀሎች ናቸው፡፡ ፍትህ እየተባለ የሚጠራው የውብሸት የአምስት ዓመት ልጅ እንዲህ በማለት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛል፣ “ሳድግ እና ለአቅመ አዳም ስደርስ እኔም እንደ አባቴ ሁሉ ወደ እስር ቤት እጋዛለሁን?“ ሕፃኑ ፍትህ በአሁኑ ጊዜ አጥር የሌለው እስር ቤት ውስጥ እየኖረ መሆኑን ሊገነዘብ አይችልም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት “የኢትዮጵያ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች” (የፖለቲካ እስረኞችን ከያዘው ከመሀል ከተማ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘው የ “መለስ ዜናዊ ታዋቂው የቃሊቲ እስር ቤት” ህንጻዎች ቀጥሎ የተሰየመ) እና ሌሎች ጋዜጠኞች በስም አጥናፍ ብርሀኔ፣ ዘላለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋቤላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋለም ወልደየስ እና ኤዶም ካሳዬ የክሱ ጭብጥ ባልታወቀበት ሁኔታ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ውለው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ፖሊስ በእነዚህ ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ላይ ምን ዓይነት ክስ መመስረት እንዳለበት ገና በመለግ ላይ ይገኛል፡፡
(የገዥው ፖሊስ የሚጠረጥረውን ዜጋ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር አውሎ እና እስር ቤት በማጎር እያሰቃዬ ተሰራ ለተባለው ጥፋት ማስረጃ እና መረጃ በመፈለግ በዜጎቿ ላይ ሰብአዊ መብትን በመደፍጠጥ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ብቸኛዋ አገር ናት!!! የይስሙላዎች የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር ለዋሉት ዜጎች ዋስትና በመንፈግ ፖሊስ እና አቃቤህግ የሚባሉ የገዥው አካል የማጥቂያ መሳሪያ ሎሌዎች የሚፈበረኩ የፈጠራ ውንጀላዎችን አቀነባብረው እስኪያቀርቡ ድረስ የተንዛዙ እና አሰልቺ የሆኑ ማያልቅ ቀጠሮዎችን በመስጠት እና የይስሙላውን ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ከሚገባው በላይ በማዘግየት በንጹሀን ዜጎች ላይ የቁማር ጨዋታ በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አነዚህን ፍርድ ቤቶችን “የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች እያልኩ የምጠራቸው፡፡” እውነተኛው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ወንጀል ሀሳብን በነጻ በመግለጽ የሚያምኑበትን ነገር በነጻ ማራመዳቸው እና እነርሱ የተሻለች ኢትዮጵያ በማለት ስለሚጠሯት ኢትዮጵያ ህልም ማለማቸው ነው፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ጉዳይ የሚመለከተው በቅርቡ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የዳኝነት ችሎት ለህዝቡ እና ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተሉት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ዝግ ነበር፡፡
እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን… የሚፈሯቸው ለምንድን ነው?
ናፖሊዮን ቦና ፓርት የተባሉት የፈረንሳይ አምባገነን መሪ በዚያች አገር የነጻው ፕሬስ ላይ ጦርነት ባወጁበት ወቅት “ከአንድ ባታሊዮን ጦር ይልቅ አራት ተቃዋሚ ጋዜጦች የበለጠ ይፈራሉ“ የሚለውን እውነታ የበለጠ ግልጽ አድርጎታል፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር በስልጣን ላይ ተጣብቆ ለሚገኘው ገዥ አካል ኤኬ – 47 ከታጠቀ አንድ ባታሊዮን ጦር ይልቅ ብዕር እና የኮምፒውተር ኪይ ቦርድ የያዙ ጥቂት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የበለጠ ያስፈሩታል፣ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ እንዲወሸቅ ያደርጉታል፣ ያርዱታል፣ ያስደነብሩታል፣ የሚይዝ የሚጨብጠውን ያሳጡታል፣ የቀን ቅዠት ይፈጥሩበታል፣ በላብ እንዲጠመቅም ያደርጉታል፡፡ በታሪክ መነጽር ሲታይ እና ሲገመገም ሁሉም አምባገነኖች እና ጨቋኞች የነጻውን ፕሬስ የእውቀት እና የክህሎት ኃይል አጥብቀው ይፈሩታል፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተንፈራጥጠው የሚገኙት አምባገነኖች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ከታቀው እና በልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች ተዋቅሮ በጠላት ላይ ቅጽበታዊ ድልን የመቀዳጀት አቅም ካለው እና የጠላትን ኃይል በማያንሰራራ መልኩ ከሚያደባይ የጦር ኃይል ይልቅ የነጻውን ፕሬስ የዕውቀት እና የክህሎት ኃይል አጥብቀው ይፈራሉ፡፡
ጠቅላላ የብዙሀን መገናኛዎችን እና ነጻውን ፕሬስ መቆጣጠር የገዥዎች እኩይ ምግባር ነው፡፡ የመረጃ ፍሰቶችን በመቆጣጠር በኃይል የሚገዙትን ህዝብ ልብ እና አእምሮ የተቆጣጠሩ እንደሚመስላቸው እምነት አላቸው፡፡ የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎችን በመቆጣጠር እንደ በቀቀን እየደጋገሙ ከሚቀፈቅፉት ነጭ ውሸታቸው እውነትን የሚፈበርኩ ይመስላቸዋል፡፡ ነጻውን ፕሬስ አፈር ድሜ በማብላት ሁሉንም ህዝብ ሁልጊዜ ማሞኘት የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን “እውነት ለዘላለም ተቀብራ እንደማትቀር እና ግፈኞችም በጉልበት ነጥቀው በያዙት የስልጣን ዙፋን ወንበር ላይ ለዘላለም ተጣብቀው እንደማይቆዩበት ድንጋይ በሆነው ልባቸው ያውቁታል፡፡“ ሁልጊዜም ስልጣናቸውን የሚያጡ እየመሰላቸው እለት በእለት የውሸት ድሪቷቸውን እየደረቱ ኑሮ አድርገው ይዘውታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተጣብቆ የሚገኘው አረመኔ አምባገነን ገዥ ከብዙ ዓመታት በፊት ናፖሊዮን ተጋፍጦት የነበረውን ዓይነት ሁኔታ ተጋፍጦ ይገኛል፡፡ “ጋዜጠኛ የህዝቡን እሮሮ የሚያሰማ፣ ስህተትን አራሚ፣ ምክርን የሚለግስ፣ የሉዓላዊነት ወኪል እና የአገሮች መምህር ነው፡፡“ ጋዜጠኛ “አገርን የሚያስተምር” ነው፣ መረጃን ለህዝብ የሚሰጥ ነው፣ ህዝቡን በእውቀት የማነጽ እና የማስተማር ኃላፊነት አለው፡፡ እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች ነበሩ ናፖሊዮን ነጻውን ፕሬስ እንዲፈሩት ያስገደዳቸው፡፡ የነጻው ፕሬስ ኃይል የናፖሊዮንን አምባገነናዊ አገዛዝ ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚያጋልጠው እና በህዝቡ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚያደርገው ናፖሊዮን ይገነዘቡ ነበር፡፡ ናፖሊዮን የፈረንሳይን ህዝብ ለማስፈራራት በማሰብ መጠነ ሰፊ የሆነውን የስለላ መረባቸውን በመዘርጋት ሲያካሂዱት የነበረውን ስለላ ሲያጋልጡ የነበሩትን ጋዜጠኞች ለማስፈራራት፣ በእስር ቤት ለማጎር፣ በስራዎቻቸው ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እና አንደበታቸውን ለመሸበብ ጊዜ አላባከኑም፡፡ ነጻው ፕሬስ የናፖሊዮን ወታደራዊ እቅድ መክሸፉን አጋልጧል፡፡ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማንንም ሳይለይ በጅምላ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተካሄዱትን ጭፍጨፋዎች እና የእርሳቸው የፖለቲካ ተቀናቃኝ በሆኑት ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይ የተካሄደውን እስራት፣ ማሰቃየት እና ግድያ አውግዟል፡፡ በኢትዮጵያ እንደ መዥገር በስልጣን ወንበር ላይ ተጣብቀው የሚገኙት አምባገነኖች በናፖሊዮን ቅዠት በመውደቅ በተመሳሳይ መልኩ ወጣት ጦማሪያንን እና የነጻው ፕሬስ አባላትን ያስራሉ፣ ያሰቃያሉ፡፡ እውነታውን በመፍራት እንቅልፋቸውን አጥተው በነጭ ላብ ተዘፍቀው ያድራሉ!
የኢትዮጵያ ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ልዩ የኢትዮጵያ ጀግናዎች እና ጀግኒቶች ናቸው፡፡ የእውነት ተናጋሪ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ አረመኔ አምባገነኖችን በብዕሮቻቸው እና በኮምፒውተር ኪቦርዶቻቸው ይዋጋሉ፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ጥይቶች እውነት፣ ቃላት፣ ሀሳቦች፣ እውነታዎች እና እምነቶች ብቻ ናቸው፡፡ የተንሰራፉትን ውሸቶች በእውነት ጎራዴ ይከትፏቸዋል፡፡ መጥፎ እና መሰሪ ሀሳቦችን በጥሩ ሀሳቦች ያሳድዷቸዋል፣ እናም ያረጁ እና ያፈጁ፣ እንዲሁም የጃጁ፣ እና የበከቱ አሮጌ አስተሳሰቦችን በአዲስ እና ተራማጅ በሆኑ አስተሳሰቦች ለመተካት የማስተማር ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የህዝቦችን ተስፋቢስነት በመዋጋት በተስፋ ቃላት ያለመልማሉ፡፡ ፍርሀት በጀግንነት እና በደፋርነት ድል እንደሚመታ ለህዝቡ ያስተምራሉ፡፡ ድንቁርናን እና ኃይለኛ ደንቆሮዎችን በእውቀት እና በምክንያታዊነት ይዋጋሉ፡፡ በእብሪት እና ትእቢት ለተወጠሩት የገዥው አካል አባላት በሰለጠነ መልኩ ለማስተማር እና ለማግባባት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ትዕግስትየለሽነትን በታጋሽነት፣ ጭቆናን ከመሸከም በጽናት ታግሎ በማስወገድ እና በጥርጣሬ ከመሸነፍ በሙሉ እምነት አሳድሮ ድል በመምታት ለመቀየር ይፈልጋሉ፡፡ የህዝቡን ልብ እና አእምሮ ለመያዝ በሚደረገው የትግል አውድ እንደ ወሮበላው የገዥ አካል ስብስብ በተራ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እና በኃይል በጉልበት ጨፍልቆ ለመያዝ ሳይሆን እውነታውን እና እውነቱን ብቻ ለወገኖቻቸው በማሳየት በብዕሮቻቸው እና በኮምፒውተር ኪቦርዶቻቸው ይታገላሉ፡፡
ክህደት፣ ውሸት እና ፍርሀት በተንሰራፋባት ምድር ላይ መኖር፣
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል እውነት ውሸት በሆነባት፣ እውነት በእየለቱ በምትደመሰስባት እና ሸፍጠኛ አታላዮች በፍርሀት ተዘፍቀው የሚኖሩባት የእራሳቸውን ምድር ፈጥረዋል፡፡ ገዥው አካል እንዲህ የሚለውን የካርቴሲያንን መርህ አዛብቷል፣ “በኛ አስተሳሰብ ብቻ ነገሮች ሁሉ ህልውና ይኖራቸዋል ወይም ደግሞ ህልውና አልባ ይሆናሉ“፡፡ መለስ ዜናዊ የክህደት አለቃ ነበር፡፡ ሁልጊዜ በሱ የማጎሪያ አስር ቤቶች ውስጥ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኛ የለም በማለት ሽምጥጥ በማድረግ ይክድ ነበር፣ እንዲህ በማለት፣ “በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኛ የለም፡፡ በእስር ቤት ያሉት አመጸኞች እና አሸባሪዎች ናቸው፡፡ እናም በእስር ቤቶቻችን የፖለቲከ እስረኞች አሉ ብሎ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ምክንያቱም የፖለቲካ እስረኞች አይደሉምና፡፡ በሱ የንጉስነት ወቅት ምንም ዓይነት ረሀብ እና ቸነፈር እንዳልነበረ ሙልጭ አድርገው በመካድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ በጣም ጥቂት የሆኑ በጣት የሚቆጠሩ በምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ የወረዳ ኪስ ቦታዎች እና በሶማሊ ክልል አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ብቻ ነው የነበሩት በማለት ዓይኔን ላፈር ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ያፈጠጠ እና ያገጠጠ እውነታ ሙልጭ አድርገው በመካድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም“ ብለዋል፡፡ ይህንን ለማስረገጥ በማሰብ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኦጋዴን አካባቢ መንደሮችን አቃጥለዋል እየተባለ ውንጀላ ቀርቦብናል፡፡ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፤ ኑስ አንድ መንደር እንኳ አልተቃጠለም፡፡ እናም እኔ እስከማውቀው ድረስ አንዲት ጎጆ አልተቃጠለችም፡፡ እኛ እየተከሰስን ያለነው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቀድሞ ከነበሩባቸው መንደሮች በማንቀሳቀስ ወደ መጠለያ ካምፖች በማስገባታችን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅንጣት መረጃ ሊቀርብ አይችልም“ ብሎ ነበር፡፡ የአሜሪካ የሳይንስ እድገት ማህበር/American Association for the Advancement of Science በኦጋዴን መንደሮች ላይ የተካሄደውን የጅምላ የመንደሮች ማቃጠል ወንጀል በሳቴላይት ምስሎች የተረጋገጠው እውነታ ለመለስ ምድር ምናባዊ ህይወት ምንም አይደለም፡፡ አደናጋሪ የፕሬስ ህግ አዋጅ በማውጣት በደርዘን የሚቆጠሩ ምርጥ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ለእስር እና ግዞት ሲዳረጉ የሌባ አይነ ደረቅ እንዲሉ በሀሰት በነተበው አንደበታቸው መልሰው “ከዓለም የተሻለ ምርጥ የፕሬስ ህግ” በማለት ያደናግራሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የተካሄደውን አገር አቀፋዊ “ምርጫ” ተከትሎ አቶ መለስ ፓርቲያቸው ምርጫውን በ99.6 በመቶ ያሸነፈ መሆኑን በኩራት ተናግረው ነበር፣ ምክንያቱም ህዝቡ ፓርቲያቸውን የሚወደው ስለሆነ ነው በማለት አፋቸውን ሞልተው ተናግረው ነበር፡፡ አቶ መለስ የኦርዌላን/Orwellian የእንስሳት ትረካ ዓይነት እውነታን የሚያራምዱ ሰው ነበሩ፡፡ ውሸታቸውን ለመንዛት ሲፈልጉ “የፖለቲካ ቋንቋን በመጠቀም የለየለትን ነጭ ውሸት እውነት እንዲመስል አድርገው በማቅረብ፣ ግድያ መፈጸም ወንጀል እና የስነምግባር ዝቅጠት መሆኑ ቀርቶ የሚያስከብር እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ነጩን ውሸት የእውነት ቅርጽን እንዲላበስ አድርገው በማስመሰል የማቅረብ የባዶ ብልጣብለጥነት አካሄድ መንገድን ይጠቀሙ ነበር፡፡”
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው አገሪቱን እያተራመሱ በመግዛት ላይ ስለሚገኙት ስብስቦች አንድ የማይካድ ሀቅ አለ፡፡ ሁሉም በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተወሽቀው ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ ያገጠጠውን እና ያፈጠጠውን እውነታ አየፈሩ ነው በመኖር ላይ ያሉት፡፡ የነጻው ፕሬስ ኃይል እውነታውን የሚያጋልጥ ስለሆነ የነጻውን ፕሬስ ኃይል በመፍራት ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ በአንድ ወቅት የእነርሱ የአመለካከት ፍልስፍና አለቃ ቁንጮ የነበሩት ቪላድሚር ሌኒን “የመናገር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት ለምንድን ነው የሚፈቀደው? ለምንድን ነው መንግስት ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ሲሰራ ትችት እንዲቀርብበት የሚፈቅደው? ተቃዋሚዎችን የጠላት መሳሪያ እንዲሆኑ መንግስት መፍቀድ የለበትም፣ ሀሳቦች ከጠብመንጃ የበለጠ የገዳይነት ባህሪ አላቸው፡፡ ለምንድን ነው ማንም ሰው የማተሚያ ቤት እንዲገዛ እና የሚቀርቡ ሀሳቦችን አትሞ በማሰራጨት በስልጣን ላያ ያለውን መንግስት በተቀነባበረ ስሌት ለመተቸት እና ለማሳፈር እንዲችል የሚፈቀደው?“ እንዳሉት ማለት ነው፡፡
እውነታውን በሚገባ ያውቁታል ምክንያቱም እውነታው ህዝቡን ነጻ እንዲሆን ያግዘዋል፡፡ ነጻነትን ይፈራሉ ምክንያቱም አዲስ ሀሳቦችን ይፈራሉ፡፡ አዲስ ሀሳቦችን ይፈራሉ ምክንያቱም ለውጥን ይፈራሉ፡፡ ነጻ የሆነ ህዝብ የእውነትን ጥሩር ታጥቆ የሀሳብ ነጻነትን ተጎናጽፎ በእራሱ ፈቃድ የእራሱን የመንግስት ዓይነት ለመመስረት ሙሉ ነጻነት አለው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ስላለው ገዥ አካል ያለው እውነታ ምንድን ነው? እውነታው በሰው ልጆች ላይ ግፍን የፈጸሙ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ህጋዊነት የላቸውም፡፡ በጠብመንጃ ኃይል በጉልበት በስልጣን ወንበር ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙ አምባገነኖች ናቸው፣ ምርጫዎችን በመስረቅ እና በመዝረፍ ተመርጠናል እያሉ በማታለል ተክነዋል፣ በጥልቅ የሙስና ማእበል ውስጥ ተዘፍቀው የአገሪቱን ሀብት በማውደም ላይ ይገኛሉ፣ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በህገወጥ መንገድ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፣ የህግ የበላይነትን በመደፍጠጥ በጫካው ህግ የሚገዙ ህገወጦች ሆነዋል፣ እውነታው ሲታይ በአጠቃላይ በሸፍጥ የታወሩ የጫካውን አስተዳደር ወደ መንግስታዊ አስተዳደርነት አዙረው ህዝብን በማተራመስ ላይ የሚገኙ የስግብግብ ወሮበላ ቡድን ስብሰቦች ናቸው፡፡ እውነታው በአጠቃላይ ሲታይ የአፍሪካን የጨካኝ ዘራፊነት ስርዓት በሀገራችን ላይ የሚተገብሩ ወሮበላ ዘራፊዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ወሮበላ ዘራፊዎች ነጻ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ይፈራሉ ምክንያቱም እነዚህ ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች አምባገነኖቹ የሚሰሯቸውን ወንጀሎች እና ሙስናዎች፣ የመከኑ እና የወደቁ ፖሊሲዎቻቸውን፣ የአቅም ድሁርነታቸውን እና ድንቁርናቸውን በማጋለጥ እውነታውን ያወጡባቸዋል፡፡ እነዚህ ጭራቃዊ ፍጡሮች በጫማቸው ስር እረግጠው የያዟቸው የግፍ ሰለባዎች ነጻ ቅዱስነት እና የያዙት ጸበል ስለሚያቃዣቸው ነጻ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ በያዙት ሁሉ ኃይል በመጠቀም እውነቱ ወጥቶ ለህዝብ እንዳይደርስ እና እንዳይታወቅባቸው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡ የሳቴላይት ስርጭቶችን ሳይቀር አፍነዋል፣ የኢንተርኔት ግንኙነቶችን አቋርጠዋል፣ ጋዜጦችን በመዝጋት ጋዜጠኞችን በእየእስር ቤቶች አጉረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የአረብሳት ለዓለም አቀፉ የግንኙነት ህብረት/International Communication Union እና ለአረብ ሊግ/Arab League ኢትዮጵያ ስርጭቱን ያፈነች መሆኗን እና “ወንጀለኛውን ለመቅጣት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ” እና በዚህ ህገወጥ ድርጊት ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ወይም በዚህ ህገወጥ የአፈና ተግባር ምክንያት ወደፊት ለሚደርስ ማንኛውም አደጋ ተገቢውን ካሳ እንድትከፍል እንዲደረግ ተማጽዕኖውን አቅርቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገዥው አካል በገበያ ላይ የቀሩትን እና በገዥው አካል ላይ ጠንካራ ጥችት የሚያቀርቡትን ጥቂት ጋዜጦች በየመንገዶች እያዞሩ የሚሸጡትን ጋዜጣ አዟሪዎችን እያሳደደ፣ እያስፈራራ እና በቁጥጥር ስር እያዋለ ይገኛል፡፡
እውነታው በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ ከመግለጽ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እየተካሄደ ላለው ጭቆና እና አፈና የቻይናዎች ስውር እጆች ያሉበት መሆኑ ነው፡፡ ቻይናዎች ለገዥው አካል የማፈኛ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ማቅረብ ብቻ አይደለም የሚያከናውኑት፡፡ ሆኖም ግን ለተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ለኢንተርኔት አገልግሎት የመሰረተ ልማት ስራዎችም ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው፡፡ የመረጃ ፍሰት ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ እና ወደ ኢትዮጵያም እንዳይገባ ለመገደብ እና ለማቋረጥ የአንድ መስኮት ፈጣን የአግልግሎት መስጫ ኪቶችን ይዘዋል፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመታት ገደማ በፊት የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄላሪ ክሊንተን ዛምቢያን በመጎብኘት ላይ ሳሉ የቻይናውያን በአፍሪካ አህጉር ላይ ያላቸውን ሚና በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በቅኝ ግዛት ዘመን ጊዜ መምጣት እና ለመሪዎቹ ገንዘብ በመስጠት የተፈጥሮ ሀብቶችን ከአፍሪካ መውሰድ ቀላል ነበር፣ በምትለቅቅበት ጊዜ እዚህ ላለው ህዝብ ምንም ነገር ትተህ አትወጣም፣ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ቅኝ ተገዥነት በአፍሪካ ማየት አንፈልግም“ ብለው ነበር፡፡ እውነታው ግን ቻይናውያን በኢትዮጵያ መቆየታቸው እና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ለገዥው አካል የቴክኒክ እገዛ በመስጠት፣ የኦዲዮ እና ቪዲዮ መሳሪያዎችን በማቅረብ የመረጃ ምርመራ በማድረግ እና በኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙሀን ላይ አፈናዎችን በማካሄድ ነጻ አሰተሳሰብን በመጨቆን በዋናነት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡
ነጻነትን ይፈራሉ፡፡ ነጻነት ምንድን ነው? የሁሉም የሰው ልጆች ነጻነቶች ባህሪያት ከፍርህት የሚገኙ ነጻነቶች ናቸው፡፡ በተግባራዊ ሁኔታ ሲታይ አንድ ሰው ያሰበውን ለመናገር መፍራት ወይም ደግሞ አንድ ሰው ደስ ያለውን መጻፍ መፍራት ወይም በአንድ ሀሳብ ማለትም ሀይማኖት ወይም ፍልስፍና ላይ ማመን እና አለማመንን መፍራት ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከመረጠው ሰው ጋር አብሮ መምጣት መፍራት ማለት አይደለም፡፡ ዋናው እና የመጨረሻው የሰው ልጅ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባው ህዝቡ እራሱ ስልጣን የሰጣቸው በስልጣን ወንበር ላይ ያሉት ሰዎች ናቸው በህብረተሰቡ የኑሮ ሂደት ላይ መፍራት እና ህዝቡን ማክበር ያለባቸው፡፡
ሀሳብን ይፈራሉ፡፡ “ሀሳቦች ከጠብመንጃ የበለጠ ገዳዮች ናቸው“ በማለት ሌኒን አስጠንቅቀዋል፡፡ ሀሳቦች ሳይንስን፣ ፖለቲካን እና ማናቸውንም የሰው ልጅ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉ የመለወጥ ኃይል አላቸው፡፡ ከምንም በላይ ዓለም ጠፍጣፋ አይደለችም፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ያሉ ገዥዎች የአዲስ ጠፍጣፋ መሬት ባለቤቶች ናቸው፡፡ እንደ ጥንቱ ንጉሶች፣ ዛሮች፣ እና ማሃራጃሆዎች ሆነው ከህዝቡ ፈቃድ ውጭ ( በተሰረቀ ስምምነት) መሰረት መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ ጥቂት ሞራላዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሀሳቦች ሲኖሯቸው ነገሮችን በቀላሉ ለመገንዘብ እና አዳዲስ ሀሳቦችንም ለማድነቅ እና ተቀብሎ ወደ ተግባር ለማዋል የምሁርነት አቅሙ የሌላቸው የመንፈስ የአስተሳሰብ ድሁሮች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የጎሳ ክፍፍልን ለማራመድ፣ ስግብግብነት እና ጥላቻን ለማምጣት፣ የጥላቻ ከባቢን የመፍጠር፣ ግጭትን የመጫር፣ ሙስናን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር፣ ህብረትን በመናድና የጥላቻ መንፈስን በመዝራት እንዲሁም በሰዎች መካከል ጥርጣሬ እና አለመተማመን እንዲነግስ በማድረግ ጭንቅላቶቻቸው ዋና የዲያብሎሳዊነት ቤተሙከራዎች ናቸው፡፡ ህዝብን ሊያስተባብሩ እና ሊያፋቅሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ለማመንጨት፣ በጎሳዎች መካከል ፍቅርን የማስፈን፣ ብሄራዊ አንድነትን የማምጣት፣ የጋራ መግባባትን የመፍጠር፣ የጓዳዊነት መንፈስ የማጠናከር እና እምነትን የማራመድ አቅመቢሶች ናቸው፡፡
አዳዲስ ሀሳቦችን የሚፈሩ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተቆናጥጠው የሚገኙ አምባገነኖች የአዲስ ሀሳብ አመንጭ እና ባለራዕይ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፡፡ ህዝቡ እና ዓለም ወደፊት ጥሩ ነገር የሚያስቡ መልካም ነገር አላሚዎችና ፈጣሪዎች እንደሆኑ አድርጎ እንዲመለከታቸው እና እምነት እንዲኖረው ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ግን በህልም የቅዠት ፍርሀት ተዘፍቆ ያለ ማንም ሰው መልካም አላሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ባለራዕይ መሪዎች ለሚያደርጓቸው ማለትም ታማኝነት፣ ኃላፊነትነትን የመሸከም ብቃት፣ ሌሎችን አነቃቅቶ እና አሳምኖ በስራ የማሳተፍ ችሎታ፣ ያለፉትን ስህተቶች በግዴለሽነት እንዳሉ ከመድገም ይልቅ ከስህተት እና ከውድቀት መማርን፣ ስህተት በሚሰሩበት ጊዜ ይቅርታ አድርጉልኝ ብሎ መጠየቅን፣ ግልጽነት፣ ትክክለኛውን ነገር ለመስራት ፍትሀዊነት እና በፍቅር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከመገኘት ተግባራት ጋር ሁሉ አይተዋወቁም፡፡ መጥፎ እና ዕኩይ ተግባራትን ለማድረግ ፍቅር ያላቸው መሰሪ መሪዎች ናቸው፡፡ ኪሶቻቸውን የሚወጥሩትን የተዘረፉ በርካታ ገንዘቦችን ዓይኖቻቸው በቀላሉ ማየት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን አሁን እየፈጸሟቸው ያሏቸው በርካታ ወንጀሎች በዘለቂነት ለወደፊት ሊያስከትሉት የሚችሏቸውን እንደምታዎች ለማየት የታወሩ ናቸው፡፡ ጠንካራን ሀሳብ ጊዜው እየመጣ ያለውን ሀሳብ የሚያቆመው ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት የሚያደርገውን ተጋድሎ የሚያቆመው ኃይል የለም፡፡ አንዴ ከተጀመረ በመንገዱ ላይ ያለውን ጋሬጣ ሁሉ እየጠራረገ ወደፊት ይገሰግሳል፡፡
ለውጥን ይፈራሉ፡፡ ለውጥ ምንድን ነው? ለውጥ በሁሉም ነገር የሚከሰተውን የዕድገት እና የመበስበስ ዓለም አቀፋዊ ዘላለማዊ የለውጥ ህግ የሚገዛ ሂደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ለውጥን አጥብቆ ይፈራል ምክንያቱም በህበረተሰቡ ላይ ያላቸውን የኢኮኖሚ እና የፖሎቲካ የበላይነት ቦታ ስለሚያሳጣቸው ነው፡፡ ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱትን ማናቸውንም ሙከራ ሁሉ ይደመስሳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር “በሰላማዊ መንገድ የለውጥ አብዮት እንዳይመጣ የሚከለክሉ ሁሉ የአመጽ ለውጥ በኃይል እንዲመጣ ይገደዳሉ“ የሚለውን ሀቅ ለመገንዘብ የተሳናቸው ይመስላል፡፡
በፖለቲካ ህጋዊነት ማጣት እና በመንግስት አቅም ማጣት ምክንያት ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ መበስበስ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ያለችበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ የጨነገፈ መንግስት ሆናለች፡፡ ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት የጎሳ ክፍፍል ፖሊሲ (የጎሳ ፌዴራሊዝም) “ልማታዊ መንግስት” ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገብን በማለት የሚራገበው እርባናየለሽ ፕሮፓጋንዳ ቢኖርም እንኳ ኢትዮጵያን በሁለት አማራጮች ላይ ጥሏታል፡፡ የእነርሱ ነጭ ውሸት ብቻ ነው በባሁለት እና በባለሶስት አሀዝ እድገት ያስመዘገበው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ እንደተባበረች ሀገር አንድ ሆና ወደፊት ተገሰግሳለች ወይም ደግሞ ወደተለያዩ ትናንሽ የተበጣጠሱ ክልሎች ትገነጣጠላለች፡፡ የአፓርታይድ ዓይነት ባንቱስታንስ በኢትዮጵያ ክልል እየተባለ በዘር እና በቋንቋ የተቀየደ የአገዛዝ ስርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተበጣጠሱ ግዛቶች ስብስብ የምትሆን ከሆነ የመጀመሪያው ቸግር ቀማሽ የሚሆኑት አሁን በስልጣን ላይ ተጣብቆ የሚገኘው ገዥው አካል፣ የእነርሱ ጋሻጃግሬዎች እና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በፖቲካ ስልጣን ማጣት ብቻ የሚቆም ሳይሆን ቢያንስ እስከ አሁን ድረስ በአገር ውስጥ የሚደረግ ለውጥ ዘግይቶ እንደደረሰ ባቡር ይቆጠራል፡፡ በምስራቅ አውሮፓ በመካከለኛው ምስራቅ ሲነፍስ የነበረው የለውጥ ነፋስ ያለምንም ጥርጥር በኢትዮጵያም መንፈሱ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ሊነሳ የሚችለው ብቸኛ ጥያቄ ግን እነዚህ ነፋሶች ተስማሚ እና በሰላም የሚያልፉ ወይስ ደግሞ ሁሉንም ነገር እየገነደሱ እና እየቦደሱ የሚጥሉ ኃይለኛ የሁሪኬን/hurricane-force ሞገዶች ይሆናሉ የሚለው ነው፡፡
እውነት ነጻ ያወጣሀል ነጻ አስከሆንክ ድረስ ሆኖም ግን ነጻ ያልሆኑት ይሰቃያሉ፣
“እውነት ነፃ ታወጣሀለች” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ነጻነት እና ፍርሀት ለእየራሳቸው ተነጥለው የሚኖሩ ናቸው፡፡ የነጻው ፕሬስ እና ጦማሪያን ብቸኛው ተግባራቸው እንዳዩት እውነታውን ወዲያውኑ መናገር ነው፡፡ ስለ እውነታው ያላቸውን ሀሳብ የለምንም ፍርሀት የመግለጽ ነጻነት አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ህዝቡ እውነታውን ቀድሞም ቢሆን ያውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች የሚለው ነጭ ውሸት ቢሆንም ህዝቦች እውነታውን ያውቁታል፡፡ የሚበላ በቂ ምግብ እንደሌለ ያውቃሉ፣ እናም ሚሊዮኖች በየቀኑ እየተራቡ እንዳሉ ያውቃሉ፡፡ እንዲሁም በቂ የውኃ አገልግሎት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ አናሳ የህክምና አገልግሎት ነው እየተሰጠ ያለው፣ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት አያገኙም እናም ስራ አጦች ናቸው፡፡ ገዥው አካል በሙስና ማጥ ውስጥ የተዘፈቀ እና የበከተ ነው፣ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን ይፈጽማል፡፡ ህዝቦች በግልጽ የአየር ድባብ ውስጥ እስረኛ ሆነው እንደሚኖሩ ያውቃሉ፡፡
የነጻ ጋዜጠኞች እና የጦማሪዎች ወንጀል የሚያውቁትን ነገር ለማያውቁት ወገኖቻቸው መግለጻቸው ብቻ ነው፡፡ የእነርሱ ወንጀል የማዕድን ሙስና እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን ወንጀሎች እየቆፈሩ በማውጣት ማስረጃ በማቅረባቸው ነው፡፡ ለዚህም በስልጣን ላያ ያለው ገዥ አካል እየፈራቸው ያለው፡፡ ገዥው አካል እውነታው ሳይታወቅ ተቀብሮ እንዲቀር እና እንዲረሳ ይፈልጋል፡፡ ገዥው አካል እውነታው እንዳይታወቅ በመደበቅ፣ እውነት ተናጋሪዎችንም ጸጥ በማስደረግ እና በየእስር ቤቶች በማጎር ለዘላለም ጸጥ በማድረግ ትንፍሽ እንዳይሉ በማድረግ እውነትን የመግደል እምነት አለው፡፡ ጆርጅ ኦርዌል እንደጠቆሙት፣ ”የማጨበርበር እና የሀሰት ሸፍጥ በተንሰራፋበት ጊዜ እውነትን መናገር አብዮተኛነት ድርጊት ነው“ ብለው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ጦማሪያን የኢትዮጵያ የማይበገሩ አብዮተኞች ናቸው፡፡
ፍርሀትን በብዙሀን መገናኛ እንደ መሳሪያ መጠቀም፣
በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ዋና ድክመትን እንደ ትልቅ መጠቀሚያ መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ህዝብን ግራ ለማጋባት፣ እርስ በእርስ ለመከፋፈል፣ ለማታለል፣ ጥላሸት ለመቀባት እና ሀሳብን ከዋናው ጉዳይ አቅጣጫውን ለማስቀየስ ፍርሀትን በዋና መሳሪያነት ይጠቀምበታል፡፡ ማቋረጫ የሌለው የፍርሀት ዘመቻ በህብረተሰቡ ላይ ለመንዛት ሲፈልግ፣ ጥላሸት ለመቀባት እና ለማጠልሸት ሲፈልግ በህዝብ የግብር መዋጮ የሚተዳደረውን መገናኛ ብዙሀን ለእኩይ ምግባር ሌት ቀን ይጠቀማል፡፡ ገዥውን አካል የሚቃወሙትን ቡድኖች እና ግለሰቦች ጸጥ ለማድረግ ሲፈልግ እርባናየለሽ በውሸት ላይ ተመስርተው የተቀነባበሩ ዘጋቢ ፊልሞችን በመፈብረክ “አሸባሪ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ በአሰልችው የመገናኛ ብዙሀን እንደበቀቀን ይደጋግማቸዋል፡፡ የውሸት ሸፍጥ በታጨቀበት እና ለመስማት እና ለማየትም አስቀያሚ በሆነው “አኬልዳማ” ብሎ በሰየመው ለምንም የማይውል እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም ኢትዮጵያ በዲያስፖራው ተቃዋሚ ኃይል እና በአገር ውስጥ ባሉ የእነርሱ የግብር ተመሳሳዮች አማካይነት እንዲሁም ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ትብብር እና ርብርብ አደገኛ የሽብር አደጋ ተደቅኖባት እንደሚገኝ አደንቋሪ ጩኸታቸውን አሰምተዋል፡፡ “አኬልዳማ” በዓለም ላይ የተደረጉትን በጣም አስፈሪ እና አስቀያሚ ምስሎችን ሁሉ ለቃቅሞ በቪዲዮ በማሳየት በቅርቡ በህይወት የተለዩት አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቻቸውን ጥላሸት በመቀባትና በሶማሌ የሚንቀሳቀሰው የአልቃይዳ እና አልሻባብ ቅጥረኞች ናቸው ብለው በአሸባሪነት በመፈረጅ የጥቃት ብቀላቸውን በንጹሁነ ዜጎች ላይ በሰፊው ተግብረውታል፡፡
በሌላ “ጅሃዳዊ ሀራካት” በተባለ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም በክርስቲያን እና በሙስሊሙ ህብረተሰብ መካከል ፍርሀት እና ጥላቻን ለማስፋፋት በማሰብ ጸረ እስልምና እሳትን የመጫር ሙከራ አድርገው በህዝቡ አርቆ አስተዋይነት እና የንቃት ደረጃ ምክንያት እኩይ ምግባራቸው ሳይሳካ መክኖ ቀርቷል፡፡ ለዘመናት አብሮ እና ተከባብሮ እየኖረ ያለውን የክርስቲያን እና የሙሰሊም ማህበረሰቡን በማጋጨት የእስልምና አሸባሪዎች በድብቅ ጅሀዳዊ መንግስት ለመመስረት ዕቅድ አውጥተው ተንቀሳቅሰዋል በማለት በሁለቱ ታላላቅ ኃይማኖቶች እምነት ተከታዮች መካከል የማያባራ እልቂት እና የደም ጎርፍን ለማዝነብ የታቀደ ዲያብሎሳዊ የድርጊት ዕቅድ ነድፈው ነበር፡፡ አሁንም ህዝቡ የነቃባቸው እና ከእነርሱ እኩይ አስተሳሰብ ውጭ የመጠቀ ሀሳብ ስላለው እና ስላወቀባቸው ዕቅዳቸው አሁንም መክኖ ቀርቷል፡፡
ፍርሀት እና ጥላቻን በህዝቡ ውስጥ ለማስፋፋት እና ምናባዊ የሆነ የዘር እና የጎሳ እልቂት እንዲሁም የኃይማኖት ጽንፈኝነት እልቂት እንደሚከሰት በመስበክ ይህንንም እልቂት ለማስወገድ ብቸኛ ቅዱሶች እነርሱ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ እና በማደናገር ጸረ ኢትዮጵያ እና ዘረኛ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጎጠኞች መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል፡፡ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ አንዱን ጎሳ በሌላው ላይ በማስነሳት ለማጋጨት ሌት ቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ “የጎሳ ፌዴራሊዝም/ethnic federalism” በሚል እኩይ ስልት የዘር ማጽዳት ዘመቻቸውን ቀጥለውበታል፡፡ የጎሳ ጥላቻን ለመቀስቀስ ታሪካዊ ብሶቶችን እየፈበረኩ እና ጥቃቅን ነገሮችን እያጋነኑ በህዝቡ ዘንድ አለመተማመን እና ግጭቶች እንዲነሱ አበርትተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ ግን ስለነቃባቸው በባዶነታቸው ቀልበቢስ በመሆን እንደ አበደ ውሻ ከወዲያ ወዲህ በመቅበዝበዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእራሳቸውን ፍርሀት እንደ መሳሪያ በመጠቀም ህዝቡን ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ትንታግ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ላይ የተከፈተው ጦርነት በእራሷ በእውነት ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው፣
በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል በነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና በጦማሪያን ላይ ያወጀው ጦርነት በእውነት በእራሷ ላይ ያወጀው ጦርነት ነው፡፡ ገዥው አካል ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በተደረጉት ጦርነነቶች እና ግጭቶች ሁሉ በድል አድራጊነት ተወጥቷል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ጎራዴ እና ኤኬ 47 አውቶማቲክ ጠብመንጃዎችን በታጠቁ አምባገነኖች እና ብዕሮች እና የኮምፒውተር ኪቦርዶችን በሚጠቀሙ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን መካከል የሚደረገው ወሳኙ ፍልሚያ ተቃርቧል፡፡ ያ ጦርነት እና ፍልሚያ በኢትዮጵያውያን/ት ልብ እና አእምሮ ውስጥ ሰርጾ ሁሉንም ዜጎች ለወሳኙ ፍልሚያ እና ለድል ጉዞ ጥርጊያ መንገዱን የሚያመቻች ይሆናል፡፡ የዚያ ጦርነት እና ፍልሚያ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በእርግጠኝነት የምናገረው ነገር ቢኖር ፍልሚያው የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል፡፡ በእርግጥ ያ ጦርነት በእውነት አራማጅ ወገኖች አሸናፊነት እንደተደመደመ እምነት አለኝ፡፡ ኤድዋርድ ቡልዌር ሊቶን የተባሉት ገጣሚ በትክክል እንዳስቀመጡት ጎራዴ በታጠቁት እና ብዕርን በጨበጡት ተዋጊዎች መካከል በሚደረግ የጦርነት ፍልሚያ በመጨረሻ ሁልጊዜ የወሳኙ ድል ባለቤት የሚሆኑት ብዕርን የጨበጡት ናቸው፡፡ እውነትን ጨብጠዋልና!
እውነት፣ ይህ!
ከሰዎች አገዛዝ ስር ሌላ ታላቅ ነገር አለ፣
ብዕር ከጎራዴ የበለጠ ኃይል አለው፡፡ አስተውል/ይ
ቀስት ተሸካሚዎች ይፈነድቃሉ፣ ግን ምንም የሚመጣ ነገር የለም!-
ልዩ ታምር ከጌታቸው እጀ ይቀበላሉ፣
እናም ቄሳሮችን በድን ለማድረግ ያምጻሉ
ታላቋ መሬት ትንፋሽ ያጥራታል!- ጎራዴውን ከዚህ ወዲያ ውሰዱ-
መንግስታት ከእርሱ ውጭ ሊጠበቁ ይችላሉና!
ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል ማዳን ወይስ ደግሞ የኢትዮጵያን ነጻ ፕሬስ እና ጦማሪያንን ማዳን የሚል ወሳኝ ጥያቄ ቢቀርብልኝ ቶማስ ጃፈርሰን እንደመረጡት ሁሉ እኔም የኋለኛውን ማዳን የሚለው እንዲጠበቅልኝ እመርጣለሁ፡፡ ቶማስ ጃፈርሰን እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተው ነበር፣ ”የእኛ መንግስት መሰረቱ የህዝብ ሀሳብ እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያው ዓላማ መሆን ያለበት ያንን መብት ማስከበር ነው፡፡ እናም ጋዜጦች የሌሉበት መንግስት ከሚኖር ወይም ደግሞ መንግስት በሌለበት ጋዜጦች ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ ነው የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ስል ማንኛውም ሰው እነዚህን ጋዜጦች መቀበል እና ማንበብ መቻል አለበት፡፡“
በተመሳሳይ መልኩ ለእኔም ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሌሉበት ገዥ አካል ከሚኖር ወይም ደግሞ ገዥ አካል በሌለበት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ ነው የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዓላማ በጽናት የቆምኩ፣ ለምሰራው ትክክለኛ ስራ ሁሉ ኩራት የሚሰማኝ፣ ላመንኩበት ዓላማ ከልብ እና በወኔ የቆምኩ፣ ዓላማየን ለማስፈጸም በከባድ እርምጃ ወደፊት የምገሰግስ፣ ላልሰራሁት ወንጀል ይቅርታን የማልጠይቅ፣ በምሰራው ስራ ሁሉ የማላፍር፣ ቆራጥ እና የማያወላውል ባህሪን የተላበስኩ የኢትዮጵያ ጦማሪ ነኝ!!!
ኃይል ለነጻ ጋዜጠኞች እና የኢትዮጵያ ጦማሪያን!
ውድቀት እና ሞት ህዘብን በጠብመንጃ ኃይል አስገድደው ለመግዛት ለተነሱ የዕኩይ ምግባር አራማጆች!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar