June 12, 2014
በሐሰት የሽብር ክስ ህገ መንግስታዊ መብቶችን በጣሰ ሁኔታ መሪዎቻችንን እያጉላላ የሚገኘው መንግስት በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያደርገውን ወከባ ቀጥሎበታል፡፡ ገና ወደማረሚያ ቤት ከተዛወሩበት ጊዜ አንስቶ ጠያቂዎችን በማጉላላት፣ የጥየቃ ሰአትን ከሌሎች በተለየ መልኩ በመገደብ፣ እንዲሁም በጠያቂዎች ቁጥር ላይ ገደብ በማድረግ በተለያዩ ወቅቶች መብታቸውን ሲነግፍ የቆየው መንግስት ዛሬ ደግሞ በታሪካዊው የካንጋሮ ፍርድ ቤት የችሎት ሂደት ምስክሮቻቸውን እያቀረቡና ትክክለኛው የህዝበ ሙስሊሙ ትግል ገጽታ በችሎት እየተመሰከረ ባለበት በዚህ ወቅት በፍርድ ቤት እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት ለመቋቋም ወኪሎቻችን ላይ የተለያዩ ወከባዎችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ በእስር ቤቱ ታሪክ በምንም መልኩ የማያስጠይቅን፣ ይልቁንም በማረሚያ ቤቱ ደንብ ጥበቃ የተደነገገለትን ገንዘብ የመያዝ መብት እንደወንጀል በመቁጠር በኮሚቴው ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና በሸኽ መከተ ሙሄ ላይ፣ እንዲሁም በሌሎች ታሳሪዎች ላይ ሲያደርስ የነበረውና በቅርቡ የተረጋጋው ወከባ መሪዎቻችንን የማጥቂያ ሰበብ ፍለጋ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ግልጽ ነበር፡፡
አሁንም ይህንኑ ህገወጥ ድርጊቱን የቀጠለበት የእስር ቤቱ አስተዳደር በዞን አንድ በሚገኙ ጀግኖቻችን፣ (ማለትም በሸኽ መከተ ሙሄ፣ በኡስታዝ አቡበከር፣ በኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ በኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ፣ በጋዜጠኛ አቡበከር ዓለሙ፣ በወንድም አብዱረዛቅ አክመል እና በወጣት ሙባረክ አደም) ላይ በዞን አንድ በሚገኙት 8 ክፍሎች እንዲበታተኑና እንዲለያዩ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ ጓዞቻቸውንም ወደየተመደቡበት ክፍሎች እንዲቀይሩ እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡ ባለበት የጤና ችግር ምክንያት ልዩ ትኩረትና ረዳት ጓደኛ የሚያስፈልገውን ወንድም አብዱረዛቅን ድጋፍ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንበት እያወቁ ብቻውን መድበውታል፡፡ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋንም እንዲሁ ጊዜያዊ ማቆያ ተብሎ በሚታወቀውና በእስረኞች ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭነት ምክንያት ማህበራዊ ትስስር መመስረት አስቸጋሪ በሆነበት ክፍል ሆን ተብሎ እንዲመደብ ተደርጓል፡፡
የማረሚያ ቤቱ ደንብ በአንድ የክስ መዝገብ ችሎት የሚከታተሉ ታራሚዎች በችሎታቸው ዙሪያ በየጊዜው መነጋገርና መወያየት እንዲችሉ በአንድ ዞን የመታሰር መብት የሚሰጥ ቢሆንም አስተዳደሩ ግን ይህንን የሚያደርገው ሆን ብሎ የችሎታቸውን ፍሰት ለማስጓጎል እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ ሆነ ተብሎ እነሱን ብቻ የለየ ጥቃትና የመብት ጥሰት የሚፈጸምባቸውም በእስር ቤት ውስጥ ባለቻቸው ውስን ነጻነት የገነቧትን ማህበራዊ ትስስር ለማፍረስና የመጪውን ረመዳን ጾምም ተረጋግተው መጾም እንዳይችሉ ጫና ለማሳደር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አወዛጋቢው የፍርድ ሂደት ቀጥሎ የሰው ምስክርነት እየተደመጠ ባለበት ሁኔታ የመጨረሻ ውሳኔ የማስለወጥ ሃይል ባይኖረውም እየተደመጠ ያለው ምስክርነት እጅግ እንዳደናገጣቸውና በዚህም ይህንን እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደዱም የሚያሳብቅ ሆኗል፡፡ መንግስት በሃሰት የሽብር ክስ ማንገላታቱ ሳያንሰው በእስር ቤት ውስጥ እንኳን ታራሚዎች ላይ የሚያደርሰው በደል በእርግጥም የአገሪቱ የፍትህ ስርአት የቁልቁለት ጉዞውን እያፋጠነ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ምስክር ነው፡፡
የእስር ቤቱ አስተዳደር ውስጥ ያሉት አንዳንድ ሀላፊዎች በግፍ እስር ላይ ለሚገኙት የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ያላቸውን ጥላቻ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያሳዩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ካሁን ቀደም የደሴ ወጣት ታሳሪዎች ወደጨለማ ክፍል እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎ ሌሎች እስረኞች ተቃውሟቸውን ለማሰማት በተሰበሰቡበት ወቅት በቅጽል ስሙ ሻእቢያ ተብሎ የሚጠራው የማረሚያ ቤቱ የጸጥታ ሀላፊ ‹‹እኒህን አሸባሪዎች ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ መረሸን ነበር!›› ብሎ ቁጭቱን ሲገልጽ በግላጭ የተሰማ ሲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎችም ጥቃት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ መታዘብ ተችሏል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ካሁን ቀደምም በሌሎች በርካታ ታሳሪዎች ላይ አሰቃቂ የጅምላ ድብደባ ሲፈጸም የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ይህን መሰል የህገ መንግስቱን የእስረኛ አያያዝ ደንብ በግላጭ የሚጥሱ ወከባዎችና በደሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ይጠይቃል! ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ያወጁትን ጦርነት ሲያስፈጽሙ የቆዩት ደህንነቶችና የመዋቅራቸው አካላት ከህግ በላይ የሆነ አካሄዳቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ያሳስባል! በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ወንጀል በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ እነርሱ ላይ የሚደርስ በደል ፈርሞ ወደመንግስት በላካቸው ሰፊው ህዝበ ሙስሊም ላይ የሚደርስ በደል ነው፡፡ በመሆኑም በወኪሎቻችን ላይ አንዳች ነገር ቢደርስ ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ የሚወስደው መንግስት መሆኑን እያስታወቅን ሰላማዊው ህዝበ ሙስሊምም ይህን መሰሉን ድንበር ያለፈ ጥቃት እስከመጨረሻው የሚፋረደው መሆኑን በጥብቅ እናሳውቃለን!
በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ በማረሚያ ቤት ውስጥ እየተደረገ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!
የእስር ቤቱ አስተዳደር ከህግ በላይ መሆኑን በአስቸኳይ ያቁም!
የህዝብ ወኪሎችን ማጉላላት ይብቃ!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
የእስር ቤቱ አስተዳደር ከህግ በላይ መሆኑን በአስቸኳይ ያቁም!
የህዝብ ወኪሎችን ማጉላላት ይብቃ!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar