ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ
በመጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ‹‹ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ›› በሚል ርዕሥ የውይይት መነሻ ሀሳብ ከሙያ አጋሮ ቼ ጋር እንዳቀርብ ስለጋበዘኝ በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
፩
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29
ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ የፈረሙበት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ይህ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 29 (1) እና (2) ላይ ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29
ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ የፈረሙበት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ይህ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 29 (1) እና (2) ላይ ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ማናኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡ ፣ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ-ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ በማንኛውም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡››
‹‹እንደ ጥሩ ምሳሌ የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን እና የእስክንድር ነጋን ጉዳይ መውሰድ እንችላለን፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት፣ ርዕዮት እንደጋዜጠኛ የፈለገችውን ሐሳብ ጽፋ ለየትኛውም ሚዲያ የማቀበል መብት አላት፡፡ ይህ ተጥሶ ‹‹ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላት›› ተብሎ ተፈረደባት፡፡ እስክንድር ነጋ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤታችን ድረስ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ተጋብዞ በመምጣት የቀረበውን ሐሳብ ከተሰብሳቢዎች ጋር ተቀምጬ አዳምጫለሁ፡፡ ሐሳቡን በመግለጹ ‹‹ሽብርተኛ ነው›› ተብሎ ተፈረደበት፡፡ እነ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳ ‹‹ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ጋር ለምን ተነጋገራችሁ?›› ተብለው ነበር የታሰሩት፡፡ በተጨማሪም በአንድነት ፓርቲ ስር ትታተም የነበረችው የ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋዜጣ ያለመታተም ጉዳይ፣ የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ መታገድ፣ የ‹‹አዲስ ነገር›› እና የ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ጋዜጦች የደረሰባቸውን ችግር እናውቃለን፡፡ አንቀጽ 29 እስከአሁን አልተከበረም፡፡››
፪
ከሕገ-መንግሥቱ በፊት
ከነጻ ፕሬሱ እወጃ በኋላ ባሉት ዓመታትም፣ እስከአሁን ድረስ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲዳክር መጓዙን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ስለሚሆን አልፈዋለሁ፡፡
አንድ ጉዳይ ግን በውስጤ ብዙ ጊዜ ይብሰለሰላል፡፡ እራሴንም ደጋግሜ ጠይቄ ለራሴ መልስ አግኝቼለታለሁ፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕገ መንግሥቱ ብቻ መሆኑን ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሕገ-መንግሥቱ በፊት ቀዳሚ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህንን የምለው፣ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ በነጻነት እንዲያስብ፣ ሐሳቡን ሐላፊነት በተሞላው መልኩ እንዲናገር፣ እንዲጽፍ፣ በተለያዩ ጥበባቶችና የመግባቢያ መንገዶች እንዲያስተላልፍ እና እንዲቀበል ቀድማ ለግሳዋለች፡፡ ይህንን የላቀ የተፈጥሮ ሕግ ከሕገ-መንግሥት ጋር ተሰናስሎ በሕግ ማዕቀፍ መደገፉ ጥቅሙ የላቀ መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አምባገነን ሥርዓቶችን ያየች ሀገር ቀላል የማይባሉ ዜጎች ተፈጥሯዊውንም ሆነ ሕገ-መንግሥታዊ የማሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ …ወዘተ መብቶቻቸው ተሸብቦ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ መውደቃቸውን አምናለሁ፡፡ ይህም ሥርዓታቱ (ደርግ የለየለት፣ ኢህአዴግ ደግሞ ዴሚክራሲያዊ ካባ የደረበ አንባገነን ነው) ለሥልጣናቸው ማቆያ እና ማራዘሚያ ሲሉ ከእነሱ ሃሳብ በተቃራኒው በሚያስቡ እና በድፍረት በሚናገሩ፣ በሚጽፉ …ዜጎቻቸው ላይ በሚወስዷቸው ኢ-ፍትሃዊ የግድያ፣ የድብደባ፣ የእስር፣ የእንግልት፣ የስደት …እርምጃዎች በዋነኝነት የሚመጣ ነው፡፡ አፋኝ የሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁም ኢትዮጵያኖችን ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን የማሰብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር …መብቶች በእጅጉ የሚጨቁን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በመሆኑም ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ የማክበር እና የማስከበር ግዴታን እንዴት እንወጣው? በሚለው ላይ ብንወያይበት መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
፫
የእስረኞች አያያዝ እና ሰብዓዊ መብቶች
በመጨረሻም በጣም በማከብራቸው ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ‹‹ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን ማን ይፈራቸዋል?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ የማረከኝን ሀሳብ በመውሰድ የውይይት መነሻ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡
‹‹ …ለእኔም ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሌሉበት ገዥ አካል ከሚኖር ወይም ደግሞ ገዥ አካል በሌለበት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዓላማ በጽናት የቆምኩ፣ ለምሰራው ትክክለኛ ሥራ ሁሉ ኩራት የሚሰማኝ፣ ላመንኩበት ዓላማ ከልብ እና በወኔ የቆምኩ፣ ዓላማዬን ለማስፈጸም በከባድ እርምጃ ወደፊት የምገሰግስ፣ ላልሰራሁት ወንጀል ይቅርታን የማልጠይቅ፣ በምሰራው ሥራ ሁሉ የማላፍር፣ ቆራጥ እና የማያወላውል ባህሪን የተላበስኩ የኢትዮጵያ ጦማሪ ነኝ፡፡››
ኃይል ለነጻ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ጦማሪያን!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar